የትራምፕ ስሁት ትርክት የማይሽረው የሕዳሴ ግድብ እውነታና ቀጣይ አቅጣጫዎች፤

Date:

በአለባቸው ጉብሳ – ነፃ አሰተያየት 

ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓመታት ስትከተለው የቆየችው የዲፕሎማሲ መከላከል አክትሞ፣ ዛሬ ግንባታው ተጠናቆና ኃይል ማመንጨት መጀምሮ “በመሬት ላይ ያለ ሀቅ” በመሆኑ ሀገሪቱ የራሷን ደንብና ሁኔታዎች የምታስቀምጥበት ጠንካራ የመደራደር ቁመና ላይ ትገኛለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ግድቡ የተገነባው በአሜሪካ ገንዘብ ነው” ወይም “ኢትዮጵያ የአባይ መሸጋገሪያ ናት” በማለት የሚሰነዝሯቸው ንግግሮች፣

85% የውሃ ምንጭነቷንና የግድቡ ግንባታ በዜጎች መዋጮ፣ የላብና ደም መስዋዕትነት የተመሰረተውን ጥሬ ሃቅና እውነት አይሽረውም። ስለሆነም ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (CFA) እንደ ዋነኛ የሕግ መሣሪያ በመጠቀም፣ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን በተግባር ለማረጋገጥና የቅኝ ግዛት ውሎችን ውድቅ ለማድረግ ወደ አዲስ የአጀንዳ ቀራጭነት ምዕራፍ ተሸጋግራለች። 

ይህንን አዲስ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማስቀጠል፣ በኃይል ፖለቲካ (Realpolitik) የታጀቡና ወገንተኝነት የሚንጸባረቅባቸውን የሽምግልና ጥረቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ መመልከት ብሄራዊ ግዴታ ነው። ትራምፕ ግብፅን “ታላቅ ወዳጅ” በማለት እያሞካሹ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጉት ጥረት፣ ዓለም አቀፍ የሕግ የበላይነት በኃይል የበላይነት እየተተካ መሆኑን አመላካች ነው። 

በመሆኑም ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ሀብቷ ላይ የምታደርገው ድርድር በሌሎች ፖለቲካዊ ትርፍ እንዳይቀለበስ፣ የራሷን የማይታለፉ “ቀይ መስመሮች” በማስመርና ማንኛውም ስምምነት የወደፊት የልማት መብቷን እንደማይገድብ አስቀድሞ ማረጋገጥ ለድርድሩ ስኬት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። 

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የትራምፕን ንግግሮች በሳይንሳዊና ታሪካዊ ሀቆች በመሞገት፣ በኃይል ፖለቲካ የታጀበውን የሽምግልና ስጋት በመዳሰስ እና የውስጥ ግንባር አንድነትን አስፈላጊነት በመተንተን፣ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን የምታስከብርባቸውን ቁልፍ ስትራቴጂያዊ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንናመላክታለን። 

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝምንጭ ወይስ መሸጋገሪያ?” 

ስለ አባይ ወንዝ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች ከፖለቲካዊ አፈ ታሪኮችና ከዲፕሎማሲያዊ ሽንገላዎች በጸዳ መልኩ፣ በማይናወጡ ሳይንሳዊ ሀቆች ላይ ብቻ ሊመሰረቱ ይገባል። በቅርቡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዳቮስ ከአል ሲሲ ጋራ ባደረገው  የጎንዮሽ ውይይት ትራምፕ “ናይል በኢትዮጵያ በኩል የሚያልፍ ወንዝ ነው” በማለት የገለጹት አገላለጽ፣ የወንዙን ተፈጥሯዊ የሃይድሮሎጂ መዋቅር ፍጹም የሳተና የኢትዮጵያን የታሪክና የተፈጥሮ ባለቤትነት የሚያቃልል ነው። እውነታው ግን ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ መሸጋገሪያ ወይም ጊዜያዊ ማለፊያ ሳትሆን፣ የወንዙ ህልውና መሰረትና ዋነኛ መነሻ ናት። 

ከጠቅላላው የናይል የውሃ ፍሰት ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ስፍራዎች ሲሆን፣ ይህም በታላቁ ዓባይ (53%)፣ በባሮ-አኮቦ-ሶባት (24%) እና በተከዜ (8%) ገባር ወንዞች አማካኝነት የሚገኝ ነው። ይህ ማለት ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎና ያለ ተፈጥሯዊ ስጦታዋ፣ በአፍሪካ ምድር “ናይል” የሚባል ትርጉም ያለውና ለታችኞቹ ሀገራት ህይወት የሚዘራ ወንዝ ሊኖር አይችልም ማለት ነው። 

በመሆኑም የወንዙ አጠቃቀምና አስተዳደር ጉዳይ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙና ኢትዮጵያን ባላካተቱ ኢ-ፍትሃዊ ውሎች ሳይሆን፣ በዚሁ ጂኦግራፊያዊና ሃይድሮሎጂያዊ እውነታ ላይ ተመስርቶ ሊመራ ይገባዋል። ኢትዮጵያ የውሃው ምንጭ በመሆኗ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቷን ለህዝቦቿ ብርሃንና ልማት የመጠቀም መብቷ በማንም ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚገደብ ሳይሆን በተፈጥሮ የተቸራት የማይገሰስ ሉአላዊ መብት መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው ይገባል። 

የኢትዮጵያውያን ላብና ደም ወይስ የአሜረካ ገንዘብ ?  

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ መድረኮች ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሰጧቸው መግለጫዎች ከመሬት ካለው ተጨባጭ ሀቅ ጋር በእጅጉ የተጋጩና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጥረት የሚያሳንሱ ናቸው። ከንግግሮቻቸው ሁሉ እጅግ አስገራሚውና ትልቁ ስህተት “ግድቡ የተገነባው በአሜሪካ ገንዘብ ነው” የሚለው ትረካቸው ነው። ይህ አባባል ፍጹም መሰረት የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ቅጽበት አንስቶ አንድም ሳንቲም ከውጭ እርዳታ ወይም ብድር ያልተቀበለ መሆኑን የዓለም የገንዘብ ተቋማትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያውቁት ሀቅ ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ጉልበትና በደምና በአጥንት ጭምር የተገነባ ብሄራዊ ሀብት ነው። ከቀን ሰራተኛው እስከ ከፍተኛ ምሁሩ፣ ከገበሬው እስከ ነጋዴው፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ በገዙት ቦንድና ባደረጉት የቀጥታ መዋጮ የተገነባ የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት ነው። 

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ሀብ፣ ደምና ላብ ብቻ እንዲገነባ የተደረገው፣ የውጭ ሀይሎችና የገንዘብ ተቋማት በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ተፅዕኖ ምክንያት ለግንባታው የሚሆን ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበሩ ነው። ኢትዮጵያ ይህን መሰናክል ያለፈችው “የራሳችንን በራሳችን አቅም” በሚል ጽኑ ብሄራዊ ስሜትና ቁርጠኝነት እንጂ በአሜሪካ ወይም በማንኛውም የውጭ አካል የገንዘብ ድጋፍ አይደለም። ስለሆነም ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢትዮጵያን ህዝብ የዓመታት መስዋዕትነት ወደ ጎን በመተው፣ የአሜሪካ ገንዘብ እንዳለበት አድርገው የሚያቀርቡት ትረካ ታሪካዊ ስህተት ያለበትና በሀገሪቱ የልማት ሉአላዊነት ላይ የሚሰነዘር የተዛባ አመለካከት ነው። የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ነፃነት አርማ እንጂ በማንም የውጭ ሀይል መልካም ፈቃድ ወይም ፋይናንስ የቆመ ፕሮጀክት አይደለም። 

የውሃ መገደብወይስየውሃ ፍሰት አስተዳደር“? 

ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ግድቡ አባይን ይገድባል” በማለት ደጋግመው የሚያነሱት ስጋት በሳይንሳዊ እና በሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ምህንድስና መርሆዎች ሲመዘን ፍጹም ውድቅ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) አላማው የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት እንጂ ውሃውን ለመስኖ ተግባር ውሎ እንዲቀንስ ማድረግ አይደለም። በሳይንሳዊ አሰራሩ መሰረት፣ ውሃው ከከፍተኛ ቦታ ወደ ዝቅተኛ ቦታ በሚወርድበት ወቅት ግዙፍ ተርባይኖችን በማሽከርከር የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫል፤ ከዚያም ያለምንም ቅነሳ በቀጥታ ወደ ታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት (ሱዳንና ግብፅ) መፍሰሱን ይቀጥላል። ግድቡ ውሃውን አይበላውም፣ አያስተናልም፣ ወይም አቅጣጫውን አይቀይርም። ይልቁንም ግድቡ የውሃውን ፍሰት በዓመት ሙሉ ወጥ እና ተከታታይ እንዲሆን በማድረግ በክረምት ወቅት የሚከሰተውን ድንገተኛ ጎርፍ እና በበጋ የሚከሰተውን ድርቅ የመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። 

ከዚህም ባለፈ፣ ግድቡን “ግብፅን ለማጥፋት እንደ መሳሪያ (Weapon)” አድርጎ የማቅረቡ ትረካ፣ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት እንደ ጦርነት የመቁጠር የተዛባ አመለካከት ውጤት ነው። የተለያዩ ዓለም አቀፍ የውሃ ምሁራን እንደሚያረጋግጡት፣ ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚፈጥረው ጉልህ “ጎጂ ተጽዕኖ” የለም። እንዲያውም ውሃው በኢትዮጵያ በረዷማና ቀዝቃዛ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ መቆጠሩ፣ በግብፅ ዝቅተኛና ሞቃታማ በረሃዎች ላይ ከሚገኘው የአስዋን ግድብ ጋር ሲነጻጸር፣ በትነት (Evaporation) የሚባክነውን ከፍተኛ የውሃ መጠን በእጅጉ ይቀንሳል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የገነባችው ግድብ የጥፋት መሳሪያ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጨለማ የሚያወጣ እና ለቀጠናውም ትርፍ የኤሌክትሪክ ሀይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚፈጥር የልማት አርማ ነው። ይህንን ሳይንሳዊ ሀቅ ወደ ጎን በመተው ግድቡን እንደ ስጋት መሳል፣ የቴክኒክ እውነታዎችን ለፖለቲካዊ ፍጆታ የመጠቀም ሙከራ ከመሆን አያልፍም። 

ጥንቃቄ የሚሻው ከሽምግልና በስተጀርባ ያለው የሃይል ፖለቲካ 

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለሽምግልና ያሳዩት ዳግም ፍላጎት፣ በሁለት እኩዮች መካከል የሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ሳይሆን የሀያላን ሀገራትን ፍላጎት በታዳጊ ሀገራት ላይ የመጫን መንፈስ ይንጸባረቅበታል። ባለፉት 12 ወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደታየው፣ የቀድሞው በህግና በደንብ ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ ስርአት እየተሸረሸረና በሀይል የበላይነት (Realpolitik) እየተተካ መጥቷል። በዚህ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ “ሽምግልና” የሚለው ቃል ትርጉሙ ተቀይሮ፣ ፍትሃዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የሀያላኑን ስትራቴጂካዊ ፍላጎትና የወዳጅ ሀገራትን ጥቅም ማስከበሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትከተለው የቆየችውን “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ ወደ ጎን የሚገፋና የአህጉሪቱን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ አደገኛ አካሄድ ነው። 

ይህ የአሜሪካ የሽምግልና ጥረት የኢትዮጵያን የልማት መብት ለሌላ ወገን የፖለቲካ ትርፍ አሳልፎ ለመስጠት የሚደረግ ስልታዊ ጥረት ይመስላል። ትራምፕ በመግለጫቸው ወቅት ግብፅን “ታላቅ ወዳጅ” በማለት ሲያሞካሹ፣ የኢትዮጵያን ግድብ ግን እንደ “አደገኛ” እና “የውሃ ፍሰት ገዳቢ” አድርገው መሳላቸው፣ ሽምግልናው ገና ሳይጀመር ወገንተኝነት ያለበት መሆኑን ያሳያል። ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ምሁራን እንደሚጠቁሙት፣ እንዲህ አይነቱ የሀይል ፖለቲካ ተደራዳሪ ወገኖች ያላቸውን ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብት ሳይሆን፣ የሀያላኑን የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅምና ቀጠናዊ ሚዛን ብቻ ታሳቢ ያደርጋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በሉአላዊ ሀብቷ ላይ የምታደርገው ድርድር በፍትህ ላይ ሳይሆን በሀይል አሰላለፍ ላይ እንዲመሰረት የሚደረገው ግፊት ለሃገራዊ ጥቅሟ ትልቅ ስጋት ነው። 

በዚህ ፈታኝ ወቅት ኢትዮጵያ ይህንን የ“ሽምግልና በር” ከመክፈቷ በፊት፣ በሰከነ መንፈስና በአንድነት ቆማ የራሷን ቀይ መስመሮች በግልጽ ማስመር ይኖርባታል። ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ በሀያላን ሀገራት ግፊት የሚደረጉ ስምምነቶች ብዙ ጊዜ የደካማ ሀገራትን የረጅም ጊዜ ጥቅም የሚጎዱና ለወደፊት ግጭቶች በር የሚከፍቱ ናቸው። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው ድርድር ወቅት የታዘበችው የጫና ፖለቲካ፣ አሁንም በሌላ መልክ ሊደገም እንደሚችል መገንዘብ ይገባል። ስለሆነም ሽምግልናው ከውሃ ክፍፍልና ከሉአላዊነት ጥያቄ ጋር መያያዝ እንደሌለበት፣ እንዲሁም ማንኛውም ስምምነት የኢትዮጵያን የወደፊት የልማት እድሎች የማይገድብ መሆኑን አስቀድሞ ማረጋገጥ ለድርድሩ ስኬት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። 

አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ዲፕሎማሲን እንደ ቴያትር፣ ውልና ስምምነቶችን ደግሞ እንደ መድረክ ጌጦች የሚጠቀምበት እየሆነ መጥቷል። የትንንሽ ሀገራት እጣ ፈንታ በሀያላን የቢሮ ጠረጴዛዎች ላይ እንዳይወሰን፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካዊ ወንድሞቿ ጋር ያላትን ትስስር በማጠናከር የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (CFA) እንደ ዋነኛ ህጋዊ መሳሪያ ልትጠቀምበት ይገባል። ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለማልማት ለሚጥሩ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የህልውና ፈተና ነው። በመሆኑም በሀይል ፖለቲካ የታጀበን ሽምግልና በጥንቃቄ መመልከትና የሀገርን የክብርና የሉአላዊነት አጀንዳ በጽናት ማስጠበቅ አማራጭ የሌለው ብሄራዊ ግዴታ ነው። 

አዲሱ ምዕራፍ፡ ከተከላካይነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነት 

ኢትዮጵያ ለዓመታት በድርድር ጠረጴዛ ላይ ስትከላከልና የልማት ፍላጎቷን ለዓለም ስታስረዳ የቆየችበት ምዕራፍ አብቅቶ፣ ዛሬ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆና ኃይል ማመንጨት ጀምሮ በተጨባጭ “መሬት ላይ ያለ ሀቅ” ሆኗል። ይህ ስኬት ሀገሪቱ የራሷን ደንብና ሁኔታዎች የምታስቀምጥበት ጠንካራ የመደራደር ቁመና (Position of Strength) ላይ እንድትገኝ ያደረጋት ሲሆን፣ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) በይፋ ሥራ መጀመርም ኢትዮጵያን በተፋሰሱ ጉዳይ ላይ ዋነኛ አጀንዳ ቀራጭ አድርጓታል። ከእንግዲህ ድርድር ማለት የቆዩና ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ “ታሪካዊ መብቶችን” ማስጠበቅ ሳይሆን፣ በሳይንሳዊ ሀቅ ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን በተግባር ማረጋገጥ መሆኑን ዓለም ሊገነዘበው ይገባል። 

ይህንን አዲስ ምዕራፍ በድል ለመወጣት ግን የውስጥ ግንባር ጥንካሬ እና ብሄራዊ አንድነት እንደ ዋነኛ የዲፕሎማሲ መሳሪያ ሊያገለግሉ ይገባል። ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም የተጋረጡባቸውን የውጭና የውስጥ ወረራዎች በአንድነት እንደመከቱት ሁሉ፣ አሁን በሉአላዊነት ላይ የተደቀነውን የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም በሰከነ ስትራቴጂ፣ በባለሙያዎች ዝግጅትና በታቀደ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ስራ ሊደገፉ ይገባል። በዲጂታል ዲፕሎማሲ የታጀበውና በሐሰት መረጃዎች ላይ ያነጣጠረው የመረጃ ማጥራት ስራ፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕን መሰል የተሳሳቱ ትረካዎችን በማረም የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቁም በላይ፣ የኢትዮጵያን የልማት ሉአላዊነት በማይናወጥ መርህ ላይ ያቆማል። እነዚህንም የድርድር ወሳኝ ተግባራት እንደመከተለው በዝርዘር እናያለን።  

የውስጥ ግንባር ጥንካሬ ለዲፕሎማሲያዊ ድል 

በዚህ የኃያላን ሀገራት ፍላጎትና ፉክክር በነገሰበት ዓለም ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ዋነኛና የማይበገር የመደራደሪያ አቅም የህዝቧ አንድነት ነው። ታሪክ እንደሚመሰክረው፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ ምንጩ ሁልጊዜም የውስጥ አንድነቷ ነው። ቀደም ሲል በምዕራባውያን ኃይሎች ሲደገፍ የነበረውን የህወሃት ታጣቂ ቡድን ወረራ፣ ኢትዮጵያውያን የአመራር፣ የዓላማና የተግባር አንድነት በመፍጠር እንዲሁም የማይበገር የመከላከልና የመቋቋም ፍላጎታቸውን (The Will to Resist) በተግባር በማሳየት እንደመከቱት ሁሉ፣ አሁንም በሉአላዊነት ላይ በተደቀነው የዲፕሎማሲያዊና የጂኦ-ፖለቲካዊ ጫና ያንኑ ጽኑ አንድነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተቀናቃኞች ሁልጊዜም የሚፈልጉት የተከፋፈለችና በውስጥ ሽኩቻ የደከመች ሀገርን በመሆኑ፣ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ስኬት ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አማራጭ የሌለው ብሄራዊ ጉዳይ ነው። 

ግብፅና መሰል የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያን የውስጥ ልዩነትና የፖለቲካ አለመግባባት እንደ ቀዳዳ በመጠቀም በድርድር ጠረጴዛ ላይ የመደራደር አቅማችንን እንዳታዳክም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ማለት በሁሉም ጉዳይ ላይ አንድ መሆን ማለት ሳይሆን፣ በሀገር ሉአላዊነትና በብሄራዊ ጥቅም ላይ ግን አንድ ወጥ የሆነ ጠንካራ አቋም መያዝ ማለት ነው። የውስጥ ትርምስ ባለበት ሁኔታ የሚደረግ ድርድር ሀገርን ለተፅዕኖና ለጥቅም አሳልፎ የመስጠት እድሉ ሰፊ በመሆኑ፣ የውስጥ ግንባርን ማጠናከር ከየትኛውም የውጭ ዲፕሎማሲ ስራ ቀድሞ ሊሰመርበት የሚገባ ተግባር ነው። 

ለዚህም ሲባል፣ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቃውሞና በሽምቅ ትግል ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። መንግስት ለሰላም፣ ለውይይትና ለድርድር በሩን ክፍት በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና ቅሬታ ያላቸውን ወገኖች ወደ ብሄራዊ መግባባት ማምጣት ይኖርበታል። የቤት ስራውን በውስጥ የጨረሰ፣ ሰላሙን ያረጋገጠ እና በጋራ ዓላማ ዙሪያ የተሰለፈ ህዝብና መንግስት፣ በዓለም አቀፍ የድርድር ጠረጴዛ ላይ የሚኖረው ድምጽ ሰሚ፣ ክብሩ የተጠበቀና የማይደፈር ይሆናል። 

በመጨረሻም፣ የሕዳሴው ግድብ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ላብና ሀብት ያፈሰሱበት የጋራ ውጤት እንደመሆኑ፣ የግድቡን ደህንነትና የውሃ አጠቃቀም መብት ማስከበርም የጋራ ኃላፊነት ነው። የውስጥ ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ፣ በጋራ የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ ግን እንደ አንድ ልብ መምከርና መቆም፣ ለፕሬዝዳንት ትራምፕም ሆነ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የሚተላለፍ ጠንካራ መልዕክት ነው። አንድነታችን የውስጥ ሰላማችንን ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያለንን የድርድር የበላይነትና የሉአላዊነት ጥበቃ የሚያረጋግጥ ታላቅ ሀገራዊ መሳሪያችን ነው። 

የባለሙያዎች ዝግጅትና የስትራቴጂ ቀረጻ፡ የዲፕሎማሲያዊ የበላይነት መሳርያ 

ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችን ከስሜታዊነት በጸዳ እና በሰከነ ሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት፣ የሕግ፣ የቴክኒክ እና የዲፕሎማሲ ባለሙያዎችን ያቀፈ ጠንካራ ብሄራዊ የድርድር ቡድን በቋሚነት ማደራጀት ይኖርባታል። ይህ ቡድን በየጊዜው የሚለዋወጡ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ክስተቶችን በንቃት የሚከታተል፣ ሊመጡ የሚችሉ ጫናዎችን አስቀድሞ የሚተነብይ እና ለተለያዩ ሊከሰቱ ለሚችሉ ሁነቶች አማራጭ የድርድር ስልቶችን (Scenario Planning) ቀድሞ የሚያዘጋጅ መሆን አለበት። የድርድር ሂደቱ በሀያላን ሀገራት ፍላጎትና ጫና የሚመራ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የጸና መሆኑን ማረጋገጥ የዚህ የባለሙያዎች ስብስብ ዋነኛ የቤት ስራ ነው። 

ይህ የባለሙያዎች ቡድን በድርድር መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በማንም መልካም ፈቃድ ላይ የማይቆም መሆኑን በቴክኒክና በሕግ ማስረጃዎች አስደግፎ የማቅረብ ታላቅ ተልዕኮ አለበት። ድርድሩ በሉአላዊነት ላይ እንደማይመሰረትና ኢትዮጵያ በራሷ ወንዝ ላይ ያላትን የመጠቀም መብት ለድርድር እንደማታቀርብ በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርበታል። በተለይም በዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግጋት (International WatLaw) እና በፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መርሆዎች ዙሪያ ጥልቅ እውቀት ያላቸው የሕግ ምሁራን፣ ግድቡ በታችኞቹ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ የሚያሳዩ የሃይድሮሎጂ ባለሙያዎች እና የሰላ ድርድር ክህሎት ያላቸው ዲፕሎማቶች ቅንጅት ለኢትዮጵያ የሐሳብ የበላይነትን ያጎናጽፋታል። 

ከዚህም በተጨማሪ፣ ይህ ስትራቴጂያዊ ቡድን ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድርድሮችን ድክመትና ጥንካሬ በመገምገም፣ የወደፊት ድርድሮች የሀገሪቱን የልማት ነፃነት እንዳያግዱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ለምሳሌ፣ የድርድር ስልቱ የኢትዮጵያን የወደፊት የሌሎች ወንዞች ልማት እድል የማይገድብና በቅኝ ግዛት ውሎች ላይ የተመሰረቱ የውሃ ክፍፍል ጥያቄዎችን የማያስተናግድ መሆኑን በጽኑ መርህ ላይ ማቆም አለበት። ባለሙያዎቹ የሚያዘጋጁት የቴክኒክ ሰነድና የሕግ ትንታኔ፣ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብና መካከለኛ ገላጋዮችን በሀቅ ሊያሳምን የሚችል ጠንካራ ይዘት ሊኖረው ይገባል። 

በመጨረሻም፣ ይህ ቡድን ከመንግስት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ ነገር ግን ከፖለቲካዊ ግፊቶች ነፃ በሆነ የሙያ ብቃት (Professionalism) ሊመራ ይገባዋል። የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር፣ የድርድር ባለሙያዎች ቀጣይነት ያለው ዝግጅትና የምርምር ስራ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ በድርድር ጠረጴዛ ላይ ያላትን የሞራልና የሕግ የበላይነት በተደራጀ የባለሙያዎች ዝግጅት ስታጀብ፣ የቱንም ያህል የሀያላን ሀገራት ጫና ቢበረታባት የሀገርን ክብርና ጥቅም ሳታስደፍር በድል ለመውጣት ያስችላታል። 

የተቀናጀ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻና የዲጂታል ዲፕሎማሲ ፋይዳ 

በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚነዙ የተሳሳቱ ትረካዎችን ለመመከት፣ ኢትዮጵያ በታቀደ፣ በተደራጀና በሰለጠነ መልኩ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት (PR) ዘመቻ ማካሄድ ይኖርባታል። ፕሬዝዳንት ትራምፕም ሆኑ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት ስለ ግድቡ የሚሰጧቸው የተዛቡ መረጃዎች በዝምታ ሊታለፉ አይገባም። ይህ ስራ በዓለም አቀፍ ታዋቂ ሚዲያዎች፣ በታዋቂ ምሁራንና በዲፕሎማቶች አማካኝነት መተግበር ያለበት ሲሆን፣ ዋነኛ ግቡም የሐሰት መረጃዎችን በማጥራት (Fact Checking) የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ጥያቄና የግድቡን ሳይንሳዊ ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረጽ ነው። ለዚህም የውጭ ግንኙነት ስራው ከመደበኛው ዲፕሎማሲ ባለፈ፣ ዘመኑ የደረሰበትን የመረጃ ፍሰት ተጠቅሞ የሀገሪቱን እውነት ለአለም ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል። 

ይህን ስትራቴጂያዊ ንቅናቄ ውጤታማ ለማድረግ፣ ኢትዮጵያውያን ምዕራብ አገር መራሹን የሕወሃት ወረራ ለመመከት የተጠቀሙበትንና ድንበር ተሻጋሪ ድምፅ መሆን የቻለውን “በቃ” (No More) የተሰኘ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንደ ተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል። ያ ንቅናቄ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ረገድ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የተቀናጀ አቅም ያሳየበትና የተሳሳቱ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ትረካዎችን የሰበረበት በመሆኑ፣ አሁንም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ፖለቲካዊ ጥቃቶችን ለመመከት እንደ ትልቅ ስልት ሊያገለግል ይገባል። ዲጂታል ዲፕሎማሲው በተለይም በትዊተር (X)፣ በፌስቡክና በሌሎች መድረኮች ላይ የሚገኙ የሀሰት መረጃዎችን በወቅቱ ምላሽ በመስጠትና እውነተኛውን የሳይንስ ሀቅ በማሰራጨት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። 

የመረጃ ማጥራት (Fact Checking) ስራው የትራምፕን ንግግሮች ስህተት ከማሳየት ባለፈ፣ ግድቡ ለቀጣናው የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊ ትስስርና የአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ በጥልቀት ማብራራት ይኖርበታል። ለምሳሌ“ግድቡ ውሃ ይበላል” የሚለውን የተሳሳተ ስጋት፣ ውሃው ተርባይኖችን አሽከርክሮ ለታችኞቹ ሀገራት መፍሰሱን እንደሚቀጥልና በትነት የሚባክነውን የውሃ መጠን እንደሚቀንስ በግራፊክስና በቪዲዮዎች የታገዘ መረጃ ለዓለም ማሰራጨት ይገባል። ይህ ዘመቻ በባለሙያዎች የተደገፈና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የልማት ሉአላዊነት ከፖለቲካዊ ጫናዎች ለመከላከል የሚረዳ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ጋሻ ይሆናል። 

በመጨረሻም፣ ይህ የሕዝብ ግንኙነት ስራ ከመንግስት ተቋማት አልፎ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በንቃት የሚሳተፉበት ብሄራዊ ንቅናቄ ሊሆን ይገባል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በያለበት ዲፕሎማት በመሆን፣ በታላላቅ የዓለም ሚዲያዎችና የፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ትክክለኛውን መረጃ የማድረስ ኃላፊነት አለበት። የተቀናጀው የዲጂታል ዲፕሎማሲና የሕዝብ ግንኙነት ስራ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቁም በላይ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ናይል ወንዝ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ቀይሮ ለኢትዮጵያ የልማት መብት እውቅና እንዲሰጥ የሚያስገድድ የሀሳብ የበላይነትን ይፈጥራል። 

በአጠቃላይ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ኃይል ማመንጨት መጀመር፣ ኢትዮጵያን በናይል ተፋሰስ የድርድር ጠረጴዛ ላይ ከተከላካይነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነት አሸጋግሯታል። ፕሬዚዳንት ትራምፕም ሆኑ ሌሎች የውጭ ኃይላት የሚያሰራጯቸው “ግድቡ አሜሪካ በሰጠችው ገንዘብ ተገነባ” ወይም “ኢትዮጵያ የአባይ መሸጋገሪያ እንጂ መነሻ አይደለችም” የሚሉ የተሳሳቱ ትረካዎች፣ በመሬት ካለው ሳይንሳዊና ታሪካዊ ሀቅ ጋር ፍጹም የሚጋጩ ናቸው። ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ 85 በመቶ የውሃ ምንጭ መሆኗንና ግድቡም በዜጎቿ ላብና ጥሪት የተገነባ የኢኮኖሚ ነፃነት አርማ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተቀናጀ የሕዝብ ግንኙነትና በዲጂታል ዲፕሎማሲ ማስረዳት የወቅቱ ቀዳሚ ተግባር ነው። 

ለዚህ ዲፕሎማሲያዊ ድል ስኬታማነት ግን የውስጥ ግንባርን በአንድነት ማጠናከርና በሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ የማይበገር ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ወሳኝ ነው። በሀይል ፖለቲካ (power politics) የታጀቡ የሽምግልና ጥረቶች የሀገሪቱን የልማት መብት እንዳያደናቅፉ፣ በህግና በቴክኒክ ዘርፍ የተካኑ ባለሙያዎችን ያቀፈ ጠንካራ የድርድር ቡድን ማሰለፍና ቀይ መስመሮችን በግልጽ ማስመር ይገባል። ባጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን በማስከበር ረገድ የምትከተለው መንገድ በፍትሃዊነት፣ በሳይንሳዊ ሀቅና በህዝቦቿ ጽኑ አንድነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ማንኛውንም አይነት ውጫዊ ጫና በብቃት የመመከት አቅም አላት። 

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

“ባርነትና ባንድነት” ዕርቃናቸው ታዩ፤ የሻዕቢያ መሪዎችና መንጋችው ለምን ተነኩ ጩኸትና “ተኮፊልና” ላሉት ኢሳያስ ጥብቅና መቆም!

“ጄኖሳይድ የምትሉትን ክስ አቁሙ፣ ሴቶች ተደፈሩ የሚባል ነገር እንዳታነሱ”...

ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች እንዴት ተቋረጡ? እንዴትስ እንዲጀምሩ ተወሰነ?

አዲስ ሪፖርተር - ላለፉት አምስት ቀናት የተቋረጠው የአየር ትራንስፖርት...