“አማራ ክልልን ሲመሩ የነበሩ ምንም እንዳልተፈጠረ አዲስ አበባ ሲንጎባለሉ በዝምታ ሊታልፉ አይገባም“
ሻዕቢያ መንግስት እንዲወገድና የተጠናከረ አደረጃጀት ያለው ኃይል እንዲፈጠር አይፍለግልም። ፍላጎቱ አማራ ክልል ውስጥ ተራ ትርምስ የሚፈጥሩ የጎበዝ አለቆችን ማደራጀት ነው። እየሆነ ያለውም ይህ ነው። አማራ እንደ ሕዝብ በሚታወቁ ጠላቶቹ የትርምስ አውድ እንዲሆን ነው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የውጭ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመሆን የአማራን ሕዝብ ምክንያት አልባ አድርጎ የትርምስ ማዕከል ሲያደርግ ያልሆነውን ሆነ እያሉ ሳንቲም የሚለቅሙ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋኛኖች ዋንኛ የአማራ ጠላቶች ናቸው።
የአማራ ክልል አጀንዳ ተሸካሚ ሆኖ ለዚህ ሁሉ ትርምስ ሲዳረግ ከጅምሩ የሚያውቁ የክልሉና የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መኖራቸው መሰማት ከጀመረ ቆይቷል። የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በግፍ መገደልና ከዚያም በቀጣይ ክልሉን ማተራመስ የተጀመረው ሻዕቢያ በባህር ዳር ቢሮ ከፍቶ መሰራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስለመሆኑም መረጃዎች አሉ። አዲስ ሪፖርተር “የአማራ ክልል መሪዎች ግድያ ምርመራ ወደ ክልሉ ከፍተኛ ባለስልጥናት ሲያመራ አቶ ደመቀ መኮንን ለምን አሳገዱት” በሚል ርዕስ በተከታታይ እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ይገልጻል።
ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “እኔ ባህር ዳር እያለሁ ሻዕቢያ ሁለት ሺህ ዶላር በየወሩ የሚከፍላቸው የክልሉ ባለስልጣን ነበሩ፤ የሜመነዝርላቸውም ሰው ከአዲስ አበባ ነበር የሚመጣው” ካሉ በሁዋላ ሌሎችም መኖራቸውን፣ ክፍያው አሁንም ድረስ ስለመቀተሉ፣ እንደውም ከፍ ሊል ይችላል ብለው እንደሚያምኑ አምልክተዋል። አክለውም ” የቤት ስራው የፌደራል መንግስት ነው። እኛም እናግዛለን” ብለዋል።
“ግፍ፣ ወንጀል፣ ሌብነት፣ ክህደት፣ ባንዳነት፣ ተላላኪነትና የበታችነት የሚጫወትባቸው የሻዕቢያ ቁንጮዎች፣ በተለይም ኢሳያስ አፉወርቂ ለውጡን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲመጡ ከጊዜና ካሳለፉት የጨለማ ኑሮ ተምረዋል በሚል ሲደረገላቸው ከነበረው አቀባበል ጀርባ ስራ የጀመሩት ወዲያው በቅጽበት ነበር” በሚል አስተያየት ሲሰጥ እንደነበረው “ኢትዮጵያ ላይ ልዩ ቂም እንዳለው በሚለስል መልኩ ሲንቀሳቀስ ነበር” ሲሉ ማስረሻ ሰጤ የሚያውቋቸውን ማስረጃዎች በመደርደር ምስክርነት ሰጥተዋል።
ከ1997 ምርጫ ወቅት ጀምሮ “ኢትዮጵያዊ” ካባ ለበሰው በ”ጋዜጠኛነት” ስም የሚነግዱ ከሃጂዎችን አሰማርቶ የባህር ዳር የመርዝ ችግኝ ሲተክል የቆዩት የሻዕቢያ መሪ፣ በባህር ዳር የአማራ ክልል መሪዎች ቢሮ ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍተው እንደነበር ኢትዮሪቪው “በኢትዮጵያ የኢሳያስ አፉወርቂ ዲፕሎማት በባህር ዳር “ቅርንጫፍ ቢሮ ነበራቸው?” በሚል ርዕስ ከሻዕቢያ ያመለጠ እማኝ ጠቅሶ ዲሰምበር 25 ቀን 2023 መረጃ አሰራጭቶ ነበር።
ካፒቴን ማስረሻ ሰጠኝ ከኢቢሲ ካይ ካደረጉት ቃለ ምልልስ “ሻዕቢያ ሁለት ሺህ ዶላር የወር ደመውዝ የሚከፍላቸው የአማራ ክልል ባለስልጣን ነበሩ” በማለት ይፋ ያደርገው መረጃ የኢትዮሪቪውን ዜና የሚያጎላ፣ ቀን ቆጥሮ የወጣ ምስክርነት ሆኗል።
“አዲስ አበባ እምብርቷ ላይ የተተከለው የኤርትራ ኤምባሲ ስራው ዝርፊያን ማቀናጀት፣ ሻዕቢያ ላሰማራቸው የጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ አጣቢዎችና፣ ለሴራው የሚያሰማራቸውን ፍልፈሎቹን የሚያጅልበት፣ የሚያሰማራበት፣ የዘረፉትን የሚያከማቹበት “ቶራ ቦራ” እንጂ ወግ ያለው የዲፕሎማሲ ስራ የሚሰራበት ቅጽር አይደለም” በሚል የሻዕቢያን እንቅስቃሴ የማያምኑ ሲናገሩ እንደነበሩት ካፒቴን ማስረሻም “አማራ ክልልን ለማተራመስ እንጂ ቅርጽ የያዘ አደረጃጀት ይዞ የአማራ ሕዝብን የሚመራ ድርጅት እንዲፈጠር አይፈልግም” በማለት ቻካ በነበሩበት ወቅት በድርጅት ደረጃ ሲከራከሩበት የነበረውን እውነታ በማንሳት አጋልተዋል።
ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከፈጠራቸው የተለያዩ የወቶችና ማህበራዊ አደረጃጀቶች የተገኙ / እነ ሃብታሙ፣ እስክንድርን እና እዛ ዙሪያ ያሉትን ነው/ በማሰባሰብ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች በመጥለፍ ክልሉን ለማተራመስ ዕቅድ ለያዙት ሻዕቢያና ትህነግ መሳሪያ የሆኑ ዲያስፖራዎችን “ተላላኪ” ሲሉ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ አመልክተዋል።
“አማራ የለም ሲሉ የነበሩና የአማራ ወኪልን ያስበሉ” ያሉዋቸውን ተላላኪዎች / እነ ፕሮፌሰር አስራትን ወልደየስን ያስገደሉ ለማለት ነው፣ ዛሬ የአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው ፊትለፊት ሲጮሁ እንደሚታዩ ያመለከቱት ማሰረሻ ሰጤ፣ አማራ ክልል ሰላም እንዳይሆን፣ በሰላማዊ ድርድር ችግሩ እንዳይፈታ በውስጥም በውጭም ተቀናጅተው የሚሰሩ መኖራቸውን አጋልጧል።
ድርጅታቸው አህፋግ በአፍሪካ አደራዳሪዎች በጥር ወር 2017 ድርድር ሲጀመር በፌደራል፣ በክልሉና በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉ ንግግሩ በውጤት እንዳይተናቀቅ ከፍተኛ ጫናና ሴራ ይፈጽሙ እንደነበር ያስረዱት ካፒቴን ማስረሻ፣ ሻዕቢያ በቀጥታ “ድርድር ብሎ ነገር የለም፣ የምትደራደሩ ከሆነ የቁስና የመሳሪያ እርዳታ አቆማለሁ” በማለት መመሪያ መስጠቱን ይፋ አድርገዋል። በውቅቱ መረጃው ያላቸው ሻዕቢያ ድርድር እንዳይደረግ መመሪያ መስጠቱን ሲያስታውቁ “የብልጽኛ ተከፋይ” በሚል ሻዕቢያ እንደሚያስተዳድራቸው የሚታወቁ ሚዲያዎች በስፋት ቅስቀሳ ሲያካሂዱ እንደነበር አይዘነጋም።
ካፒቴን ማስረሻ በሰላማዊ መነገድ መግባታቸውን ተከትሎ የኤርትራ የወሬ ሚኒስትር የማነ በቲወተር ገጻቸው ” አንድ ሰው እጅ ሰጠ ማለት ፋኖ ገባ ማለት አይደለም” የሚል ይዘት ያለው የማንኳሰስ መረጃ ሲስያሰራጩ ” እውነትም ነገሩ የሻዕቢያን ቆጣሪ የነቀለ እርምጃ ነው ለካ” በሚል የአህፋግ ወደ ሰላም መጣት ከፍተኛ ፖለቲካዊ እንደምታ እንዳለው ማረጋገጫ ሆኖ ተወስዷል።
ሻዕቢያ የሚመራቸው ሚዲያዎች ነገሩን ሊቃልሉ ቢሞክሩም ካፒቴኑ ” በዚህ ድርድር አፋህድ ከፍተኛ የኃይል ማዛባት ስራ ሰርቷል። በጥቅም የተሳሰሩ ሲያራምዱት የነበረውን ፖለቲካ አምክንነናል” ማለታቸው አቶ የማነ ቲዊት ካደረጉት ጋር ሲመዘን በትክክልም ሻዕቢያ ሊያኮላሸው የሞከረው ድርድር መሳካቱ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳሳደረበት እንደሆነ አመላካች ሆኗል።
በኤርትራ ወልቃይትን አሳልፎ ለመስጠት የተደረሰ ስምምነት
ሌላው ማስረሻ ሰጤ ያጋለጡት ትልቁ ጉዳይ “ተላላኪ” የሚባለው ፋኖ ወልቃይትን ለመስጠት መስማማቱን ነው። አማራ አገር እንዲሆን እንዲገነጠል የተዘጋጀ ሰነድ ይዘው ይዘው ኤርትራ አረና በሚባል ቦታ ስለተደረው ስብሰባ ነው።
ይኸው በቅርቡ በ2018 አረና ኤርትራ በተደረገው ስብሰባ ዘመነ ካሴ ጎጃምን በመወከል፣ ቡሩክ ከርክ ከሸዋ፣ ሄኖክ ከውወሎ፣ ሃብቴ ከጎንደር እንዲሁም የትህነግና ሻዕቢያ ጀነራሎች የተሳተፉበት ስብሰባ ዋናው ጭብጡ “ወልቃይትን አስረክቡን፣ አራት ኪሎን እናስረክባችኋለን” የሚል እንደነበርና ይህም ሻዕቢያና ትህነግ የፈጠሩት ስትራቴጂካል ግንኙነት አካል እንደሆነ ከካፒቴን ማስረሻ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።
ይህንኑ ዜና መርጃውን ያገኙና ብሄራዊ ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ሚዲያዎች በስፋት ሲያጋልጡ፣ ሻዕቢያ የሚከፍላቸውና የሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎችና ባለቤቶቻቸው በማስተባበል “ተራ የብልጽግና ወሬ ነው” በሚል ሲሟገቱ እንደነበር አይዘነጋም።
የካፒቴን ማስረሻ ቃለ ምልልስ ከሻዕቢያና ትህነግ ደባ በተጨማሪ አድበተው የተቀመጡና ክልሉን ሲመሩ የነበሩ ባለስልጣናትን ጉዳይ ነው። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ተፈፀመ በተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች የአዴፓ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ከተገደሉ ክልሉን በመቀባበል የመሩትና የክልሉ የፓርቲ መሪ በመሆን ለረዥም ጊዜ የቆዩት አቶ ደመቀ ስለተጠቀሱት ጉዳዮች መረጃ እንዲሰጡ መገደድ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ነው።
ዶክተር ይልቃል ከፋለ ግድያ ሲፈጸም ምክትል ነበሩ። ዘመነ ካሴና እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በሁዋላ እንዲፈቱ ሲደረግም እሳቸው ነበሩ። አቶ ደመቀ የክልሉ ፓርቲ መሪ በመሆን ረዥም ዓመታት ከመቆየታቸውም በላይ በክልሉ አመጽ ውስጥ እጃቸው ካለበትና ራሳቸው በገሃድ ትግሉን እንመራለን ካሉት ባለሃብት ጋር ጭምር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው መረጃዎች አሉ። የሰኔ15 ግድያ ምርምራ ወደ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ሲያመራ በፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አስወስነው ያሳገዱትም እሳቸው ናቸው። አዲስ ሪፖርተር በዚህ ዙሪያ በቂ መረጃ አሰባስባ ያጠናቀቅች ሲሆን በተከታታይ ለንባብ ታቀርባለች።
የክልሉ ባለስልጣናት ከሻዕቢያ ጋር ሲሰሩ፣ ሻዕቢያ ባህር ዳር እክልሉ መስተዳድር ውስጥ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲከፍት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በግልጽ ቀርበው መጠየቅ እንዳለባቸው የሚጎተጉቱ አካላት ይህን አጅንዳ ለፍትህ እንቆማለን የሚሉ በሙሉ በማጉላት ጫና ሊፈጥሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። ይህ ሲሆን ምን አልባትም የአማራ ክልል ቀውስ ሊያጥርና የመፍትሄው ቁል በቶሎ ሊገኝ እንደሚችል ይገልጻሉ።
Website፡ https://addisreporter.com/
Email፡ info@addisreporter.com
Telegram፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
Phone no ፡ +251981866434 / +251116393393






