የክፉ ጊዜ ወዳጅነት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤምሬትስ ጉብኝት አንድምታዎች  

Date:

      የኢትዮጵያን ቀጠናዊ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚከፈለው መስዋዕትነት ታሪካዊ ዋጋ አለው። በመሆኑም፣ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ሳይከፋፈሉ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን፣ የአገሪቱን የዲፕሎማሲ ድል ማስቀጠልና የሚመጡ ተጽዕኖዎችን በጽናት መቋቋም ይገባል። ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ ብቻ ነው ኢትዮጵያን በሁከተኛው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ በድል አድራጊነት ሊያሻግራት የሚችለው።

አለባቸው ጉብሳነፃ አስተያየት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ረፋዱ ላይ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ገብተዋል። ጠቅላይ ሚንስቴሩ ወደ ኤምሬቶች ያቁኑት፣ ትናንት ወደ ጅቡቲ ተጉዘው ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጌሌ እና ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ ጋር በቀጠናዊ ደኅንነትና ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ ነው። የሦስቱ መሪዎች ውይይት ለጋራ ቀጣናዊ ተግዳሮቶች የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደነበር የጅቡቲ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የጠቀሠ ሲሆን፣ መሪዎቹ በቀጠናው አገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ሂደት ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

የኔ ትኩረት በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅና በገልፍ ቀጠና የታየው ወታደራዊ ውጥረት፣ በተለይም ኢራን በዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ላይ ወታደራዊ ጥቃት እየፈፀመች ባለበት ሁኔታ  እና  የዓለምን ትኩረት በሳበበት በዚህ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አቡ ዳቢ ማምራት ምን አይነት ስትራቴጂያዊና ጂኦፓለቲካዊ አንድምታ አለው? እንደዚህ አይነት ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝቶች በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አስተምህሮ ምን አይነት ቦታ ይሰጣቸዋል? የሚለው ነው። 

በኢራን ወደ ኤምሬትስ የተሰነዘረ ጥቃት

አንባቢ ይህ የጠቅላይ ሚንስቴሩ ይፋዊ የስራ ጉብኝት  በጦርነት መሃል የተደረገ እንደሆነ በቅጡ እንዲረዳ ትላንት ተዋቂው የአሜሪካ የጦርነት ጥናት  ኢንስቲትዩት (Institute for the study of War) ያወጣውን መረጃ እንመልከት።

ከየካቲት 21 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከኢራን ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተሰነዘረው ጥቃት በዋናነት በድሮኖች የበላይነት የተመራ ነበር። በጥቃቱ ወቅት በአጠቃላይ 1,486 ድሮኖች፣ 262 ባሊስቲክ ሚሳኤሎች እና 8 የክሩዝ ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፣ በተለይም በየካቲት 22 ቀን ብቻ የተተኮሱት 332 ድሮኖች የጥቃቱን ከፍተኛ መጠን ያሳያል። የጥቃቱ ስልት እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ድሮኖች በመጠቀም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የአየር መከላከያ ሥርዓት ለማጨናነቅ ያለመ እንደነበር መረዳት ይቻላል።

ምንም እንኳን የጥቃቱ መጠን ከፍተኛ ቢሆንም፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደ THAAD እና Patriot ያሉ ዘመናዊ የመከላከያ መሣሪያዎችን በመጠቀም አብዛኞቹን ሚሳኤሎችና ድሮኖች ማክሸፍ ችላለች። ይህም በጥቃቱ ሊደርስ የሚችለውን የሰው ሕይወት ጥፋት በእጅጉ የቀነሰ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ አንዳንድ ድሮኖች መከላከያውን ጥሰው በመግባት በነዳጅ ማከማቻዎች፣ በኢንዱስትሪ ቀጠናዎች እና በሲቪል አየር ማረፊፓ ላይ መጠነኛ የመሰረተ ልማት ጉዳቶችን አድርሰዋል። እንግዲህ ጠቅላይ ሚንስቴር ይህን ታሪካዊ ጉዞ ወደ አቡ ዳቢ ያደረጉት በዚህ የጦርነት ቀጠና ውስጥ መሆኑን አንባቢ ልብ ይሏል። 

ጉብኝቱ ከአጋርነት መርሆዎች አንፃር ሲፈተሽ

 ሚራ ራፕ-ሁፐር በአሜሪካ የባይደን አስተዳደር ውስጥ ብሄራዊ ደህንነት ረዳት አማካሪ ሆና ሰርታለች። በቅርቡ ሃገራት ኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ እና ትክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ  ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ወይም አጋርነት(Alliance) ለምን እንደሚመሰርቱ የሚያትት Shields of the Republic ተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች።  በዚህ መፅሃፏ፣ አጋርነት ከመደበኛ ዲፕሎማሲ ባለፈ የጋራ ሕልውና መጠበቂያ  ዋስትና እንደሆነ ነው። ጠቅላይ ሚንስቴሩ በጦርነትና በስጋት ውስጥ ያደረጉት  ጉዞ፣ ኢትዮጵያና ኤምሬትስ ከጥቅም ትስስር ባለፈ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚዘልቅ “ጥልቅ ስትራቴጂካዊ አጋርነት” (Deep Strategic Alliance) ላይ መድረሳቸውን ለዓለም ያበሰረ ክስተት ነው።

የታዋቂው የአለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ስቲፈን ዋልት (Stephen Walt) “The Origins of Alliances” በሚለው መጽሐፉ፣ አገራት አጋርነትን የሚመሰርቱት ስጋትን ለመመከት (Balance of Threat) እንደሆነ ይገልጻል። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ያሳየችው ቆራጥነት ዋልት የሚለውን “የስጋት ሚዛን” መርህ በተግባር ያሳየ ነው፤ ይህም ኤምሬትስ የገጠማትን ስጋት ኢትዮጵያ እንደራሷ ስጋት በመቁጠር አብሮ የመቆም ፖለቲካዊ ውሳኔ መውሰዷን ያሳያል። ራፕ-ሁፐር “የመከላከያ ጋሻ” (Defensive Shield) የምትለውን ፅንሰ-ሐሳብ የሚያጠናክረው ይህ ድርጊት፣ አጋርነት በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመከራ ወቅት የሚጸና “ውድ ዋጋ ያለው ምልክት” (Costly Signaling) መሆኑን ያረጋግጣል።

ሌላኛው ታዋቂ ተመራማሪ ግሌን ስናይደር (Glenn Snyder) በአጋርነት ፖለቲካ ውስጥ “የአጋርነት አጣብቂኝ” (Alliance Dilemma) በሚለው ንድፈ-ሐሳቡ፣ አገራት በአጋሮቻቸው “መተው” (Abandonment) እንዳይገጥማቸው የሚያሳዩትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ይተነትናል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት ለኤምሬትስ መንግስትና ህዝብ  የሚያስተላልፈው መልዕክት  “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አንተዋችሁም፣ 130 ሚልዬን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ከጎናችሁ ነው” የሚል ጠንካራ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው። ይህ ድርጊት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከመደበኛ የንግድ ልውውጥ አልፎ ወደ “ወታደራዊና ደህንነት ትብብር” (Security Alignment) ያሸጋገረ ሲሆን፣ ስናይደር እንደሚለው የአጋርነትን ተዓማኒነት (Credibility) ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ ነው።

ራፕ-ሁፐር በመፅሃፏ እንደምትሞግተው፣ እውነተኛ አጋርነት የሚለካው አጋር አገር አደጋ ላይ በሚወድቅበት ወቅት በሚታይ ቁርጠኝነት ነው። ኢትዮጵያ በገልፍ ቀጠናው እየተካሄደ ያለውን የቀጥታ ጦርነትና የሚሳኤል ስጋት ተጋፍጣ ጉብኝት ማድረጓ “አንተ ላይ የተቃጣ ጥቃት በእኔም ላይ ነው” የሚል የጋራ መከላከያ ስሜትን (Collective Defense Sentiment) የሚያንጸባርቅ ነው። ከጥቅም አንፃር ሲታይ፣ ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ በጂኦ-ፖለቲካዊ መድረክ ያላትን ሚና ከፍ የሚያደርግና ወደፊት ለሚመጡ ቀውሶች እንደ ዋስትና የሚያገለግል የስትራቴጂክ ጥምረት መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።

በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው “የአጋርነት ድል” (The Triumph of Alliance) የሚገለጠው፣ አንዱ አጋር በሌላው ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመጋራት ዝግጁ ሲሆን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ኤምሬትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገለለች እንዳይመስላትና የሞራል ድጋፍ እንድታገኝ ያደርጋታል። ይህ በጦርነት ወቅት የሚደረግ “የዲፕሎማሲያዊ ግንባር” (Diplomatic Front) ግንባታ ሲሆን፣ በባላጋራ ኃይሎች ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከኤምሬትስ ጀርባ መኖሯን የሚያሳይ ጠንካራ መልእክት ያስተላልፋል። ስቲፈን ዋልት እንደሚለው፣ ይህ አይነቱ አጋርነት ጠላት ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ደግሞ እንዲያስብ የሚያደርግ (Deterrence) አቅም አለው።

በሌላ በኩል፣ ራፕ-ሁፐር “የአጋርነት ስጋት” (The Peril of Alliance) ስትል የምትገልጸው፣ አንዱ አጋር በሌላው ጦርነት ውስጥ የመሳብ እድሉን ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ያሳየችው ድፍረት፣ ይህንን ስጋት በጸጋ የመቀበል ያህል ይቆጠራል። ይህም ግንኙነቱ “እስከ ሕይወት መስዋዕትነት” የሚዘልቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በኤምሬትስ ሰማይ ላይ ድሮኖች በሚበሩበት ወቅት መገኘት፣ ለወታደራዊ አጋርነት ከሚሰጡት ከፍተኛ ዋጋዎች መካከል ቀዳሚው ነው። ይህ አይነቱ “የማይናወጥ ቁርጠኝነት” (Irrevocable Commitment) በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ወደ ስልታዊ ውሕደት ያሳድገዋል።

በተጨማሪም፣ ይህ ጉብኝት በምስራቅ አፍሪካና በገልፍ ቀጠና መካከል ያለውን የደህንነት ትስስር (Security Linkage) ይበልጥ ያሳያል። ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ፣ ኢትዮጵያም በዲፕሎማሲያዊና በሞራል ቆራጥነት እየመለሰችው መሆኑን ያሳያል። ራፕ-ሁፐር እንደምትለው ፣ አጋርነት የሚጸናው በጋራ ጠላትና በጋራ ስጋት ላይ በታየ ጽናት ነው። ኢትዮጵያ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ገብታ ወዳጅነቷን ማሳየቷ፣ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ “ተአማኒ አጋር” (Reliable Partner) መሆኗን ያስመሰክራል፤ ይህም ኢትዮጵያን የቀጠናው ቁልፍ ተዋናይ (Regional Hegemon) እንድትሆን መንገድ ይከፍታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉብኝት በዲፕሎማሲው ዓለም “ጀግንነት የታከለበት አጋርነት” ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። Shields of the Republic ላይ እንደተገለፀው ፣ አጋርነቶች ለቀጠናዊ መረጋጋት እንደ ጋሻ ያገለግላሉ። ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኤምሬትስ ጎን መቆሟ፣ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባራዊና መስዋዕትነት ወደሚጠይቅ “እውነተኛ አጋርነት” (True Alliance) ማሳደጓን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ እርምጃ ነው። ይህ ወዳጅነት በሁለቱ አገራት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ለቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካ አዲስ አቅጣጫ የሚጠቁም  ነው።

ተመልከት ሰንደቅህን ተከተል አለቃህን!

ይህ ይፋዊ ጉብኝት የሚፈጥረውን አንድምታ ከላይ እንደተመለከትነው ወታደራዊ አጋርነትነት የሚፈጥር ሲሆን በሌሎች ቀጠናዊ ብሄራዊ ጥቅም ባላቸው ሃገሮች ደግሞ እንደ ጥላትነት ተግባር ይታያል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ተፅዕኖ እና ጥቅሟን የማይሹ ኃይሎች መደበኛ ባልሆነ ጦርነት (Unconventional Warfare) አገሪቱን ለማዳከም እንዲነሳሱ ሊያደርግ ይችላል።

ይህንን ስጋት ለመመከት የመጀመሪያውና ዋናው ምሰሶ የዜጎች ንቃት ነው። እያንዳንዱ ዜጋ የአገሩን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በመገንዘብ፣ የሐሰት መረጃዎችንና የውስጥ ልዩነቶችን ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል። “ተመልከት ሰንደቅህን” እንደሚባለው፣ የጋራ ምልክታችን የሆነችው አገር አደጋ ላይ ስትወድቅ የግልና የቡድን ፍላጎቶችን ለብሔራዊ ህልውና ማስገዛት የዜግነት ግዴታ ነው።

የተቃዋሚ ፖርቲዎች ሚናም በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ እጅግ ወሳኝ ነው። ዲሞክራሲያዊ ውድድርና የሐሳብ ልዩነት በሰላም ጊዜ የሚታዩ የፖለቲካ ውበቶች ቢሆኑም፣ አገር የውጭ ስጋት ሲጋረጥባት ግን “ተከተል መሪህን” የሚለው መርህ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሳይሆን ለጋራ ቤት መዳን ተግባራዊ ሊሆን ይገባል። ተቃዋሚ ኃይሎች በመንግሥት የአገር ውስጥ ፖሊሲ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ወደ ጎን በመተው፣ በውጭ ጉዳይና በብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር የጋራ ግንባር መፍጠር ይኖርባቸዋል። ይህ አንድነት ለጠላቶች ግልጽ የሆነ “ኢትዮጵያ አትበገሬ ናት” የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ከመሆኑም በላይ፣ በውስጥ ድክመት ተጠቅመው አገርን ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ተስፋ ያስቆርጣል።

የገዥው ፓርቲና የመንግሥት አካላት ደግሞ ይህንን የሕዝብና የተቃዋሚዎች ድጋፍ ለማግኘት ግልጽነትና አካታችነትን መከተል ይኖርባቸዋል። ብሔራዊ ጥቅምንና የተወሰዱ የዲፕሎማሲ እርምጃዎችን ለሕዝቡ በግልጽ በማስረዳት፣ ጥርጣሬዎችና ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ መስራት ይጠበቅባቸዋል። መንግሥት የሕዝቡን የደኅንነት ስጋት የሚቀንሱ መዋቅሮችን በማጠናከርና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የብሔራዊ መከላከል ስትራቴጂ በመንደፍ፣ አገሪቱን መደበኛ ባልሆኑ ጥቃቶች (እንደ ሳይበር ጥቃትና የኢኮኖሚ አሻጥር) መጠበቅ አለበት። የመሪነት ሚናው የሚለካው ሕዝቡን አስተባብሮ ለጋራ ዓላማ በማሰለፍ ብቃት ላይ ነው።

በመጨረሻም፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታሪካዊ ጠላቶቹና ከአጋሮቹ የሚመጡትን ጥቅሞችና ጉዳቶች በሚገባ መመዘን ይኖርበታል። በኤምሬትስና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወዳጅነት የሚያመጣው ስጋት ቢኖርም፣ የኢትዮጵያን ቀጠናዊ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚከፈለው መስዋዕትነት ታሪካዊ ዋጋ አለው። በመሆኑም፣ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ሳይከፋፈሉ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን፣ የአገሪቱን የዲፕሎማሲ ድል ማስቀጠልና የሚመጡ ተጽዕኖዎችን በጽናት መቋቋም ይገባል። ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ ብቻ ነው ኢትዮጵያን በሁከተኛው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ በድል አድራጊነት ሊያሻግራት የሚችለው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ማርኮ ሮቢዮ ከአብይ ጋር መከሩ፤ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በቀይ ባህርና በአፍሪቃ ቀንድ አሰላለፋቸው ይፋ እየሆነ ነው

አዲስ ሪፖርተር - አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የጠብመንጃ ግብግብ...

How Ethiopia Anchors the Horn Against Sudan’s Ongoing War

Civil wars are often explained as the inevitable eruption...

ነዳጅ ከዋጋ ተመን በላይ የሚሸጡ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፤ ከ 3 እስከ 10 ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ - የገንዘብ ሚኒስቴር በመካከለኛው ምስራቅ...

የ“ትዕይንተ ሕዝቦች አዘጋጅ ግብረ ኃይል የቴክኒክ ኮሚቴ” የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገቡ

አዲስ ሪፖርተር - በትናንትናው ዕለይ ራሱን “ትዕይንተ ሕዝቦች አዘጋጅ ግብረ-ኃይል...