ኢትዮጵያ ከቢሾፍቱ ሰማይ ስር የኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ካርታዋን እንደገና ለመሳል ተዘጋጅታለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በንግግራቸው “ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ የቆዩ ግዴታዎችን የሚሰብር እና ወደ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚያመራ ዋና መደብ ነው” ሲሉ የገለፁት ይህ ፕሮጀክት ንግድ፣ ጭነትና ንብረት እንቅስቃሴን በመሃል የሚያከናውን ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን በግልፅ ያመላክታል። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ አፍሪካ የሎጂስቲክስ ኃይል መቀየር የሚችል ታላቅ ራዕይ እንዳለው ያሳያል።
ቀድሞውን በአፍሪካ ሁለተኛ ሆኖ ከሚከተለው አየር መንገድ በእጥፍ ርቆ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ አሁን በተጀመረው አዲሱ የኤርፖርት ፕሮጀክት ግን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም በጣት የሚቆጠሩ ሀገራት ያሳኩትን 110 ሚሊዮን ህዝብን በአመት ሊያጓጉዝ የሚችል እጅግ ዘመናዊ ኤርፖርትን ለመገንባት ተነስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ በፕሮጀክቱ ምርቃት መርኃግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 አመታት የመጣበትን እጅግ አስደናቂ ጉዞ ካደነቁ በኋላ “የሚቀጥለው 80 ዓመት ከባለፈው 80 አመት በብዙ መልኩ ይለያል።” ሲሉ የአለም አቀፉን አየር መንገድ መፃኤ ጊዜ በእጅጉ እንደሚለወጥ አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ የማንዘጋጅ ከሆነ አብዛኛውን የአውፕላን ተግባራት የሚፈፅመው ማሽን በሚሆንበት ጊዜ ይህንን ክብራችንን ይዘን መቀጠል አንችልም።” ሲሉ አሳስበዋል።
ለዚህ አዲስ ፈተናሞ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “ህፃናት ላይ የምንሰራው ስራ እና በአርቴፊሺያል እንተለጀንስ የጀመርነው ፕሮጀክት ሲደመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚቀጥለውን 80 ዓመት የሚገጥመውን አዳዲስ እውቀትና ተጋፍጦ ለማለፍ እና ለመሻገር የሚያስችለውን ብቃት እንዲጎናፀፍ ያስችለዋል።” በማለት የመፍትሄ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን የወደፊት ህልውናን ይወስናል ያሉት ይህ የቢሾፍቱ አየር መንገድ በአጠቃላይ 5000 ሄክታር ለምን እንዲህ እንዲሰፋ እንደተፈለገ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “በስፋቱ ልክ በአየር ላይ የሚመላለሱ መርከቦችን በብቃት ማስተናገድ ችሎ የኢትዮጵያን የእድገት ስብራት የሆነውን ሎጂስቲክስን ለመፍታት በእጅጉ ስለሚያግዝ ነው።” በማለት ይህ የአየር ላይ ወደብ ፕሮጀክት ለምን እንዳስፈለገ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አቢይ ከቢሾፍቱ አየር ማረፊያ እስከ ቦሌ አየር ማረፊያ የሚዘረጋውን በድምሩ 12 መኪኖችን መያዝ ሰለሚችለው አዲሱ የፈጣን መንገድ ፕሮጀክትም ያነሱ ሲሆን “ይህ ፈጣን መንገድ ከዚህ ቀደም ከተሰሩት ፈጣን መንገዶች ከሚለየው ነገር አንደኛው ከመንገዱ ቀጥሎ ግንባታዎችን ሳይሆን በእቅድ እና በእውቀት በሚሰሩ ጥልቅ የ’Green Legacy’ አሻራዎች ሙሉ በሙሉ የሚሸፈን በመሆኑ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።
ከፈጣን መንገዱ ባሻገር 38 ኪሎሜትር የሚሸፍን በያንስ 120 ኪሎ ሜትር ቢበዛ 200 ኪሎ ሜትር በሰዓት የሚፈጥን አዲስ ፈጣን የባቡር መንገድ ዝርጋታ ፕሮጀክት እንደሚጀመርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳውቀዋል። ይህ ፈጣን የባቡር መንገድ ከኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መንገድ የሚለየው ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ኩባኒያዎች መገንባቱ እንደሆነ ጠቅላይ መከኒስቴሩ አያይዘው ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ይህን የቢሾፍቱ አለም አቀፍ ኤርፖርት ግንባታ ለምን አሁን ማስጀመር እንዳስፈለገ ሲናገሩ “የቦሌ አየር መንገድ በዓመት 2 ሚሊዮን የሚጠጉ አዳዲስ ደንበኞችን ማስተናገድ ጀመሯል። አሁን ላይ 21 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞችን የሚያስተናግደው ይህ የቦሌ አየር መንገድ የደንበኛው ቁጥር አሁን ባለው እድገት የሚቀጥል ከሆነ ከሁለት እና ሶስት ዓመታት በኋላ አየር መንገዱ ተጨማሪ ሰው ማስተናገድ አይችልም። ስለሆነም ያንን ችግር ከወዲሁ ተገንዝበን ከወዲሁ ስራ ካልጀመርን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካውያን ኩራት የሚለውን ስም ተጎናፅፈን ማቆየት ስለምንቸገር ለነገ ዛሬ አስቀድመን መስራት በማስፈለጉ ነው።” ሲሉ አሳውቀዋል።
“የዛሬ 10 ዓመት የአውሮፕላን ማረፊያው ሁለቱም ፌዞች እና በርካታ የጀመርናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውን ኢኮኖሚ ትገነባለች።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አክለውም በቅርብ እና በሩቅ ላሉ ሀገራት ይህንን በመረዳት “ከሚያድግ ሀገር ጋር አትቀያየሙ” በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በንግግራቸው በዓመት 60 ሚሊዮን ደንበኞችን የሚያስተናግደው የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በፈረንጆቹ 2030 እንደሚጠናቀቅ አሳውቀዋል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አየር መንገዱ በሚገነባበት አከባቢ ያሉትን አርሶ አደሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም አባ ገዳዎች ለኢትዮጵያ ልማት ለከፈሉት ዋጋ እና ላሳዩት የባለቤትነት ስሜት ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስተሩ አክለውም ከግንባታው ጋር ተያይዞ ከቀያቸው የተነሱ አርሶ አደሮች እንግልት ሳይደርስባቸው ከተማ ላይ እንደሰፈሩ እና ለወደፊት ህይወታቸውም እክል እንዳይገጥመቸው ስልጠና ወስደው እንደሰፈሩ በማውሳት ፕሮጀክቱ ሰው ተኮር ፕሮጀክት መሆኑን በንግግራቸው ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስተሩ አክለውም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጀምሮ በዚህ ግንባታ አሻራቸውን ላሰረፉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ ለውጥ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የመሆኗን መዋቅራዊ ጉዳቶችን እና የውጪ ንግድ ወጪን ይቀንሳል። ከሁሉም በላይ ግን ለትውልድ የሚተፍ የረዥም ጊዜ ሥራ የሚፈጥር፣ የቴክኖሎጂና ክህሎት ሽግግር የሚያደርግ፣ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን የሚስብ እና ኢትዮጵያ በራሷ ራዕይና ቁርጠኝነት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶችን ማስፈጸም እንደምትችል አገራዊ እምነት የሚፈጥር ትልቅ ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከዚህ አንፃር የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ መነሻ እና ማኮብኮቢያ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ነፃነት ለማስጠበቅ፣ወጣቶቿን ከአለምአቀፋዊ እድል ጋር ለማስተሳሰር እና ሀገሪቱን በአለም ኢኮኖሚ ውስጥ ለቀጣዩ ክፍለ ዘመን ያላትን ቦታ ለመቀየር የተነደፈ የእርስ በርስ ትውልዶች ሀብት ተደርጎ ይወሰዳል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






