በዚሁ የትህነግ ደብዳቤ ጉዳይ ከእንግዲህ ቀልድ የለም። ትጥቁን ባስቸኳይ ፈቶ፣ እንደማንኛውም ክልል ወደ ሰላማዊ መንገድ የማይመጣ ከሆነ በጀመረው የኃይል አማራጭ ከትግራይ ሕዝብ ጋርና በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ይፈለግለታል” በማለት አንድ ባለስልጣን በምሬት ተናግረዋል። የትግራይ ሰላም ኃይሎች በበኩላቸው ነገሩ ሊያበቃ እንደሚችል ወስነዋል። ስለዚህ ትህነግ ሲፈልግ እሳት እየለኮሰ፣ ጠመንጃ ወልዋይ እያደራጀ፣ ሻዕቢያን እየጎተተ፣ ሳይሆን ሲቀር ውይይት እያለ በትግራይ ሕዝብ የሚቀልደበት ዘመን ሊያከትም ….
አዲስ ሪፓርተር፡- ትህነግ በትግራይ ክልል እየታዩ ባሉ ወቅታዊ ለውጦች ዙሪያ ከአፍሪካ ህብረት የቀረበለትን የሰላምና የውይይት ጥሪ እንደሚቀበል ለአፍሪካ ሕብረት በፃፈው ደብዳቤ ገልጿል። በሊቀ-መንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የተፈረመው ይህ ደብዳቤ፣ ትህነግ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
ደብዳቤው የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም ሂደት በንቃት እንዲመራና አሁን ያለውን የግንኙነት መሻከር (Impasse) ለመስበር ውጤታማ የሽምግልና ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ ያቀርባል። ሆኖም ሰነዱ የወጣበት ወቅት እና መሬት ላይ ካለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና ከቀጠናዊው ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት አንጻር ሲታይ ትህነግ ጥርሱን የነቀለበት የሴራ ፖለቲካ አካል እንደሆነ የቀጠናው ጂኦፓለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። በጦርነት ያሰበው ስላልተሳካለት ትንፋሽ መሰብሰቢያ ስልቱ እንደሆነም የገለጹ አሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ ለአዲስ ሪፓርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካ ተንታኙ ኢስማኤል አብዳላ እንደሚገልፁት፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ፀሐፊ እና የAFRICOM አዛዥ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ዋሽንግተን ለኢትዮጵያ የሰጠችውን አዲስ ስትራቴጂካዊ ክብደት ያሳያል። አሜሪካ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ቀይ ባህር ባለው መስመር ላይ የገጠማትን የደህንነት ስጋት ለመቆጣጠር፣ ኢትዮጵያን እንደ ዋነኛ የፀጥታ አጋር ዳግም መርጣለች። እንደ አብዳላ ትንታኔ፣ ይህ ወታደራዊ አጋርነትን የማጠናከር ስምምነት አሜሪካ በኢራን ላይ ለምትወስደው እርምጃ አስተማማኝ የጀርባ አጥንት እንድታገኝ ታስቦ የተደረገ ነው።
ይህ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እየተገነባ ባለበት ቅጽበት፣ “አብርሃም ሊንከን” የተሰኘው ግዙፍ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያቀና መሆኑ አሜሪካ ሙሉ ትኩረቷን ወደ ፍጥጫው ቀጠና ማዞሯን እንደሚያሳይ አብዳላ ያስረዳሉ። በዚህ ወሳኝ ወቅት ትህነግ የከፈተው ትንኮሳ በዋሽንግተን ዘንድ እንደ ስልታዊ “ሳቦታዥ” መቆጠሩን ተንታኙ ይገልጻሉ። አሜሪካ ሰላም እንዲሰፍን በምትፈልግበት ሰዓት ጦርነት መቀስቀስ፣ የዋሽንግተንን ወታደራዊ ትኩረት (Defense Posture) በመበታተን ለኢራንና ለተላላኪዎቿ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በመታመኑ ድርጊቱ በከፍተኛ ቁጣ ታይቷል።
እንደ ኢስማኤል አብዳላ ገለጻ፣ ዋሽንግተን ይህን የትህነግ ትንኮሳ እንደ “ክህደት” እንድትመለከተው ያደረጋት ቡድኑ የአሜሪካን ቀጠናዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ውስጥ መሳተፉ ነው። አሜሪካ በፕሪቶሪያው ስምምነት በኩል የገነባችው የሰላም ተስፋ በትህነግ ትንኮሳ ሲደናቀፍ፣ የኋይት ሃውስ ባለስልጣናት ቡድኑ ለቀጠናዊ ቀውስ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ተረድተዋል። ይህ እንቅስቃሴ አሜሪካ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ይበልጥ እንድትወግንና ለትህነግ ደግሞ የማያዳግም “ቀጭን ትዕዛዝ” ከዋሽንግተን እንድታስተላልፍ ማስገደዱን ተንታኙ ያክላሉ።
ይህ ተጽዕኖ የበረታበት ትህነግ፣ የዲፕሎማሲያዊ መገለልን በመፍራት በአስቸኳይ ወደ አፍሪካ ህብረት ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዱን አብዳላ ይገልጻሉ። ደብዳቤው ትህነግ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ሳይሆን፣ የፈጸመውን ስትራቴጂካዊ ስህተት ለመሸፈንና ከአሜሪካ የቀረበበትን ጠንካራ ተግሳጽ ለማለዘብ የተጠቀመበት “የጊዜያዊ ማምለጫ” ስልት ነው። ቡድኑ የአሜሪካን ቁጣ ለማርገብ “ለሰላም ዝግጁ ነኝ” በሚል የፖለቲካ ካባ ራሱን ለመሸፈን መሞከሩን ተንታኙ በስፋት ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፣ የትህነግን እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ አንጻር ይመለከቱታል። መምህሩ እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ትህነግ ራሱን ዳግም ለማስተዋወቅ የመረጠው አጋጣሚ ነው። ድርጅቱ በግንባር ትንኮሳ በመፈጸም፣ የአፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር አልሟል። “የትግራይ ጉዳይ ገና አልተቋጨምና እኔን ሳታነጋግሩ አትለፉ” የሚል ድምጸ-ከንቱ መልዕክት ለህብረቱ ለመላክ መሞከሩን ምሁሩ ያስረዳሉ።
እንደ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ገለጻ፣ በደብዳቤው ላይ የሰፈረው የሰላም ጥሪ እና በመሬት ላይ ያለው ወታደራዊ ትንኮሳ ፍጹም የሚቃረኑ መሆናቸው ቡድኑ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደ “ጊዜ መግዣ” እየተጠቀመበት መሆኑን ያረጋግጣል። የትህነግ ስሌት ግልጽ ነው፤ በውጊያ መስክ ኃይሉን ዳግም እያደራጀ፣ በዲፕሎማሲው ረገድ ደግሞ “ለሰላም የቆምኩ ነኝ” የሚል የሐሰት ገጽታ መገንባት ነው። ይህ “በአንድ አፍ ሁለት ምላስ” አካሄድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በፌደራል መንግስቱ ላይ ጫና እንዲያሳድር ለማድረግ የተወጠነ የሴራ ፖለቲካ እንደሆነ መምህሩ ያብራራሉ።
ምሁሩ አክለውም፣ ይህ ደብዳቤ አዲስ አበባ ለሚሰበሰቡት የአፍሪካ መሪዎች የሚሰጠው መልዕክት ትህነግ አሁንም እንደ “መንግስት በክልል ውስጥ” የመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው ይላሉ። የአፍሪካ ህብረትን “ልዩ ፓነል” በቀጥታ ማነጋገሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገዳደር የራሱን የውጭ ግንኙነት መስመር ለመዘርጋት መሞከሩን ያሳያል። ይህ አካሄድ ህብረቱ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገባ መጋበዝ ብቻ ሳይሆን፣ ስምምነቱን ጥሶ ግጭት እየቀሰቀሰ “ሰላም አስከብሩልኝ” የሚል አስቂኝ የፖለቲካ ተውኔት እንደሆነ መምህሩ ይገልጻሉ።
ትህነግ በዚህ ወቅት የፈጠረው ትንኮሳ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በጉባኤው ወቅት ሊያገኝ የሚችለውን ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ለማደብዘዝ የታለመ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ይናገራሉ። አፍሪካውያን መሪዎች ስለ አህጉራዊ ትብብር በሚወያዩበት መድረክ ላይ የሰሜኑን ግጭት ዳግም አጀንዳ በማድረግ ኢትዮጵያ “ያልተረጋጋች ሃገር” እንደሆነች ለማሳየት ተፈልጓል። ይህ የጥፋት ስሌት ድርጅቱ ከራሱ ህልውና ውጪ ለሀገር ሰላምና ለአህጉራዊ ገጽታ ደንታ እንደሌለው በተግባር ያሳየበት መሆኑን መምህሩ በአጽንኦት ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ የሁለቱ ተንታኞች እይታ የሚያሳየው ትህነግ በጂኦፖለቲካዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የገጠመውን ውጥረት በሴራ ለማለፍ መሞከሩን ነው። ኢስማኤል አብዳላ የአሜሪካን ስልታዊ ቁጣ ሲያጎሉ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን የመጠቀም ፍላጎቱን ያሳያሉ። ይህ የ”አትርሱኝ” ጩኸትና የዲፕሎማሲያዊ ማጭበርበር ሙከራ፣ ቡድኑ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ጥንካሬና ከአለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ይበልጥ ወደ መገለል የሚመራው እንጂ የሚታደገው አይሆንም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






