ክህደት ክራባት ለብሶ ቆሞ አየነው። ክህደት ጓሮ ለጓሮ ከሚርመጠመጥበት የከተማ ጥሻ ወጥቶ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴሊቪዝን ያለ አንዳች አፍረት ግብጽ፣ ሱዳንንና ሻዕቢያን ሲሳለማቸው አየን። ክህደት ስጋና ደም ሆኖ በኢትዮጵያዊያን ፊት ራሱን አስተዋወቀን። ክህደት ሊፒስቲክ በተቀባ አሳማ ተመስሎ በአገራችን ብሄራዊ ቴሌቪዝን ጥርሱን ሲፍቅ፣ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ጭራ ሲቆላ ተገለጠ። ተፈጥሮው እርም ነበርና እርም ሆኖ እዚህ ትውልድ ፊት ቀረበ። ቀርቦም “እኔ ክህደት ነኝ ምረጡኝ። ላስተዳድራችሁ” ብሎ ተሳለቀ። ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን የክህደት ማስተማሪያ አድርጋ በህግ “ስሙን የጠራ ወዮልኝ” የሚያሰኝ ቆፍጣና ትጣ?
አለባቸው ጉብሳ- ነፃ አስተያየት
አዲስ ሪፖርተር – በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቴሌቪዥን የፓለቲካ ፓርቲዎች በውጭ ጉዳይ ፓሊሲያቸው ዙሪያ ያቀረቡትን የምርጫ ክርክር በንቃት ተከታተልኩት። በዚህ ክርክር እጅግ አስደንጋጭ እና አሳፋሪ ሆኖ ያገኘሁት የኢሕአፓ ተወካይ (የአብን የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ተመራጭ) ያቀረበው መከራከሪያ ሃሳብ ነው።
ይህ የኢህአፓ ተወካይ ኢትዮጵያን በሱዳን ግጭት ውስጥ የ”አረብ ኤምሬትስ ተላላኪ” አድርጎ ይከሳል። ግጭት ጠማቂ እና ተንኳሽ አድርጎ ይናገራል። ክርክሩን የሚመራው ጋዜጠኛ ቢጨንቀው “ሱዳን የሕወሃትን አርሚ 70 በማሰልጠንና በማስታጠቅ ሃገራችንን እንዲወጋ እያደረገ መሆኑን ታውቃለህ?”ብሎ ጠየቀው። ምንም ምላሽ አልነበረውም። የሚገርመው ይህ የኢሕአፓ ተወካይ ለሚያቀርበው የክስ ሙግት ተጨባጭ ማስረጃ አልነበረውም። ኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በሱዳን ግጭት ውስጥ ምን ዓይነት የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ መከተለ እንደሚገባት አያመላክትም። ምንም ዓይነት የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስልት እንዳላቸው /ይኖራል ብዬ አላስብም/ አይነግረንም።
እኚሁ የኢህአፓ ወኪል የሚያቀርቧቸው የክስ ጭብጦች ታሪካዊ ጠላቶቻችን ግብፅ፣ ኤርትራና ጀነራል አልቡርሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዝሩዋቸውን የፈጠራ ክሶች በመድገም ነው። ባጭሩ የኢህአፓው ተወካይ አቀራረብ ከዚህ በፊት አዲስ ሪፓርተር ጀዋር መሃመድ እና የዲያስፓራ ሊሕቃን ከሃገራቸው ብሄራዊ ጥቅም በተቃራኒ ሚያስተጋቡትን የሃሰት ትርክት በተመለከተ በሰፊው ትችት ካቀረበችበት የተለየ አይደለም። እንደውም መናበብ የሚታይበት ነው።
ይህን ክርክር ከሰማሁ በኋላ ኢሕአፓን ከፍጥረቱ ጀምሮ የፈፀማቸውን የሃገር ክህደቶች ከታሪክ ድርሳናት ለመፈተሽ ሞክርኩ፣ ይገርማል። ኢሕአፓ በሃገር ክህደት የሚስተካከለው ሌላ ፓርቲ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። አሁንም ይህ የክህደት አባዜ የተዋንያን ለውጥ ካልሆነ በስጠቀር በግብር አንድ ሆኖ አገኘሁት። ይህ ተደጋጋሚ ክህደት በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ተዘንግቶ እንደ ፓለቲካ ሃሳብን የመግለፅ መብት ሆኖ አረፈው። ክህደት እንደ ትግል ስልት የሚቆጠርበት እና የሚያሸልም ደረጃ ላይ ደረስን። ክህደት ራሱ በአገራችን ሚሊዮኖች እየይዩት ክራባት ለብሶ ቆሞ እየነው። ኢትዮጵያ በብሄራዊ ቴሌሊቪዥን ዜጎቿ ፊት ቆሞ ለኤርትራ፣ ለሱዳንና ግብጽ የሚሟገት “ከሃጂን” ተዋወቀች። አሳዛኝም፣ አሳፋሪም፣ አስቸኳይ መላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ!! ከብዙ ትካዜና ምን አልባትም የውስጥ ለቅሶ በሁዋላ በኢሕአፓና በሌሎች የፓለቲካ ሃይሎች የተፈፀሙትን የሃገር ክህደቶች፣ እነዚሁ ከሃጂዎች ያደረሱትን ብሄራዊ የደህንነትና ኢኮኖሚ ጉዳት በመገምገም ይህ ክፉ ልምምድ በአዲሱ ትውልድ እንደይደገም ቢያንስ የዜነቴን ለተንፍስ ብዬ በጉዳዩ ላይ ሃሳቤን ለማጋራት ወደድኩ።
የኢሕአፓ የክህደት አዙሪት
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ያህል ብሄራዊ ክህደት በመፈፀም ተወዳዳሪ የሚገኝለት ፓርቲም ሆነ ይፖለቲካ ተቋም ያለ አይመስለኝም። ካለ ወዲህ በሉኝ። ኢህአፓ በስልጣን ፉክክር እና በብሔራዊ ጥቅም መካከል ያለው መስመር በማደብዘዝ የሃገር ክህደት ትርጉሙን በማጥፋት ይታወቃል። ድርጅቱ ገና ከጅምሩ ለሻዕቢያ የነፃነት ትግል እውቅና በመስጠት፣ የሀገሪቱን የግዛት አንድነትና የባህር በር ባለቤትነት መብት አደጋ ላይ የሚጥል አቋም አንግቦ የተነሳ ግርድና መሰረቱ የሆነ ፓርቲ ነው። ይህ ስትራቴጂካዊ ስህተት ኢትዮጵያን የባህር በር አልባ በማድረግ ለዘመናት የሚቀጥል የኢኮኖሚና የደህንነት ስጋት ውስጥ እንድትገባ በር ከፍቷል። የሚገርመው ዛሬ ድረስ አይጸጸትም። ይባስ ብሎ ህጻናትንና ሰባኪያንን አዲስ ካባ አልብሶ “የቀበሮ ባህታዊ” ሆኖ ብቅ ብሏል።

ድርጅቱ ከመንግስት ጋር የነበረውን ቅራኔ ከጅምሩ በሽብር ተግባራት ለመፍታት ጥረት አድርጓል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመጥለፍ የሀገርን ገጽታና ስትራቴጂካዊ ሀብት ላይ ጉዳት አድርሷል። በተጨማሪም፣ በከተማ ሽምቅ ውጊያና በ”ነጭ ሽብር” ሳቢያ ሀገሪቱ ያስተማረቻቸው የተማሩ ወጣቶች በከንቱ እንዲረግፉ አድርጉላ። ግብረ መልሱ ሌላ አነጋጋሪ ቢሆንም የኢህ አፓ ጦስ ጧሪ አልባ ያደረጋቸው እናቶችን ቤቱ ዩጠረው። ይህ ተገባሩ የሀገርን የሰው ኃይል ካፒታል ያመከነ የታሪክ ጥፋት ተደርጎ ተመዝግቧል።
በገጠር የሽምቅ ውጊያ ወቅትም፣ ለሀገር ህልውናና ለህዝብ ጥቅም ታላቅ ተስፋ የነበረው የ”ጣና በለስ ፕሮጀክት” እንዲከሽፍ በማድረግ፣ የልማት ጥረቶችን አደናቅፏል። እነዚህ ድርጊቶች የሚያሳዩት፣ ድርጅቱ “ደርግን መጣል” የሚለውን ግብ ከሀገር ህልውና በላይ አስበልጦ በመያዙ፣ የኢትዮጵያን ሃገራዊ ሕልውና አደጋ ላይ መጣሉን ነው። አሁንም በዛው በለመደው ሃዲድ ላይ እየበረረ ነው።
ኢሕአፓ በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ወቅት የፈፀመው የክህደት ተግባር ሌላው በቀይ ቀለም የተጻፈለት ገድሉ ነበር። ከወራሪው ዚያድ ባሬ ጋር “ታክቲካዊ ጥምረት” በመፍጠር፣ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ከጀርባ ሆኖ ወግቷል። ወራሪው ኃይል አዋሽን ሊዘልቅ እየተንደረደረ በነበረበት ወቅት ኢህአፓ “ጭቁን በጭቁን ላይ አይዘምትም” በሚል የተጠናገረ ርዕዮተ-ዓለም ሽፋን፣ ሰራዊቱ ለሀገሩ እንዳይዋጋ ቅስቀሳ አድርጓል። የውጭ ወራሪን ስትራቴጂካዊ ግብ (Irredentism) ከማሳካት ያልተናነሰ ሚና ተጫውቷል። ይህ የታሪክ ጠባሳ፣ የፖለቲካ ልዩነት ወደ ሀገር ክህደት ሲያድግ የሚስከትለውን አውዳሚ ውጤት በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። ይህ ፓርቲ ነው ዛሬም በአደባባይ ዓይኑን በጨው አጥቦ ለግብጽ፣ ለኤርትራና ለሱዳን ወኞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት የግርድናውን ዕድገት እያሳየን ያለው።
የሃገር ክህደት ትርጉም ሲጠፋ…..
የሲአይኤ የቀዝቃዛው ጦርነት ኦፕሬቲቭ የነበረው ጳውሎስ ዊልያምስ (Paul Williams) “How Subversion Works” በተሰኘው መጽሐፉ፣ የአንድ ሀገር መከላከያ አቅም የሚፈራርሰው ጠላት ከውጭ ሲመጣ ሳይሆን፣ ክህደት በሃገር በውስጥ ትክክለኛ ስሙን ሲያጣ መሆኑን ያስረዳል።
When Treason loses its meaning, no nation can offer effective resistance to a foreign aggressor
ነፃ ትርጉሙም “የሀገር ክህደት ትርጉሙን ሲያጣ፣ ማንኛዋም ሀገር የውጭ ወራሪን ለመከላከል አቅም አይኖራትም” እንደማለት ነው። የሀገር ክህደት (Treason) እንደ ልዩ የፖለቲካ እይታ (Political dissent) ተቆጥሮ መቻቻል ሲጀምር፣ ሀገር ለውጭ ጠላት ተጋላጭ እንደምትሆን ያሳያል። የሀገር ክህደት ትርጉሙ “ለሀገር ካለ ታማኝነት በመውጣት፣ ከጠላት ጋር ማበር ወይም የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መፈጸም” ቢሆንም፣ አሁን ላይ ይህ ትርጓሜ እየደበዘዘ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት ኢሕአፓ እንደገና በሕጋዊ መንገድ ተደራጅቶ ቢንቀሳቀስም፣ “ያደቆነ ሴጣን ሳያቄስ አይለቅም” እንዲሉ የጥንቱን አፍራሽ ባህሪውን አሻሽሎና አዘምኖ እንደ አሳማ ሊፒሲክ ተቀብቶ መጥቷል። የታሪካዊ ጠላቶቻችንን የግብፅን፣ የኤርትራን እና የጄነራል አልቡርሃንን የስነ-ልቦና ጦርነት አጀንዳዎች በማስተጋባት፣ የሀገርን የውጭ ግንኙነትና ስትራቴጂካዊ ነፃነት ለማዳከም እየሰሩ መሆኑን በገሃድ አሳይቶናል። ኢትዮጵያ በሱዳን ጉዳይም ሆነ በሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች የራሷን ብሔራዊ ጥቅም መሰረት አድርጋ የምትወስነውን ሉዓላዊ እርምጃ፣ ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ “የሌላ ሀገር ተላላኪ” ብሎ መፈረጅ፣ የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ክብር የሚነካና ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ግብዓት የሚሰጥ ተግባር በኢትዮጵያዊያን ፊት ፈጽሟል።
ይህ ዓይነቱ ድርጊት የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት የማይተናነስ “ክህደት” ነው። አንድ ፖለቲከኛ ወይም ድርጅት የራሱን መንግስት ለመቃወም በሚል ስሌት፣ የሀገሩን የደህንነት ስጋቶች ችላ ብሎ ከውጭ ኃይሎች ጋር ተመሳሳይ አጀንዳ ሲያራምድ፣ የጳውሎስ ዊልያምስ ስጋት እውን መሆኑን ያሳያል። ክህደት በ”ዴሞክራሲያዊ የመናገር መብት” ስም ሲሸፈን፣ የዜጎች ለሀገር ያላቸው ታማኝነት እየቀነሰና የሀገር መከላከያ ግንብ እየተናደ ይሄዳል። ኢህአፓ እንደ አዲስ ተቀባብቶ የመታውም ይህኑኑ ለመተግበር እንደሆነ ቅንጣት ጥርጥር የለውም።
ግብፅ እና ቱርክ ጄነራል አልቡርሃንን በግልጽ በጦር መሳሪያ እና በፕሮፓጋንዳ ሲደግፉ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ለደህንነቷ የሚበጀውን ወገን የመደገፍ ወይም የሰላም ጥሪ የማቅረብ ሉዓላዊ መብት አላት። ይህ “ፕራግማቲዝም” (Pragmatism) ይባላል። ከሀገር ጥቅም ይልቅ የሌሎች ሀገራትን ትረካ (Narrative) በማቀንቀን የራስን ሀገር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማዳከም፣ ለውጭ ወራሪ በር ከመክፈት አይተናነስም። ለዚህ ነው ክህደት ክራባት ለብሶ በኢትዮጵያዊያን ፊት ቆሞ አየነው ያልኩት።
እንዲሁም የሀገር ክህደት ወንጀልን በዘውግ የነፃነት ትግል ስም ትክክለኛ (Justify) ለማድረግ መሞከር የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ነው። ፖለቲከኞች ለራሳቸው ብሔር ወይም ቡድን ጥቅም ሲሉ ከውጭ ጠላቶች ጋር በሚያደርጉት ድብቅ ስምምነት፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ለድርድር እያቀረቡ መሆኑን መረዳት ይገባል። የልዩነት ሸንተሮቻችን በሰፉ ቁጥር፣ የውጭ ኃይሎች በእነዚህ ስንጥቆች ውስጥ ገብተው ሀገርን ለማፍረስ እንደሚጠቀሙባቸው ካለፈው ታሪካችን ልንማር ይገባል።

ትህነግ፣ ፋኖ እና ኢሕአፓን የመሰሉ ስብስቦች አሁን ላይ እያሳዩት ያለው አቋም፣ ከደርግ ጋር በነበረው ጥላቻ ሳቢያ ሶማሊያን እንደ ደጋፊ ከቆጠረው የትላንቱ ስህተት ያልተማሩ መሆናቸውን ያሳያል። “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚለው ብልሹ የፖለቲካ ስሌት፣ ሀገርን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት እንደ ምክንያት ሊቀርብ አይችልም። የኤርትራን እና የሌሎችን ቀጠናዊ ተዋንያን ስትራቴጂካዊ ግብ ሳይረዱ፣ በታክቲካዊ አንድነት ስም እናት ሀገርን መውጋት የውርደት ውርደት ነው።
የኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት እየተሸረሸረ በሄደ ቁጥር፣ የብሔራዊ ጥቅም ትርጓሜውም ይደበዝዛል። አንድ ፖለቲከኛ የራሱን መንግስት ለመጣል ሲል የሀገሩን ሰራዊት የሚሳደብ፣ የሚከስ እና ለጠላት መረጃ አሳልፎ የሚሰጥ ከሆነ፣ ያ ድርጅት ወይም ግለሰብ የትኛውን ህዝብ ነጻ ሊያወጣ እንደሚችል ግልጽ አይደለም። ክህደቱ በደምና በቃላት እየታጀበ በሄደ ቁጥር ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ሀገር እንዳትኖረን ያደርጋል።
እንደ መውጫ
በመሆኑም ከዚህ ከጥፋት መንገድ ተመልሶ በአንድ ሃገር ልጅነት ልዩነቶችን በውይይት እና በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍታት ብቸኛው አማራጭ ነው። የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ኢትዮጵያን ማዳከም እንጂ የትኛውንም ብሔር ወይም የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን ማውጣት አይደለም። ይህን ተረድቶ ለሀገር ክብር መቆም ካልተቻለ፣ ታሪክ በክህደት መዝገቡ ላይ ስማችንን ከማስፈር አይመለስም። አልፎ ተርፎም የወንጀል ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል። በተጨማሪም አዲስ ሪፓርተር በተደጋጋሚ እንደምታሳስበው የውጭ ጠላቶች የሚነዙትን የሃሰት መረጃ (Disinformation) እና የስነ-ልቦና ጦርነት ለመመከት፣ መንግስት እውነተኛ መረጃዎችን ለሕዝቡ በፍጥነት የሚያደርስበት እና ብሔራዊ ስሜትን የሚገነባበት ተቋም ማጠናከር ይገባዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






