አዲስ ሪፖርተር – ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ኢትዮጵያን አድን” የሚባለው የቀድሞ የኢህአፓ ጡረተኛ አመራሮች የሚመሩት ማህበር ታጣቂዎችን ለማሰባሰብ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሀምሌ 28 ቀን አቶ ገለታው፣ ፕሮፌሰር ባደግ፣ እንዲሁም ኢንጂነር ሰለሞን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ የፋኖ እና የቤኒሻንጉል ተወካዮችን አገናኝተው አወያይተዋል።
“ኢትዮጵያን አድን” የሚባለው የማህበር ይዘት ባለው ስብሰባ ውስጥ የቀድሞ የአሜሪካ ድምጽ አለቃ ንጉሴ አክሊሉ፣ ፕ/ር ባደግ፣ አቶ ክፍሉ ታደሰ፣ ፕ/ር ጌታቸው መታፈሪያ፣ ኢንጂነር ሰለሞን፣ ወዘተ በአባልነት የሚገኙበት ሲሆን ሶስቱ መግቢያው ላይ የተገለጹት ከዚሁ ህብረት የተወከሉ ናቸው።
ይህ ማህበር የፋኖ ሃይማኖታዊ ክንፍ ከሆነው ሞዐ ተዋህዶ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ በአሜሪካ ከፋኖ የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር አብረው እንደሚሰሩ የሚገልጹትን አይቀበልም። አቶ ፋንታሁን ዋቄ “የፋኖ መስራችና ባለቤት እኛ ነን። ከእኛ ትዕዛዝ ውጪ ለመሆን የሚያስቡ ይሞክሩትና እናየዋለን” ሲሉ ለፋኖ የሚዲያ ክንፍ አካል ለሆነችው መዐዛ መሐመድ መናገራቸው አይዘነጋም። አቶ ፋንታሁን ይህን የመለሱትና ፋኖ ሃይማኖታዊ ክንፍ እንዳለው በንዴት ይፋ ያደረጉት “በፊት አግዘናችኋል፣ አሁን ፋኖ የራሱ አደረጃጀት አለው፤ ለምን እናንተ ዘወር አትሉም?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ነው።
ኢህአፓ ከስሞ፣ ከነመኖሩም በተረሳበት ወቅት ዳግም ድምጹ የተሰማው እነዚሁ ጡረተኛ የቀድሞ የኢህአፓ አመራሮች ከሞዐ ተዋህዶ አደረጃጀት ጋር በፈጠሩት ህብረት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት መረጃው ማፈትለኩ ይታወሳል።
“እግዚአብሔር የለም” የሚለው ኢህአፓ፣ ሞዐ ተዋህዶን በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ በማግኘት በድንገት ለአዲስ አበባው ኢህአፓ “የብሉይ ኪዳን ሊቅ” መሪ ሲሰይም በርካቶችን አነጋግሮና አስገርሞ ነበር። አንዳንዶች “ኢህአፓ ‘እግዚአብሔር የለም’ ከሚል አስተሳሰብ ወደ ‘ብሉይ ኪዳን ሊቅ’ መሪነት” በማለት አስተያየት ሁሉ ጽፈው ነበር።
“መጋቢ ብሉይ” የሚለው ማዕረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜ ላይ ከፍተኛ እውቀትና የማስተማር ብቃት ላላቸው ምሁራን የሚሰጥ ልዩ ማዕረግ ነው። የዛሬው የኢህአፓ ፕሬዚዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ተስፋ በዚህ ዘርፍ እጅግ አንቱ የተባሉና ለዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስተምሩ የቆዩ በመሆናቸው ነው ይህን ስም ያገኙት። እናም እሳቸው ኢህአፓን መምራት ከጀመሩ በኋላ ፓርቲው የ“ያ ትውልድ” ካባውን አውልቆ በዚህ ደረጃ ድፍረት ተላብሶ ህዝብ ፊት እንዴት ሊቆም ቻለ? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው። ከዚህም በላይ የክርስትና እምነት ምንጭና ቁልፍ የሆነውን አምላክ የካደ ድርጅት፣ አንድ የብሉይ ኪዳን መምህር እንዲመሩት እንዴት ወሰነ? የሚለው በርካቶችን ያነጋገረና ዛሬም ድረስ መነጋገሪያ የሆነ አጀንዳ ነው።
“የፋኖ መስራች ነኝ፣ ከእኛ ትዕዛዝ ውጪ እንሆናለን ካሉ ይሞክሩት” የሚሉት አቶ ፋንታሁን ዋቄ ከመዐዛ መሐመድ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ፋኖን ያደራጁት ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ፋኖ እየተመራ ያለው በሞዐ ተዋህዶ አስተሳሰብና እሴት እንደሆነ በይፋ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። አቶ ፋንታሁን፣ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ስለ ሞዐ አደረጃጀትና ሃሳብ ሰምተው የሞዐ አደራጆችን ሲያነጋግሯቸው ሃሳቡን እርሳቸውም አምነው የተቀበሉት ብቻ ሳይሆን “የኔም ሃሳብ ነው፤ በሉ እኔና እናንተ አልተነጋገርንም” ብለው ሁለቱም በየፊናቸው እንዲሠሩ ተስማምተው እንደነበር መግለጻቸውን በተያያዘው የቪዲዮ ማስረጃ የሚያቀርቡት፣ ከላይ በስም የተዘረዘሩት አንጋፋ የኢህአፓ የዛ ዘመን መሪዎች ይህንን አደረጃጀት ተቀላቅለዋል። በዚሁ መነሻ “አብዮታዊ” የሚለውን አምላክን የካደ ካባ አውልቀው የብሉይ ኪዳን ሊቅ መሪ እንዲሆን አምነው ተቀብለዋል።
በሃይማኖታዊ ክንፍ የተከለለው፣ የሞዐ ተዋህዶን ህቡዕ አደረጃጀት ተጠግቶና በዚያው መዋቅር ተከልሎ አዲስ አበባ ላይ “የቅንጅት ወራሽ ነኝ” እስከማለት የደረሰው ኢህአፓ፣ ውሎ አድሮ የትጥቅ ትግል እናደርጋለን የሚሉትን ሰብሳቢና ጠርናፊ ሆኗል።
የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ እንዳለው፣ የተጠቀሱት የኢህአፓ አዛውንት አመራሮች በሱዳን የሚገኙትን የቤኒሻንጉል ታጣቂዎች መሪ አተይብ አል አሚን፣ የኦኤልኤ (OLA) ቃል አቀባይ አቶ ጂሬኛን እና የአፋብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስረስ ማረን ነበር ያገናኙት። ከአፋር ክልል በደሞዝ ተጣልተው ወደ አስመራ የኮበለሉት አቶ አቢራሂም “በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ሊከሰት ስለሚችል አይመቸኝም” በማለታቸው ባይሳተፉም ተጋባዥ ነበሩ።
ህወሓት (ትህነግ) ፈቃደኛ ባለመሆኑ ያልተሳተፈበት ይህ በኢህአፓ ጡረተኞች ጠርናፊነት የተደረገ ውይይት፣ ከቤኒሻንጉል ለቀረበለት የሎጂስቲክስ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ አልቻለም። በትውውቅ ጀምሮ ከሁለት ሳምንት በኋላ ዳግም ለመገናኘት ቀጠሮ የያዘው የሃያ ደቂቃ ስብሰባ ዓላማውም ሆነ ሃሳቡ ግልጽ አልነበረም።
የንግግሩ መረጃ ያላቸው የ”ኢትዮጵያን አድን” ምንጭ እንደጠቀሱት፣ አሁን ላይ “ነጻ አውጪ ነን” የሚሉትን መቀራመት ስራ በመሆኑ የተደረገ እንጂ ከዚያ የዘለለ ውጤት የሚያመጣ አይደለም።
በሱዳን 300 የማይሞሉ ታጣቂዎችን ይዞ የመሸገውና በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኝ የገለጸው የቤኒሻንጉል ታጣቂዎች መሪ፣ ስለ ሸረሪና ኦፕሬሽን በሰማው ዜና መደሰቱን በውይይቱ ወቅት አመልክቷል። “ህወሓት (ትህነግ) እና ሻዕቢያ የመንግስትን ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ደምስሰዋል፤ በቅርቡ እነሱ ወዳሉበት የሱዳን ድንበር ያመራሉ” የሚል መረጃ በጉጉት እየጠበቀ እንደሆነ ሲናገር “እሱ ሌላ አደረጃጀት ነው። የእኛ ኃይል አይደለም” በማለት ሰብሳቢዎቹ መልስ ሰጥተዋል።
አቶ አበይ ግደይ የሚባሉት የህወሓት (ትህነግ) ወኪል በጋራ መድረክ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው “እኛ ብዙ ስራ አለብን፤ እዚያ ውስጥ አንሳተፍም” በማለት ማስታወቃቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የፋኖ በዚህ ስብሰባ ላይ በአስረስ ማረ መወከል ቅሬታ አስነስቷል።
የህወሓት (ትህነግ) ደጋፊ ሚዲያዎች በአስረስ ማረ ላይ ሰሞኑን “ለምን ለብልጽግና ቅርብ በሆነ ሚዲያ ቃለ ምልልስ አደረግክ?” በማለት ያቀረቡት ተቃውሞ ዋና መነሻም ይህ እንደሆነ የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ ዘግቧል።
ኢህአፓ በምርጫ በመሳተፉ ከጡረተኞቹ የውጭ አገር አመራር አባላት ጋር ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በውይይትና በይቅርታ በቅርቡ መፍታታቸውን ገልጸን መዘገባችን አይዘነጋም። በወቅቱ ጡረተኞቹ አመራሮች ከፍተኛ በጀት ለአገር ውስጥ እንቅስቃሴ ማፍሰሳቸውን በመግለጽ፣ በጀቱ የፈሰሰው በምርጫ ለመሳተፍ እንዳልነበር አመልክተው ነበር።
አሁን አሁን ኢህአፓ ላይ የሚነሳው ጥያቄ “በዚህ ደረጃ በጀትና አቅም ከየት አገኙ?” የሚለው እንደሆነ የሚናገረው የዋሽንግቶን ተባባሪያችን፣ የጡረተኞቹ ክንፍ ከውጭ አገራት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል የሚል ጥቆማ እንዳለ አመልክቷል። ይሁን እንጂ እነማን፣ ከየትኛው አገራት ጋር ይገናኛሉ የሚለውን በመረጃ አላጠናከረም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






