“አማራ ክልል ንብረቱ የሸጠ ሰው ወዲያውኑ ከባንኮች በሚሰጥ ጥቆማ ይታገታል”

Date:

  • አዲስ ሪፖርተር – “በአማራ ክልል ንብረት መሸጥና መለወጥ ቆሟል” ይላል የባህር ዳር ደላላ። ለምን ቢሉ ንብረትዎን ከሸጡ ወዲያውኑ ቤተሰብዎ ወይም እርስዎ ይታገታሉ። “ከፍኖተ ሰላም ለቅቄ ወጥቻለሁ። ንብረቴን እንዳልሸጥ እግት ፈራሁ” ትላለች ሌላ ብሶተኛ። አንድ ላይ ያለው ድባብ ግን አማራ ክልል ሕዝብ ተማሯል። ምሬቱን ሲገልጽ መሰረታዊ በአመክንዮ የተደገፉ ጥያቄዎችን ባማንሳት ነው።

በቀደመው ውበቷ ላይ የነበረባትን ጉድፍ አራግፋ በተዋበችው ባህር ዳር የተገኘው የአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢ ይህን የሰማው በአንድ ግሮሰሪ ውስጥ ከደላሎች ጋር ባደርገው ኢመድበኛ ወሬ ነው። በዙ ጉዳዮች ተነስተዋል። እግትና ቁርጥ ክፍያ የሕዝቡን አንጀት እየበጠሱ ያሉ ችግሮች ናቸው። ከምንም በላይ ሕዝብ ግራ የተጋባው በህጋዊ የሚታወቅ የባንክ አካውንት፣ በሚታወቅ ህጋዊ ስልክ፣ በሚታወቁ ተቋማት ስም ዝርፊያ ሲፈጸም ዝም በማብሉ ነው።

አራት በማሻሻጥ ስራ የተሰማሩ ደላሎችን በማነጋገር መረዳት እንደተቻለው ባህር ዳር በበርክታ ዘርፎች መፋዘዝ ቢኖርም የድለላ ስራ ግን ሞቷል። ንብረት የሚሸጥ የለም። ንብረት ሸጦ ማገላበጥ፣ አንዱን ንብረት ሸጦ ሌላ ለመግዛት ማሰብ አሁን ላይ ጨንግፏል። በዚሁ ሳቢያ ደላሎች ከቤት ኪራይ ስራ ውጭ ሌላ ስራ የላቸውም።

ዋናው ጉዳይ የደላሎች ገቢ መራቆቱ ሳይሆን ሰው ለፍቶ ያፈራውን ንብረት መሸጥና መለወጥ አለመቻሉ ነው። በባህር ዳርና በተመሳሳይ አጎራባች ከተሞች ሰው ንብረቱን ለመሸጥ የፈራው በሚታወቁ ተቋማት በታገዘ ዝርፊያ ስለሚፈጸምበት ነው።

“ብትፈልግ ስሜንም ጻፈው” ሲል ሞትን እንደሚዳፈር ገልጾ ያየውን ምስክርነት የሰጠ ደላላ እንዳለው አንድ ሰው ንብረት በሸጠ / የንብረቱ ስም ያልተጠቀሰው ለጥንቃቄ ነው/ በማግስቱ ቤቱ ደርስ በመጡ የፋኖ ታጣቂዎች ያገተ። ከዛም በድርድር አምስት ሚሊዮን ከፍሎ ተለቀቀ። ገንዘቡም የገባው በሚታወቅ የባንክ አካውንት ነው። ድርድሩም ሲደረግ የነበረው በሚታወቅ ስልክ ነው።

በዚህ ዙሪያ አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው እንደሚሉት አንድ ሰው ንብረት ሸጦ ገንዘብ ወደ ባንክ ሂሳቡ ሲዛወርለት ወዲያውኑ ለአጋች የፋኖ ታጣቂዎች መረጃ ይደርሳል። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት መኪና እያስቆሙ የሚያስከፍሉት የፋኖ ታጣቂዎች ብር የሚገባላቸው በሚታወቅ የባንክ ሂሳብ ነው። ምስክርነት የሰጠ የኤፍ ኤስ አር ሾፌር ገንዘብ ያስገባበትን የባንክ ሂሳብ ለአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢ አሳይቷል። ምስክሩም ሆነ መረጃውን የሚሰጡት እንደሚሉት ይህን ጉዳይ መንግስት አያውቀውም ማለት እንደማይቻል ነው። ለዚህም በቂ ማብራሪያ አላቸው።

ድለላው ብቻ ሳይሆን በርካታ መልካም ዕሴቶች በአማራ ክልል ተበላሽተዋል። ስልክ ይደወላል። “ይህን ያህል ክፈል ወይም ክፈይ” ይባልና ቁርጥ ብር ይቀመጣል። አንዳንዴ ድርድር ይኖራል። ካልሆነም በቀነገደቡ መሰረት የተጠየቀውን ብር ማስገባት ግድ ነው።

” ከቡሬ ወደ ባህር ዳር ተሰድጃለሁ” የምትል አንድ እናት የገጠማትን ስታስረዳ ” ደወሉ። 25 ሺህ ብር እንዳስገባላቸው የባንክ አካውንት ላኩ። መልሰው ደወሉና ቀነ ገድብ ሰጡኝ። መልሼ ስደውል ስልኩ አይሰራም። በተባለው ቀነ ገደብ ደወሉና አስፈራሩኝ። ማታ ማደር ስለማልችል ቤቴንና ንብረቴን ጥዬ ወጣሁ። አሁን ያለሁት ዘመድ ጋር ነው”

በተለያዩ አግባቦች የአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢ በግልጽና ኢመደበኛ በሆነ አግባብ የተለያዩ መረጃዎችን ሰብስቧል። “የፈት ያለህ” የሚል ጩኸት የሚያሰሙት የባህር ዳርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጥያቄ የክልሉ መንግስትና የፊደራሉ ኃይል በሚታወቅ ስልክ፣ በሚታወቅ ኔትዎርክ፣ በሚታወቅ የባንክ ሂሳብ ዘረፋ የሚያካሂዱ ዘራፊዎችን እንዴት መለየትና መመንጠር አቃተው? የሚል ነው።

“አንድ የባንክ አካውንት ባለቤት አለው” የሚለው ጠያቂ፣ በዛ በሚታወቅ አካውንት ገንዘብ ሲገባ የባንክ ሂሳቡን ባለቤት መያዘ ቀላል ሆኖ ሳለ ዝምታ የሚመረጠው እንደኤትና በምን ሂሳብ እንደሆነ ሊገባው እንደማይችል፣ በዚህም የተነሳ በፍርሃት ያየውን እንዳላየ ሆኖ እንደሚኖር፣ ጥቆማ ቢሰጥ ተመልሶ እራሱ ላይ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል እንደሚሰጋ ይናገራል።

ድሬደዋ ፖሊስ በቅርቡ ይፋ እንዳደርገው እገታ ላይ ተሰማርተው የነበሩና ክልሉን ለማተራመስ መሽገው የነበሩ የኦነግ ሸኔ አባላትን ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር መደምሰሱንና መቆጣጠሩን ሲያስታውቅ፣ ከቻይኖች ጋር ሲሰሩ የነበሩ ንጹሃንን አግተው በባንክ ሂሳብ ገቢ እንዲደረግላቸው ጠይቀው እንደነበር ማመልክተቱን አስታውሶ “ይህ አማራ ክልል ለምን አይሆንም” ሲል የሚጠይቀው ሌላው የባህር ዳር ነዋሪ፣ ” የድሬደዋ ፖሊስ ገንዘቡ የገባበትን አካውንት በመከታተል በርካታ የቡድኑ ኔት ዎርክ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ አቅርቧል። ይህ በአማራ ክልል የማይሆነው ለምንድን ነው?” ሲል ጥያቄው አቅርቦ ” ነገርማ አለ” በማለት የተስፋ መቁረጥ ምልክት በማሳየት…

አጋቾች በአማራ ክልል ሕዝብ ተማሯል። አዝኗል። ለማን እንደሚጮህም ግራ ተጋብቷል። “ትግል” የዘረፋ የንግድ ምልክት ሆኗል። በትግል ስም ፣ ስልክ እየተደወለ የሚጣል ግብር መረን ነው። በፈለጉት ሰዓት መኖሪያ ቤት እየመጡ ዘረፋ የሚያካሂዱ የፋኖ ታጣቂዎች ከልክ ያለፈ ግፍና መከራ የሰለቻቸው የቻሉ ወደ ባህር ዳር፣ ከዚያም በላይ አቅም ያላቸው ወደ አዲስ አበባ ሸሽተዋል። ከፋኖ ጋር ሕብረት የሌላቸው ባለሃብቶች በክልሉ የሉም ማለት ይቻልላ። ይህን ሁሉ ችግር የታቀፈው የአማራ ክልል እንዴትና ስለምን ውስጡን ማጥራት አቃተው? ምላሽ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው።

“በርበሬውን ለፍቶና ተንከባክቦ አሳድጎ የለቀመው ገበሬ ከዛሬ ነገ ለማስጫን እያቅማማ በለበት ሰዓት ማታ በሩ በኃይል ተንኳኳ። ተበረገደ። የታጠቁት ፋኖዎች መኪና ይዘው መጥተው የከመረውን በርበሬ ጫኑ። አይኑ እያየ ለፍቶ ያመረተውን በርበሬ አሟጠው ወሰዱበት። ንቅንቅ እንዳይል አስጠንቀቀውት እብስ አሉ” ይህ ቡሬ የሆነ አሳስዛኝም አሰገራሚም ድራማ ነው።

የአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢ ብዙ ሰምቷል። በየፈርጁ የሚያቀርበው ይሆናል። የእገታ ደራማና ባንክ ውስጥ የሉ የደንበኞችን ሚስጢር በማውጣት “እገሌ ይህን ያህል ገባለት” በማለት መረጃ እየሰጡ ኮሚሽን የሚሰበስቡትን መታገስ ለአፍታም ዝም ሊባል የማይገባ አሳፋሪ ተገባር እንደሆነ ግን መጠቆም ይወዳል። ሕዝብ እያለቀሰ ነው። ዛሬ በአማራ ክልል የመብት፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የቅንጦት ሆነዋል። ዘጋቢያችን እንድተረዳው አማራ ክልል ዛሬ የሕዝብ ጥያቄ “በሰላም እንኑርበት” ብቻ ነው። ሕዝብ የሰላም አየር እንዳይተነፍስ ሁለት ቦታ የሚጫወቱ የቢሮ ውስጥ ፋኖዎች ሚናቸውን እንዲለዩ መድረግ እንዳለበት ሕዝቡ አምርሮ ይናገራል። በአንዳንድ ቦታዎች ሕዝብ የመጣው ይምጣ በሚል ጥቆማ መስጠት መጀመሩን የሚናገሩ ” መንግስት የማይልመጠመጥ ከሆነና ራሱን የሚያጸዳ ከሆነ ሕዝብ ጥቆማ ለመስጠት ይነሳሳል”

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በወቅታዊዉ ጉዳዮች ላይ መክሮ ባወጣው መግለጫ ስድስት (6)ነጥቦች ጠቅሶ “ሁሉም ኃይሎች” ላላቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስቧል። ከላይ ከተነሳው አሳብ ጋር የሚገጥም በመሆኑ እንዳለ ከስር አትመነዋል።

1. በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የስርቆት፣ የእገታ እንዲሁም የግድያ ወንጀሎች እጅጉን እየተበራከተ መጥቶ ማኅበረሰባችን በሰቀቀን ለመኖር ተገዷል፤ በመሆኑም የወንጀሉ ተዋናዮች እንዲለዩ፣ ማኅበረሰባዊ ፍትሕ እንዲመጣ እና ሕዝባችንም አፎይታ እንዲያገኝ እንጠይቃለን።

2. እንደ ማዳበርያ፣ ምርጥ ዘር እና መሰል የግብርና ግብአቶች በግጭቱ ምክንያት በወቅቱ ማሰራጨት ባለመቻሉ የግብርና ምርት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል፤ የተመረተውም ቢሆን በመንገድ መዘጋት፣ በቀረጥ እና ዝርፊያ ምክንያት የገበያ ትስስሩ ስለተዳከመ ሕዝባችን እጅጉን ተጎድቷል። ስለሆነም ሁለቱም ኃይሎች በዚህ ዘርፍ ላይ ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

3. ለማኅበረሰባችን ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ያላቸው በክልሉ በንግድ እና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ ባለሀብቶች በተለዬ ሁኔታ ተጠቂ መሆናቸውን እና ይህን ሽሽትም ሥራቸውን ትተው ወደ ትልልቅ ከተሞች መፍለሳቸውን መረዳት ችለናል። ስለሆነም የሕዝባችንን ስቃይ ለመቀነስ ንግድ እና ኢንቨስትመንቶች እንዳይቋረጡ ለእነዚህ ባለሀብቶች ልዩ ጥበቃ እና ከለላ ይደረግ ዘንድ እናሳስባለን።

4. በብዙ የክልሉ አካባቢዎች በተለይ በገጠራማው ክፍል ላለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት ቆሞ እንደነበር በዚህም ትውልድ ተሻጋሪ ማህበራዊ ጉዳት እንደደረሰ ተረድተናል። በዚህ ዓመት በአንጻራዊነት የተሻለ ትምህርት የማስጀመር ሂደት እንዳለ የገምገምን ሲሆን ሂደቱ ምልዑ ይሆን ዘንድ እንጠይቃለን።

5. በጦርነቱ የሕዝብ ሃብት የሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መስተናገዱን ለማወቅ ችለናል። በመሆኑም የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ፣ ቤተ እምነቶች እና ቅርሶች ልዩ ጥበቃ እና ከለላ ይደረግላቸው ዘንድ እያስጠነቀቅን ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትም በቶሎ እንዲጠገኑ እና ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ እናሳስባለን።

6. በመጨረሻም በክልሉ በሚደረገው ጦርነት ልዩ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ያላቸው የውስጥና የውጭ ኀይሎች መኖራቸውን ታዝበናል። እነዚህ የሕዝባችን ጥንተ ጥላት የሆኑ ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እያስጠነቀቅን ሕዝባችንም በአንክሮ እንዲከታተላቸው አደራ እንላለን።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን)

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የአዲስ አበባ ሕዝብ የእናት ሀገር ጥሪ ተሳትፎና ኮሎኔል መንግሥቱ

የእናት አገር ጥሪ ከተደረገ በኋላ መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ...

ቢሾፍቱ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ፤ ኢትዮጵያን ወደ መፃኤ ዘመን የሚያሻግር የሎጂስቲክስ አብዮት

ኢትዮጵያ ከቢሾፍቱ ሰማይ ስር የኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ካርታዋን እንደገና ለመሳል...

“ጥርስ የሌለው ውሻ” የሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም መፃኢ እጣፈንታ

አዲስ ሪፖርተር - ፕሬዛዳንት ትራምፕ አሜሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት...

በዘመነ ትራምፕ ጫና ውስጥ የወደቀችው ሶማሊያ እና ለሶማሌ ላንድ ተስፋን ያለመለመው አዋጅ

አዲስ ሪፓርተር - ከሶማሌላንድ የሉዓላዊነት ጥያቄ እና ከእስራኤል እውቅና...