አዲስ ሪፖርተር – በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚያዊ ፎረም ስብሰባ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመግዛት ወይም ለመቆጣጠር የወሰኑበትን አግባብ አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር ላይ ከወትሮው ለስለስ ብለው ግሪንላንድን በኃይል እንደማይወስዱ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ግዛቷን አሜሪካ ብቻ እንደምትጠብቃት በመግለፅ ወዲያውኑ ድርድር እንዲጀመሩ ጠይቀዋል። ፕረዜዳንት ፑቲን የግሪን ላንድ ዋጋ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኗን ለሮይተርስ መናገራቸው ደግሞ ነገሩን አክሮታል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ፑቲን የግሪንላንድን ጉዳይ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዴንማርክ ሊፈቱት ይገባል ብለዋል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዴንማርክ ክፍል የሆነችው ራስ ገዟን ደሴት ለመቆጣጠር ያላቸውን ፍላጎት በአፅንዖት መግለፃቸው በአሜሪካና በአውሮፓ መካከል ክፍተት መፍጠሩና የተለያየ አቋም ሲያስተናግድ ቆይቷል።
የግሪንላንድን ጉዳይ በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ሐሳባቸውን የገለፁት ቭላድሚር ፑቲን፤ ሀገራቸው የትራምፕን ዕቅድ እንደማትቃወም ጠቁመዋል። “በግሪንላንድ የሚፈፀም ማንኛውም ጉዳይ የኛ ጭንቀት አይደለም” ሲሉ ፑቲን በሩሲያ የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። “ዴንማርክ ግሪንላንድን እንደ ቅኝ ግዛት ነበር የምትቆጥራት። ጭካኔ የተሞላበት ነበር ማለትም ይቻላል” ሲሉ አክለዋል። ዴንማርክ ለዩክሬን የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ካደረጉ ሀገራት መካከል መሆኗ ሩሲያን ማስቆጣቱን ተናግረዋል። በአውሮፓው 1867 ዓ.ም ሩሲያ አላስካን ለአሜሪካ በ7.2 ሚሊዮን ዶላር መሸጧን ያወሱት ፑቲን፤ ግሪንላንድ ብትሸጥ ዋጋዋ 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ቢሆን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ፑቲን ለምን ደገፉ የሚለውን ጉዳይ በዩክሬን ካለው ሁኔታና የሩሲያ ፋልጎት ጋር ያያዙ በርከተዋል።
- ግሪንላንድ ለምን ይህን ያህል አስፈላጊ ሆነች?
በአርክቲክ በረዶ መቅለጥ ምክንያት አዲስ የባህር መንገዶች እየተከፈቱ መሆናቸው ፣ ለቴክኖሎጂና አረንጓዴ ኢነርጂ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ሊቲየምና ኒዮዲሚየም ያሉ ማዕድናት በብዛት መገኘታቸው ከምክኒያቶቹ መካከል ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ትራምፕ “ጎልደን ዶም” የሚለውን ሚሳይል መከላከያ ሲስተም ለመገንባት ይህን ደሴት ይፈልጋሉ።
ጉዳዩን ተከትሎ ቀጣይ የሚከሰተው ነገር በአንጻራዊነት ግልጽ ይመስላል። የአውሮፓ መንግስታት የግሪንላንድን ደህንነትና ስትራቴጂያዊ አስተዳደር በዴንማርክ መንግስት ሉዓላዊነት ስር እንድትቆይ በማድረግ ነገር ግን በተግባር ለአሜሪካ ተጠቃሚነት በሚያደላ መልኩ እንዲጠቀምበት ሊያሳምኑት ይሞክራሉ።
በእንደዚህ አይነት ስምምነት ውስጥ አሜሪካ በደሴቷ ሙሉና ረጅም ጊዜ የሚቆይ መብት እንድታገኝ ያስችላታል። በዚህም አሜሪካን ኪራይ ሳትከፍል መጠቀም ፣ የማዕድን ሀብቶችን ያለ ገደብ ማውጣት እንዲሁም ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ፣ አየር ማረፊያዎችን ፣ ሚሳይል መጫኛ ቦታዎችን እና ሌሎች ስትራቴጂያዊ መገልገያዎችን ከግዛቷ ማግኘት እንድትችል ያደርጋታል።
የፕሬዝዳንቱ ዓላማ ግን ይሄ ብቻ አይደለም። እሳቸው ደሴቷን በአሜሪካ ባንዲራ ቀለም በካርታ ላይ ማስቀመጥ ይፈልጋሉ። ከዚህ ቀደም ካናዳ እና ቬንዙዌላን ያካተተ የአሜሪካ ካርታ እንዲሁም እሳቸው በግሪንላንድ መሬት ላይ የአሜሪካን ባንዲራ ሲተክሉ የሚያሳዩ AI generated ምስሎችን በይፋዊ ማህበራዊ ደህረ ገፃቸው እንዳሰፈሩ ይታወሳል።
ራሳቸውን ከታሪካዊ መሪዎች ተርታ ለማስቀመጥ እየጣሩ ያሉት ፕሬዝዳንቱ እንደ ሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግዛታቸውን ለማስፋፋት የሚያደርጉት ጥረት ነው ተብሎ ይታሰባል። ሆኖም ሩሲያ በልዩ ወታደራዊ ተግባሯ ለዘመናት የራሷ ግዛት የነበሩ መሬቶችን ነበር የመለሰችው። በአንፃሩ ግሪንላንድ ግን ለዘመናት የአሜሪካ መሪዎች ካቀረቡት የግዢ ጥያቄ ባሻገር ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ኖሯትም ሆነ የአሜሪካ ግዛት ሆና አታውቅም።
ምንም እንኳን ብዙዎች ይህ እርምጃ የሚያመጣውን የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ትርጉም በተደጋጋሚ እየገመቱ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ግን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በግልጽ የተናገረው ፍላጎት ብቻ አይደለም።
የብዙዎች አስተያየት የተመረኮዘው እንደዚህ ያለ የግዛት ግዢ የአሜሪካን መሬት ስፋት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስፋፋው እንዲሁም የአሜሪካ ኃይልን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት እንደሚቀይረው ነው። ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ጉዳዩ ከዚህም ባሻገር በጊዜ የተገደበም ጭምር ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ መንግስት መሪነት የቀራቸው ጊዜ ውስን ስለሆነ፣ የማይናወጥና በታሪክ ውስጥ የሚቀመጥ ቅርስ ወይም legacy ለመገንባት ግልጽ ፍላጎት አላቸው። ስማቸው በታሪክ መዛግብት ውስጥ በጥብቅ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ውሳኔ ለማስቀመጥ ሌት ተቀን እንደሚታትሩ ያሳያል። ዋናው ጥያቄ የሚሆነው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ግብ ለማሳካት ምን ያህል ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው? የሚለው ነው።
ኔቶን ማዳከም ወይም ሙሉ በሙሉ መፍረስ እና ከደካማ ሀገራት ውስጥ የተገለሉ ፖለቲካዊ ሰዎችን በኃይል መግዛት ወይም መጥለፍ በእጅጉ የበለጠ ከባድና ተዘዋዋሪ ውጤት ያለው እርምጃ ነው። በተጨማሪም እንዲህ ያለ ዕቅድ በፖለቲካዊ ፣ በህጋዊና በተቋማዊ ደረጃ አስፈላጊውን ድጋፍና ፍቃድ ማግኘት ይችል እንደሆነ አሁንም ግልጽ አይደለም።
ኔቶን ማፍረስ ማለት የአውሮፓ ደህንነትን መሠረት ማናጋት፣ የአሜሪካን ዓለም አቀፍ አጋርነት ማፍረስ፣ እና በአርክቲክ ክልል ላይ ሩሲያና ቻይና ተጽእኖ ለማጠናከር የሚያገለግል መንገድ ማመቻቸት ማለት ነው።
ኔቶ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መሠረት ነው፣ እና መፍረሱ የአውሮፓ አጋሮችን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ኮንግረስን፣ የመከላከያ ሚኒስቴርን፣ የፔንታጎንን፣ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተቃውሞ ሊያስነሳ ይችላል። በተጨማሪም ግሪንላንድን በኃይል ወይም በግዳጅ ማግኘት ዓለም አቀፍ ህግን ሊጥስ፣ የዴንማርክ ሉዓላዊነትን ሊያፈርስ፣ እና በአርክቲክ ክልል ላይ አዲስ የጦርነት አደጋ ሊፈጥር ይችላል።
ትራምፕ ይህን ለማሳካት የሚያስፈልገውን ዋጋ መክፈል ይችላሉ ወይ? ይህ የእሱ የታሪክ ‘legacy’ ህልም እውን ሊሆን ይችላል ወይስ በፖለቲካዊና በዲፕሎማሲያዊ ተቃውሞ ይቆማል?
በዳቮስ 2026 ውይይቶች የተጀመረው ድርድር አሁንም እየቀጠለ ነው፣ ነገር ግን የኔቶ አባላት፣ የአውሮፓ መሪዎች፣ እና የአሜሪካ ውስጣዊ ፖለቲካ ሁሉ ተጽእኖ ይኖራቸዋል። ውጤቱ ምን ይሆናል? ጊዜው ይነግረናል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






