አዲስ ሪፖርተር – ራሱን “የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የጋራ የትግል መድረክ” በማለት የሚጠራው ስብስብ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ያሬድ ኃ/ማሪያም “ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እየረዱን ለምን ተቃዋውሞ ይሰነዘርባቸዋል” በማለት ተናገሩ። ሰብሳቢው ይህን ያሉት በጋራ መድረኩ የጋራ መገናኛ የዋትስ አፕ ግሩፕ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው።
በተለያዩ ጊዜያት ከአባላቱ “የብሄራዊ ጥቅምና ጉዳይ እንዴት ይታያል? ከሻዕቢያ ጋር ያለው ግንኙነት ጥንቃቄ ያሻዋል” በማለት ለሚነሱ ጥያቄዎች “ስለ ኤርትራ እዚህ አታንሱ” በማለት አቶ ነዓምን ጉዳዩን በማስቆም ወደ ሌላ አጀንዳ እንደሚመሩት አባላቱን በመጥቀስ የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ ዘጋቢ ከዋሽንግቶን ደጋግሞ መዘገቡ አይዘነጋም።
“ኤርትራ በቀጥታ ወደ ጦርነቱ እንደምትገባ አረጋግጣለች” በማለት ኢንጂነር ግደይ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ጥቂት ሰዎች በተገኙበት በጋራ መድረኩ ውይይት ላይ መናገራቸውን በመጥቀስ አዲስ ሪፖርትር ይፋ ባደረገው ዜና የተበሳጩት አቶ ያሬድ “አዲስ ሪፖርተርን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ለምን ኤርትራን ይቃወማሉ? እነሱ እየረዱን አይደል? እነሱ መንግስትን ለመጣል እየረዱን መቃወም ትክክል አይደለም። እዚህ ላይ በግልጽ መስራት አለብን” በማለት የጋራ መድረኩ በሻዕቢያ የሚመራ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። አክለውም አብረዋቸው በሚሰሩ ሚዲያዎች እንዲህ ያለውን አካሄድ መቃወም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ራሱን “አርበኛ መሳይ መኮንን” አነከር የሚባለውን ሚዲያ ከጀመረ በኋላ ባደረገው ቃለ ምልልስ “ከኤርትራ ጋር አብረን እንሰራለን” በማለት በይፋ መናገሩ አይዘነጋም። “ይህ ባንድነት አይደለም?” ለተባለው “እንኳን ከኤርትራ ከሌላም ጋር እንሰራለን። ይህ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም” በማለት አስረግጦ መናገሩ በታሪክና በትውልድ አዕምሮ የተመዘገበ ታሪካዊ ክህደት መሆኑን በርካቶች መግለጻቸውም የሚታወስ ነው። በተደጋጋሚ የሚያዘጋጀው ዝግጅትም ኤርትራና ሱዳን ከሚመላለሱት አቶ አንዳርጋቸው፣ ሶማሌ ነኝ ከሚሉት የሻዕቢያ ወዳጅ ፕሮፌሰር መሀመድ፣ እንዲሁም አቶ ነዓምን ከሚያዘጋጇቸው ሰዎች ጋር እንደሆነ ፕሮግራሙን የሚከታተሉ የሚመሰክሩት ጉዳይ እንደሆነ፣ ይህም በጋራ መደረኩ ላይ ተነስቶ እንደነበር ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ማዳከም በሚለው መሰረታዊ ዕቅዱ የውክልና ጦርነት እንደሚያካሂድ፣ በወያኔ አመራሮች ድጋፍ ኤርትራን አገር አድርጎ ከመስረተበት እለት ጀምሮ ኢትዮጵያ ላይ ተቃዋሚ በማደረጃት እና ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት አባላቱ በኮንትሮባንድ፣ በህገወጥ ንግድና በገንዘብ አጠባ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚሰራ፣ አሁን ደግሞ በይፋ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ግብጽ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለመበታተን “ኢትዮጵያዊ” የሚመስሉ ሚዲያዎችን በመቀለብ ዘመቻውን ያጧጧፈ የኢትዮጵያ ነቀርሳ መሆኑን አገራቸውን የሚወዱ ሁሉ በመረጃና ማስረጃ አስደግፈው እያቀረቡ ባለበት ወቅት “ሻዕቢያን አትንኩ” የሚለው መፈክር ሚስጥሩን ለማያውቁ የጋራ መደረኩ አባላት አስደንጋጭ እንደሆነ ተመልክቷል።
አቶ ያሬድ ይህን በመጻፍ የጋራ መደረኩ ከጀርባ የሚመራውና የሚደጎመው በሻዕቢያ መሆኑን ይፋ እንዳደረጉ የተፈጠረውን ግራ መጋባት እና ይህንኑ ተከትሎ የሚሰጡ አስተያየቶች ለማቀብ፣ አቶ ነዓምን የግሩፕ ውይይቱን አስቁመውታል። አቶ ነዓምን በይፋ የሚታወቁ የሻዕቢያ ወኪል መሆናቸውን አዲስ ሪፖርተርና የተለያዩ ሚዲያዎች መረጃና ማስረጃ እያቀረቡ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
“በአገር ቤት ካሉ ባለድርሻ አካላት በአፋጣኝ ጥንቃቄ የተሞላው ግንኙነቶችን መፍጠርና በጋራ መድረኩ የትግል አካሄድ ላይ አንድ አይነት መግባባት ላይ መድረስ፣ በመላ አገሪቱ ባሉ የተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ አመጽ የሚቀጣጠልበትን መንገድ በአገር ውስጥ ካሉ የለውጥ ሃይሎች ጋር በመምከር አቅጣጫዎችንና ስልቶችን መቀየስና ሕዝቡ በእምቢተኝነት ከትግል ሃይሎች/ የታጠቁ ኃይሎች ጋር አብሮ እንዲቆም የሚያስችሉ የቅስቀሳ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል” የሚል የዕቅድ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለአባላቱ ያሰራጨው የጋራ መደረኩ፣ በመስከረም ወር አዲስ አመጽ ለማነሳሳት፣ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች ይነሳሉ ከተባሉት ግጭቶችና ጦርነት ጋር ተናቦ ለመስራት መዘጋጀቱን የጋራ መድረኩ ይፋ አድርጓል።
አባላቱ እየሸሹትና ስብሰባዎችን በተሟላ አባላት ማካሄድ ያቃተው ይህ የጋራ መድረክ፣ ቀደም ሲል “እናንተ ከግብጽና ኤርትራ ገንዘብ ትቀበላላቹህ፤ እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። double standard አትጫወቱ” በማለት ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የመድረኩ አመራሮች መውቀሳቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
በዚሁ የግሩፕ መነጋገሪያ አውድ ላይ የሰው ልጆች መብት ተከራካሪ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ያሬድ በይፋ ኤርትራ የጋራ መደረኩን እንደምትረዳ ይፋ ማድረጋቸውን ለዋሽንግቶን ተባባሪያችን ይፋ ያደረጉት የመደረኩ አባል፣ ያጋራ መድረኩ ብሄራዊ አገራዊ የምክክር ኮምኒሽን እያካሄደ ያለውን ውይይት ለመቃወምና በመስከረም ሊያደርጉት ያሰቡትን አመጽ አስመልክቶ ለመወያየት በተጠራ ስብሰባ አራት ሰው ብቻ በመገኘቱ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል።
አዲስ አበባ በህቡዕ የሚሰሩ አባላትን እንዳደራጀ የሚገልጸው የጋራ መደረኩ የሙያ ማህበራት ለጥሪው ጀርባ እንደሰጡት ተመልከቷል። ሻዕቢያ የሚመራውን ጦርነት በአመጽ ለማገዝ ተናበው ለመስራት ድጋፍ የሚደረግለት የጋራ መድረክ ያለፉት ሁለት ስብሰባዎች ባለመግባባት መበተኑን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






