አንዳንድ ቁሞ ቀር ሊህቃን ያውም በሰለጠነው ዓለም የሚኖሩ እና በባህላዊው የአስተሳሰብ አጥር ውስጥ የታጠሩ ግለሰቦች የአይሾው ስፒድን (IShowSpeed) የኢትዮጵያ ጉብኝት ሲተቹ አስተውለናል። እነዚህ ሰዎች ባሉበት ተቸክለው ዘመኑን ሳይዋጁ ዓለም ጥሏቸው እየሄደ መሆኑን እንኳ ሊረዱ አልቻሉም። የሚተቹበት መንገድ የዘመኑን “የትኩረት ኢኮኖሚ” ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። እነዚህ ወገኖች ቱሪዝምና የሀገር ገጽታ ግንባታን አሁንም ድረስ የሚያዩት በአሮጌው የመንግስት ኮሙኒኬሽን፣ በረጅም የዶኩመንታሪ ፊልሞችና በደረቅ ዲፕሎማሲያዊ መግለጫዎች መነጽር ብቻ ነው። ሆኖም ግን በአዲሱ ትውልድ (Gen Z) እና በዓለም አቀፉ የዲጂታል ገበያ መስፈርት “ክብር” የሚለካው በተመልካች ቁጥር፣ በንቁ ተሳትፎና በይዘቱ “ቫይራል” መሆን ላይ መሆኑን ባለመረዳታቸው፣ ስፒድ የሚያሳየውን ከፍተኛ ጉልበትና ለየት ያለ ባህሪ እንደ “ባለጌነት” ወይም “የሀገርን ስም ማጠልሸት” አድርገው ይረዱታል።
(ነፃ አስተያየት – በአለባቸው ጉብሳ)
አዲስ ሪፖርተር – በአሁኑ ዘመን “የትኩረት ኢኮኖሚ” (Attention Economy) የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ የዓለምን የንግድና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የሚመራበት ቀዳሚ ስልት ሆኗል። በዚህ ዲጂታል ዘመን መረጃ በየሰከንዱ እንደ ጎርፍ በሚፈስበት ሁኔታ፣ የሰው ልጅ ትኩረት እጅግ ውድና ውስን “ሀብት” ሆኖ ተገኝቷል። የትኩረት ኢኮኖሚ መርህ “መረጃ በበዛ ቁጥር የሰው ልጅ ትኩረት ይቀንሳል፤ ስለዚህም ያንን ውስን ትኩረት የሳበ አካል የዓለምን ሀብትና ስልጣን ይቆጣጠራል” የሚል ነው። በዚህም ምክንያት የንግድ ተቋማትም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ምርታቸውን ወይም ሀሳባቸውን ከመሸጥ ይልቅ፣ የሰዎችን አይንና ጆሮ ለረጅም ጊዜ ጠምዶ ለመያዝ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ።
በንግዱ ዓለም፣ ትኩረት እንደ አዲሱ የዓለም ምንዛሬ (Currency) ይታያል። ኩባንያዎች ትኩረትን ለማግኘት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለማስታወቂያ ከማውጣት ይልቅ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ትኩረት መሳብ ወደቻሉ እንደ አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) ወደ መሳሰሉ ግለሰቦች ፊታቸውን አዙረዋል። ምክንያቱም የሸማቾች ትኩረት ባለበት ቦታ ሁሉ ሽያጭና ትርፍ አለ። ዛሬ አንድ ምርት ጥራት ስላለው ብቻ አይሸጥም፤ ይልቁንም በማህበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝሞች ውስጥ አልፎ የብዙዎችን ትኩረት ማግኘት ሲችል ብቻ ስኬታማ ይሆናል። ይህም የንግድ ዓለሙን ከመደበኛ የምርት ማሳያነት ወደ “መዝናኛና ትኩረት የመሳብ ጥበብ” ቀይሮታል።

በፖለቲካው ረገድም የትኩረት ኢኮኖሚው ያለው ተፅዕኖ እጅግ የጎላ ነው። የፖለቲካ መሪዎችና ማህበራዊ አንቂዎች የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት ረጅም መግለጫዎችን ከመስጠት ይልቅ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰራጭተው የብዙዎችን ትኩረት የሚስቡ “ቫይራል” (Viral) የሆኑ መልዕክቶችንና ምስሎችን ይጠቀማሉ። የፖለቲካ ትርክቶች የሚገነቡት በውይይት ጥልቀት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያገኙት “ላይክ” እና “ሼር” ብዛት ሆኗል። ይህም ፖለቲካን ከፖሊሲ ክርክር ይልቅ ወደ “የትኩረት ሽሚያ” የቀየረው ሲሆን፣ ብዙ ትኩረት ማግኘት የቻለ ሀሳብ ትክክል ባይሆን እንኳ የብዙዎችን አመለካከት የመቀየርና የሀገርን አቅጣጫ የመወሰን አቅም እንዲኖረው አድርጎታል።
በአጠቃላይ፣ የትኩረት ኢኮኖሚው ዓለማችንን የምትመራበትን መንገድ ቀይሮታል። ኃይል ያለው መረጃ ባለው ሰው እጅ ሳይሆን፣ መረጃውን ተጠቅሞ የሰዎችን ትኩረት መቆጣጠር በሚችል አካል እጅ ላይ ወድቋል። ይህ ሁኔታ ግለሰቦችና ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነት ለማግኘት የግድ የዲጂታል ትኩረትን የመሳብ ጥበብን ማወቅ እንዳለባቸው ያስገነዝባል። በዚህ አዲስ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ “መታየት” ማለት “መኖር” ማለት ሲሆን፣ ትኩረት ማጣት ግን ከገበያውም ሆነ ከፖለቲካው መድረክ መገለልን ያስከትላል።
የሳኡዲና የዱባይ ተሞክሮ…
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (በተለይም ዱባይ) እና ሳዑዲ አረቢያ ዝነኞችንና የዲጂታል ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀም ሀገራዊ ገጽታን የመገንባት ስራ ላይ የዓለም ቀዳሚ ተሞክሮ ባለቤቶች ናቸው። እነዚህ ሀገራት ቱሪዝምንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚከተሉት ስልት፣ ከመደበኛው የማስታወቂያ ስራ ወጥቶ የሰዎችን ትኩረት በቀጥታ መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነው።
ዱባይ በዲጂታል ማስተዋወቅ ረገድ ያላት ስኬት የሚመነጨው ዝነኞችን እንደ ጊዜያዊ እንግዳ ሳይሆን እንደ ቋሚ የሀገር አምባሳደር አድርጎ ከመመልከት ነው። ሀገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንቁ ተከታዮች ላሏቸው ዩቲዩበሮችና የይዘት ፈጣሪዎች የ “ጎልደን ቪዛ” (Golden Visa) በነፃ በመስጠት እዚያው እንዲኖሩና እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎችን ትፈጥራለች። ዓላማው እነዚህ ግለሰቦች ስለ ዱባይ ዘመናዊነት፣ ደህንነትና ምቾት በየቀኑ ለተከታዮቻቸው እንዲያጋሩ እድል መፍጠር ነው። በተጨማሪም ታዋቂ ሰዎች ወደ ከተማዋ ሲመጡ የሚደረግላቸው ልዩ የቪአይፒ (VIP) መስተንግዶ፣ ምርጥ ሆቴሎችና የመዝናኛ ስፍራዎች በነፃ እንዲቀርቡላቸው ይደረጋል። እነዚህ ዝነኞች የሚያሳዩት የቅንጦት ህይወትና አስደናቂ ትዕይንት በተመልካቾች ዘንድ “ዱባይን የመጎብኘት ጉጉት” እንዲፈጠር በማድረግ የሀገሪቱን የቱሪዝም ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል። ይህም ዱባይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሁልጊዜም የምትታይና ንቁ መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል።
በሌላ በኩል ሳዑዲ አረቢያ በ “ቪዥን 2030″ (Vision 2030) ስልታዊ እቅዷ አማካኝነት የነበራትን ” መጥፎ” ገጽታ ለመስበርና ለዓለም ክፍት መሆኗን ለማሳየት የዓለም ታዋቂ ሰዎችን ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀመችበት ትገኛለች። እንደ ሊዮኔል ሜሲ ያሉ የስፖርት ቁንጮዎችን የቱሪዝም አምባሳደር አድርጋ በመሾም እንዲሁም እንደ Nas Daily ያሉ ታዋቂ የጉዞ ቪሎገሮችን (Vloggers) በልዩ ግብዣ ወደ ሀገር በማስገባት፣ ስለ ሳዑዲ ባህል፣ እንግዳ ተቀባይነትና ግዙፍ የልማት ስራዎች አዲስ ዓለም አቀፍ ትርክት እንዲገነባ አድርጋለች። ሳዑዲ ይህን የምታደርገው ከመዝናናት ባለፈ፣ የዓለምን ትኩረት በመሳብ ኢኮኖሚዋን ከዘይት ጥገኝነት ለማውጣትና ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት ለመቀየር ነው። እነዚህ የታዋቂ ሰዎች ምስክርነቶች ስለ ሀገሪቱ የነበረውን አሮጌ አመለካከት በመቀየር ረገድ ከመደበኛው የዲፕሎማሲ ስራ በበለጠ ፍጥነት ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ የአይ ሾውስፒድ ጉብኝት አንድምታ…
ታዋቂው ዩቲዩበር አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ያከናወነው የቀጥታ ስርጭት (Livestream) ከ48 ሚልየን የዓለም ሕዝብ በላይ ተከታትሎታል ይህም በዲጂታል ዓለም ውስጥ ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለቱሪዝም ዘርፍ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከላይ በመግቢያችን እንዳብራራነው በአሁኑ ዘመን “የትኩረት ኢኮኖሚ” (Attention Economy) የዓለምን የንግድና የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየመራ ባለበት ሁኔታ፣ እንደ ስፒድ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንቁ ተከታዮች ያሏቸው ግለሰቦች የሚያስተላልፉት ምስል ከመደበኛው ዲፕሎማሲ በበለጠ ፍጥነትና ጥልቀት ተደራሽነት አለው።

ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ ያላትን ትርክት (Narrative) ከመቀየር አንጻር ያለው ፋይዳ ወደር የለውም። በየቪዲዮዎቹ ስር የሚሰጠው የአድናቆት አስተያየት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ስሟ ሲነሳበት ከነበረው የተለየ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለረጅም ጊዜ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለ ኢትዮጵያ የሚነገረው ታሪክ በችግርና በድርቅ ላይ ያተኮረ ነበር። መዝገበቃላት ላይ ሳይቀር ከረሃብና ቭግር ጋር የተቆረኘ ትርጉም ተለጥፎባት የኖረች አገር ነበረች። ሆኖም እንደ ስፒድ ያለ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ላይ በነፃነት ሲንቀሳቀስ፣ ከህዝቡ ጋር ሲጫወትና ደማቁን ባህል ሲያሳይ፣ ያ አሮጌውና የተሳሳተው ምስል በዘመናዊና ሳቢ ምስል ይተካል። ይህ “ተፈጥሯዊ ማስተዋወቅ” (Organic Promotion) በተመልካቹ ዘንድ የሚፈጥረው አዎንታዊ ስሜት፣ ከመደበኛ ዲፕሎማሲ በላይ የሀገሪቱን ገጽታ የመገንባት አቅም አለው። በዚህም ኢትዮጵያ በዲጂታል ዓለም ውስጥ ያላትን “Soft Power” ወይም “ለስላሳ ተፅዕኖ” በከፍተኛ ሁኔታ እንድታሳድግ በር ከፍቶላታል።
የዚህ ዓይነቱ ማስተዋወቅ ሌላኛው ዋና ጥቅም ኢትዮጵያን እንደ ንቁ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ አድርጎ ለነገው ጎብኝ ለወጣቱ ትውልድ (Gen Z) ማስተዋወቁ ነው። ስፒድ በጎዳናዎች ላይ ሲንቀሳቀስ፣ የአካባቢውን ምግብ ሲመገብና ከህዝቡ ጋር ሲገናኝ የታየበት ትዕይንት፣ ሀገሪቱ ያላትን ሰላማዊ እንቅስቃሴና ባህላዊ ውበት በተፈጥሯዊ (Authentic) መንገድ ለዓለም አሳይቷል። ይህ ደግሞ የዘልማዱ መገናኛ ብዙሃን ከሚነገረው “ደረቅ” መረጃ ይልቅ በተመልካቹ ዘንድ ከፍተኛ መተማመንን ይፈጥራል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የቀጥታ ስርጭቱን መመልከታቸው በራሱ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ የፍለጋ ድረገፆች (Search Engines) እና የማህበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝሞች ላይ ከፍ እንዲል በማድረግ የዲጂታል አሻራዋን ያጎላዋል።
ከኢኮኖሚ አንጻር ሲታይም፣ እንዲህ ያሉ ኩነቶች የረጅም ጊዜ የቱሪዝም ገቢን ያነቃቃሉ። በቢሊዮን የሚቆጠር ተመልካች ያለው ግለሰብ ስለ ሀገር ሲያወራ፣ ያ ሀገር በብዙዎች የጉዞ ዝርዝር (Bucket list) ውስጥ እንዲካተት ያደርጋል። ይህም ወደፊት ለሚመጡ ቱሪስቶች፣ ለሆቴሎች ስራ፣ ለትራንስፖርት ዘርፉና ለአነስተኛ ንግዶች መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተጨማሪም፣ የሀገሪቱን ወጣቶች ከዓለም አቀፉ የዲጂታል ፈጠራ ዓለም ጋር በማስተሳሰር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በቴክኖሎጂና በይዘት ፈጠራ (Content Creation) ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉና የራሳቸውን ታሪክ ለዓለም እንዲነግሩ የሚያበረታታ ሞራል ይፈጥራል።
ቁሞ ቀሩ ተጎታቹ ሊህቅ…
አንዳንድ ቁሞ ቀር ሊህቃን ያውም በሰለጠነው ዓለም የሚኖሩ እና በባህላዊው የአስተሳሰብ አጥር ውስጥ የታጠሩ ግለሰቦች የአይሾው ስፒድን (IShowSpeed) የኢትዮጵያ ጉብኝት ሲተቹ አስተውለናል። እነዚህ ሰዎች ባሉበት ተቸክለው ዘመኑን ሳይዋጁ ዓለም ጥሏቸው እየሄደ መሆኑን እንኳ ሊረዱ አልቻሉም። የሚተቹበት መንገድ የዘመኑን “የትኩረት ኢኮኖሚ” ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።

እነዚህ ወገኖች ቱሪዝምና የሀገር ገጽታ ግንባታን አሁንም ድረስ የሚያዩት በአሮጌው የመንግስት ኮሙኒኬሽን፣ በረጅም የዶኩመንታሪ ፊልሞችና በደረቅ ዲፕሎማሲያዊ መግለጫዎች መነጽር ብቻ ነው። ሆኖም ግን በአዲሱ ትውልድ (Gen Z) እና በዓለም አቀፉ የዲጂታል ገበያ መስፈርት “ክብር” የሚለካው በተመልካች ቁጥር፣ በንቁ ተሳትፎና በይዘቱ “ቫይራል” መሆን ላይ መሆኑን ባለመረዳታቸው፣ ስፒድ የሚያሳየውን ከፍተኛ ጉልበትና ለየት ያለ ባህሪ እንደ “ባለጌነት” ወይም “የሀገርን ስም ማጠልሸት” አድርገው ይረዱታል።
ይህ ዓይነቱ ትችት የሚያሳየው ትልቁ ክፍተት፣ ዓለም የደረሰችበትን የዲጂታል ግብይት (Digital Marketing) ስልት አለመዋጀት ነው። የዛሬው ዓለም ታዋቂነትንና ገቢን የሚለካው በሰዎች “ትኩረት” መጠን ነው። አንድ ዝነኛ ግለሰብ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አይን ወደ ኢትዮጵያ እንዲዞር ሲያደርግ፣ ይህንን አጋጣሚ “ከባህላችን ጋር አይሄድም” በሚል ጠባብ አስተሳሰብ መተቸት፣ ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሊያወጣ የሚችልን የነፃ ማስታወቂያ እድል በገዛ እጇ እንድታጣ እንደመገፋፋት ይቆጠራል። እነዚህ ቁሞ ቀሮች ትኩረት መስጠት ያለባቸው ስፒድ በሚያሳየው የጩኸት ድምፅ ላይ ሳይሆን፣ በዚያ ድምፅ አማካኝነት በሚሊዮኖች አእምሮ ውስጥ በታተመው “የኢትዮጵያ” ስምና ምስል ላይ መሆን ነበረበት።
ዘመኑን ያልዋጁ ሊህቃን እንዲህ ያሉ ኩነቶችን ሲያጥላሉ፣ ሳውዲ አረቢያና ዱባይ የመሰሉ ሀገራት ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየከፈሉ እንዲህ ያሉ “ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን” ይጋብዛሉ። ይህ የሚያሳየው የእኛ ሊቃውንት አሁንም ባልተለወጠው “የኩራትና የዝምታ” ፖለቲካ ውስጥ ሲቀሩ፣ ዓለም ግን “ጩኸትና በትኩረት” ኢኮኖሚ ውስጥ እየተመራች መሆኑን ነው። ጌታዬ፣ በዚህ ዘመን ኩራት እራት አይሆንም። ስለዚህ የአይሾው ስፒድን ጉብኝት መተቸት ማለት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኘችውን ወርቃማ የማስተዋወቅ እድል መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ሀገሪቱ ከዲጂታሉ ዓለም ተነጥላ እንድትቀር መፈለግ ማለት ነው። አናሎግነትን ይሻላል ብሎ ማወጅ ነው።
በአጠቃላይ እነዚህ ተቸካይ ቁሞ ቀሮች መገንዘብ እና ሳይረፍድ መንቃት ያለባቸው ዛሬ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እና ቱሪዝም መሳብ የሚቻለው በቤተ-መጽሐፍት እና በሆቴል እንግዳ መቀበያ ጠርጴዛ ላይ በሚቀመጡ በራሪ ወረቀቶችና መፅሄቶች ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች ስልክ ውስጥ በሚዘዋወሩ አጫጭር ቪዲዮዎች በሚሊዮን በሚታዩ “የቀጥታ ስርጭት” መሆኑን ማወቅ እና እውነታውን መቀበልን ነው።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






