የፕሪቶሪያው ስምምነት በትህነግ በኩል መፍረሱን የትግራይ ተቃዋሚ ፓሪዎች አስታወቁ፤ ትግራይን የጦር ማዕከል የሚያደርገው የሻዕቢያ ዕቅድ ተግባራዊ መሆኑ በትግራይ ዳግም ቀውስ አስነሳ፤ አፈሳና ሽሽት መጀመሩ ተነገረ።
- ያለፈውን ጦርነት የሚያስታውሱ “ጦርነትን ተቃወሙ፣ ጦርነትን እምቢ በሉ “ የሚል ጥሪ ለትግራይ ወጣቶች እያቀረቡ ነው
- ጦርነትን አንፈልግም ያሉ እየሸሹ ነው
- የአገር መከላከያ ከአላማጣ ወደ ቆቦ አመራ።
- ትህነግ፣ ሻዕቢያና ፋኖ በግብጽ አስተባባሪነት የተቀናጀ ጦርነት ለመክፈት በቋፍ ላይ ናቸው
- በምዕራብ ጠለምትና በዋልድባ አቅጣጫ መከላከያ ከባድ የተባለ የመከላከያ እርምጃ ወስዷል። ነጥቦቹ እነዚህ ናቸው እንደሚከተለው አጠናክረነዋል።
አዲስ ሪፖርተር – ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ በሚል ስያሜ የሚጠራው ቡድን ረቡእ ሰባት ሰዓት አካባቢ በምዕራብ ጠገዴ አቅጣጫ የዲማን ከተማ ለመያዝ ስድስት ኮሮችን አስገብቶ ነበር። ሶስቱን ኮሮች ከፊት ለፊት አድርጎ፣ አራቱን በግራና ቀኝ በማሰለፍ ጥቃት ጀመረ። ነገር ግን ብዙ ሳይዋጋ አፈገፈገ።
በውጊያው ከተሳተፉ የአካባቢው አስተዳደር አመራሮች የተገኘው መረጃ እንደሚያለከተው፣ የአገር መከላከያ ባለበት ሆኖ የሰጠው የመከላከል አጻፋ ከባድ ነበር። በአየርና በከባድ መሳሪያ የተደገፈ አጭርና ጠንካራ ምላሽ ከተሰጠ በሁዋላ ከፊት ለፊት የገባው ሶስት ኮር ምን እንደገጠመው ወደፊት ታሪክ እንደሚዘግበው እነዚሁ ወገኖች አስታወቀዋል። ጥቃቱን የሰነዘረው ትህነግ በጉዳዩ ዙሪያ በድልም ሆነ በሽንፈት እስካሁን ያለው ነገር የለም።
መከላከያ በርቀት ሆኖ የሰጠውን ምላሽ መቋቋም ያቃተው ቀሪው ኃይል አፈግፍጎ ተከዜ ጫፍ ማይበሌ በየጉድጓድ ራሱን መደበቁን ዜናውን ያጋሩን አመልክተዋል። ከትህነግ በኩል ምንም ዓይነት ማብራሪያ ያልቀረበበት ይህ ውጊያ የተካሄደው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ቀጣዩ ዕቅድ ምን እንደሆነ ለመናገር እንደሚችገሩ የዜናው ምንጮች አመልክተዋል።
ዜናውን ያጋሩን የአስተዳደሩ አካል “ የትህነግ አዋጊዎች ስትራቴጂ ይቀይራሉ፣ ዕቅዱ ስላልተሳካ ሰላም ይሻላል ብለው ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ መጡበት ይመልሳሉ፣ ቦታ ቀይረው ሌላ ዕድል ይሞክራሉ?” ለሚለው ለጊዜው ምንም ምላሽ መስጠት እንደማይቻል አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ኃይላቸውን ዳግም እያሰባሰቡ ስለመሆኑ መረጃና ምልክቶች እንዳሉ አልሸሸጉም።
“የአገር መከላከያን ሳይጨምር በእኛ በኩል ጠንካራ ዝግጅት አለ” ያሉት አስተዳደሩ፣ እስካሁን ባለው እውነታ ክስድስት ኮር በላይ አሰልፎ የመጣው ኃይል ክፉኛ ጉዳት ደርሶበታል። ከዚያ በላይ ደግሞ ሰራዊታቸው የመዋጋት ፍላጎት የለውም።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የትግራይ ሰላም ኃይሎች የስፍራው አመራር፣ መንግስት ከባድ እርምጃ መውሰዱን መታዘባቸውን፣ በርካታ ታጣቂዎችም እነሱን እየተቀላቀሉ መሆኑን በትግርኛ ካደረጉት ቃለ ምልልስ ለማረጋገጥ ተችሏል።
የአስተዳደሩ አካላት እንደሚሉት ሕዝቡ “አጎሳቆላችሁን፣ አታለላችሁን፣ ጦርነት አንፈልግም፣ በቃን” በማለት በትህነግ ኃይሎች ላይ ተቃውሞ ሲያሰማ መቆየቱን አመልክተዋል። ይህን አስመልክቶ የትህነግ ኃይሎች በግልጽ መረጃ ሲሰጡ ወይም የጀመሩትን ጦርነት በህዝብ ዘንዳ ድጋፍ ያለው ስለመሆኑ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ ያስታወቁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት “ደህና ሁኚ ሽሬ” በማለት እናቶች ሲጨፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ተሰራጭቶ ነበር።
በዋልድባ አቅጣጫ ተጀምሮ ከከሸፈው ጥቃት በሁዋላ በምዕራብ ጠለምት የተካሄደው ጦርነት የተሳካ ውጤት ባያስመዘግብም፣ ሶስቱን ኃይሎች አስተባብራ የምትመራው ግብጽ ዓላማዋ የኢትዮጵያን መንግስት በማፍረስ አገሪቱን ለጎበዝ አለቆች መናኸሪያ ማድረግ እንደሆነ እጃቸውን የሰጡ መናገራቸው ይታወሳል።
“ለባዕዳን ተልዕኮ አስፈጻሚ አንሆንም፣ ትግሉ ተጠልፎ የግብጽና የሻዕቢያ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኗል” በማለት ወደ ሰላም መንገድ የተመለሱት የፋኖ የተለያዩ አደረጃጀቶች እንዳሉት፣ ዘመነ ካሴ የሚመራው የፋኖ ኃይል ወልቃይትን አሳልፎ ለመስጠት ስምምነት አድርጓል። ይህ ስምምነት ደግሞ ሰፊውን የፋኖ ኃይል አስቆጥቷል። አሁን ላይ እንደሚሰማው ከሆነ ወልቃይትን አስመልክቶ አዲስ መረጃ ለመስጠት የፋኖና የትህነግ ኃይሎች እየተዘጋጁ ነው።
አቶ ጣሂር መሐመድ ወልቃይትን ለማስረጀብ የተስማሙትን የፋኖ ጥቂት አመራሮች አስመልክቶ “ባንዳ” በማለት ዝርዝር ማብራሪያ መስተቱን ተከትሎ “ከድል በሁዋላ ያገናኘን” በማለት በአርበኛ መሳይ መኮንን አመካይነት ማስፈራሪያ ደርሶታል።
ኤርትራዊ ሚስት ያላቸው ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ “የአገር መከላከያ ሰራዊት በአማራ መሬት ላይ ተረማምዶ ሻዕቢያንና ትህነግን ለማጥቃት ሲሞክር ከጀርባው እንሰፍርበታለን” ማለታቸው አይዘነጋም። በዚህና በተለያዩ መረጃዎች መነሻ የፋኖ ኃይል ቁጣ ማሰማቱና ወደ ሰላም ማምራቱ በሻዕቢያና ትህነግ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩ እየተዘገበ ሰንብቷል።
ይህንኑ ስሜት ተከትሎ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የፋኖ ታጣቂዎችና የተለያዩ አደረጃጀቶች ወደ ሰላም እየገቡ በመሆኑ ሻዕቢያ ጦርነቱ ቶሎ እንዲቀጣጠል አመራር መስጠቷን ጠቅሰን ከሳምንት በፊት መዘገባችን አይዘነጋም።
በስተመጨረሻ አዲስ ሪፖርተር ባሰባሰበችው መረጃ በራያ አቅጣጫ፣ በአፋር ጨርጨር፣ በወልቃይት ሙሉ በሙሉ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ነው። በትግራይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አቁሟል። ባንኮች በይፋ ባያቆሙም አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ለሕዝብ ጥቅም ወደ ትግራይ የተላከ ነዳጅ ወደ ግዳጅ ጣቢያዎች ተሰራጭቷል። ገሚሱም ወደ ኤርትራ ተልኳል።
የአፋር ቀይ ባህር አመራሮች ለአዲስ ሪፖርተር እንዳሉት በቂ ዝግጅት አድርገው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የጦርነቱን አድማስ በማስፋት በሁሉም በኩል በይፋ ጦርነት ከመለኮሱ በፊት የአገር መከላከያ ሰራዊት ከአላማጣ ለቆ በመውጣት ወደ ቆቦ ተመልሶ ስትራቴጂክ የተባሉ አካባቢዎችን መያዙ ታውቋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






