ልክ እንደ ሞዐ ተዋህዶ በሚስጢር ሳይሆን ሙስሊም ዜጎችን በመሰብሰብ በአክቲቪዝም ስም ማሰልጠንና ማብቃት በይፋ ተጀምሯል። ወጣቶችን ማሰልጠን፣ ማስተማር፣ ማነጽ ክፋት የለውም፤ ነገር ግን “በአካባቢያችን በሜንጫ ነው የምንቀነጥስህ” የሚለው እብለት ሲተነፍስና የሚገዛው ሲያጣ፣ መልኩን ቀይሮ ብቅ ያለው “የአቅም ግንባታን” ካባ የለበሰው ስልጠና መሰረታዊ ፍላጎቱ የተሸፈነ ቢመስልም ግልጽ ነው። “ሚዲያውን ተቆጣጠር” የሚለው ስልጠናና የሰዎችን የስነ-ልቦና ውቅር እስከመቀየር የሚያደርሰው የስልጠና ማኑዋል አዘጋጅቶ መበተን “ጨፍኑ ላታላችሁ” ካልሆነ ዓላማው ግልጽ ነው። ሞዐ ተዋህዶ ውስጥ ውስጡን ሰርቶ ይፋ እንዳደርገው ሁሉ፣ አሁን ለኢትዮጵያ ላይ እየደገሱ ያሉት ስብሰቦች በጌቶቻቸው ትዕዛዝ “ጥምረታችን በኃይማኖት ስርዓት ውስጥ አድርጎ ወደ ህዝብ ይስረጽ” የሚል አዋጅ ዋሳለፋቸውን ሰምተናል።
አዲስ ሪፖርተር –ብልጽግናን ጨምሮ በኢትዮጵያ ድንኳን ውስጥ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መምጣት አለባቸው። በአገራቸው የሚያገባቸው ሁሉ ማንም ከማንም ሳያንስ ተስታፊ የሚሆኑበት አግባብ አሁን ከተጀመረው በላይ መቀጠል አለበት። ለአገር የሚጠቅም አጀንዳ ላላቸው በሩ ክፍት መሆን አለበት። የፈጀውን ፈጅቶ ልዩነቶች በውይይት ሊፈቱ ግድ ነው። ከምንም በላይ ህዝብ እንዲፈርድ መፍቀድ አግባብ ይሆናል። እየተገባደደ ያለው ብሄራዊ የምክክር መድረክ፣ የተጀመረው ስምምነት ስላልነበረ ነውና ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። “ጭሬ ልበትነው” እንደምትለው ዶሮ በየቀኑ አጀንዳ በመቀያየር ሕዝብን ማዛል፣ ተስፋ ማስቆረጥ፣ “እኔ ስልጣን እስክይዝ ሴራ አመርታለሁ፣ ከየትኛውም ወገን ጋር አብሬ እሰራለሁ” የሚለው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሊቆም ይገባል። ምክንያቱም ለማንም አይጠቅምምና!! ከሙከራዎቹ እንደምናየው አገር አልባ ያደርጋልና። “ኢትዮጵያ ፈርስ ማየት ነው ምኞቴ” የሚሉ የሚዲያ ተወዛዋዦች አምልጧቸው የገለጡትን ሚስጢር ማለባበስ አይጠቅምምና ሁሉንም “በምሳቸው” ጠርቶ ማግለል ከዜጎች ሁሉ ይጠብቃል።
አሁን አሁን ለሚያስተውሉ “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” ያለው ድሃ ባል ተረት የሚያስታውስ ዘመን ላይ ስለመድረሳችን ለመረዳት አዳጋች ነገር የለም። ሰውየው ድሃ ነበር። እመቤቱ በአንድ ድንገት ቀመሰችውና ወደደችው፤ ተጋቡ። ብዙም ሳይቆይ አባቷ ሞቱ። አባቷ “ጌቶች” የሚባሉ ነበሩ። እናም መኳንንቱ አስከሬናቸውን አጅቦ እያለቀሰ ሲሸኝ ባል ሚስቱ ጎን ሆኖ እንደ እሷ “አባቴ አባቴ” እያለ ሲያለቅስ፣ “የት የወለደህን ነው? ዝም በል” አለችው። ድሃ በመሆኑ አባቷን “አባቴ” ማለት ነውር ተደረገበት። ዝም ብሎ ጎን ጎኗን ሲሄድ መለስ አድርጋ “ምን ዝም ትላለህ?” ስትለው “አባቷ አባቷ” ብሎ መጮህ ጀመረ። አሁንም መልሳ “የበላኸው ጮማ፣ የጠጣኸው ጠጅ … አያንቅህም?” በማለት “አባቷ” ብሎ ማልቀሱን አሸሞረችበት። ግራ የገባው ባለ አፍታ ቆይቶ “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” እያለ ቀብር ደረሰ። “አባቴ” ቢል መከራ፣ “አባቷ” ቢል መከራ።
የኢትዮጵያም ነገር “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” የሚያሰኝ ሆኗል። ጭር ሲል የሚጠሉ፣ በእሳት ላይ እሳት፣ በቀውስ ላይ ቀውስ፣ በችግር ላይ ችግር፣ በዝለት ላይ ሌላ ዝለት የሚጨምሩ ጉዶች እዚያም እዚህም እየሰማን ነው። እነዚህ ጉዶች በፖለቲካ፣ በእምነት፣ በማህበራት፣ በአክቲቪዝም፣ አንዳንዴም በ”ሊቅ” ስም የሚጠሩና እያሳሳቱ ወጣቱን ወዳልተገባ መስመር የሚነዱ ናቸው።
የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰው “ኢትዮጵያዊ” በመምሰል፣ የሃይማኖት ሊቅ በመምሰል፣ የሃይማኖት አባት በመምሰል፣ የሃይማኖት ሰባኪ በመምሰል፣ በሃይማኖት ስም በሚሰጡ የክብር ስሞች በመሸፈን፣ ተመራማሪና አዋቂ በመምሰል፣ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በጋዜጠኛ ስም በመከለል፣ በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ “ሰላማዊ ታጋይና ፖለቲከኛ ነን” በማለት፣ በህጋዊ ታጋይነት በመጠቅለል ወዘተ. ኢትዮጵያ ላይ በግል፣ በማህበር፣ በመናበብ፣ በገፊና ጎታች ስልት አጀንዳ በመቀባበል ኢትዮጵያ ላይ የሚያዘንቡት የትርምስ መርዝ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
አገሪቱ ከአንድ አደጋ ስትላቀቅ ሌላ የትርምስ አጀንዳ በመትከል፣ አንዱ ትርምስ ሲርግብ ሌላ በመፍጠር፣ ህዝብ “ተገላገልን” ሲል ሌላ ጭንቀት በመፈልፈል የተጠመዱት እነዚህ ሁሉ ፍላጎታቸው ምንድን ነው? ለማን ነው የሚሰሩት? ዓላማቸው ከየት ሰፈርና ከባቢ የተቀዳ ነው? ማን ነው ጭነት እየቀያየረ የሚልካቸው፣ የሚያሰማራቸው? የመጨረሻው መዳረሻቸው የት ነው? ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ለመትከል ነው? የሚለውን ስንጠይቅ “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” ከማለት ውጭ ምንም ማለት ይቻላል? “ምን ጉድ ነው?” ብሎ ከመጠየቅ ውጪ እነዚህን ጉዶች እንዴትና እንደምን በአመክንዮ መሞገት ይቻላል?
ጎበዝ፣ አንድ እውነት አለ። ግብጽ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት መሆኗና ኢትዮጵያን የማፈራረስ የማይቀየር አቋም ማደሯ! ግብጽ ብሯን፣ መሳሪያዋን፣ ጊዜዋን፣ ሚዲያዋን፣ ሰላዮቿን አሰልፋ ሌት ተቀን ኢትዮጵያ ላይ የምታደራውን የጥፋት ድር የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም። ይህ እውነት ከሆነ ከግብጽ ጋር በገሃድ እንደሚሰሩ የሚነግሩን “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉትን ቡድኖች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ሚዲያዎች፣ ክልሎች ወዘተ. ከግብጽ ጋር አብረው የሚሰሩት “ለኢትዮጵያ ምን ሊያመጡላት ነው?” ይህን ጥያቄ ጠይቆ ግልጽ የሆነውን ምላሽ ለሚረዱ ሁሉ “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” ከማለት ሌላ ምን ይላሉ? ክፉ መረገም።
ኤርትራ የምትባለውን አገር የሚመሩት ኢሳያስም በተመሳሳይ የጌቶቻቸው አገልጋይ፣ በበታችነት ስሜት የሚሰቃዩ፣ ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ አገራቸውን ሲዖል ያደረጉ፣ ህዝቡን በስለላ መዋቅራቸው በየደጁ ቀርቅረውበት የሚያሰቃዩ፣ ለጌቶቻቸው ሲሉ በዚህ ዘመን የጋርዮሽ ወቅት ኑሮን መኖርን እንደ ክብር የሚያዩ፣ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ተምሳሌት የሆኑ፤ ቅጥረኛ የኢትዮጵያ ጠላት እግር ስር የተንበረከኩ ባንዳዎች፣ ከርባንዳነትም ዝቅ ያሉ ተላላኪ አሽከሮች ቢሳካላቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ይዘው ሊመጡ ነው ያሰቡት? ይህንን ማሰብ እና ቀላሉን ምላሽ መረዳት “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” እንጂ ሌላ ምንም አያሰኝም።
በብሔር ልዩነት ላይ ተቸክለው ሕዝብ እነሱን መስማት እስኪያቅረው ልዩነትን ሰበኩ። በአንድ አገር ብሔራዊ ሚዲያ ሳይቀር የቆየ ቁስል እየጎረጎሩ ለማባላት ሲሉ አልቃሽና አስለቅሽ ተጫወቱ፤ የትርምስ ሃውልት ሰርተው ትርክት ሰሩ፤ ጨቋኝና ተጨቁኝ በሚል ይህ ትውልድ በሌለበትና በማያገባው ጉዳይ እንዲባላ ክፋትን ጋቱት። እነሱን የተከተሉ የተመረተላቸውን ትርክት እያስተጋቡ ህዝብ አለቀ፤ ተፈናቀለ፤ ተሰደደ፤ ሃብትና ንብረቱ ተዘረፈ፣ ተማገደ።
ብዙ ብዙ ጉድ በተፈጸመባት አገራችን፣ ሰው ተሰቅሎ፣ መሰቀልና መሞት በቂ አይደለም ተብሎ እንደገና በድንጋይ ሲወገር አየን። ህዝብ እርስ በርስ እንዲባላ በተሰሩ የፈጠራ ትርክቶች፣ ከግፉ የተነሳ “ወንዝ አንገቱን ደፋ” ተብሎ በታተሙና በተሰራጩ የቅጥፈት ድርሰቶች እየተኮተኮተ ያደገው ትውልድ ይህን ሲፈጽም እንደ ትልቅ ጀብዱ በቪዲዮ እየተቀረጸ፣ እያሽካካና እየጮኸ ነበር። ይህን ምስል አነሳን እንጂ ብዙ ለንግግርም ለጽሁፍም የማይመቹ ጉዶችን ታዝበናል።
ህጻናት ልጆቻቸው ፊት የተገደሉ አሉ። በስለት የተተለተሉ አሉ። የምስኪኖችን ጎጆ አቃጥለው እያሽካኩ ሽንታቸውን እሳቱ ላይ የሚሸኑ “ነጻ አውጪዎችን” አይተናል። አታሞ እየደበደቡ “ውጣልን” የሚሉትን የሚያበረታቱ “አንቱ” የተባሉ ፖለቲከኞችን ታዝበናል። “እገሌን አታግቡ፣ ለእገሌ አትሽጡ” ሲባል እንደ ትልቅ ወግ የሚገለፍጡ “የወደፊት መሪዎች ነን” ባዮችን ዓይናችንን እየጠራረግን፣ ጆሯችንን እየተጠራጠርን ሰምተናል። “ከግራኝ መሀመድ ቀጥሎ የዘመኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ” የሚል ዓይን አውጣ የሽብር አባትን ታዝበናል። ሲያሻው “ሜንጫ”፣ ሲያሻው “ትርክት”፣ ሲያሻው “መንግስት ነኝ” የሚል “በላ” ቲያትር ኮምኩመናል። ዘመኑ ዲጂታል ነውና ሊፋቅ አይችልም፤ መረጃውም ማስረጃውም አለ።
ብዙ ብዙ አይተናል። በቅርቡ ጦርነት ከትግራይ የተነሳው የትህነግ ጦር ደብረ ብርሃን ጫፍ እስኪደርስ፣ በሌላ አቅጣጫ በጭናና ማይካድራ እንደሆነው ሁሉ ደብረ ታቦር የተፈጸመውን ግፍ፣ ግድያ፣ በቤት እንስሳት ላይ ሳይቀር የተፈጸመውንም አንረሳም። የወደመው ንብረት፣ የተዘረፈውና እንዳይሰራ የተደረገውን ሃብት ስናስብ እንባችን እስከ አፋር ይዘልቃል።
በተመሳሳይ ቂም አርግዞ ሲጠብቅ የነበረው የሻዕቢያ ጦር፣ ጦርነቱን አስታኮ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ፣ ዘረፋ፣ የጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር “በትግራይ ሴቶች ማህጸን ውስጥ ደብዳቤ ጽፎ እስከማኖር፣ ብረት እስከ መሸንቆር” የደረሰ ዘግናኝ ግፍን ያካተተ ነው። ይህም አይረሳም። እነዚህ ወገኖች ተመልሰው “ጻድቅ ነን፤ ተጣምረናል” ሲሉን ደግሞ ያመናል። “እንዴት ቢያስቡን ነው?” ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዱናል? እነሱ ሃፍረትን ባያውቁ፣ እኛ ለነሱ እያፈርን እንሞግታቸዋለን። ሰሞኑን እንደሰማነው “ጥምረታችን በኃይማኖት ኔትዎርክ ስር ወደ ህዝብ ይስረጽ” የሚል አዋጅ አጽድቀዋል። ይህን ያወጁት በአለቆቻቸው መመሪያ ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነው። በብሄር ተብሎ ተብሎ የከሸፈው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተወጠነ ውጥን የኃይማኖት ክንፎች አብጅቶ እንዲነጠን በጀትና ተላላኪ ተመድቦለታል። ዋ!!
ሁሉንም የቻለውና “አልወድቅም” በማለት እዚህ የደረሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን አሁን በሚወደውና በሚያከብረው ሃይማኖቱ እየተመጣበት ነው። ብልጭ ድርግም ሲሉ የነበሩ አንዳንድ ምልክቶች፣ አሁን አሁን በገሃድ ስም እየጠሩ “አንተ የዚህ ወገን ነህ፤ እገሌ እንዲህ ሲያደርግህ ነበር” የሚል ቁስል ፈጥረው፣ በስልጠና ስም ወጣቱን የከዚህ በፊቱ አልበቃ ብሎት አሁንም “ቦንብ” እያስታቀፉት ነው።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ሽፋን ያላቸው፣ ነገር ግን አልፈርስ ያላቸውን አገር ወደ ትርምስና ሙሉ መናወጥ የሚከቱ እንቅስቃሴዎችን ማስተዋል ከጀመርን ሰነባብተናል ስንል እንዲሁ ለማለት ያህል ሳይሆን፣ በገሃድ ህዝብ የሚታዘባቸውንና በስልጠናና በምህላ ስም የሚፈጸሙትን የአደባባይ ላይ ሚስጥር በማመላከት “ዋ” ለማለት ነው። ሲያሻቸው ፖለቲከኛ፣ ሲያሻቸው “ፈጣሪ የለም”፣ ሲያሻቸው አማኝ፣ ሲያሻቸው ሃይማኖተኛ፣ ሲያሻቸው ጠመንጃ ነካሽ፣ ሲያሻቸው የሰላም ሰባኪዎች፣ ሲያሻቸው አደራጅና አስልጣኝ … በመሆን የሚገለባበጡ ሰዎችን ከዚሁ እንቅስቃሴዎች ጀርባ እያየን ነውና ህዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ሊነቃ እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን።
“ሞዐ ተዋህዶ” በሚል ጥንታዊቷ እና ሰላማዊቷ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተለጠፈ ኃይል፣ በዕምነት ጥላ ስር ወጣቶችን መንፈሳዊ ቅባት እያሳየ ወደ ክፉ መንገድ በመምራት ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ በአደባባይ እያየነው ያለው ሃቅ ነው። የዚሁ ንቅናቄ መሪ መምህር ፋንታሁን ዋቄ እና በዚሁ አስተምህሮት የተጠመቁ መስቀልና ክላሽ አንድ ላይ ተሸክመው፣ በገሃድ የብረት ነውጡ አባቶች መሆናቸውን ነግረውናል። ህዝብ አልሰማም እንጂ አስተምህሮቱ ከሌሎች ጋር የሚያጋጭ፣ አብሮ የማያኖር፣ ለዕልቂትና ትርምስ የሚያዳርግ የ”እሳት እራት” ፖለቲካ ነው።
አሁን አሁን ደግሞ ሙስሊም ዜጎችን በመሰብሰብ በአክቲቪዝም ስም ማሰልጠንና ማብቃት በይፋ ተጀምሯል። ወጣቶችን ማሰልጠን፣ ማስተማር፣ ማነጽ ክፋት የለውም፤ ነገር ግን “በአካባቢያችን በሜንጫ ነው የምንቀነጥስህ” የሚለው እብለት ሲተነፍስና የሚገዛው ሲያጣ፣ መልኩን ቀይሮ ብቅ ያለው “የአቅም ግንባታ” ካባ የለበሰው ስልጠና መሰረታዊ ፍላጎቱ የተሸፈነ ቢመስልም ግልጽ ነው። “ሚዲያውን ተቆጣጠር” የሚለው ስልጠናና የሰዎችን የስነ-ልቦና ውቅር እስከመቀየር የሚያደርሰው የስልጠና ማኑዋል አዘጋጅቶ መበተን “ጨፍኑ ላታላችሁ” ካልሆነ ዓላማው ግልጽ ነው።
ጽንፈኛ ወይም አክራሪ ቡድኖች የሕዝብን አስተያየት ለመቅረጽ፣ አባላትን ለመመልመል እና መልእክቶቻቸውን ለማሰራጨት የሚጠቀሙበት የሚዲያ ሰራዊት (Media Army) የማደራጃ እና የመዘጋጃ ስልት በተለያዩ የኮሙኒኬሽን እና የስነ-ልቦና ስልቶች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ለምንረዳ፣ የአህመዲን ጀበል የሰሞኑ ተከታታይ ስልጠናዎች ከዚህ የተለዩ ስለመሆናቸው የሚያስረዱ ካሉ ለመስማት ዝግጁ ነን።
አዲስ ሪፖርተር ማንኛውም ዕምነት እከሌ ከከሌ ሳይባል በእኩል ደረጃ መታየት እንዳለበት ታምናለች። ሁሉም እምነቶች ድንበራቸውን አክብረው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ፣ አንዱ የሌላውን ድንበር ሳይጥስ በመከባበር አባቶቻችን “እምነታቸውን” ብቻ ማዕከል አድርገው በሰላም እንደኖሩ ሁሉ በዚያው ስሜት የጎደለ ካለ በማረም እንዲቀጥል ትመኛለች።
ይህን ስንል ገዢውን ፓርቲ ብልጽግናን ለመከላከል ወይም “አትንኩት” ለማለት አይደለም። ፓርቲው በሌብነት የነቀዙ፣ ሁለት ቦታ በሚጫወቱ ካድሬዎች ሴራ የሚንጠራወዝ፣ በአንድ ጀነበር ሚሊዮን እንዲቆጥሩ የሚመቻችላቸው ተቀጽላዎች የሚታዩበት፣ በርካታ የአደረጃጀትና የጥራት ችግር ያለበት መሆኑንም በመካድ አይደለም። ይህ ፓርቲ በርካታ በጎ ጅምሮች ያሳየና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ታላላቅ ማርሽ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የጨረሰ፣ የተጀመሩትን ያገባደደ፣ አሁንም እየሰራ ያለ እንደሆነም እናምናለን። ከላይ ከተዘረዘሩት ገረድ ድርጅቶች፣ አገራትና የነጻ አውጪ ስብስቦች ለኢትዮጵያ ካዘጋጁት በረከት ይልቅ የተሻለ እንደሆነ እናስባለን። ከግብጽ አሽከሮች ጋር ሊወዳደር እንደማይችል አፋችንን ሞልተን ለመናገር አናፍርም። በመሆኑም ሁሉም ወገን ከላይ የተቀመጡትን “ተጣማሪዎች” በወጉ እየመረመረ አገሩን ሊጠብቅ እንደሚገባ ለማስታወስ እንወዳለን።
በድሮ ጊዜ የአስር ሳንቲም ዘይት ግዛ ብላ እናቱ የላከችው እረኛ፣ የተላከበትን መንገድ ርቀት ካሰላ በኋላ “ሳስበው ደከመኝ” በማለት ወደ ተላከበት ሳይሄድ እንደተመለሰው እረኛ “ከላይ ስለተገለጸው ህብረት ማሰብ ያደክማል” እንላለን። ከዚያም በላይ አለቆቻቸውና ጌቶቻቸው ለኢትዮጵያ “አድርሱ” ብለው የላኳቸውን መልዕክት ስለምናውቀው “ኧረ እኔስ ጨነቀኝ” የሚለውን ብሂል በማስታወስ የክፋቱን ጥግ መመርመር ግድና ግድ መሆኑን እናስታውቃለን።
በሱዳን ጦርነት እንዴት የሚዲያ ሰራዊት ተገንብቶ፣ ወደ ጦር ተቀይሮ፣ ታጥቆ አገሪቱን እንዳፈረሳት ስለምናውቅ፤ መንግስት ሆይ “ሃይማኖትን ተንተርሰው በዕቅድ እየሰሩ ያሉትን ጭምብል ግፈፍ፣ እርምጃ ውሰድ፣ ይህንንም ሳታደብቅ ለህዝብ ይፋ አድርግ” ለማለት እንወዳለን። የአገር መከላከያ ሰራዊት ፤ላይ የሚከፈተው ዘመቻና የሚለጠፈው ስም መከላከያን አፍርሶ ኢትዮጵያን ለመብላት ነውና አንሞኝ!! ኢትዮጵያን የተበተባት ዘንዶ አናቱ ቢወጋም፣ የትብትቡ አካል ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ መንቃትና መጠበቅ ላፍታም ዝም የሚባል ጉዳይ አይሆንም። የአገር ጉዳይ ነውና!!






