- አዲስ ሪፖርተር – የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በክልሉ ውስጥ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደ ጎን በመተው ሕዝብን ዳግም ወደ ጦርነት የሚከቱ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን በጽኑ ኮነኑ።
አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ፣ በተለይ ከሰሞኑ በጠለምት በኩል የተቀሰቀሰው ግጭት የአመራር ብቃት ማነስና ለሥልጣን የመቆያ ስልት መሆኑን በዝርዝር አብራርተዋል።
አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፣ የፕሪቶሪያውን ውል ለማስፈጸም እንደ ፖሊሲ ተይዘው የነበሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና ከፌደራል መንግስት ጋር የተደረጉ መድረኮች ወደ ተግባር እንዳይቀየሩ በግለሰቦች እና በቡድኖች የግል ጥቅም ተነሳሽነት ምክንያት ተከልክለዋል።
እነዚህ አካላት ግዛታዊ አንድነትን በማረጋገጥ እና ተፈናቃዮችን በመመለስ ስም ሕዝብን ዳግም ወደ ጦርነት ለመክተት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ ጌታቸው፤ ከሰሞኑ በጠለምት አካባቢ ስለተቀሰቀሰው ግጭት ሲያብራሩ፣አሁንም የወጣቱን ሕይወት እንደ ዋነኛ የጦር መሣሪያ መጠቀም በመቀጠል ግረኛውን ጦር ያለ በቂ የከባድ መሣሪያ ሽፋን ለሞት እየዳረጉት ነው ብለዋል።
ይህ “አለኹ” ለማለት ብቻ የሚደረግና ትርጉም የለሽ መስዋእትነት የሚጠይቅ እንቅስቃሴ በትግራይ መሬት ላይ ዳግም ጦርነትን የመጋበዝ ያህል መሆኑን ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮችን በዘላቂ ሰላም እና በመተማመን ላይ ተመስርቶ መመለስ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እና የዓለም አቀፍ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑ እየታወቀ፣ ሰላማዊ አማራጮችን በማጥበብ ትግራይን ዳግም የጦር ሜዳ ለማድረግ የሚደረገው ግፊት በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስበዋል።
በመጨረሻም ተጋዳላዩ ለርካሽ የፖለቲካ ሸቀጥ እንዳይውል እና የፕሪቶሪያው ስምምነት በሰላማዊ መንገድ እንዲተገበር ተቃውሞውን እንዲያሰማ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የፖለቲካ እና የወታደራዊ ሂደቱን ወጣቶችን መሰረት ያደረገውንና ወደ ሙሉ ጦርነት ሊያመራ የሚችለውን እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ በማሳሰብ፣ “ራሳቸው የለኮሱትን እሳት ራሳቸው ይሙቁት!” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






