አዲስ ሪፖርተር – “በዛሬና ምርጫው በሚደረግበት ቀን መካከል ሆነን ምርጫውን ማጨናገፍ ዋና ዓላማችን ነው” በማለት የሻዕቢያ ወኪል የሆኑት አቶ ነዓምን ንግግራቸውን ሲጀመሩ፣ የኢትዮጵያን አድን ወኪል የሆኑት ዶክተር ሚካኤል፣ “አካሄድ” በማለት ጣልቃ ገቡ። “በመግለብለብ መራመድ አያስፈልግም” ሲሉ ስብሰባው መርህ ላይ እንዲመሰረት አሳሰቡ። አለያ ከመቋቋሙ መበተኑ እንደሚፈጥን ገለጹ።
ይህ የሆነው ረቡዕ በተደረገው አቶ ነዓምን እና አቶ ልደቱ ያደራጁት የአመጽ አመቻችና አስተባባሪ ቴክኒክ ኮሚቴ ጥምረት ለመፍጠር ባለፈው እሁድ ያደረገውን ስበብሰባ ቀጣይ ውይይት ሲያካሂድ ነው።
በውይይቱ መጀመሪያ ላይ የሻዕቢያ ወኪል እንደሆኑ በባልደረባቸው የተመሰከረባቸው አቶ ነዓምን፣ ስብሰቡ በአመጽ ምርጫውን ለማኮላሸትና ቅቡል እንዳይሆን ለማድረግ ከመስራት ውጪ ሌላ ዓላማ እንደሌለው አቅጣጫ ሲሰጡ፣ ዶክተር ሚካኤል፣ ከኢትዮጵያን አድን አቋም የተያዘበት ጉዳይ መሆኑን አስታውቀው፣ ዝም ብሎ መገላበጥ እንደማያስፈልግ አስታወቁ።
“መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች አሉ” ካሉ በኋላ አንከር ላይ የለቀቀውን ማስታወቂያ በምሳሌነት አንስተው ተቃውሞ አሰሙ። ዶከተር ሚካኤል፣ አንከር ላይ በተለቀቀው የሰልፍ ጥሪ ማስታወቂያ በባለቤትነት የተጠቀሰው “የሰላማዊ ሰልፍና ትዕይንት አስተባባሪ” የሚለው ትክክል እንዳልሆነ አመለከቱ።
“ይህ ትክክል አይደለም፤ እኔ በግሌ ልደቱ የጀመረው ኢንሼቲቪ ደጋፊ የሆንኩ ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ” በማለት አካሄዱ ብዙም ሳይቆይ አሰልቺ እንደሚሆን አስታወቁ። አክለውም “ወደ አንድ የሚያያዝ መርህ ያለው የድርጅት ቅርጽ ካላመራን ነገሩ የሚሆነው ሽፍጥ ነው” በሚል የወከሉትን ማህበር አቋም አስታወቁ።
ዶክተር ሚካኤል ሌላው ያነሱት ጉዳይ፣ “የዲጂታል ስብሰባው የተሻለ ነው። የሰላማዊ ሰልፉ ጉዳይ ግን አያዋጣም፤ ሰው አይወጣልንም” ሲሉ የሁሉንም ስጋት ይፋ አደረጉ።
አብሮነትን ተሰናብተው የአቶ ነዓምንን ትብብር ንቅናቄን የተቀላቀሉት ሰብሳቢው አቶ ያሬድ፣ መረጃ በመቀያየር ለመጀመር ታስቦ እንጂ ሕብረት መፈጠሩ እንደማይቀር ሲናገሩ፣ አቶ ነዓምን ጣልቃ ገብተው፣ “ሰላማዊ ሰልፉ በብዙ ፋክተሮች አይሳካም” በማለት የዶክተር ሚካዔል ያቀረቡትን አሳብ እንደሚጋሩ ገልጸው “ይህ ህብረት፣ድርጅት፣ ቅንጀት ሳይሆን ፕሮጀክት ነው” በማለት ለማስረዳት ሞከሩ።
“እመነኝ ምንም የሚጋጭ ነገር የለም። የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው፤ እንጂ ሌላ ነገር የለውም” ሲሉ አቶ ነዓምን “ሸፍጥ ይመስላል” ለተባለው አስተያየት በኃላፊነት ምላሽ ሰጡ። ይህ ሁሉ ሲሆን አዲስ ሳምሰንግ 15 ስልክ ተገዝቶላቸው በቴክኒክ ምክንያት ሲታገሉ ቆይተው በሌላ ስልክ ስብሰባውን የተቀላቀሉት አቶ ልደቱ ያሉት ነገር አልነበረም። ከጥምረቱ በፊት በሁሉም ስብሰባ መሪ ሆነው የሚታዩት አቶ ልደቱ ከጥምረቱ በኋላ ስፍራውን ለአቶ ነዓምን እንዲለቁ የታዘዙ እንደሚመስላቸው የስብሰባው ተካፋዮች ተናግረዋል።
ከሁለት ሳንት በኋላ ይካሄዳል የተባለው የዲሲና የሎንዶን “አገር አንቀጥቅጥ” የተቃውሞ ሰልፍ፣ እንደማያዋጣ ከወር በፊትም ተጠቁሞ ነበር። በቅርቡ አሜሪካ ከሽብር ጋር አያይዛ ወደ አገር ቤት የላከችው አቶ ሰለሞን ጉዳይና የፋኖ ደረጃ ሶስት አሸባሪ ምድብ ውስጥ መካተት የፈጠረው ድንጋጤ እንኳን የአደባባይ ሰልፍ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ያለውን እንቅስቃሴ ገድቦታል።
ለዚህም ይመስላል አገር ቤት ሕዝብ እንዲያምጽ የሚያደራጁና የሚያስተባብሩ በሚል በስብሰባው ላይ አቶ ነዓምን በደፈናው ያነሷቸው ክፍሎች ላይ ኃላፊነቱ እንዲወድቅ ተደርጓል።
ስማቸውና ድርጅታቸው ሳይጠቀስ አመጽ እንዲነሳ ይቀሰቅሳሉ ለተባሉት አካላት የገንዘብና ዝርዝር ያልቀረበለት የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተመልክቷል።
ስብሰባው ላይ የነበሩት አቶ ጂረኛ የቀረበውን የመግባቢያ ሰነድ ጥሩ ጎን አንስተው “ዕቅዱን ሊተገብር የማይችል ደካማ ሰነድ ነውና ለጊዜው እንተወው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የቀድሞ የትህነግ ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ኢንጂነር ግደይ ቁጥር እየጠቀሱ “ፍጹም” የሚል አገላለጽ ትክክል አይደለም። ካሉ በኋላ እዲስተካከል ሲጠይቁ “በፍጹም መግባባት ብሎ ነገር በፖለቲካ የለም” ብለዋል።
የንግሊዘኛውን ሰነድ ወደ አማርኛ የመለሱት አቶ ያሬድ፣ ምላሽ ያሳጣቸውን ጉዳይ ያነሱት ኢንጂነር ሙሉጌታ በሰነዱ መግቢያ ላይ “የህ አምባገነንና ዘረኛ መንግስት ያላል። ይህ ትክክል አይደለም። ምን ማለት ነው ዘረኛ ማለት? የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ነው ዘረኛ የምንለው” በማለት ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል። አቶ ያሬድ “ለትርጉሙ ቃል አጥቼ ነው” ቢሉም በትርጉም ስህተተ በርካታ ልዩነት በመታየቱ “የእንግሊዘኛው ሰነድ ይቅር” እስከመባል መድረሱን አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች።
ቀደም ሲል የዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድል ያስገናል የተባለው ሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊ አልባ እንደሚሆን በታመነበት በዚህ ስብሰባ ዕቅዱ መሰረዙ በይፋ ባይነገርም፣ ሰበብ ተፈጥሮ እንደሚሰረዝ አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ የዋሽንግቶን የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ አቶ ነአምንን በስልክ ለማነጋገር ሞክሮ ስላካቸው ሰላማይነሳ አልተሳካም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






