አዲስ ሪፖርተር — ከሸረሪና ኦፕሬሽን በኋላ አነጋጋሪ የሆነው የደፈጣ ጥቃት የተወሰደው ሰኞ፣ ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2:30 ገደማ ነበር። በማንነትና በድንበር ጉዳይ የአማራና የትግራይ ክልሎችን ላለፉት አርባ ዓመታት በሚያወዛግበው በዚህ አካባቢ የተፈጸመው ጥቃት፣ የዶክተር ደብረጽዮን ታማኝ ኃይል እንደሆነ የሚነገርለትን “አርሚ 26” የሚባለውን ታጣቂ ዒላማ ያደረገ ነበር። ይህንን ሃቅ አቶ አማኑኤል በይፋ ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። እናም በጥቃቱና ዒላማ ላይ ክርከር የለም። በትምህርት ቤትና በአቅራቢያው በሚገኝ የችግኝ ጣቢያ በተከዘነ መሳሪያ፣ ለጦርነት ዝግጅት የተከማቸው ሎጅስቲክ ወድሟል። የሸረሪና እና የመረዋ ኦፕሬሽን የተካሄዱት ህወሃት ሙሉ ጦርነት ለማስጀመር ህዝብ ካወያየ በኋላ ነው።
ጥቃቱ ከተካሄደ በኋላ አዲስ ሪፖርተር በማህበራዊ ገጽ ላይ ዜናውን ከማሰራጨት ባለፈ ጉዳዩን ከተለያዩ አካላት እና የመገናኛ ዘዴዎች በማጣራት “የራያ ግንባር ጨዋታ” በማለት ከሸረሪና ቀጥሎ ህወሃት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ አስከትሏል ስለተባለው የ”መረዋ” ኦፕሬሽን የሚከተለውን ሪፖርት አዘጋጅታለች።
ኦፕሬሽን መረዋ ለምን? ህወሃት ምን አቅዶ ነበር?
በኦፕሬሽኑ ደረሰ የተባለውን የጉዳት መጠን ከመዘርዘራችን በፊት፣ የኦፕሬሽኑ አስፈላጊነት በሁለቱም ወገኖች እንዴት እንደሚታይ ማመላከቱ አግባብ ይሆናል።
ህወሃት በራያ አቅጣጫ በሚታወቁ ሶስት ግንባሮች ላይ አለኝ የሚለውን ኃይል አሰልፏል። ግንባሮቹ በጥቁር አስፓልት ቆቦ፣ በቢሶ በር አፋር እና በወልደያ አቅጣጫ ሲሆኑ፤ «በመረዋ በኩል ምን አስቦ ለመንቀሳቀስ አሰበ?» የሚለው ጥያቄ የኦፕሬሽኑን ግዝፈት ያሳያል።
በራያ ግንባር በሁሉም አቅጣጫ “ማስረግ” የሚለውን ስልት ነደፉ። በዚሁ መሰረት ትጥቅ፣ ስንቅና ኃይል በስፍራው ባለው መረዋ ትምህርት ቤት አከማቹ።
እማኞች እንዳሉት ከሆነ ስንቅ፣ ትጥቅና መሳሪያ ሲጋጋዝ የነበረው በግመል፣ በአህያና በሰው ኃይል ነበር። “ሕዝባዊ አመፅ እናነሳሳለን” በሚሉት የአሜሪካ የጋራ መድረክ ስብሰባ ላይ አቶ አባይ ግደይ የሚባሉት የህወሃት ወኪል ከሁለት ሳምንት በፊት፦ “የጥቃት ቦታዎች ተመርጠው መሳሪያና ስንቅ በጋማ ከብት እየተጓጓዘ ነው። ይህ የሆነው ከድሮን ጥቃት ለማምለጥ ነው” በማለት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በተመረጡ አቅጣጫዎች ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ መረጃ ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመረዋን ኦፕሬሽን፣ የህወሃት ታጣቂዎች ከላይ የተገለጹትን መሳሪያዎች ማጋጋዝ ከጀመሩበት ቀን ጀምሮ ይከታተለው ነበር። በራያ አቅጣጫ አሁን ላይ “ጠላት” እየተባለ የሚገለጸውን የህወሃት ኃይል የየዕለት እንቅስቃሴ በሚከታተሉ መዋቅሮች መረጃ ሲሰበሰብ እንደነበር የሚናገሩት የራያ ዘብ አካላት፤ የሀገር መከላከያ ድምጹን አጥፍቶ ከአየርና ከምድር መረጃውን ሲያደራጅ ቆይቶ ሰኞ፣ ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2:30 ገደማ አራት ጥቃቶችን ሰነዘረ።
ህወሃት የፊት ለፊት ግንባሮችን እንዳሉ በመተው በመረዋ በኩል ኃይሉን ለማስረግ ያቀደው ወልደያን በቆረጣ ለመቆጣጠር ነበር። በመረዋ አቅጣጫ አሰልፎት የነበረው ሙሉ አንድ ኮር ሲሆን፣ ብዛታቸውም እስከ 2,000 ይገመታል።
አዲስ አበባ ያሉና ስለ ህወሃት ዕቅድ በቂ መረጃ ያላቸው አካላት እንዳሉት ከሆነ፤ በመረዋ በኩል ወደ ግደን፣ ጎብዬ፣ ሮቢትና ቆቦ በማስረግ ከላይ በተዘረዘሩት ግንባሮች ያለውን የሀገር መከላከያ ኃይል የሚበታትን ውጊያ በየኪሱ ለመክፈት አቅደው ነበር። እንዲሁም በየስርቻው ያለውን ተባባሪያቸውን የፋኖ ኃይል በማሳተፍ፣ የኪስ ቦታ ውጊያዎችን በትንንሽ ቀበሌዎች በማስፋትና የዋናውን መስመር ውጊያ በመክፈት ወልደያን መቆጣጠር ዕቅዳቸው ነበር።
ይህ ቢሳካ ኖሮ ዕቅዱ
ከኤርትራ ድጋፍ የተደራጀውና አነስተኛ ቁጥር ያለው የአፋር ተዋጊ ወደ አፋር እንዲዘልቅ ማድረግ፤ በአፋር ግንባር ያለው ኃይል በጨርጨር አቅጣጫ በማጥቃት ወደ ኢትዮ-ጂቡቲ መስመር እንዲያመራ ማድረግ፤ ወልደያን የሚቆጣጠረው ኃይል ጉልበቱን አሰባስቦ ወደ ቀጣዮቹ ከተሞች እንዲያመራ ማድረግ ነበር።
የሸረሪና ግንባር ላይ የተፈጸመው ኦፕሬሽን ልዩ የሆነበት ምክንያትና የመረዋው ኦፕሬሽን ተመሳሳይነትን የሚያስረዱ ወገኖች እንደሚሉት፣ ሸረሪና የሶስት ዋና ኃይሎች መገናኛ ትሪያንግል ነበረች። ይህን ትሪያንግል የሀገር መከላከያ በተጠናና ቅጽበታዊ ምት ባያመክነው ኖሮ፣ ከሸረሪና የሚነሳው ኃይል ሁመራን ሲቆጣጠር ሻዕቢያ፣ ሱዳንና ህወሃት የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ወደ ቤኒሻንጉል በማምራት ኢትዮጵያን ከምዕራብ አቅጣጫ በስፋት ለመውጋት ያቀደ ነበር። የተማረከውና የተያዘው እጅግ ከፍተኛ ክምችት ያለው መሳሪያ፣ እንደ ፍልስጤም ተዋጊዎች ተፈልፍሎ የተሰራው የኮንክሪት ምሽግና መጋዘን የዝግጅቱን መጠን የሚያሳይ ነው (የሞቱትንና የቆሰሉትን ሳያካትት)።
በራያ አቅጣጫም በተመሳሳይ በመረዋ በኩል ኃይል ወደ ላስታ፣ ራያ፣ ቆቦ፣ ግደን፣ ጎብዬ፣ ሮቢት ወዘተ. ለማስረግ ዝግጅቱን ያጠናቀቀው “አርሚ 26” ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ በድልብ ኩል መስክ ወልደያን ለመቁረጥ አስቦ እንቅስቃሴ ለመጀመር ትንፋሽ እየሰበሰበ ባለበት ቅጽበት፣ ልክ በሸረሪና እንደሆነው ሁሉ ቅጽበታዊ እርምጃ ተወስዷል። እናም እንደ ዜና ምንጮቹ ገለጻ የከሸፈው ይህ ትልቅ ዕቅድ ነው።
ከአላማጣ ወደ ደቡብ አስፓልቱን ይዞ “አርሚ 24”፣ ወደ አፋር ድንበር ራያ ጨርጨርን ይዞ “አርሚ 43”፣ ወደ አማራ ክልል ከአላማጣ ወደ ምዕራብ “አርሚ 31” እና “26” የተሰለፈውን ሰራዊት እንዲያግዝና “ግብአት” የተባለው የመረዋ አቅጣጫ “የማስረግ” እንቅስቃሴ ከዛታ እስከ አላማጣ ወይም መረዋ የተዘረጋ ነበር። ያዘጋጀው ዕቅድ እንደከሸፈ ያወጉት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖች፦ “የዕቅዱ መክሸፍ ብቻ ሳይሆን የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። እርምጃው ስድስቱን ወረዳ ነጻ ለማውጣት ለተቋቋሙት የራያ እና ሀጉምብሩዳ ዘብ ከፍተኛ መነሳሳት ሆኗል” ብለዋል።
ስለደረሰው ጥቃት ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
ህወሃት በመረዋ ትምህርት ቤት እና ከትምህርት ቤቱ ጥቂት ራቅ ብሎ በሚገኝ “ቸግኝ ጣቢያ (ዘሎንጎ)” በሚባል ቦታ መሳሪያና ኃይል አከማችቶ ነበር። መነሻቸው በትክክል ያልታወቀ (የህወሃት ሰዎች ከደብረ ብርሃንና ደብረዘይት ይላሉ) ድሮኖች የሰፈረውን ኃይልና የተከማቸውን መሳሪያ ከጥቅም ውጭ አድርገዋል። እማኞች እና ለኦፕሬሽኑ ቅርብ የሆኑ አካላት እንዳሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተዋጊዎች ቆስለዋል፤ የሸሹም አሉ።
የሕወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል አሰፋን ጠቅሶ AFP እና ሌሎች እንደዘገቡት፣ ጥቃቱ በቦታው የነበሩ የትግራይ ኃይሎችን (በተለይም “አርሚ 26” ተብሎ የሚጠራውን ክፍል) ዒላማ ያደረገ ነበር። በተጨማሪም የመረዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመቷል። አክሎም የትግራይ ባለሥልጣናትን እና የአላማጣ ሆስፒታል የሕክምና ምንጮችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ በጥቃቱ ቢያንስ 4 የትግራይ ኃይል አባላት የቆሰሉ ሲሆን ሁለቱ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።
ህወሓት ለዜና ወኪሉ በላከው መግለጫ ጥቃቱ በትግራይ ኃይሎች እና በነዋሪዎች ላይ የሰው ሕይወት እና የአካል ጉዳት ማድረሱን አልሸሸገም። መግለጫው ክስ ከማቅረብ በዘለለ ለምን መከላከል እንዳልተቻለና የጉዳቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ያለው ነገር የለም። ቢቢሲ ትግርኛ በበኩሉ የህወሃት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ በተፈጸሙት ሶስት የድሮን ጥቃቶች 3 የትግራይ ኃይል አባላት መገደላቸውን እና ሰባት መቆሰላቸውን ዘግቧል።
አዲስ ሪፖርተር ባሰባሰበችው መረጃ ጥቃቱ የተሰነዘረው በሁለት ቦታዎች በተመሳሳይ ወቅት በአራት የድሮን ጥቃቶች ሲሆን፣ ያረፈውም “አርሚ 26” በሰፈረበት ትምህርት ቤትና መሳሪያ በተከማቸበት ችግኝ ጣቢያ ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ነው። ጥቃቱ ዒላማውን የመታና ለጊዜው በቁጥር ሊገልጹት የማይችሉት ታጣቂ ኃይል ሙትና ቁስለኛ እንደሆነ አመልክተዋል።
አላማጣ እና ኮረም ሆስፒታሎች ለሌሎች ታካሚዎች ዝግ ሆነው ቁስለኛ ሲያስተናግዱ እንደነበር ያመለከቱ ሲሆን፣ ወደ አይደር ሆስፒታል ሪፈር የተባሉትን አምቡላንሶች ሲያመላልሱ ማምሸታቸውን እንዳረጋገጡ የገለጹት ምስክሮች፣ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችን አሰራጭተዋል። የመቀሌ ነዋሪ የሆኑ ባልደረቦቻቸውን የጠየቁ አካላት እንዳሉት፣ አምቡላንሶች እና የጭነት መኪናዎች ቁስለኛ እየጫኑ ወደ አይደር ሆስፒታል ሲገቡ መታዘባቸውን ገልጸውላቸዋል። የጉዳቱን መጠን ህወሃት ይህ እስከታተመ ድረስ ይፋ አላደረገም። ከአገር መከላከያም ሆነ ከመንግስት ወገን ኦፕሬሽኑን አስመልክቶ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
በቲክቶክ ገጹ የሚታወቀው የትግራይ ተወላጅ በበኩሉ፦ “’የተገደሉት 10 ብቻ ናቸው …15 ብቻ ናቸው’ እያላችሁ ሕዝብ የምታደናግሩ ሰዎች እረፉ። እውነቱን ልንገራችሁ? 369 ታጋዮች ናቸው ትናንት የተሰዉት። ትናንት 2 አይሱዙ አስከሬን ነው ወደ ድሮው የቀብር ቦታቸው ወደ መቻሬ መውጫ አካባቢ ተጓጉዞ የተቀበረው። ዛሬም በቀን 5 ወደዛው ወደ መቻሬ መውጫ አንድ አይሱዙ ሙሉ አስከሬን ወስደዋል። አሁን እየቀበሯቸው ነው” በማለት ሲናገር ተደምጧል። ይህ መረጃ በየትኛውም ሌላ የመረጃ ምንጭ አልተረጋገጠም። ሁሉም የሚስማሙበት አንድ ሀቅ ግን የጉዳቱ መጠን የሚያሳዝን፣ ከባድና ዒላማውን የጠበቀ መሆኑን ነው።
የራያና ሀጉምብርዳ ዘብ
የራያና ሀጉምብርዳ ዘብ አላማጣ ከተማን፣ ራያ አላማጣ ወረዳን፣ ኮረም ከተማን፣ ወፍላ ወረዳን፣ ዛታ ወረዳንና ራያ ባላን ነጻ ለማውጣት በአካባቢው ተወላጆች የተደራጀ ሰፊ ኃይል እንደሆነ ተመልክቷል። ይህ ኃይል ልክ እንደ ተከዜ ኃይል ከሀገር መከላከያ ጎን ሆኖ ፊት ለፊት ለመዋጋትና ውስጥ ውስጡን የሚሰርጉ የህወሃት ታጣቂዎችን ለማደን የተቋቋመ እንደሆነ ስማቸውን ለጊዜው ያልጠቀሱ የአደረጃጀቱ አባል አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም ህወሃት በራያ ግንባር እየገሰገሰ ደሴ ሲዘልቅ በየከተማው ተባባሪና የራሱ የሆኑ ሴሎች እንደነበሩት የሚናገሩት እኚሁ የአደረጃጀቱ አካል፦ “ያ የቀድሞ የውስጥ ለውስጥ አካሄድ አሁን አይሰራም። አደረጃጀቱ በአካባቢው ተወላጆች የተገነባ ስለሆነ ሁሉም አካባቢውን ያጸዳል” በማለት ህወሃት ውስጥ ውስጡን በመስረግ የኪስ ውስጥ ውጊያ ማድረግ እንደማይችል ተናግረዋል።
በሁለት አቅጣጫ የተፈናቀለው የራያ ወሎ ሕዝብ ወደ ቀዬው መመለስ እንደሚፈልግ ያስታወቁት የአደረጃጀቱ አካል፣ የሕዝብን ጥያቄ በማክበር በሰላም መኖር እየተቻለ እዚህ ሁሉ ውጥንቅጥና በየአቅጣጫው ቃታ መሳብ አሳዛኝ እንደሆነ አመልክተዋል።
ማጠቃለያ
መረዋ ቀደም ሲል ጀምሮ ሻዕቢያም ሆነ ህወሃት መሳሪያ በተሽከርካሪ ካጓጓዙ በኋላ ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ የሚያከፋፍሉበት ቦታ ነች። በዚሁ መነሻ፣ ቦታዋ ቁልፍ የጦር መሳሪያ የሚሰራጭባት አካባቢ በመሆኗ መንግስት ዘወትር ዓይኑን ሳይነቅል ይከታተላት እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ። ከምንም በላይ ግን ህወሃትን ለመታገል የወሰኑ በመብዛታቸው እንደ ቀድሞው ብዙ ምስጢር የለም። እናም ኦፕሬሽኑ “ስኬታማ” የተባለው በእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው።
በሸረሪናም ሆነ በራያ መረዋ በተፈጸመው ጥቃት የሰው ልጆች ስለመሞታቸው፣ መቆሰላቸውና መጎዳታቸው የትኛውም አካል አያስተባብልም። የሸረሪናውን ኦፕሬሽን ተከትሎ የወጡ በምስል የተደገፉ መረጃዎችን “የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፎቶና ቪዲዮ ናቸው” በማለት ለማጣጣል ቢሞከርም፣ ህወሃት ድል እንዳደረገና በሺህ የሚቆጠሩ የሀገር መከላከያ ወታደሮችን እንደማረከ ቢገልጽም፣ በገቢር የታየው ግን ሌላ ነው። ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ አንጋፋ አባቶችን ጨምሮ የ14 ዓመት ሕጻናት በየተራ ምርኮኛ ሆነው ተሰልፈው እውነታውን ተርከውታል።
እያደር በርካታ መረጃዎች እንደሚወጡ ቢታወቅም አሁን ላይ፦ “የአርሚ 13 አመራሮች ታጣቂውን ማግደው እነሱ ተከዜን በጀልባ ተሻግረው ወደ መሃል ሱዳን ሸሹ። 58 ታጣቂዎችን በተከዜ ወንዝ ተበሉ ወይም ወሰዳቸው” በማለት በቪዲዮ ምስክርነቱን እንደሰጠው የህወሃት ታጣቂ፣ ሌሎችም እያደር ብዙ መረጃዎች ይፋ ይሆናሉ። ዋናው ጉዳይ ግን ከማንም ወገን እልቂትን እንጂ ሌላ ውጤት ለማያስከትል የውክልና ጦርነት “የትግራይ ሕዝብ እስከመቼ በዚህ አግባብ ይቀጥላል?” የሚለው ጥያቄ ጎልቶ እየወጣ መሆኑ ነው።
በማይጽብሪ ግንባር ጦር እየፈረሰበት ያለው ህወሃት ከኤርትራው መሪ ኢሳያስ ጋር ተወዳጅቶ የግብጽን አጀንዳ ለማስፈጸም የትግራይን ታዳጊዎችና አባቶች የሚያስጨፈጭፈው ለምን ይሆን? “በቃኝ” የሚለውስ መቼ ይሆን? የትግራይ ሕዝብም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በህወሃት አማካይነት መከራ የሚያየው እስከመቼ ነው? “ይህ ዘመኑን ሁሉ በደም ሲጨማለቅ የኖረ ቡድን ሊያበቃለት ይገባል” በማለት ልዩነታቸውንና ጥያቄያቸውን በመግባባት፣ አብሮ በመኖር መርህ ለመፍታት የወሰኑ አካላት ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ መረጃዎች ቢኖሩም፤ “መቼ?” የሚለው የዕለት ተዕለት ጥያቄ ነው።
ድምጽ አልባው የሀገር መከላከያ እና ዝምታ ላይ የተመረኮዘው የመንግስት ፖሊሲ፣ ዝምታውን ሰብሮ ይፋ ሕዝብ እንዲነሳ ባያስታውቅም፤ ሻዕቢያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ህወሃትና እሱ የፈለፈላቸው ታጣቂዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ህብረት ከፈጠሩ ቆይተዋል። በሚዲያ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እየረጩ፣ በኢትዮጵያ ስም በሚምሉ እስስቶች ሕዝቡ ላይ የጥፋት መርዝ እየደፉ፣ ማታ ማታ ተኳኩለው በዩቲዩብ ሀገር የሚያፈርስ የቅጥፈት ትርክት እያራገቡ፣ በተከፈላቸው መጠን ኢትዮጵያውያንን ሀገር አልባ እና የጎበዝ አለቃ መፈንጫ እንድትሆን በመናበብ እየሰሩ መሆኑን ሕዝብ እንዲያውቅ አዲስ ሪፖርተር በዚህ አጋጣሚ ታሳስባለች።
ኢትዮጵያን ተሸክሞ የያዘውን የሀገር መከላከያን ሲያሻቸው “የሸኔ ጦር”፣ ሲመቻቸው “የአብይ ሰራዊት”፣ እንደሁኔታው “ቅጥረኛ”፣ “ጨፍጫፊ”፣ “የብልጽግና ሰራዊት”፣ አንዳንዴም “የትምክህት ኃይል” በማለት እንደ 1983 ዓ.ም. ሊያፈርሱት የሚጋጋጡት ኢትዮጵያን የዱሪዬ መፈንጫ በማድረግ ሊያሽመደምዱን በቅዠት ስለሚመኙ ነው። ኢትዮጵያን አፈራርሰው ዳር ሆነው ለመሳለቅ ባላቸው ምኞት የተነሳ ነው። ኢትዮጵያን ለመበታተን ከተዘጋጀው ሕገ-መንግስት ጀምሮ በሴራ፣ በጥይት ወዘተ. የተሞከሩትንና የሚሞከሩትን ደባዎች ሁሉ የሚያፈራርሰው የሀገር መከላከያ ላይ ለምን ጣት እንደሚቀሰር ኢትዮጵያዊ የሆኑና ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ ሊረዱ ይገባል። መረዳት ብቻ ሳይሆን ተረድቶም መንቃት ግድ ነው።
አዲስ አበባ የተሸከመቻቸው የሻዕቢያ ቅጥረኞች በራሳችን ኢንተርኔት፣ ገንዘብና ሀብት ሀገራችን ላይ የሚፈጽሙትን ደባ መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው። ያለ አንዳች ልዩነት በራይድ፣ በተራ እና ለውጭ ሀገር ዜጎች በተከለከሉ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እየባጠጡ ያሉ የሻዕቢያ ጉጠቶችን መከታተል የሕዝብ ኃላፊነት የመሆኑን ያህል፣ በታችኛው የአስተዳደር መዋቅር በድራፍትና በአረቄ የሚደለሉ ካድሬዎችም አደብ እንዲገዙ ጫና መፈጠር አለበት። በ1983 ዓ.ም. ኢህአዴግን አጅበው አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት በየመንደሩ ያሉ የሻዕቢያ እና የወያኔ ሰዎች ከአልጋቸው ስር መሳሪያ እየጎተቱ እንደ ርችት ሲተኩሱ እንደነበር ማስታወስ ደግ ነው።
ሲጠቃለል ዶላር ከማግበስበ ይልቅ ለሁሉም የሚበጀው ሰላም ነውና መንግስትም ሆነ ኢትዮጵያዊ የሆኑ አካላት፣ ድርጅቶች ወይም ፓርቲዎች ጠብመንጃ አውርደው ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምራት አለባቸው። በብሔራዊ ጥቅም እና በሀገር ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ከባንዳነት፣ ከሴራና ከሸፍጥ ፖለቲካ በመራቅ ሰላም ለናፈቀው ሕዝብ ሲባል በሰጥቶ መቀበልና በይቅርታ መታረቅ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ እስከዛሬ ታይቷል፤ አይጠቅምም።
በአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ የተዘጋጀ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






