አዲስ ሪፖርተር – በትህነግ የሰዓት አቆጣጠር የጦርነት ማስጀመሪያ ግብአቶች ተሟልተዋል የሚሉ እየበረከቱ ነው። ዝርዝር ጉዳዮንም እየቆጠሩ ይህንኑ ኣባቸውን ያጠናክራሉ። “በሕዝብ ለሕዝብ” ስም የተጀመረውን “ጽምዶ” የመንግስት ለመንግስት ለማለት የሻዕቢያና የትህነግ አመራሮች ትግራይ እየመከሩ እንደሆነ እየተሰማ ነው።
በሌላ በኩል “ምርጫውን እንቅደም” የሚሉ ሕዝብ እንዲያምጽ ተግተው እንደሚሰሩ እያስታወቁ ነው። “የኃይማኖት ግጭት” ውጤታማ የአመጽ ማቀጣጠያ ስልት እንደሆነ ተገምግሞ እንዲቀጥል ውሳኔ መሰደረሱ በተሰማ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የሰከነችውን ጎንደርን ለማተራመስ የሙስሊሙ ህዝብረተሰብ የሚያከብራቸው መሪ ተገድለዋል።
በአርሲ በተደጋጋሚ እየተካሄደና አሁን ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንደሆነ ማረጋገጫ የወጣበት የንጹሃን ግድያ ልዩ የእምነት አጀንዳ ተበጅቶለት ህዝብ እንዲበሳጭ በማድረግ ሚዲያዎች እየተቀባበሉት ነው። ከተፈጸመው ግድያ በተጨማሪ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የበለጽጉ ፎቶዎች እየተሰራጩ ነው።
በወለጋ ጃዋር የብሄር ግጭት እንደሚነሳ አስቀድሞ ይፋ ባደርገው መሰረት የፋኖ ታጣቂዎች ነጹሃንን መግደላቸው ይፋ ሆኗል። በርካቶች ተፈናቅለዋል። ጃዋር አስቀድሞ እልቂት እንደሚፈጸም ካስታወቀ በኋላ “መንግስት ያጣራ” በሚል ጥያቄ አቅርቧል። ጃዋር ግብጽ ደርሶ ከመጣ በኋላ የተከመረው ይህ ግድያና መፈናቀል ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ሕዝብ እንዲቆጣ የሚዲያ ስራ እንዴት እንደሚሰራ ስልት ተነድፏል። አዲስ ሪፖርተር ያየችው የሚዲያ አጠቃቀም ሰነድ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
“እነ ጃዋር ኢትዮጵያ የሱዳን ፈጣን ኃይሎችን እየረዳች ነው” በሚል በይፋ የጄኔራል አልቡርሃንን መንግስት በመደገፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ሳይቀር ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው። ቅሰቀሳቸውና አቋማቸው ከሱዳን፣ ከግብጽና ከሻዕቢያ ደጋፊዎች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ጎን ለጎን ሌላ የአመጽ ጥሪ ለማስተላለፍ ለመጪው ማክሰኞ ቀጠሮ ይዘዋል።
ጄኔራል አልቡሃንና የኤርትራ መንግስት ከግብጽ በሚቀርብላቸው የጦርነት ግብአትና በጀት ኢትዮጵያ ላይ ታጣቂ በማደራጀት፣ በማሰልጠንና በማስታጠቅ፣ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነት በመደገፍ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እያደረጉ ያለው ዘመቻ አገሪቱን ለመበተን ያቀደ እንደሆነ አብረዋቸው የሚሰበሰቡ እየገለጹ ነው። ይህ ሁሉ እየተካሄደና እየተጠነሰሰ ጎን ለጎን የአገር መከላከያን የፓርቲና የግለሰብ ሰራዊት በማድረግ ለክ እንደ 1983 እንደሚበተን እየተዛተ ያለው።
“በትግራይ የቀን አቆጣጠሩ አሁን ላይ 2018 ሳይሆን 2014 ዓ.ም ነው” ሲል የሽሬው ነዋሪው ለአዲስ ሪፖርተር እንዳለው አሁን ላይ ትግራይ እየሆነ ያለው ልክ እንደ ነሃሴ 18 ቀን 2014 ሁለተኛው ዙር ጦርነት ሊጀመር ሰሞን የነበረው ዓይነት መልክ ነው። አዲሱ ነገር የሻዕቢያ ኃይሎችና የፋኖ ኃይሎች መታከላቸው ነው። ግብጽና ሱዳን በይፋ አጋር ተደርገው ኢትዮጵያዊ ነን በሚሉት ሳይቀር የመወደሳቸው ጉዳይ ነው።
የጦር ካሚዮኖች ይሯሯጣሉ። ምሽግ ይቆፈራል። መሳሪያ ይጋጋዛል። ወታደሮች ይመረቃሉ። አዳዲሶች ይሰለጥናሉ። ስብሰባዎች፣ የድጋፍ ሰልፎች፣ ቅሰቀሳ ማሰባሰብ፣ ድርቆሻ ማዘጋጀት፣ በሶና ቆሎ ወዘተ መቋጠር ተጧጡፏል። መዋጮ ቤት ለቤት እየተሰበሰበ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ለሁለት ከተከፈለ በኋላ አሁን ላይ የጦርነት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ይመስላል። ነገር ግን “ዘው ብሎ ጦርነት ውስጥ ገባ እንዳይባል፣ የጦርነት ግብአቶችን እያሟላ ነው” የሚሉ ከዝግጅቱ ጎን ለጎን እየቀረቡ ያሉትን የፕሮፕጋንዳ ዓይነቶች ይዘረዝራሉ። ትህነግ ትግራይ ተከባለች፣ ፌደራ መንግስት በጀት ከልክሏል፣ መድሃኒት የለም፣ ነዳጅ አይገባም፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሷል ወዘተ የሚሉ ድምጾችን በስፋት እያስተጋባ ነው። የፌደራል መንግስት ስምምነቱ እንዲከበር ቁርጠኛ መሆኑን ይናገራል። ስምምነቱን የፈረሙት የትህነግ ወኪሎች የፕሪቶሪያው ስምምነት የተጣሰው በትህነግ እንደሆነ ይመስክራሉ። ሕገመንግስት ጥሶ ከውጭ ኃይሎች ጋር በይፋ ህብረት መፍጠሩንም ለሕዝብ እያስታወቁ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትግርኛ ቋንቋ “|አልሰማንም” እንዳይባል ሁሉንም ጉዳይ ይፋ ማድረጋቸውን ያስታውቃሉ።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ በርዕስ ለኢትዮጵያ መንግስትና የሚኒስትር ተቋማት የሚላኩ ደብዳቤዎች ወደ ዓለም ዓቀፍት ተቋማት ይላካሉ። ደብዳቤዎቹ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለተባበሩት መንግስታትና ለተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች በተከታታይ ይላካሉ። የሁሉም ደብዳቤዎች ዓላማቸው ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ዘንድ መረጃ ማድረስ እንደሆነ የተለያዩ ወገኖች እየተናገሩ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት መሪ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የድርጅታቸውን ደዳቤዎች እያሰራጩና እያዳረሱ መሆኑን በመግለጽ የሚከሱ አሉ።
ጎን ለጎን ትህነግ በተደጋጋሚ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ፍላጎት እንዳለው ያሳያል። በድርድር ጥያቄው ላይ የቀደመው የወልቃይት ጠገዴ አስተዳደር እንዲመለስ፣ የታገደው የትህነግ ፈቃድ እንዲመለስ፣ ከዚህ ቀደም የተደረገው ምርጫ እንዲጽድቅለትና በትግራይ በ2018 ምርጫ እንዳይደረግ ወዘተ በቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል። የትግራይ ሰላም ኃይሎች እንደሚሉይ ትህነግ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ የማያግባቡ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ትህነግ ይህን የሚያደርገው “ወደ ጦርነት የገባሁት ሁሉንም አግባብ ተጠቅሜ ከአቅሜ በላይ ስለሆነብኝ ነው?” ለማለት ባሰላው ስሌት መሆኑን ይናገራሉ። በሌላ በኩል መግለጫ እያወጣና የድርድር አሳብ እንዳለው እየገለጸ ጊዜ ሲገዛ መቆየቱን ያመልክታሉ።
ነሀሴ 18 ቀን 2018 ሁለተኛው ዙር ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ትህነግ በተመሳሳይ የዓለም ዓቀፍ ተቋማትን፣ አገራትን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪዎችን፣ ሚዲያዎችን ወዘተ በመጠቀም መድሃኒት፣ ቀለብ፣ ነዳጅ፣ ተሽከርካሪ፣ በጀት በበርና በውጭ ምንዛሬ፣ አልሚ ምግብ ወዘተ በገፍ ገብቶለት እንደነበር የሚያስታውሰው የሽሬ ነዋሪ፣ አሁንም በተመሳሳይ ትህነግ ይህንን ዘመቻ መጀመሩን ያስታውቃል።
የትግራይ አንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ነዋሪዎች ነዳጅ ወደ አስመራ እንደሚጋዝ ይናገራሉ። ሸቀጥ በገሃድ እየተጫነ በሰልፍ ወደ አስመራ ሲተም በድንበር አካባቢ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ቪዲዮ እየቀረጹ ይፋ አድርገዋል። ማዕድን በተለይም ወርቅ በገሃድ በአስመራ በኩል ለሽያጭ እንደሚቀርብ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ የትህነግ ወዳጅ ሚዲያዎች ሳይቀር በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርገዋል። እነዚህን መረጃዎች የሚጠቅሱ ወገኖች እንደሚሉት ትህነግ አሁን የሚያሰማው ድምጽ ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ምክንያት እንዳለው ለማሳየት ነው።
የትህነግ ኃይሎች መንግስት እጁን ተጠምዝዞ አስፈላጊ ግብአቶችን ካቀረበላቸው በኋላ፣ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በስፋት በመግባት እስከ ደብረ ብርሃን እና ጭፍራ ድረስ ዘልቀው ገቡ። ጦርነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም. ድረስ ቆየ። እስር ቤት የነበሩ የትህነግ አመራሮች የሽግግር መንግስት መመስረት ጀመሩ። እነ ጃዋርና እነ ስብሃት ነጋ እስር ቤት ሆነው በሽግግር መንግስት ምስረታ እየተወያዩ ሳለ ጦርነቱ በድንገት መልኩን ቀይሮ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈረመ። ሻዕቢያና የሚታወቁ መንግስት ውስጥ የነበሩ የፋኖ መስራቾች በስምምነቱ ማኩረፋቸው ተሰማ።
ዛሬ 2018 ዓ.ም ቢሆንም የ2015 ቱን ወቅት እያስታወሰ ያለው ከላይ በተቀመጡት ምክንያቶች ነው። ለትህነግ እንደሚሰሩ የሚታሙና አድልዎ ሲፈጽሙ የተያዙ የሰብአ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መካከል አምነስቲ የጃልመሮ ሰራዊትን ግፍ በመዘገብ በትህነግ ጉዳይ የቀድሞ ድጋፉን ለማስጀመር እየተሟሟቀ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው። ጦርነት በበር ላይ መሆኑንና ፊሽካ ሊነፋ መቃረቡን በመረዳት ለትህነግ የሚዲያ ድጋፍ ለመስጠት እንዲቻል እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቅድመ ሁኔታ በማመቻቸት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች እየወጡ ነው።
የትግራይ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ተደጋጋሚ መረጃዎች በማሰራጨት ለዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች መግለጫ ግብአት እያቀበለ ሲሆን እንዴት እንደሚሰራ ለዜጎች ሁሉ ግራ የሆነው የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሲተነፍስ አይሰማም። ማስተባበያም ሆነ አዲስ መረጃ መስጠት የተሳነው የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለምን እንደተቋቋመ የማይገባቸው “በአዋጅ እንደተቋቋመ በአዋጅ ቢፈርስስ” እያሉ ነው። ምክንያቱም ይህ ተቋም ጦርነት ቢጀመር ወይም የከፋ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቢከፈት ምንም የማድረግ አቅም የለውም በሚል ነው።
በየትኛውም መስፈርት ጦርነት እንደማያዋጣ የሚመክሩ ሁሉም ወገኖች ለውይይት ደግመው ደጋግመው እድል እንዲሰጡ ይወተውታሉ። በትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደሰለቸው በተደጋጋሚ ይነገራል። ያም ሆኖ የጦርነት ዝግጅቱ አልቆመመ። ዛሬ እንደተሰማው የሻዕቢያና የትህነግ ኃይሎች በመቀለ ስብሰባ ተቀምተዋል።
ንግግራቸውም የሕዝብ ለሕዝብ የሚባለውን ስምምነት ወደ መንግስት ለመንግስት አሳድገናል በሚል በይፋ ለማወጅ ነው። የትግራይ ሰላም ኃይሎች የፕሮፓጋንዳ ክፍል ኃላፊ “ስብሰባ መቀመጣቸውን እናውቃለን። ይህ ጽምዶ ለትግራይ ሕዝብ አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም። አመራሮቹ ለሌብነታቸው ምሽግ እንዲሆናቸው የፈጠሩት ነው” ሲሉ ለአዲስ ሪፖርተር ተናግረዋል።
የትህነግ አመራሮች በኤርትራ ቢሮ፣ የወታደር ማሰልጠኛ፣ የፓስፖርትና ተመሳሳይ አገልግሎቶች እየተመቻቸላቸው እንደሆነ እኚሁ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊ አመልክተዋል። አያይዘውም ይህ ጦርነቱ ከተጀመረ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሳያ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






