- አዲስ ሪፖርተር – ፑንትላንድ በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ የተያዙ እንደሆነ በመግለጽ ሃምሳ የሚጠጉ የውጭ አገር ዜጎች ሆነው ለISIS የሚዋጉ ታጣቂዎችን መያዟን ይፋ አድርጋለች። የተያዙት ታጣቂዎች ስምና ምስላቸው ይፋ ተደርጓል።
ይህ የታወቀው በቦሳሶ ወደብ ከተማ ንግግር ያደረጉት የፑንትላንድ ባለስልጣናት የእስረኞቹ ስም እና የትውልድ ሀገራቸውን ጨምሮ መረጃቸውን ለዕይታ ባቀረቡበት ወቅት ነው። እንደ ባለሥልጣናቱ ገለጻ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እስረኞች የቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞሮኮ፣ የመን፣ ሶሪያ እና ታንዛኒያ ዜግነት ያላቸው ናቸው።
የፑንትላንድ መንግስት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በቁጥጥር ስር ከዋሉት የአይኤስ አባላት መካከል ከፍተኛው ቁጥር ወይም አስራ ስምንት የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ያሳዘናቸው “እንደ እነዚህ ያሉ የእፉኝት ልጆች የአሸባሪዎች ቡድን ተቀላቅለው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አደጋ ሆነው መታየታቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ደህንነትን ለማቃወስ ለውጭ ሀይሎች የግርድና ስራ እንደሚሰሩ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል” ሲሉ ዜናውን የሰሙ ገልጸዋል።
ዜናው ኢትዮጵያ በቀጠናው የሚያጋጥሟት የአሸባሪዎች ሴራ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ምን ያህል ስር የሰደደ ለመሆኑ እንደ ማረጋገጫ እንደሚወሰድ የገለጹም አሉ። በቅርቡ ፊልድ ማርሻል ብረሃኑ ጁላ፣ በሶማሊያ አልሸባብ ላይ በተወሰደ እርምጃ ከተገደሉት መካከል ኢትዮጵያዊያን እንዳሉበት ካስታወቁ በሁዋላ “አሁን ኢትዮጵያዊያን ሆነው ምን ለማሳካት ነው ለአልሸባብ ወግነው አገራቸውን ለመውጋት የሚወስኑት” በማለት ማዘናቸውን ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም።
እነዚህ ግለሰቦች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ ሲሆኑ፣ በISIS ቡድን ውስጥ ተቀላቅለው በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው።
አዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪውን በመጥቀስ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ኢትዮጵያን ለማጥቃትና ጦርነቱን ለማስፋት ከተበታተነ የኦብነግና የኦነግ ሸኔን ኃይል ከአልሸባብ ጋር ለማቀናጀት ከግብጽ ውክልና ወስደው ሶማሊያ የሚመላለሱ፣ ቱርክና ጎረቤት ኬንያ በመገኘት ምልመላ የሚያካሂዱ መኖራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ቀደም ሲል የአገር መከላከያ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በሶማሊያ የተደረገውን የፀረ-ሽብር ዘመቻ አስመልክተው እንደገለጹት፣ በዚያ ዘመቻ የተደመሰሱት አሸባሪዎች መካከል ኢትዮጵያውያን እንዳሉ በጠቆሙበት ወቅት፣ “ለምን እርምጃ ተወሰደባቸው” በሚል በአሜሪካ የሚገኙ የተቃዋሚ ድርጅትና የተለያዩ ማህበራት መሪዎች ተቃውሞ አሰምተው ነበር። እነዚህ ወገኖች ይህ ዜና እስከተሰራ ድረስ በፑንትላንድ ይፋ ስላደረገቸው መረጃ ያሉት ነገር የለም።
ኢትዮጵያውያን በአልሸባብ እና በISIS የመሳሰሉ ቡድኖች ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች ኢትዮጵያን ለማዳከም እንዴት እንደሚጠቀሙባቸው ማየት እንደ ዜጋ አሳፋሪ መሆኑን አመላክቷል።
አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ከአልሸባብ ወይም ከአይሲስ ጋር ተቀላቅሎ ኢትዮጵያን ለማጥቃት መምረጡ እጅግ አሳፋሪ እና የማይታሰብ ነው። ኢትዮጵያ በውስጥ ቅጥረኛ አማፅያን እና አሸባሪዎች ለማተራመስ ከሚሰራው በተጨማሪ ከውጭ ሃይል ጋር፣ በተለይም ከዓለም ዓቀፍ አሸባሪዎች ጋር በመሆን፣ ኢትዮጵያን ለመውጋት ማበር ባንዳነት ስለመሆኑ አገራቸውን የሚወዱና ጉዳዩን አርቀው የሚመለከቱ በተደጋጋሚ ያሳስባሉ።
በምስራቅ ኢትዮጵያ አንዳንድ የታጠቁ ቡድኖች ከግብጽ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ በቂ መረጃዎች በተለያዩ ጊዜያት እየወጡ ነው። ከግብጽ ጋር ኮንትራት ገብተው እነዚህ ቡድኖች የሚያደራጁ በስም የሚታወቁ “ኢትዮጵያዊያን” የሞቃዲሾ መንግስትን እንደሚጠቀሙ የሚገልጹ መረጃዎች ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ ሲነታረኩ ከወጡ ሰነዶች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
በፖለቲካ ትንተና፣ መንግሥት ይህንን ለመቆጣጠር የብሔራዊ የስለላ ስርዓትን በማጠናከር እና የክልል ትብብርን በማሳደግ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገሮች እነዚህን ቡድኖች ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያደርጉትን ጥረት ማቆም ያስችላል የሚሉ አካላት ዜጎችም ይህን መሰሉን የትርምስ ቅንጅት ለአገራቸው ሲሉ ሊያወግዙና ከወዲሁ ሊታገሉት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ይህ ዜና ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የማንቂያ ደወል እንደሆነ ዜናው ተቀንጭቦ በማህበራዊ ሚዲያ ቀርቦ የተመለከቱ አስታውቀዋል። “የአገሬን ሰላም እና አንድነት እፈልጋለሁ የሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ትብብር ማድረግ እና የውስጥ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት የሚደረገውን ትግል መደገፍ የውዴታ ግዴታው ነው። ይህም ኢትዮጵያን ከእንደዚህ ዓይነት አደገኛ አደጋዎች የመታደግ ብቸኛው መንገድ ነው” ሲሉ የተደመጡም አሉ።
ከላይ ያለው ምስል የቱርክ ዜግነት ያለው የአይሲስ ተዋጊ ውሃ ሊቀዳ ሲል በፑንት ላንድ የጸጥታ ኃይሎች በተያዘበት ወቅት ነው። ቀኑም ጁነ 20 ቀን 20225 ነው፤ ቱርክ መሳሪያ የጫነ መርከብ ሳይቀር እንደተያዘባት አይዘነጋም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






