አዲስ ሪፖርተር መቀለ – ብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ ለውጥ አራማጅ የሚባሉ አዲግራት የሚገኘው የአርሚ 15 አዛዥ ናቸው። ከኮር በላይ ያሉ የሰራዊት አዛዦች ተሰብሰብው ከእነ ዶክተር ደብርጽዮን ጋር ለማበርና የትግራይን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማፍረስ ሲስማሙ ከተቃወሙት መካከል አንዱ ናቸው። “ጽምዶ” የሚባለውን የትህነግና ሻዕቢያ ቅንጅት አጥብቀው ይቃወማሉ። የሻዕቢያን አገዛዝ ወንጀለኛ እንደሆነ በገሃድ የሚናገሩ መኮንን ናቸው። ትናት ለውይይት በማለት መቀለ ተጠርተው ታስረዋል። ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ልፍዓተይ ተስፋ በመባል የሚታወቀው አክቲቪስትም ሽሬ ላይ ተይዞ ታስሯል።
ዜናው በአዲስ ሪፖርተር የፌስቡክ ገጽ ላይ ከታተመ በሁዋላ፣ በተደረገ ማጣራት ጄኔራሉ ከሚመሩት ሰራዊት ጋር አዲግራት እያሉ ጥሪ ይደርሳቸዋል። ጥሪው እንደደረሳቸው ወደ መቀለ ይመጣሉ። ጥሪውን ያስተላለፉላቸው ብ/ጄ ማሾ በየነ ነበሩ። ጥሪውም “ለውይይት ወደ መቀለ ና” የሚል ነበር።
በአርሚ 15 አባል የሆኑ በማነጋገር የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ እንዳለው ብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ ለስብሰባ በሚል ከተጠሩ በሁዋላ መታሰራቸውን የሰራዊቱ አባላት ሰምተዋል። ከአምስት እስከ ሰባት ሺህ የሚሆኑት የአርሚ 15 የሰራዊት አባላት የአለቃቸውን መታሰር አስመልክቶ ምን እርምጃ ወይም አቋም ሊወስዱ እንደሚችሉ ለጊዜው መገመት አይቻልም። መጠኑና አፈጻጸሙን ማወቅ ባይቻልም ተቃውሞ የማይቀር እንደሆነ፣ ይህም የሚሆነው ብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ በሰራዊቱና በሕዝብ ዘንድ የሚወደዱ በመሆናቸው የተነሳ ነው።
በትግራይ ውስጥ ለውጥ እንደሚያስፈልግና፣ ታጣቂ ኃይሎች ከሲቪል አስተዳደር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይገባ በጽኑ የሚያምኑት ብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ፣ “ፖለቲካና ሰራዊቱ ሊነጣጠሉ ይገባል” በሚለው አቋማቸው አሁን ያሰሯቸው ወገኖች ጥርስ እንደነከሱባቸው ቀደም ሲል ጀምሮ ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል።
እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ወደ ሃራ መሬት ከወጡት ሌላ ሶስት የተለያዩ የአርሚ አዛዦች፣ ከብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸውም አስቀድሞ ተገልጾ እንደነበር የሚያስታውሱ ይህ እስር ሌሎች አርሚዎች ዘንዳም ቅሬታ እንዳያስነሳ ስጋት መኖሩን ሲገልጹ መስማቱን ተባባሪያችን አመልክቷል። ስማቸውን ያልጠቀሱ የመቀለ ነዋሪና አክቲቭ ፖለቲከኛ “በመጨረሻም አብዮት ልጇን ትበላለች እንደሚባለው ነው” ብለዋል። ልዩነቱና ግጭቱ የእርስ በርስ ሆኖ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
ምንም እንኳን የትህነግ የሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች የአንድ አካባቢ ተወላጅና በአምቻና ጋብቻ የተያያዙ ቢሆኑም እንዲህ ያለው አካሄድ ውሎ አድሮም ቢሆን ልዩነት እንደሚያስነሳ የሚያምኑ፣ ብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ በተመሳሳይ የአካባቢያቸው ሰው ህነው ሳለ በዚህ ደረጃ መታሰራቸው በመንደርተኝነት ወስጥም ሌላ ጥቃቅን መንደርተኝነትን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
“ለምን ታሰሩ? ለምን ይህ ግዜ ተመረጠ?” ለሚለው ተባባሪያችን ባሰባሰበው መረጃ አሁን ላይ ትህነግ በሻዕቢያ ጉትጎታ ላሰበው ጦርነት መኮንኑ እንቅፋት ይሆናሉ በሚል እንደሆነ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
ብ/ጄ ጉዕሽ ገብረ የሻዕቢያን አገዛዝ ቀደም ሲል ጀመረው የሚቃወሙ፣ የሚተቹና ጂኖሳይደር በመሆኑ ለፍርድ መቀረብ የሚገባው እንደሆነ በግልጽ ስለሚናገሩ እስሩ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚናገሩ “ትዕዛዙ ከሻዕቢያ እንድመጣና ተላልፈው እንዲሰጡት ፍላጎት አለው። በትህነግ በኩል ኝ ደፍረው መስጠት አይችሉም ከሰጡ ጣጣው ብዙ ስለሆነ እያመናቱ ነው”
አንዳንድ ማህራዊ ገጾች ተላልፈው እንደተሰጡ ቢናገሩም፣ የአዲስ ሪፖርተር ታማኝ ምንጭ መኮኑኑ መታሰራቸውን እንደሚያውቁ፣ ይሁን እንጂ ተላልፈው ለሻዕቢያ ሊሰጡ እንዳማይችሉና ይህንኑ እርምጃ ደፍሮ የሚወስድ እንደማይኖር፣ ካደረጉትም ከፍተኛ ቀውስ እንደሚፈጠር አመልክተዋል።
በሌላ ዜና በማህበራዊ ሚዲያዎች ልፍዓተይ ተስፋ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ሽሬ ከተማ ተያዞ መታሰሩ ታውቋል።
አክቲቪስቱ የታሰረው ቀደም ሲል “ጽምዶ” የተሰኘውን አዲስ ግንኙነት በመደገፍ አስመራ ድረስ ሄዶ ቃለ ምልልስ ከሰጠና ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰራ ቆይቶ “ተዘነጋሁ፣ ተገፋሁ” በማለት ተቃዋሚ በመሆኑ እንደሆነ ታውቋል።
የሚቀርቡትን ባመነጋገር ዜናውን የላከለን የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ ብርሃነ አስመራ በመሄድ ከወል ሰኢድ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርግ “ያልፈውን ረስተን አንድ እንሁን፣ እንታረቅ” ብሎ ነበር። ብርሃነ ከቃለ ምልልሱ በሁዋላ ቁጥር አንድ የ”ጽምዶ” ቀስቃሽና የማህበራዊ ሚዲያ መሪ አድርጎ ራሱን ይቆጥር ነበር።
እየዋለ ሲያድር ሌሎች አክቲቪስቶች ዘመቻውን ተቀላቅለው ዋጡት፡፡ ይህን ጊዜ ብረሃነ “እኔን አገለሉኝ” የሚል ስሜት እንደተሰማው ለሚቀርቡት ማናገር ጀመረ። ቆየት ብሎ በሻዕቢያ ተቃዋሚ ሚዲያ ቀርቦ ሻዕቢያን “ጂኖሳይደር ነው መተየቀ አለበት። ጽምዶውን እደግፋለሁ ሻዕቢያ ግን ጨፍጫፊ ነው” በማለት ተናገረ። በራሱ የማህበራዊ ሚዲያ አውድም ትህነግ የማይለውጥ ተቸካይ መሆኑን፣ ሻዕቢያ ደግሞ ፍርድ የሚጠብቀው ወነጀለኛ መሆኑን በመግለጽ በተደጋጋሚ ይጽ ጀመር።
በቃል ምልልሱ ወቅት “ስለ ጄኖሳይድና በትግራይ ሕዝብ ላይ ስለተፈጸመ ወንጀል አታንሱ” በማለት ሻዕቢያ ጫና ያሳድር እንደነበር በመጥቀስ ትህነግ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈጸመን ወንጀል ትቶ ከሻዕቢያ ጋር መወዳጀቱ አግባብ እንዳልሆነ መግለጹ ሁለቱን ቡድኖች በማበሳጨቱ መጨረሻው እስር ቤት ሊሆን እንደቻለ ተባባሪያችን ካሰባሰበው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ይህ እስከታተመ ድረስ ሁለቱም እንዳልተፈቱ ወይም የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ታውቋል። በሚታወቅ የህግ አግባብ መታሰራቸው አልተረጋገጠም። ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ በስልክ ለሽሬ ፖሊስ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ተከታትለን መረጃ ስናገኝ እናካትታለን።






