የዓለም የነዳጅ ቀውስ እና የኢትዮጵያ ፈተና [ታሪካዊ አርበኝነት ጥሪ] ወቅቱን ለሚመረምሩ ሁሉ

Date:

ኢትዮጵያን እንወዳለን፣ ኢትዮጵያ አገሬ ናት፣ ኢትዮጵያ እናቴ ናት፣ ሌላ እናት የለኝም የምትሉ ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የምትሉ የመንግስት አካላት፣ ተቀናቃኝ ድርጅቶች፣ በየትኛውም የፖለቲካ አቋም የተሰላፋችሁ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ኃይማኖተኞች፣ ወዘተ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያኖች ሚዲያ ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ ታላላቆች፣ ታናናሾች፣ ይህ ለገራችን ወደንና ፈቅደን ታሪካዊ አርበኛ የምንሆንበት ወቅት ነው። ለምን? ጊዜውን እንመርመር!!

አዲስ ሪፓርተር- የኢራንና የአሜሪካ ጦርነት አራተኛ ቀኑን ሲያስቆጥር፣ የዓለም የነዳጅ ዝውውር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተገትቷል። በየቀኑ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ድፍድፍ ነዳጅ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ተዘግቶ መቆየቱ፣ የዓለምን አቅርቦት ከ15% በላይ እንዲቀንስ አድርጎታል። የነዳጅ ፍላጎት የማይቀንስ (Inelastic) በመሆኑ፣ ይህ አይነቱ ከፍተኛ መስተጓጎል የነዳጅ ዋጋን ሰማይ እንዲነካ ከማድረጉም ባለፈ፣ መላውን ዓለም ወደ ከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እየገፋው ይገኛል። በመሆኑም ይህን የዓለም የነዳጅ ቀውስ ለማለፍ ኢትዮጵያዊያን ታሪካዊ የአርበኝነት ታሪክ ሊስፉ ይገባል።

ለምን ይህ አልን? ለምን ሲባል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአርበኝነት ጥሪ አቀረብን? ምክንያቱም የኢነርጂ ቀውሱ በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ የተገደበ ስለማይሆን ነው። ቬንዙዌላ ወደ ገበያው ለመመለስ ገና ወራትን ትፈጃለች፣ በሌላ በኩል ዩክሬን ትላንት ምሽት በሩሲያ የነዳጅ መውጫ ወደብ “ኖቮሮሲስክ” ላይ በመቶዎች በሚቆጠሩ ድሮኖች ጥቃት አድርሳለች። ዩክሬን ይህን ጥቃት የፈጸመችው አሜሪካ “የነዳጅ ዋጋ እንዳይጨምር ጥቃት አታድርጉ” የሚለውን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ነው። ይህም የዓለምን የነዳጅ አቅርቦት ውገቡን ቆርጦታል።

በዚህ እንደሰንሰለት የተያያዘ ቀውስ ሳቢያ ዓለምን የፈተናት የነዳጅ ቀውስ ቀውስ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የሚያስከትለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያ ነዳጅን ከውጭ የምታስገባ ሀገር በመሆኗ፣ የዋጋው መጨመር በቀጥታ የኑሮ ውድነትን ያባብሰዋል። የጭነት መኪናዎች ነዳጅ ሲወደድባቸው የእህልና የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ይጨምራል፤ የፋብሪካዎች ምርት ይቀንሳል፤ ይህም በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ከባድ ጫና ያሳርፋል። በዚህ ፈታኝ ወቅት፣ ሀገርን ከኢኮኖሚ ውድቀት ለመታደግ የመንግስት ጥረት ብቻ በቂ ስላልሆነ፣ የዜጎች የነቃ ተሳትፎና የጸና አርበኝነት ወሳኝ የሚሆንበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ከዋጋ መናሩ በተጨማሪ የባህር በር የለንምና በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ እጥረትም ሊያጋጥመን ስለሚችል አርበኝነታችን መልከ ብዙ ስለሚሆን ከወዲሁ መዘጋጀት አለብን። ለጥበቃ፣ ለተማሪዎች፣ ለሚስትና ለራስ ተሽከርካሪ ደራርባችሁ የምትጠቀሙ ባለስልጣናትና እዛው ዙሪያ ያላችሁትንም ይህ ጥሪ ይመለከታልና ሁሉንም በወጉ አድርጉ!!

ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ መሰል ቀውሶችን በድል ለመሻገር የዜጎች የሞራል ልዕልና ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1973 በነበረው የዐረብ-እስራኤል ጦርነት ወቅት፣ የአረብ ሀገራት በአሜሪካና በእስራኤል ደጋፊዎች ላይ የነዳጅ ማዕቀብ (Embargo) ጥለው ነበር። በወቅቱ የነዳጅ ዋጋ በአራት እጥፍ አድጎ አሜሪካውያን ለከፋ ችግር ተጋልጠው ነበር። (ለጃንሆይ መወደቅም ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ልብ ይሏል) ሆኖም አሜሪካውያን ይህንን የኢኮኖሚ ጦርነት የተቋቋሙት በአርበኝነት ስሜት ነበር። ዜጎች ነዳጅን በመቆጠብ፣ አላስፈላጊ ጉዞዎችን በመቀነስና የመንግስትን የቁጠባ መመሪያዎች በመተግበር ሀገራቸው ከጥገኛነት እንድትወጣና ቀውሱን እንድትቋቋም ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

ይህ የአሜሪካውያን ታሪካዊ ተሞክሮ ዛሬ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትምህርት ነው። አርበኝነት በጦር ሜዳ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገር በሰው ሰራሽ ተፅዕኖ በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ስትገባም ጥረት ማድረግ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ዜጎች ነዳጅንና የሃይል አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም፣ ብክነትን በመቀነስና በገበያ ላይ የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪዎችንና ህገ-ወጥ ደላሎችን በመታገል ከመንግስት ጎን መቆም አለባቸው። ይህ አይነቱ “የኢኮኖሚ አርበኝነት” ሀገራዊ ህልውናን ለማስጠበቅ የሚደረግ የትግል አካል ነው። ዜግነት ማለትም ይህ ነው።

መንግስት ይህንን ቀውስ ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸውን የፖሊሲ ማስተካከያዎችና የድጋፍ እርምጃዎች ዜጎች በታጋሽነት በመፈፀም ሊደግፉ ይገባል። በችግር ጊዜ የሚታይ መደጋገፍ፣ ያለንን በቁጠባ መጠቀምና ለሀገር ሰላም ቅድሚያ መስጠት ከዓድዋና ከሌሎች ታሪካዊ ድሎች የምንወርሰው ኢትዮጵያዊ እሴት ነው። አሁን ያለው የነዳጅ እጥረትና የዋጋ መናር ጊዜያዊ ፈተና ቢሆንም፣ ይህንን ፈተና በአንድነት የምናልፍበት መንገድ ግን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው የታሪክ ድል ይሆናል። ይህ ታሪካዊ ድል ልክ አሜሪካኖችን በምሳሌ እንዳነሳበው፣ ይህን ትውልድ ሌሎች በበጎ የሚያነሱት ገድሉ ሆኖም ይመዘገብለታል።

የዩክሬንና የሩሲያ ግጭት እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ዓለምን እያወከ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ጥንካሬዋና በዜጎቿ ጽናት መቆም አለባት። የነዳጅ ጫናው የሚያመጣውን የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም የአምራችነት መንፈስን ማሳደግና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማበረታታት የግድ ይላል። እያንዳንዱ ዜጋ በቤቱና በስራ ቦታው የሚያሳየው የቁጠባ ስነ-ልቦና፣ ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን ውድ የውጭ ምንዛሬ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

በዚህ የጀግነነት መንፈስ ከመነሳት ይልቅ አጋጣሚውን በመጠቀም መስገብገብ፣ ማግበስብሰና የምስኪኑን ሕዝብ አጥንት መጋጥ ከቶውንም ሞራላዊ አይደለምና በዚህ ተግባር የተካናቹህ ቀልብ ግዙ። ከዚህ ቀስ ለማትረፍ የተቧደናችሁ የመንግስት አካላትም ሆናችሁ፣ የመንግስትን ኃላፊዎች ተጠግታችሁ የምትቦጠብጡ ጊዜው አይፈቅድምና እረፉ። ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በቅጥረኞች ተከባ ባለችበት በዚህ ወቅት ከአርበኝነት ውጪ ሌላ አማራጭ የለምና ለአገርም፣ ለምሲኪኑም ሕዝብ ማሰብን አስቀድሙ።

ይህ የኢነርጂ አቅርቦት መስተጓጎል በዓለም ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ላይም ማረፉ አይቀሬ ነው። ሆኖም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን፣ ዛሬም በኢኮኖሚው ግንባር የአርበኝነት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ጊዜ ነው። ከመንግስት ጋር በመቀናጀት፣ ችግሮችን በጋራ በመጋራትና ለሀገር ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት፣ ይህንን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ በድል እንደምንሻገረው ጥርጥር የለውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጽናትና አርበኝነት ሁልጊዜም ከመከራ በላይ መሆኑን ለዓለም የምናሳይበት ሌላው የታሪክ አጋጣሚ አሁን ነው። በዚህ ወርቃማ ታሪክ መመዝገብና፣ የዚህ ወርቃማ ታሪክ አካል እንሁን። የዓለም የነዳጅ ቀውስ እና የኢትዮጵያ ፈተና ጠንካራ ሊሆን ስለሚችል ለመላው ኢትዮጵያዊያን ማንንም ከማንም ሳንለይ [ታሪካዊ አርበኝነት ጥሪ] እናቀርባለን።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የክፉ ጊዜ ወዳጅነት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤምሬትስ ጉብኝት አንድምታዎች  

      የኢትዮጵያን ቀጠናዊ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚከፈለው መስዋዕትነት ታሪካዊ ዋጋ...

ማርኮ ሮቢዮ ከአብይ ጋር መከሩ፤ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በቀይ ባህርና በአፍሪቃ ቀንድ አሰላለፋቸው ይፋ እየሆነ ነው

አዲስ ሪፖርተር - አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የጠብመንጃ ግብግብ...

How Ethiopia Anchors the Horn Against Sudan’s Ongoing War

Civil wars are often explained as the inevitable eruption...