አዲስ ሪፖርተር – ላለፉት ሁለት ወራት ከየአቅጣጫው ሲሰማ የነበረው ጩኸት መልስ አግኝቷል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሄሜቲ ከሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ – ሰሜን ጋር በመተባበር ስትራቴጂካዊ የምትባለዋን የድንበር ከተማ ኩርሙክን መዳፋቸው ውስጥ አስገብተዋል። ይህ ዜና ለኢትዮጵያ ተራ ዜና አይደለም። ዜናው ለኢትዮጵይና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለሚያሰሉ ከሰበርም በላይ ነው። ለምን?
ላለፉት ሁለት ወራት ጃዋር መሐመድ የኢትዮጵያን መንግስት በተቃውሞ ይከተክት ነበር። ኢትዮጵያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ትረዳለች በሚል ያበጥራት ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሳሪያ አጋጋዘ በሚል ይወነጅል ነበር። ከግብጽና ኤርትራ ጋር በግልጽ ተሰልፎ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ለሚላላከው የጄኔራል አልቡርሃን ኃይል በመወገን ከነሱ በላይ ይከራከርላቸው ነበር።
ጃዋር ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ጋር የሚሰሩና ግብጽ በሱዳን የምታደራጃቸው ግንባር ፈጥረው ኢትዮጵያን “ወራሪ” በማለት እየወነጀሉ ነበር። ውንጀላው ከሩቅ ብቻ ሳይሆን፣ በምርጫ የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ክርክርም ላይ በአደባባይ ኢትዮጵያ “ተንኳሽ” ተብላ የተረገመችበት ነበር። ለምን በዚህ ደረጃ “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ለሱዳን ወግነው አገራቸውን ቀጠቀጡ? ይህ እውነት የፖለቲካ ልዩነት ነው? ወይስ ሌላ ጉዳይና ተልዕኮ በማለት በከፍተኛ ደረጃ ጥያቄ ላነሱ ዛሬ መልሱ ግልጽ ሆኗል።
“ሮይተርስ ኢትዮጵያ በጄኔራል ሃመቲ የሚመራውን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ትረዳለች” በሚል የተቀነባበረ ዘመቻ ታጅቦ ኢትዮጵያ ላይ የተከፍተው ዘመቻ የቅጥፈትና የተዛባ መረጃ መሆኑን ገልጠን መጻፋችን የሚታወስ ነው። ሮይተርስ ይህን የቅጥፈት መረጃ ያዘጋጀው ኢትዮጵያ እምብርት ውስጥ ባሉ የሚዲያ ቢሮዎች በአንዱ እንደሆነ ይፋ ማድረጋችንም አይዘነጋም። እስኪ ይህ ከሩቅ እስከ መካከል ተደራጅተው ሲያግለበልቡት የከረሙትን ጉዳይ በየፈርጁ ከፋፍለን እኘው
የኩርሙክ ከተማ ለምን ተጮኸላት?
/አባይ የአባይ ግድብ ስም ስለሆነ ዝግጅት ክፍላችን ህዳሴ ግድብ ብሎ አይጠራውም/ አሁን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የተቆጣጠሯት የኩርሙክ ከተማ ለአባይ ግድብ በጣም ቅርብ ናት። ከድንበር በጥቂት አስር ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች። ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ያለባት ቦታ ናት። ማንኛውም በግድቡ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሚሞክር ኃይል ይህን አካባቢ እንደ መነሻ ይጠቀማል። ስለዚህም የአገር መከላከያ በዚህ አቅጣጫ በምድርና በሰማይ የሚያደርገው ክትትል ጥብቅ እንደሆነ ይታወቃል።
በኩርሙክ እና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ መካከል ያለው የድንበር ጥበቃ እና የፀጥታ ሁኔታ እጅግ ጥብቅና ስልታዊ (Strategic) በሆነ መልኩ ነው የሚመራው። በተለይም ግድቡ ለኢትዮጵያ ካለው የህልውና ፋይዳ አንጻር፣ ይህ ቀጠና “ልዩ የፀጥታ ቀጠና” ተብሎ የተወሰደ ነው። እንግዲህ ይህን ግልጽ ጉዳይ ነው እንደ ምናምንቴ በመቁጠር ኢትዮጵያን ወራሪ፣ ተንኳሽና ጣልቃ ገብ በማለት የራሷ ልጆች በክህደት የሚወነጅሏት። ውንጀላው ለምን ተፈለገ ቢባል፣ የከተማዋ በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እጅ ብትወድቅ የሚሆነው ስለሚገባቸው፣ የተቀጠሩበት ዓላማ ስለሚከሽፍ፣ ያሰቡት የራሳቸውም ዕቅድ እንከን ስለሚገጥመው እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የኩርሙክን ከተማ መቆጣጠራቸው ለኢትዮጵያ ያላቸው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው። ኩርሙክ በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ውስጥ የምትገኝና ከአሶሳ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር የምትዋሰን ስትራቴጂካዊ ከተማ በመሆኗ፣ ይህቺ ከተማ በኢትዮጵያ ወዳጅ በሆኑ ኃይሎች እጅ መውደቋ በቤኒሻንጉል በኩል የሚገባውን የተቃዋሚ ኃይሎች እንቅስቃሴ ለማገድ ይረዳል። በተለይም የአባይን ግድብ ደህንነት አስተማማኝ ከማድረግ አንጻር ጠቀሜታው ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። እናም ኩምሩክ ልትያዝ ትችላለች በሚል ስጋት ነበር ጩኸቱ።
ግብጽ ሱዳን ላይ አደራጅታና አስታጥቃ በዚህ አቅጣጫ የላከቻቸው፣ እየላከቻቸው ያሉትና ወደፊትም የምትልካቸው ታጣቂዎች፣ በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት በዚህ በር በመሆኑ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ድል ለግብጽና ግብጽ ለምታሰማራቸው ኃይሎች በሙሉ መልካም ዜና አይሆንም። ጃዋር ይህን አስልቶ ነበር ሲጮህ የነበረው። ሌሎችም ክራባት ለብሰው በቴሊቪዥን ህዝብ እያየና እየሰማ አገራቸውን በወራሪነት ለመወንጀል ያስደፈራቸው ጉዳይ ሚስጢር እዚህ ላይ ፍንትው ብሎ ይታያል።
በብሉ ሱዳን ይዞታቸውን እያሰፋ ያለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች፣ ከሰባቱ የብሉ ሱዳን የዞን ከተሞች ውስጥ አምስቱን ነጥቋል። ዋና ከተማዋ አድ-ዳማዚን እና ሮሴይረስ ብቻ ናቸው አልቡርሃን የሚመሩት ኃይል የሚቆጣጠረው። የተቀሩት አምስቱ ኩርሙክ፣ባው፣ገይሳን፣ አል-ታዳሞን እና ዋድ አል-ማሂ በሱዳን ፈጣን ኃይሎችና በሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ – ሰሜን እጅ መውደቃቸው ቀጣዩን የአካባቢው አሰላለፍ እንደሚቀይረው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምን ልዩ ጥቅም ታገናለች
ኩርሙክ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ጋር በቀጥታ የምትገናኝ የድንበር ከተማ ናት። በጄኔራል ሃምቲ የሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ይህንን አካባቢ መቆጣጠራቸው ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም መካከል ዋናውና ግንባር ቀደሙ ጉዳይ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ “ጸረ-ሰላም ኃይሎች” ለመቆጣጠር አመቺ እድል መፈጠሩ ነው።
የሱዳን መደበኛ ጦር ከግብፅ ጋር ያለውን ጥብቅ ወታደራዊ ግንኙነት ተከትሎ፣ በድንበር በኩል በህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን ማናቸውም ስጋት ከማቃለል አንጻር ሰፊ ትርጉም አለው።
በሲዳን ፈጣን ኃይሎችና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ጤናማ ግንኙነት ስላለ፣ የደህንነት ተቋማት መካከል ያለው መስተጋብር ይጠነክራል። በድንበር አካባቢ ስለሚንቀሳቀሱ “ጸረ-ሰላም ኃይሎች” ፈጣን መረጃ ለመለዋወጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ስትከፍለው የነበረውን ዋጋ ያቀልላታል። ማንም ተንደርድሮ በዚያ በኩል አይፈነጭባትም።
በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ (በደርግ ዘመን)፣ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሮ ነበር። ብዚያን ወቅት ኩርሙክ ለተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎች እንደ መሸጋገሪያ ወይም መደበቂያ ሆና አገልግላለች። በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በሱዳን በኩል ድጋፍ ሲያገኙ ይህን መስመር ይጠቀሙ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በአሁኑ ወቅትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አቅራቢያ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የኢትዮጵያ ታጣቂ ቡድኖች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን እንደሚገቡና በኩርሙክ በኩል ትጥቅና ሎጂስቲክ እንደሚያሸጋግሩ፣ መመሸጊያ እንደሚሆናቸውና ከዚያ እየተነሱ ጥቃት እንደሚያደርሱ ይታወቃል። በዚህ መነሻ የኩምሩክ ኢትዮጵያ ወዳጅ እጅ መውደቅ ጉዳዩ ለገባቸው እልልታ፣ አሳባቸው ለከሸፈባቸው ሃዘን ሊሆን ችሏል።
በነገራችን ላይ የሱዳን መንግስት ተቃዋሚዎች (ለምሳሌ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ – SPLM) በኢትዮጵያ በኩል ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩት በኩርሙክ በኩል ነበር ማስታወስ የስፍራዋን ቁልፍነት ለመረዳት እንደሚረዳ እዚህ ላይ ጠቆም አድርጎ ማለፉ አግባብ ይሆናል።
ይህ ሲባል ግን ምንም ስጋት የለም ማለት እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ጥቂት አይደሉም። ምንም እንኳን የRSF በድንበር አካባቢ መገኘት ለኢትዮጵያ መንግስት በአጭር ጊዜ እንደ ጥቅም ቢታይም፣ የስደተኞች መብዛት፣ በሱዳን ያለው ትርምስ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጋጋዝ በር ሊከፍት ስለሚችል፣ ይህንኑ አጋጣሚ ተጠቅመው እዛና እዚህ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ትጥቅ ሊያገኙ የሚችልበት አግባብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንደሚያሻ የሚመክሩ አሉ።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አሁን ላይ አብዛኛውን የካርቱም አካባቢ፣ የዳርፉር ግዛቶችን እና የግብርና ማዕከል የሆነችውን የገዝራ ግዛትን ጨምሮ ወደ ምስራቅ (ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር) እየተጠጋ ነው። ይህ ለኤርትራ ስጋት ሲሆን በሱዳን በኩል መውጪያ ለማግኘት አልሞ ለሚንቀሳቀሰው የትግራይ ነጻ አውጪ ሰራዊት ህልም እንቅፋት ነው። እዚህ ላይ የአካባቢውን ጂኦፖለቲካ የሚተነትኑ ነገሮችን ከብሄራዊ ጥቅም አንጻር ማየት አግባብ እንደሆነ የሚናገሩት።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የሰሞኑ ድልና ቀጣይ አቅጣጫ የኤርትራ መንግሥት በሱዳን ግጭት ውስጥ ካለው አቋምና ከቀጣናዊ ስትራቴጂው አንፃር የሚከተሉት ጉዳቶች ሊገጥሙት እንደሚችል ይሰማል።
ኤርትራ ከሱዳን መደበኛ ጦር መሪ ጀነራል አል-ቡርሃን ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወደ ምስራቅ ሱዳንና ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየተቃረበ መምጣቱ፣ የኤርትራ ወዳጅ የሆነው የሱዳን መደበኛ ጦር አቅም እንዲሟሟ ያደርጋል። ይህ ሲሆን ኤርትራ በሱዳን ያላትን እጅ ይቆራርጠዋል።
ኤርትራ በምስራቅ ሱዳን (ካሳላ እና ገዳሪፍ አካባቢ) ሰፊ ተፅዕኖ እንዳላት ይታወቃል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እንደ ኩርሙክ ያሉ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን መያዛቸው፣ ቀስ በቀስ ወደ ምስራቅ ሱዳን በመጠጋት ለዓመታት የኤርትራ መንግስት የደህንነት ቀጠና (Security Buffer) ብሎ ቆንጥጦ የያዘውን መሰረቱን እንዲያጣ ይገደዳል። እንዲያውም የመኖርና አመኖር ትግል ውስጥ ሊገባ ይችላል። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ እፎይታ ታገኛለች።
ኤርትራ በሱዳን በኩል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችን ትከታተላለች። ድንበሩ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቅ ለኤርትራ ተቃዋሚዎች እድል ይፈጥርላቸዋል። አካባቢውን ተቆጣጥራ በነበረችበት ዓመታት ያልነበረው ስጋት ይህን ለውጥ ተከትሎ መናጋቱ አይቀሬ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ይህ እውን ከሆነ የኤርትራ መንግስት እንደ መንግስት ለማሰብ ይገደዳል። ይህ ለኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ ላይ ጫና ለማሳደር ይረዳዋል።
በተመሳሳይ ለትግራይ ኃይሎች የኩርሙክ በየሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መያዝ ከጂኦ-ፖለቲካዊ አሰላለፍ አኳያ አስደንጋጭ መርዶ እንደሆነም እየተመለከተ ነው።
ትግራይ ኃይሎች ከሱዳን መደበኛ ጦር ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው ይታመናል። የሱዳን መደበኛ ኃይል የድንበር አካባቢዎችን ሲቆጣጠር ለትግራይ ኃይሎች እንደ አማራጭ የመገናኛ ወይም የድጋፍ መስመር ሊያገለግል ይችል ነበር። አሁን ግን መስመሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የቀረበ ግንኙነት ባላቸው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እጅ መውደቁ ይህ በር እንዲዘጋ ያደርገዋል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለው የወታደራዊና የደህንነት ትብብር ጠንካራ በመሆኑ፣ በትግራይና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠበቅ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ በትግራይ ኃይሎች ላይ የሚፈሩትን የከበባ ስሜት ያሰፋዋል።
የሱዳን መደበኛ ጦር በኢትዮጵያ ላይ የሚይዘው ጠንከር ያለ አቋም ለትግራይ ኃይሎች እንደ ዲፕሎማሲያዊ መጠቀሚያ ሲያገለግል መኖሩ፣ ይህም ከበረሃ ትግሉ ጀምሮ አሁን ላይ እስከሚሰማው ጽምዶ ድረስ የዘለቀ መሆኑ፣ ወታደር በመስጠት የደምና የአጥንት እስከ መክፈል ያደረሰ ወዳጅነት እንደሚፈርስ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ወዳጅ የሆነው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ድንበሩን መቆጣጠራቸው የትግራይን የድርድር አቅም እንደሚያዳክም የሚናገሩ፣ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ድል በዚሁ ከቀጠለ፣ ከጄኔራል አልቡርሃን አሸባሪ ተብሎ መፈረጅ ጋር ተዳምሮ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አንድ ክፋይ የሆነው ኃይል ፊቱን ወደ አገር ውስጥ መፍትሄዎች እንዲያዞር ሊገፋው እንደሚችል ባለኡያዎች ቅድመ ትንበያ ይሰታሉ።
ውድ ተከታታዮቻችን፣ ሰሞኑን የፋኖ ኃይሎችም በቤኒሻንጉል በኩል መውጪያ ለማግኘት ሲነቀሳቀሱ እንደነበር ተሰምቶ ነበር። ኦነግ ሸኔም በዚያ አቅጣጫ መውጪያና መግቢያው እንደሆነ ይታወቃል። እናም የኩምሩክ በኢትዮጵያ ወዳጅ ኃይሎች እጅ መውደቅ ከብሄራዊ ጥቅም አንጻር ለኢትዮጵያ ትልቅ ዜና ነው። ጫጫታውም፣ ተቃውሞውም፣ በቅብብል የነበረው ክስም ከላይ የቀረበውን ባሰሉ ኃይሎች አማካይነት የሆነ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። ሁሌም እንደምንለው የፖለቲካ ልዩነትና የፓርቲ ፖለቲካ በብሄራዊ ጥቅም አይለካም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






