“እስከመገንጠል” የሚለው እና ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና ከጅምሩ የተቃወመው የህገመንግስት ክፍል እንዲሰርዝ ከስምምነት መደረሱ ይፋ ሆነ። ይህ ሆነ ተብሎ ኢትዮጵያን ለመፍረካከስ በአገሪቱ ህገመንግስት ውስጥ የተካተተውና ከህጻን እስከ አዋቂ የሚጠየፈው “አንቀጽ 39” በአገራዊ ምክክሩ ተወያዮች እንዲሰረዝ ከስምምነት መደረሱ በህዝብ ዘንዳ ልዩ ደስታ የሚፈጥር እንደሆነ ተመልክቷል። በዚሁ መሰረት “እስከመገንጠል” የሚለው ሃረግ ለወደፊቱ አይኖርም።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምክክር በተቋቋመበት “እፈርሳለሁ አለ” በማለት ዘመቻ ከጀመሩበት የከተማ ውስጥ “ተገዳዳይ ሚዲያዎች” ጀመሮ ውይይቱን ማድረግ በጀመረበት ዕለት በደቦ የተሳሳተ መረጃ በማሳረጨት ህዝብ እንዲሳዳት ሲያደርጉ ለነበሩ ሁሉ ሃዘን የሆናል የተባሉ ጉዳዮች ስምምነት እየተደረሰባቸው መሆኑ ተመልክቷል።
አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ – ማንኛውም ብሔረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ «እስከ መገንጠል» እና «ያለገደብ» የሚሉ ድንጋጌዎች እንዲሰረዙ በብሔራዊ ምክክሩ የጋራ አቋም መያዙ ተገልጿል። የአንቀጽ 39 ድንጋጌዎች ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጋር በጥብቅ የተያያዙ እና ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ የፖለቲካ ክርክር ሲያስነሱ የቆዩ ጉዳዮች ናቸው። በተለይም «ያለገደብ እስከ መገንጠል» የሚለው የሕገ መንግስት ድንጋጌ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ክርክር ውስጥ ለብዙ ዓመታት ተቃውሞና ውይይት ሲያስነሳ ቆይቷል። ይህንን የተቃወሙ “ጸረ ህዝብና አህዳዊ” በሚል በአደባባይ እንዲፈረጁ መደረጋቸውም አይዘነጋም።
አሁን በብሔራዊ ምክክሩ የቀረበው አቋም ግን የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ «እስከ መገንጠል» እና «ያለገደብ» የሚሉት ድንጋጌዎች ከሕገ መንግስቱ እንዲሰረዙ የሚል ነው። ይህ አቋም በ«የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ» አጀንዳ ሥር ከተደረሱ የጋራ ስምምነቶች አንዱ ሲሆን፣ በአጀንዳው ላይ ከቀረቡት 53 ሐሳቦች መካከል 50ዎቹ ላይ ስምምነት መደረሱ ተገልጿል። ሆኖም የመንግስት አወቃቀር ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን? የሚለውን ጨምሮ በሦስት ዋና ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች በመኖራቸው ስምምነት ሳይደረስባቸው ለቀጣይ ውሳኔ ተላልፈዋል።
ለአስማሚ ኮሚቴ እና ለድምፅ ውሳኔ የሚሻገሩት ጉዳዮች
1. የመንግስት አደረጃጀት
የመንግስት አወቃቀር ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን? የሚለው ጉዳይ በተመካካሪዎች ምክረ ሐሳብ መሠረት ሁለት አማራጮችን ይዟል።
በአንድ በኩል፣ «ፓርላሜንታዊ ሆኖ ፕሬዚዳንቱ ከፓርላማ ይመረጥና አሁን ያለውን የፕሬዚዳንትና የጠቅላይ ሚኒስትር ተግባር አንድ ላይ ይዞ ይሠራል። የጠቅላይ ሚኒስትሩም የፕሬዚዳንቱም ሥራ በአንድ ላይ ሆኖ ለሀገር መሪው/ፕሬዚዳንቱ ይሰጠዋል። ሀገር መሪው ከፓርላማ ይመረጣል» የሚል ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።
በሌላ በኩል፣ «ፕሬዚዳንቱ ተወዳድሮ ቀጥታ ከሕዝብ ይመረጥ። ያሸነፈው ሀገሪቱን ይምራ» የሚል መከራከሪያ ቀርቧል።
2. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና ጉዳይ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔረሰቦች መወከያ መሆኑን፣ አሁን ባለው አሠራር ከእያንዳንዱ ብሔረሰብ አንድ ተወካይ እንደሚሰጥ፣ ለቀሪው ደግሞ በየአንድ ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት አንድ ተወካይ እየተጨመረ እንደሚሰጥ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። ይህም «በሕዝብ ቁጥር ይሆናል ማለት ነው» ሲሉ አስረድተዋል።
«ሁሉም ማንነቶች በአንድ ይወከሉና ባላቸው የሕዝብ ቁጥር ደግሞ በአንድ፣ አንድ ሚሊዮን አንድ፣ አንድ እየተጨመረ ይኬዳል» ሲሉ አክለው፣ በአንድ በኩል ይህ አሠራር «ይቀጥል» የሚል አማራጭ ሐሳብ ከተመካካሪዎች መቅረቡን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ «ሁሉም ብሔር ማንነቱ እኩል ነው፤ ትንሽ የሚባል ማንነት የለም። ስለዚህ ሁሉም ብሔረሰቦች እኩል ቁጥር፣ እኩል ተወካይ ይኑራቸው» የሚል መከራከሪያ ሐሳብ መቅረቡን ገልጸዋል።
3. ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔረሰብ ተወካዮች አመራረጥ
ይህም ሌላው አከራካሪነቱ የቀጠለ ጉዳይ ነው። ሕገ መንግስቱ «የብሔረሰቦችን ተወካዮች የክልል ምክር ቤቶች ይልካሉ፤ ወይም ምርጫ ይደረጋል» የሚል ሲሆን፣ «ነገር ግን ተግባራዊ እየሆነ ያለው ክልሎች እየላኩ ያሉት ነው፤ እስካሁን ባለው አሠራር» ያሉት አቶ ሰለሞን፣ በአንድ በኩል ይህ አሠራር እንዲቀጥል የሚል ሐሳብ መቅረቡን ገልጸዋል።
በአንፃሩ ደግሞ፣ «እንደዚህ ሳይሆን ራሱ የብሔረሰብ/የማንነት ውክልና ስለሆነ ብሔረሰቡ ራሱ ምርጫ ያድርግ» በሚል መከራከሪያ መቅረቡን አቶ ሰለሞን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች የቀረቡት ሁለት ሁለት የተለያዩ ምክረ ሐሳቦች በቀጣይ በአስማሚ ጉባዔና በሽማግሌዎች ታይተው ወደ ስምምነት ለማምጣት እንደሚሠራ፣ ካልሆነ ግን ወደ ድምፅ ብልጫ የሚያልፉ ጉዳዮች ሆነው መያዛቸው ታውቋል።
በኮሚሽኑ መመሪያ መሠረት፣ 75 በመቶ ድምፅ ያገኘ ሐሳብ ይጸድቃል፤ ከዚህ በታች ድምፅ ያገኘ ሐሳብ እንደገና እንዲታይ ተደርጎ፣ 70 በመቶ ድምፅ ካገኘ ይያዛል።
ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች
በ«መንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ» አጀንዳ ሥር ወደ 53 የሚሆኑ ሐሳቦች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ «50ዎቹ ላይ ተስማምተናል። አንድ ሁለት ያልተስማሙ ቢኖሩ እንኳ ምክረ ሐሳብ ስለሆነ ብዙኃኑ ምን አለ? የሚለው ነው የሚወሰደው» ብለዋል።
በዚህ መሠረት፣ ለምሳሌ፣ «ከአሃዳዊና ኮንፌዴራላዊ ይልቅ ፌዴራሊዝሙ ይቀጥል» በሚል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
በተያያዘ፣ የብሔር ወይስ የጂኦግራፊ ፌዴራሊዝም መቀጠል አለበት? የሚል አማራጭ መቀመጡን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ከመኖራቸው አንፃር በጂኦግራፊ ብናዋህዳቸው አዳጋች ስለሚሆን፣ «ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም» ወይም «ሁሉን አቃፊ፣ አሳታፊ» የሆነ ፌዴራሊዝም ይሁን በሚል የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
የክልልና የፌዴራል መንግስት አወቃቀር
የፌዴራል መንግስት በፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚዋቀሩት ክልሎች በመሆናቸው፣ የፌዴራል መንግስት በሕገ መንግስቱ በዝርዝር ተገልጸው የሚሰጡት ሥልጣኖች ይኖሩታል፤ ከተሰጡት ሥልጣኖች ውጭ የሚሆኑትም ለክልሎች ተዘርዝረው ይሰጣሉ ተብሏል።
እንዲሁም፣ ለሁለቱም የመንግስት ደረጃዎች ሥልጣኖች በዝርዝር ተሰጥተው ሳይዘረዘሩና በሕገ መንግስቱ ያልተጠቀሱ፣ በቀጣይ ቴክኖሎጂ የሚወልዳቸው አዳዲስ ጉዳዮች ቢመጡ፣ ሥልጣኑ ለማን ይሰጥ? የሚለው ጉዳይ «ለክልሎች እንዲሰጥ» በሚል የስምምነት ሐሳብ ላይ መደረሱን አቶ ሰለሞን ነግረዋል።
የአንቀጽ 39 ጉዳይ
ማንኛውም ብሔረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ «እስከ መገንጠል» እና «ያለገደብ» የሚሉት ድንጋጌዎች እንዲሰረዙ የጋራ አቋም መያዙ ተገልጿል።
የሕገ መንግስት ትርጓሜ ጉዳይ
ሕገ መንግስት የሚተረጎመው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሆን፣ በምክክሩ በተሰጠ ምክረ ሐሳብ «በፍርድ ቤት እንዲተረጎም የራሱን የቻለ ሕገ መንግስት ተርጓሚ ፍርድ ቤት ይቋቋም» የሚል ሐሳብ ቀርቧል።
«ሕገ መንግስት የሚተረጉመው ፍርድ ቤት ጉዳይም የመጨረሻ ይሁን፣ ይግባኝ አይኑረው» እና «ሕገ መንግስት ተርጓሚው ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚታዩ ጉዳዮች ይኑሩ» የሚሉት አማራጮች ግን ተመካካሪዎችን አከራክረዋል። ይግባኝ ይኑረው የተባለው፣ ለምሳሌ፣ «ወንድ ለወንድ ይጋባ» የሚል፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት የሚነካ ወይም «ቤተሰብን ከቤተሰብ የሚያጋጭ» ውሳኔዎች ቢሰጡ ከሚለው አኳያ ነው። በመጨረሻም፣ «በሦስቱ ሐሳቦች ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንዲያርመው» በሚል ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ሰለሞን ነግረዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






