“ሁሉም ሰው ደኅንነቱ እና ክብሩ በተጠበቀ ሁኔታ ቀጣይ ሕይወቱን የት መመስረት እንዳለበት እንዲወስን በኢትዮጵያ የሚመራ እና በተባበሩት መንግሥታት የሚታገዝን ሂደት አሜሪካ ትደግፋለች” አሜሪካ
አዲስ ሪፖርተር – በወልቃይት ግንባር ትህነግ ያሰማራውን ሰራዊት የሚመሩት ጄኔራል ምግበይ ዓርብ ዕለት “ከኤርትራ አስፈላጊ ተተኳሽ መሳሪያ በበቂ ሁኔታ አግኝተናል። የፈለግነውን መሳሪያ በድንበር ለማሰገባት ተስማምተናል። በሚወጥለው ሳምንት ምዕራብ ትግራይን እናስመልሳለን” በማለት መናገራቸው ታውቋል።
ምግበይ “ሻዕቢያ አይታመንም” በማለት የተናገሩበት የድምጽ ማስረጃ ይፋ ከሆነ በሁዋላ መሻከር መፈጠሩና ከሁለቱ ጎራ የተሰለፉ አክቲቪስቶች ይህንኑ ተከትለው ጎራ ለይተው ሲነታረኩ መሰንበታቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኤርትራ መንግስት የላከውን ከሃምሳ ሺህ በላይ ተተኳሽ መያዙን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ኤርትራ ኢትዮጵያን ለማተራመስ መሳሪያ እያስገባች መሆኑን ጠቅሶ ያሰራጨውን መረጃ እንደ ቢቢሲ፣ ሲኤን ኤን፣ ሮይተርስና የመሳሰሉት ታላላቅ የዓለም ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል።
ይህ ይፋ በሆነ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ጄ. ምግበይ ከኤርትራ በቂ ተተኳሽ መሳሪያ ማግኘታቸውን ለሚመሩት ሰራዊት ሲናገሩ፣ በስፍራው የነበሩ የመረጃ ሰዎችን ጠቅሶ የትግራይ የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ እንዳለው “ በሚቀጥለው ሳምንት ወልቃይትን ለመያዝ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ይካሄዳል” ብለዋል።
በሱዳን ጦርነት ውስጥ የሱዳን ጦር ሠራዊት መሪ አብደል ፋታህ አል ቡርሐንን ወግኖ እንደሚዋጋ መረጃ የምወጣበትንና እዛው መሽጎ የነበረውን ለአርሚ 70 በኤርትራ ድንበር በኩል ማስጠጋታቸውን ለሰራዊቱ የገለጹት ምግበይ፣ ይህ ኃይል በሱዳን በኩል ኤርትራን ታኮ ወልቃይት ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ተናግረዋል።

በሰራዊቱ ዘንዳ ውጊያ የማድረግ ፍላጎት ስለመኖሩ ጥርጣሬ ስላላቸው በቂ ኃይል፣ መሳሪያና ቅንጅት መኖሩን ከታቀደው ኦፕሬሽን ጋር በማያያዝ ያብራሩት ምግበይ፣ እሳቸው የሚመሩት ሰራዊት ከምዕራብ አቅጣጫ፣ አርሚ 70 ከሱዳን በኩል፣ በጋር ጥቃት ይሰነዝራሉ።
“የከፋ ነገር ካለ የኤርትራ መንግስት ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ ጣልቃ እንደሚገባ ቃል ተገባብተናል። ስምምነት ላይም ተደርሷል። ጽምዷችንን በይፋ ለትግራይ ህዝብ ይፋ ለማድረኛ ለማወጅ በዝግጅት ላይ ነን” ሲሉ ሰራዊቱ ለማሸነፍ ሞራሉ እንዲነሳሳ ሞክረዋል።
“እጅ የማይሰጠው የፋኖ ኃይል ትግራይ ነው።ምንፈልገውን ነገር ያደርግልናል” በማለት ጄኔራል ምግበይ አመልክተዋል። አከሉና “የተቀሩት ፋኖዎች በወልቃይት ጉዳይ አቋማቸው ግልጽ አይደለም አይታመኑም” ብለዋል።
ንግግራቸውን አድመጠው ለተባባሪያችን ያስረዱት አካላት እንዳሉት፣ በአማራ ፋኖ ውስጥ የታየው የአደረጃጀት መፍረስ በሻዕቢያ ዘነድ ስጋት ፈጥሯል። “መሳሪያ እየያዙ ለመንግስት እጅ እየሰጡ ነው” ያሉዋቸውን ፋኖዎችና አመራሮቻቸውን የወቀሱትና የማይታመኑ መሆናቸውን ያስታወቁት ምግበይ፣ “ልክ በራያ እንዳደረግነው መዕራብ ትግራይን በሚቀጥለው ሳምንት ካልተቆጣጠርን ተፈናቃዮችን ብቻ ወደ መኖሪያቸው መልሰው የትግራይን ነባር አስተዳደርና የጸጥታ ኃይል ያስቀሩታል” ብለዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደርና ልዑካቸው ጉዞም ይህ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባደሳር ኧርቪን ማሲንጋ በሰሜን ሁመራን ከጎበኙ በኋላ ተፈናቃዮች “መጻኢ ፖለቲካዊ ዕድላቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲወስኑ” ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል በማለት በማህበራዊ ገጻቸው ጥሪ አቅርበው ነበር። አምባሳደሩ “ሁሉም ሰው ደኅንነቱ እና ክብሩ በተጠበቀ ሁኔታ ቀጣይ ሕይወቱን የት መመስረት እንዳለበት እንዲወስን በኢትዮጵያ የሚመራ እና በተባበሩት መንግሥታት የሚታገዝን ሂደት አሜሪካ ትደግፋለች” ሲሉ ተፈናቃዮችን የማስመለሱ ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት መሆኑን አንስተው የአገራቸውን አቋም አንጸባርቀው ነበር። “ሁሉም ወገኖች ከፖለቲካ በላይ ሕዝብን በማቀስደም የወደፊት የፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታቸውን በተገቢው ወቅት እንዲወስኑ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን” በማለት ለአምስት ዓመታት ተፈናቅለው በአስከፊ ሁኔታ የሚኖሩትን ዜጎች ታሳቢ ሊደረጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አብረዋቸው የተጓዙት አቶ ጌታቸው ረዳ በሪፖርተር እንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ፣ የፊደራል መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት አሁን ያለውን አስተዳደር አፍርሶ ተፈናቃዮችን ለመመልስ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል። ግጭትና የይገባኛል ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች የፊደራል መንግስት እንዲያስተዳድራቸውና ወደፊት በሕዝብ ውሳኔ ፖለቲካዊ ምላሽ እንዲሰጥ አቅጣጫ መቀመጡ አይዘነጋም።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ አንጻራዊ መረጋጋት የሰፈነ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የትህነግ (TPLF) አመራሮች ከጥምቀት በዓል በኋላ በወልቃይት ጠገዴ አቅጣጫ አዲስ የጦርነት ግንባር ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ከላፈው ሳምንት ጀምሮ በስፋት ሲሰራጩ ቆይተዋል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ለአዲስ ሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ ጦርነቱ በቅርብ ቀናት ውስጥ ሊጀመር እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አለ። ራሳቸውን ከትህነግ ያገለሉ ከፍተኛ መኮንን “ስሜታዊ በሆነ ውሳኔ አንድ ወገን ጦርነት ከቀሰቀሰ ማቆሚያ አይኖረውም። መሬት ላይ ባሉ እውነታዎች ግን ጦርነት እናደርጋለን የሚሉ ወገኖች ጦርነት ለመጀመር የሚያስችል አቅም የላቸው” ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“የግብጽንና የሳኡዲ አረብያን ጉዳይ ለጊዜው ተውት” ያሉት መኮንኑ ኤርትራ የውክልና ጦርነት ከማቀጣጠል ውጭ በጦረነቱ ውስጥ በቀጥታ እንደማትገባ ከልምድ ብዙ እንደሚያውቁ ጠቁመዋል። ኢኮኖሚያውም እንደማይፈቅድ አመልክተዋል።
“ተፈናቃዮች ብቻቸውን እንዲሰፍሩ እንቅስቃሴ መጀመሩና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች ወደ ሰላም አማራጭ መምጣታቸው ነው ስጋት ስለገባው ጦርነቱ እንዲጀመር ከኤርትራ በኩል ግፊት ተፈጥሯል” የሚሉ፣ ሌላ የሚታወቁ የፋኖ አመራሮች ታጣቂዎችን በመያዝ ለመንግስ እጅ እንደሚሰጡ መረጃው ስላላቸው የሚጠረጠሩትን በከበባ ትጥቅ እንዲፈቱ እንዲደረግ መመሪያ መሰጥቱም ታውቋል።
ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተና ጓደኞቻቸው በዚሁ መመሪያ ከበባ ተደርጎባቸው የነበረ ቢሆንም ጉዳት አድርሰው ከበባውን ሰብረው በሰላም መግባታቸውን አመራሮቹ አዲስ አበባ ሲደርሱ ያገኙዋቸው አስታወቀዋል። ሌሎችም በጉዞ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ካፒቴን ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ በድርድር ለመንግስት እጅ የሰጡ የፋኖ አመራሮችና ታጣቂዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆንና እጃቸውን የሰጡት ታጣቂዎች ከመከላከያ ጎን ለመስለፍና ክልላቸውን ለማጽዳት መወሰናቸው እየተሰማ ነው። በሌላ በኩል “አጋጣሚው ትግሉን አጠራው” የሚሉት በዘመነ ካሴ የሚመራው ኃይል አንድ መሆኑን አስታውቋል።
ይህንኑ የአንድነት ዜና የሻዕቢያ ወኪል ሚዲያዎችና አቶ ነዓምን “እንኳን ደስ ያለን” በማለት በየሚዲያዎቻቸው እያስተጋቡ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት በበኩሉ፣ ማንኛውንም ዓይነት የሀገርን ሉአላዊነት የሚጋፋ እንቅስቃሴ ለመመከት በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። በመከላከያ ሰራዊት በኩል የተሰጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በወልቃይት፣ በጠገዴና በአጎራባች አካባቢዎች ሊሰነዘር የሚችለውን ማንኛውንም ጥቃት ለመመለስ ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል። መንግስት የሰላም አማራጩን ቅድሚያ ቢሰጥም፣ የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የውጭና የውስጥ ሀይሎች ቅንጅትን በፅኑ እንደሚመክት ገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ያለው ሁኔታ እጅግ ውጥረት የነገሰበት ሲሆን፣ የትህነግ አመራሮች ከሻቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይፋ የሚያደርጉበትና የጦርነቱን አዋጅ የሚያውጁበትን ሰዓት ህዝቡ በስጋት እየተጠባበቀ ይገኛል። “ተዘጋጁ” የተባሉ የትግራይ ነዋሪዎች እንኳን ጦርነት በቲማቲም መፈናከት እንደማይፈልጉ፣ ይህ አቋም የሰራዊቱም እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






