አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ – በድህረ-ምርጫ የሚመሰረተው መንግስት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በወልቃይትና ራያ አካባቢዎች አፋጣኝ ምርጫ በማከናወን እና ነጻ የህዝብ አስተዳደር እንዲዋቀር በማገዝ ዋጋ ለተከፈለባቸው የመብት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ አብን ጠየቀ። በተያያዘም በአማራ ክልል እንዲሁም በመላው ሀገሪቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች የማሟያ ምርጫ በማከናወን የህዝቡ ወኪሎች በአዲሱ መንግስት ምስረታ ተሳታፊ እንዲሆኑ አሳስቧል። ምርጫው ብዙ ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነም አመልክቷል። መግለጫውን ከስር ያንብቡ።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ድርጅታዊ መግለጫ
“7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ህዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው፡፡”
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ህዝቡ ወደ ተሻለ የፖለቲካ እና የማህበረ-ኢኮኖሚ ምዕራፍ ለመሻገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ውሳኔ ሲሆን፣ የተመዘገበው ስኬት የማህበረሰባችን የአርቆ አሳቢነት ትሩፋት በመሆኑ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባም ነው፡፡ ምርጫው ህዝባችን ፈተናዎችን ተቋቁሞ በታሪክ የሚዘከር የአይበገሬነት ታሪክ የጻፈበት፣ ለዘላቂ ሰላምና እድገት የሚበጅ የፖለቲካ ባህል አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ያደረገበት፣ በዋናነት የማህበረ-ፖለቲካ ግብረ-ገብ እሴቶች ተቃራኒ የሆኑ ጯሂና እኩይ ድምጸቶችን ማሸነፍ የቻለበት፣ ለሰላም ሲባል ዋጋ የመክፈል ቁርጠኝነት የታየበትና ዋጋ የተከፈለበት እንዲሁም ምርጫውን ለማደናቀፍ በቆሙ ኃይሎች አማካኝነት ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት ክስተት ነበር። ያም ሆኖ ህዝብን ማሸነፍ አይቻልምና ድሉ የሰላም ወዳዱ ህዝብ ሆኗል።
በዚህ መልኩ ህዝቡ ከፍተኛ ጫናዎችን በመቋቋምና ዋጋ በመክፈል ጭምር ምርጫው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መድረክ መሆኑን ሲገልጽ፣ ቀጣይ ለሚመሰረተው መንግስት ከፍ ያሉ የህግና የፖለቲካ ግዴታዎች ተጥለውበታል እንደማለት ነው፡፡ ይህም ሰላም የማስፈን፣ የደህንነት ዋስትና የማረጋገጥ፣ የልማት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን የማረጋገጥ ግዴታን የጠየቀበት መድረክ ሆኖ አልፏል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኃይሎችም ምርጫው ጠቃሚ መልዕክቶችን አስተላልፏል፡፡ አንድም የህዝባችንን የፖለቲካ ተሳትፎ መብትና ነጻነቱን በኃይል የሚገፍ የጎበዝ አለቃዎች አዋጅና የተፈጸመውን ጥቃት እንደሚቃወመው ህዝቡ አቋሙን ያሳወቀበት ነው፡፡ ሁለትም ለሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር ያለውን ፍላጎትና ለዚህም ዋጋ ለመክፈል በቁርጠኝነት እንደተነሳ በድርጊት የተደገፈ መልዕክት ያስተላለፈበት መድረክ ሆኗል፡፡ በዚህም “የአማራ ክልል ለመዋዕለ-ንዋይ ፍልሰት፣ ለፖለቲካዊ ተሳትፎ መቀጨጭ እና ለሰብአዊ ቀውስ ወዘተ የተዳረገው በክልሉ ከተፈጠረው የጸጥታ ቀውስ ጋር ተያይዞ ስለመሆኑና በተለይም ታሪካዊ ጠላቶች ይህንን አጋጣሚ እንደመልካም በመጠቀም የራሳቸውን እኩይ አጀንዳ ለማሳካት በህዝባችን ላይ ሰፊ የማሳከርና የተቀናጀ የሽብር ዘመቻ እየፈጸሙ መሆኑን ህዝባችን ጠንቅቆ የተገነዘበ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ስለሆነም ህዝባችን ባሳለፋቸው በሳል ውሳኔዎች “የአማራ ክልል የቀውስ ፖለቲካ ተምሳሌት እንዲሆን፣ አማራ እንደ ህዝብ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል፣ ከተቋማዊነት ስርዓት እና ከማህበረ-ኢኮኖሚ ልማቶች እንዲነጠል ሁለንተናዊ ርብርብ ሲያደርጉ የነበሩ አካላትን አላማ በማክሸፍ አኩሪም-አስተማሪም ታሪክ ጽፏል ፍላጎቱንም ግልጽ አድርጓል፡፡ ይህ ፈተናዎችን በጽናት የማለፍ ማህበረሰባዊ ስኬት በማህበረ-ኢኮኖሚ ልማት እና በተቋም ግንባታ ስራዎች ለመድገም ስርዓታዊ መደላድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ድሎችም የሞራል መነቃቃትን የሚፈጥር ነው፡፡
ምርጫው ለውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችም ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡ በሌላ በኩል ከምልዐተ ህዝቡ በተጨማሪ ለምርጫው ስኬታማነት በርካቶች አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ በልዩ ልዩ ተልዕኮዎች ሚናቸውን የተወጡ ባለድርሻ አካላት የህዝብን መብትና ነጻነት የማክበር እና ስርዓትን የማንበር ጉዟችን ዋልታና ማገሮች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ የድካም ዋጋቸውን የኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት እንደሚከፍላቸው በመተማመን እንደ አብን ለሁሉም አካላት ድርጅታዊ ምስጋና እናቀርባለን፡፡
1/ በድህረ-ምርጫ ለሚመሰረተው መንግስት የቀረበ ጥሪ:-
ህዝቡ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ባሳለፈው ውሳኔ አዲስ ለሚመሰረተው መንግስት ከወትሮው የተለየ ኃላፊነት እና የማይደገም እድል እንደሰጠ አብን ይገነዘባል፡፡ በመላው ሀገሪቱ ህግና ስርዓት በማስከበር ለዜጎች የደህንነት ዋስትናን የማረጋገጥ፣ በኃይማኖትና በብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን የማስቆም፣ ተንቀሳቅሶ የመስራት ነጻነትን የማስከበር፣ እንዲሁም ሀገራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ ኃላፊነቶች ጊዜ የማይሰጣቸው የድህረ-ምርጫ መንግስት የቤት ስራዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም ለእነዚህ ብሎም ከህዝብና ከሀገር ህልውና ጋር ለሚያያዙ መሰረታዊ ኃላፊነቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በህዝቡ የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ አዲሱ የሚመሰረተው መንግስት የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ከዳር በማድረስ፣ በሰላም ተቋማትን በማጠናከር እና የሰላም ኮሚዩኒኬሽንን ስርዓት ገቢራዊ በማድረግ አኩራፊ ኃይሎችን ወደ ፖለቲካ ምህዳሩ የማስገባት ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡
እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ ያሉ አካላትን ከአቀባበል እስከ መልሶ ማደራጀት ባሉ ሂደቶች ተቋማዊ ስርዓት በመዘርጋት እየፈነጠቀ ያለውን የሰላም ጮራ ማስቀጠል የሚያስችሉ እርምጃዎች አጠናክሮ እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡
ከአማራ ብሄራዊ ክልል አንጻርም ክልሉ በመሰረተ-ልማት ወደ ኋላ እንዲቀር የተደረገ መሆኑ ሳያንስ፣ የተቋረጡ ልማቶችን በማስቀጠል ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና የክልሉን ጸጋ በመለየት በቀሪዋ ኢትዮጵያ እየደረሱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች እየተቀረጹ እንዲተገበሩ እና የህዝባችን የመልሶ ግንባታ፣ እና የአዲስ ልማት ተጠቃሚነቱ በተጨባጭ እንዲረጋገጥ እናሳስባለን፡፡ በተያያዘም ተቆጥረው ያደሩ የህዝባችንን መዋቅራዊ፣ የትርክት፣ የህግና የፖለቲካ ጥያቄዎች በአግባቡ የሚስተናገዱበት ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰናዳና በተግባር እንዲተረጎም እንጠይቃለን፡፡
2/ ለሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች የቀረበ ጥሪ:-
ህዝባችን ለሰላማዊ ትግል እና ለሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳር መጠናከር ስላለው ጽኑ ፍላጎት 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በቂ ማሳያ ነው፡፡ አብን እንደ አንድ ሀገራዊ የፖለቲካ ተዋናይ ያለ ቅድመ ሁኔታ የህዝባችንን ድምጽ የሚያከብርና በህዝቡም ድምጽ የሚገዛ መሆኑን እያረጋገጠ፣ የማንኛውም በህዝብ ስም የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል ቡድናዊ ፍላጎት ከህዝቡ ፍላጎትና ውሳኔ ሊበልጥ እንደማይገባው ለማስታወስ ይወዳል፡፡ በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታጠቁ ቡድኖች ጭምር የህዝቡን ውሳኔ የማክበር ግዴታቸውን እንዲወጡ እና የሽምቅ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንም ወደ ፖለቲካዊ መድረክ በመምጣት በህዝቡ ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲያቀሉለት ጥሪ እናቀርባለን።
3/ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት:-
የወልቃይት እና ራያ ህዝብ ማንነቱን ተገፎ ለዘመናት የህይወት ዋጋ ጭምር እየከፈለ ሲታገል የነበረው ከግፍ አገዛዝ ተላቆ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ራሱን የማስተዳደር መብቱን ለማስከበር እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም በምርጫ ሂደት የስልጣን ባለቤትነት መብቱ እንዲረጋገጥለት እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ ከመደበኛው የምርጫ መርሃ-ግብር ውጭ በመደረጉ የተነሳ የተፈጸመውን የመብት ጥሰት አብን በጽኑ ይቃወማል በቀጣይም በጽኑ የሚታገልበት መድረክ መሆኑን ከወዲሁ አስምሮ ይገልጻል፡፡
በተለይም የራያ ህዝብ ለዘመናት በህወሃት ኃይሎች ሲደርስበት የነበረውን ግፍና ጭቆና ተቋቁሞ፣ ከግፍ አገዛዝ ተላቆ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ለማስከበር አሁንም ድረስ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል፡፡ አብን የህወሃት ኃይሎች በአካባቢው ላይ እያደረሱት ያለውን ሰብአዊ ጥሰት በጽኑ የሚያወግዝ ሲሆን፣ የህዝቡ የነጻነት ጥያቄ በምርጫ ሂደት ብቻ የሚወሰን አይደለም። ስለሆነም አካባቢዎቹ ከማንኛውም የኃይል ወረራ ነጻ መውጣት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። በተለይ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ስልጣኑን እያስቀጠለ ለሚገኘው ብልጽግና መር መንግስት በአጽንዖት ማሳወቅ የምንፈልገው ጉዳይ ቢኖር በህዝብ መስዋዕትነት የተገኘን ድል ለተደጋጋሚ ግዜ አሳልፎ ለህወሐት በመስጠቱ የራያ ህዝብ ድልን ባከበረ ማግስት የበቀል ዶፍ እንዲወርድበት የማድረጉ የፖለቲካ ስሌትና ታሪካዊ ህፀፅ በፍጹም እንዳይደገም፤ ህዝባችንም ነጻ ወጥቶ ለዘመናት የጠየቀውና የህይወት ዋጋ የከፈለበት የነጻነት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አግኝቶ፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲረጋገጥ አፋጣኝ የመንግስት እርምጃ እንዲወሰድ በጽኑ ጥሪ እናቀርባለን!!!
በድህረ-ምርጫ የሚመሰረተው መንግስት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተጠቀሱት አካባቢዎች አፋጣኝ ምርጫ በማከናወን እና ነጻ የህዝብ አስተዳደር እንዲዋቀር በማገዝ ዋጋ ለተከፈለባቸው የመብት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ እንጠይቃለን፡፡ በተያያዘም በአማራ ክልል እንዲሁም በመላው ሀገሪቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች የማሟያ ምርጫ በማከናወን የህዝቡ ወኪሎች በአዲሱ መንግስት ምስረታ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንጠይቃለን፡፡
4/ የተከበራችሁ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት:-
ዳያስፖራው ማህበረሰብ እምቅ የሀገር ሀብት እንደሆነ አብን ይገነዘባል፡፡ በሀገር ቤት የፖለቲካና በማህበረ-ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ሚና እየተወጡ ያሉ በርካታ ዳያስፖራ ወገኖቻችን 7ኛው ሀገራዊ ምርጫም በሰላምና በስኬት እንዲጠናቀቅ አወንታዊ ሚና እንደነበራቸው ስለምንረዳ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ በቀጣይም ሁሉም በውጭው አለም የሚኖር ወገናችን በምርጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳለፈውን ውሳኔ በማክበር፣ በማስከበርና ከዚህም ትምህርት በመውሰድ በአወንታዊ የለውጥ ተግባራት ተዋናይ እንዲሆን፣ ልማቶችንና የሰላም እንቅስቃሴዎችን እንዲደግፍ እንዲሁም ለሀገራዊ መረጋጋት ፋይዳ ከሌላቸው አጀንዳዎች ራሱን እንዲያርቅ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ላገኘው ብልጽግና ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን፤ በሀገራችን ውስጥ የተንሰራፋውን ሰፊ የጸጥታ ችግር ባለማቃለልና የሰላም ጥረቶችን ይበልጥ በማጠናከር፣ የህዝቦችን አንድነት በማጎልበት የተሻለ ሰላምና ፍትሀዊ ልማት እንዲሰፍን፣ የህዝቡ ድምጽ ይህንን የሚጠይቅ መሆኑን እያስታወስን መጭው ግዜ ሀገራችንን ወደ ሁለንተናዊ የመሻል ምዕራፍ የምናሻግርበት እንዲሆን እናሳስባለን።
ሰኔ 14/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






