የትግራይ የፖለቲካ አቅጣጫና የቀጠናው ጂኦፖለቲካ፤ የግብጽ፣ ሱዳንና ሻዕቢያ የ”ጽምዶ” ቃል ኪዳን ይፈጸማል? ኢትዮጵያ አዲስ የደህንነት ፈተና ይገጥማት ይሆን?

Date:

ለአዲስ አበባ የሚወረወሩ ወጥመዶች፡ ድርጅቱ ባለው የዲጂታል ሰራዊት እና ደጋፊ አክቲቪስቶች አማካይነት በጠንካራ ንግግሮች፣ በተወሰኑ አከባቢዎች በሚደረጉ ጥቃቶች እና በራሱ ክልል በሚከናወኑ ወታደራዊ ሰልፎች የማዕከላዊ መንግስቱን ስሜት በመንካት፣ በመተንኮስ፣ ወዘተ የፌደራል ጦር የመጀመሪያውን ስህተት እንዲሰራና ያልተመጣጠነ ወታደራዊ ጥቃት ወይም የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲጥል ማነሳሳት…።

አዲስ ሪፖርተር | OPINION | July 31, 2026 By Ayele Worku በአየለ ወርቁ | ከአዲስ አበባ

የአፍሪካ ቀንድ ዛሬ በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ፣ በአባይ ውሃ፣ በወደብ መዳረሻ እና በክልላዊ የደህንነት ውጥረት የተወሳሰበ ቀጠና ሆኗል። በዚሁ መነሻና አውድ ሲሰላ በትግራይ የሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ግጭት እድሉን አሰፍሰፈው ከሚጠብቁት አካላት ፍላጎት ጋር ተዳምሮ የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ሊሆን እንደማይችል የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። እንደ እነዚህ አካላት ገለጻ፣ በትግራይ ክልል ጉዳይ የተሰባሰቡ አገራትና ቡድኖች እያሳዩት ያለው እንቅስቃሴ የቀጠናውን ሚዛን ሊነካ እንደሚችል የሚናገሩት ለአስተያየታቸው ማስደገፊያ ማስረጃ ይጠቅሳሉ። 

በ2022 የተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን አውዳሚ ጦርነት ለማስቆም ወሳኝ እርምጃ ቢሆንም፣ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ እንዳይውል በመደረጉ፣ የፖለቲካ መተማመን እና የደህንነት መረጋጋት በሚፈለገው ደረጃ እውን ሊሆን አልቻለም። 

በተለያዩ ምንጮችና የቀጣናው ታዛቢዎች ግምገማ መሠረት፣ የህወሓት “ጽንፈኛ” የሚባሉት አመራሮች ከቀደምው ጠላቶቻቸው ጋር ሳይቀር አብረው ከ2022ቱ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጎን ለጎን ሌላ ስትራቴጂካዊ እቅድ የጀመሩት ገና የውሉ ፊርማ ሳይደርቅ ነበር። ከተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን የጀመሩት አዲስ እቅድ ዋና ዓላማ የትግራይ ኃይሎችን ወታደራዊ አቅም በምስጢር በማጠናከር በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋት መፍጠርና በመጨረሻም የትግራይ ክልልን ነፃ ሀገር አድርጎ ወደ ማወጅ (መገንጠል) ቃል በመግባት ነበር። ሰሞኑን የህወሃት አመራሮች “ሁሉንም ዓይነት የህገ መንግስቱ አማራጮች ለመተግበር እንሰራለን” እንዳሉት፤ 

“እስከ መግንጠል እንዳእሳቹሃለን” በሚለው ማማለያ የጀመረው አዲስ ጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ህወሓት ከዚህ ቀደም በጠላትነት ፈርጆት ከኖረውና በቅርቡ ጦርነት ከህዝብ አእምሮ ሊወጣ የማይችል ግፋ ከፈጸመው የኤርትራ መንግስት ብቻ ሳይሆን፣ ሱዳን እና ግብፅ እንዲካተቱበት አድርጓል። ግብጽ የምትመራው እንቅስቃሴ ህወሓትን የመገንጠል ዓላማውን እንዲገፋበት በማድረግ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት ለማዳከም ቀደም ሲል የተያዘውን አቋም ለመተግበር አመቺ ሁኔታ መፍጠር ነውና ገፍተውበታል። 

በቅርቡ የተሰራጨ አንድ የትንታኔ ሰነድ እንደሚለው ከሆነ በትግራይ ውስጥ እንደገና የሚፈጠር ወይም ሊፈጠር የሚችል ማናቸውን ግጭት ወይም አለመግባባት፣ የኢትዮጵያ የወደፊት መረጋጋት በሚፈትን መልኩ የሚሰላ በመሆኑ አሁን  ላይ አካሄዱ ያለበት ደረጃ ስጋት አስነስቷል። ይፋ የሆነው ሰነድ ስጋቱ በቀላሉ ሊታለፍ የማይችል በመሆኑ ሕዝብ “ጉዳዬ” ብሎ እንዲመረመረው ማሳሰብ የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ነው።

የአፍሪካ ቀንድ ዛሬ በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ መልኩን በቀየረበት በአሁኑ ሰዓት በትግራይ እየጎነ ያለው የፖለቲካ መከፋፈል፣ ያልተፈቱ የድንበር ጉዳዮች፣ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር እና የውጭ ኃይሎች በቀጠናው ያላቸው ፍላጎቶች ተመሳሳይ ዓላማ ባይኖራቸውም፣ አንድ ላይ ተሰባስበው መምጣታቸው ስጋት ሊሆን የሚችሉበት እድል እንዳለ መካድ አይቻልም። ይህ ስጋት በተግባር ከተፈጸመ፣  የኢትዮጵያን የደህንነት አቅም፣ የኢኮኖሚ መረጋጋት እና የቀጠናውን አጠቃላይ ሰላም በእጅጉ ሊፈትን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይህንኑ ጉዳይ እንደ ፖለቲካ ድል በመቁጠር አሁን ትግራይን እየመሩ ያሉት የህወሃት አንድ ክፍል በይፋ እያስታወቁ ይገኛሉ። 

የዚህ ስትራቴጂካዊ እቅድ ባለቤቶች በዋናነት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) እና ጌታቸው አሰፋ ሲሆኑ ከሱዳን ጦር ኃይሎች (SAF) መሪ ከጄነራል አልቡርሃን ጋር መክረውበታል። ሰነዱ እንደሚለው የአልቡርሃንን የአስመራ ጉብኝት ተከትሎ በኤርትራ መዲና አስመራ በተደረገ ስብሰባ። እነዚህ አመራሮች ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በፌደራል መንግስቱ ድጋፍ የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያስወግዱ፣ በፓርቲው እና በትግራይ ክልል ምክር ቤት ላይ ያላቸውን ቁጥጥር እንዲያስመልሱ ከስምምነት ተደርሷል።

ከዚሁ ኦን ለጎን ይፋ በሆነው የውስጥ መረጃ መሰረት ሰነዱ እንዳለው በእቅዱ ውስጥ የየአመራሮቹ ዋና ዋና ሚናዎች ተለይተው ተቀምጠዋል።

  • ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፡ የህወሓት ሊቀመንበር እንደመሆናቸው መጠን በክልሉ የፖለቲካ እና የተቋማት ቀጣይነት ማዕከላዊ ሰው ወይም “ሴንተር” እንዲሆኑ፣
  • ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)፡ የፓርቲው አመራርና የሎጅስቲክስ መሪ በመሆን የመቋቋም ስትራቴጂዎችንና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በማመቻቸት እንዲንቀሳቀሱ፤
  • ጌታቸው አሰፋ፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (NISS) ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ በውስጥ ደህንነትና በድንበር ተሻጋሪ የመረጃና የግንኙነት መረቦች ላይ በስውር ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ምድብ ተሰጥቷቸዋል። 

የዚህ አመራር ዋና አላማ በኤርትራ እና በሱዳን ጦር ኃይሎች ወይም “ጽምዶ” በተባለው ኃይል እየተደገፈ፣ ህዝባዊ ብስጭትን እንዲያጋጋመ፣ “የመከበብ” ስሜትን በማስፋፋት በመጀመሪያ የምዕራብ ትግራይ አከባቢዎችን በኃይል ለማስመለስ፣ በመቀጠልም ሰፊ ወታደራዊ ግጭት (Casus Belli) ለመፍጠር መስራት ነው። 

ሰሞኑን በተለያዩ መድረኮች “አታስቡ፣ ስጋት አይገባቹህ” በማለት በተደጋጋሚ እነዚሁ ዋና የህወሃት አመራሮች “ኤርትራ፣ ሱዳንና ፋኖ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወዘተ ከኛ ጋር ናቸው” በማለት መናገራቸው ከላይ ሰነዱ ካነሳቸው ጭብጦች ጋር የሚገጥሙ ናቸው። 

ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ወታደራዊ አሊያንስ (The International Axis)

ይህ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ በቀጣናው የታየውን ድንገተኛ የጂኦፖለቲካዊ ኩነቶች መሠረት ለማድረግ የሞከረ ነው። በዚሁ መነሻ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ  ኢትዮጵያ ያሳየቸውን የባህር በር ፍላጎት ለማጨናገፍ ህወሃት አይነተኛ መሳሪያ ሆኖላቸዋል። ኢሳያስ በትግራይ ጦርነት ወቅት አጋጣሚውን በመጠበቅ ታሪክና ዘመን ይቅር የማይለውን የበቅለ አረር በትግራይ ላይ አውርደዋል። ትግራይ ላይ ሰብአዊ፣ ቁሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ውድመትና ዘረፋ እንዲካሄድ መመሪያ ሰጥተዋል። ጦርነቱን በፕሪቶሪያ ስምምነት ሲቋጭ “ተኮፊልና” በማለት ወዲያውኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተጣሉት ኢሳያስ፣  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የቀይ ባህር መውጫ ፍላጎቶች እና በሁለቱ ሀገራት ድንበር ውጥረቶች ምክንያት ኢትዮጵያን ጠላት አድርገዋል። በመሆኑም ኤርትራ ከህወሓት ጋር ጊዜያዊ ስትራቴጂካዊ ጥምረት በመፍጠር፣ የትግራይ አገር መንግስት ምስረታ ዋና አጋፋሪ በመሆን  የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት ለማዳከም እየሰሩ መሆኑን አዲስ ጉዳይ ባይሆንም ሰነዱ በበርካታ ማስረጃዎች ያትታል።  

የሱዳን መኢ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን  የሱዳን ጦር ኃይሎች መንግስት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ለRSF ፈጣን ደጋፊ ኃይሎች ድጋፍ ይሰጣል ብሎ ይከሳል። በመሆኑም በበቀልና በስትራቴጂካዊ ፍላጎት ምክንያት የሱዳን ጦር በገዳሪፍ ድንበር በኩል ለህወሓት የሎጅስቲክስና የስንቅ መስመር እንዲከፈት በማመቻቸት የገንጣይነት እቅዱን እየደገፈ ይገኛል። ለዚህም ስኬት ህወሃት ቀደም ሲል ወደ ሱዳን ካሰረገው ወታደር በተጨማሪ በኤርትራ በኩል ተጨማሪ ኃይል በመላክ የአልቡርሃን ኃይሎች እንዲያሸንፉ ደም እየገበረ ይገኛል። 

ካይሮ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት ለማዳከም ያለመ የፋይናንስ፣ የስትራቴጂካዊ እና የመሳሪያ ድጋፍ ትሰጣለች። እንደ ሰነዱ ከሆነ ግብፅ ይህንን ሁሉ ድጋፍ የምታደርገው በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች መነሻዎች ነው።

የአባይ ውሃና የህዳሴው ግድብ ጉዳይ፡ የሕዳሴው ግድብ አስመልክቶ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ያለው ቁርጠኛ አቋም ለግብፅ ህልውና ስጋት እንደሆነ ስለምታምን፣ የጽምዶን ህብረት በማጠናከር ኢትዮጵያን በአገር ውስጥ የደህንነት ጉዳይ እንድትወጠር ማድረግ የቆየ አቋሟ ቢሆንም ከቀድሞ በበለጠ ተነክራበታለች። 

የተስፋፋው የጂኦፖለቲካ አሊያንስ (ካይሮ-አስመራ-ሞቃዲሾ)፡ ግብፅ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ጋር ያደረገቻቸው የደህንነት እና የማሪታይም ስምምነቶች ኢትዮጵያን በቀጣናው ለመክበብ ያለሙ ሲሆን፣ የትግራይ ግጭት የዚህ አሊያንስ የሰሜን እና የውስጥ ግንባር ተደርጎ ይወሰዳል።

የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ማደናቀፍ፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ፣ ግብፅ ከኤርትራ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ፍላጎት ለማደናቀፍና ሀገሪቱን የየብስ እሥረኛ አድርጎ ለማስቀረት ካላት የኖረ መርህ በመነሳት ትሰራለች።

ህወሃት የሚያስፈጽመመው የእቅዱ ደረጃዎች እና ሕዝብን የማበሳጨት ስትራቴጂ የነፃነት አዋጅ ማወጅ!

ስውር ታጣቂዎችን ማደራጀትና ማሰልጠን፡ የትግራይ ታጣቂዎችን በክልል ፖሊስ ወይም በአካባቢ የደህንነት ኃይሎች ሽፋን ስር በምስጢር ሰራዊት በማደራጀት ጡንቻን ማፈርጠም። ሰነዱ ባይገልጸውም “የተጠባባቂ ወታደር ችግር አለ፤ መልምሉ” በሚለው መመሪያ መሰረት አፋሳና አስገድዶ ወታደር በማድረግ ከጊዜ ጋር መረባረብ። 

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች፣ ከኦሮሚያ ክልልና ከሌሎች ኃይሎች ጋር ውጊያ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ በሚፈጠረው ትርምስ፣ በግጭትና በሌሎች የውስጥ ችግሮች መንግስት ሲጠመድ፣ ጊዜ ጠብቆ የትግራይን መገንጠል በይፋ ለማድረግ መዘጋጀት።

ኢትዮጵያ እንድትተርመስ ከተደረገ በኋላ፣ በፍጥነት ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ለማግኘት “በተገባው ቃል” መሰረት ከአስመራ፣ ከካርቱም እና ምናልባትም ከካይሮ ፈጣን ዓለም አቀፋዊ እውቅና በማግኘት የአዲሷን ሀገር ህጋዊነት ማረጋገጥና የፌደራል ጦር ጥቃትን በድንበር አካባቢ መከላከል ዋናው የህወሃት እቅድ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል። ሰነዱ ባይገልጸውም ኤርትራ ትግራይ አገር እንድትሆን፣ ወልቃይትን አካታ ወደ ሱዳን መውጪያ በር እንዲኖራት እንደማትፈልግ በይፋ የሚታወቅ በመሆኑ “ለህወሃት የተገባው ቃል ሊተገበር የማይችል፣ ኢትዮጵያን የማተራመሻ ማማለያ ከረሜላ” የሚሉ ወገኖች ህወሃትን አሁን ከሚመሩት ውስን ሰዎች በቀር የትግራይ አብዛኛ አካባቢዎች ይህን ጉዳይ ሊተገብሩት እንደማይችሉ በተደጋጋሚ የሚያስታውቁት ጉዳይ ነው። በአማራ ፋኖ በኩልም መከፋፈል ያስነሳ ቁልፍ አጀንዳ ነው።

የማበሳጨት (Calculated Provocation) ስትራቴጂ

በደብረጽዮን፣ በሞንጆሪኖ እና በጌታቸው አሰፋ የተነደፈው እቅድ ስኬታማ እንዲሆን ህወሓት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ “አስቀድሞ ጥቃት አድራሽ” ሆኖ መታየት የለበትም። ስለዚህ የሚከተሉት ስልቶች ታቅደዋል፡-

ለአዲስ አበባ የሚጣሉ ወጥመዶች፡ ድርጅቱ ባለው የዲጂታል ሰራዊት እና ደጋፊ አክቲቪስቶች አማካይነት በጠንካራ ንግግሮች፣ በተወሰኑ አከባቢዎች በሚደረጉ ጥቃቶች እና በራሱ ክልል በሚከናወኑ ወታደራዊ ሰልፎች የማዕከላዊ መንግስቱን ስሜት በመንካት፣ በመተንኮስ፣ ወዘተ የፌደራል ጦር የመጀመሪያውን ስህተት እንዲሰራና ያልተመጣጠነ ወታደራዊ ጥቃት ወይም የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲጥል ማነሳሳት።

ታክቲካዊ የብቸኝነት/የተጠቂነት ስሜት መፍጠር፡ የፌደራል መንግስቱ ወታደራዊ ምላሽ ሲሰጥ የትግራይን ህዝብ “የህልውና አደጋ ተደቀነብን” በሚል መፈክር ስር ወዲያውኑ ማስተባበር፣ ይህም በፓርቲው ላይ የተነሳበትን የውስጥ ተቃውሞ መቀየር

ለቀጣናው አሊያንስ የጥቃት ሰበብ (Casus Belli) መስጠት፡ ከማዕከላዊ መንግስት ጥቃት እንደ ደረሰበት በማስመሰል የመገንጠል አዋጁን እንደ ህገ-ወጥ ድርጊት ሳይሆን “ህዝብን ከአደገኛ ጥቃት የማዳን የመጨረሻ የህልውና አማራጭ” አድርጎ ማቅረብ። ይህም ኤርትራና ሱዳን “በሰብአዊና በጂኦፖለቲካዊ መብት” ስም ለአዲሷ ሀገር ፈጣን እውቅና እንዲሰጡ መንገድ ይከፍታል።

የመጨረሻ ማጠቃለያ እና ስጋቶች 

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ይህንን ህወሓት፣ ሱዳን እና ኤርትራ የፈጠሩትን የሶስትዮሽ ዝግጅት በይፋ ቢያነሳውም፣ ሰነዱ የዘረዘራቸው የህወሃት ግንባር አመራሮች ደብረጽዮን፣ ሞንጆሪኖ፣ ጌታቸው አሰፋ እንዲሁም ኢሳይያስ አፈወርቂ እና አል ቡርሃን የተጋሩት የጋራ ፍላጎት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል አዲስ የጦርነት ግንባር የመክፈት እድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ አዲስ ግንባር በጎረቤት አማራ ክልል ከሚካሄደው የፋኖ እንቅስቃሴ ጋር ተደራርቦ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሉአላዊነት፣ የውስጥ እና የቀጣናውን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አጣብቂኝ ሊሆን እንደሚችል ሰነዱ ያስረዳል።

ሰነዱን በማጣቀስ ብዙም መከራከሪያ ሳላቀርብ ያጋራሁት ሃሳብ የፌደራል መንግስት ህወሃት እንዳሰበው ወጥመዱ ውስጥ ሳይገባ ምን ዓይነት አካሄድ እንደሚከተል ከወዲሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሩቅ በማሰብ እንዲመረመር ለማመላከት ነው። ከምንም በላይ ሻዕቢያን ጠንቅቆ የሚያውቀው የትግራይ ሕዝብ “ቃል ኪዳኑን” መርምሮ ራሱን ከታሪካዊና መመለሻ ከሌለው ስህተት እንዲታደግ ለማድረግ ለማሳሰብ ነው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ኢትዮጵያና አሜሪካ ወዴት? የቀይ ባህር ጉዞና የባብ ኤልመንደብ ስምምነት አዋጆች

አዲስ ሪፖርተር - “ጉዞ ወደ ባብ ኤልማንደብ” እና “የኢትዮጵያ...

የኢሳያስዋ ኤርትራ [የቀይ ባህር ስጋት] ሆና አስከመቼ? የኃያላኑ ጥያቄ ሆኗል፤ የኢትዮጵያ ባልተመረጠ መንግስት…

የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የቴክኖሎጂ አካላት በኤርትራ በኩል...

በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ግድያና ፍንዳታ ሊፈጽሙ የነበሩ ተያዙ

አዲስ ሪፖርተር ዜና - ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን...