“ባርነትና ባንድነት” ዕርቃናቸው ታዩ፤ የሻዕቢያ መሪዎችና መንጋችው ለምን ተነኩ ጩኸትና “ተኮፊልና” ላሉት ኢሳያስ ጥብቅና መቆም!

Date:

“ጄኖሳይድ የምትሉትን ክስ አቁሙ፣ ሴቶች ተደፈሩ የሚባል ነገር እንዳታነሱ” የሚሉት ሁለት ታላላቅ ወንጀሎች “ጽምዶ” የሚባለው የትህነግና የሻዕቢያ አዲስ ግንኙነት ሲጀመር ሻዕቢያ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔዎች ነበሩ፤ ቅድመ ሁኔታዎቹን በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባማለት ይፋ ያደረጉት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አክቲቪስቶችና የኤርትራው አምባገነን መንግስት ተቃዋሚ ልሳኖች እንደሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።

ከሻዕቢያ በኩል ለትህነግ የተላለፈው መመሪያ በተዋረድ ትህነግ ለሚያስተዳድራቸውና በጀት ለሚቆርጥላቸው ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና የማህበራዊ ገጾች ተሰራጨና “ሻዕቢያ ጀኖሳይድ ነው። ሻዕቢያ ጨፍጫፊ ነው። ሻዕቢያ ትግራይን አውድሟል። ሻዕቢያ የትግራይን እናቶችና ሕጻናት ደፍሯል፣ በኤች አይ ቪ ቫይረስ በክሏል ወዘተ የሚለው ክስ ተፋቀለት።

የሻዕቢያና የትህነግ አዲስ ፍቅር ሲሰማ በወጉ እንኳን ባልደረቀው የትግራይ ንጹሃን ደም ላይ የተፈጸመ ክህደት፣ በግፍ በተረሸኑ የትግራይ ንጹሃን ዜጎች አስከሬን ላይ የመደነስ ያህል ተደርጎ ቁጣ አስነሳ፤

እነዛ በሻዕቢያ አለቆች ልዩ መመሪያ በማህጸናቸው ውስጥ ባዕድ ነገር የተጨመረባቸው እህቶችና እናቶች፣በትግራይ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ ፤ በትግራይ ህዝብ ስቃይና ድፍን ትግራይ ላይ የተፈጸመው ያ ሁሉ ግፍ ተረሳና ሻዕቢያ ጻድቅ ሆነ። ውድ አድማጮች ከትናንቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ በኋላ “ኢሳያስና ሻዕቢያ ለምን ተነኩ” በሚል የሻዕቢያ ተከፋይ ልሳናትና የኢትዮጵያን ባንዲራ ተከናንበው ለሻዕቢያ ያደሩ እያሰሙ ያሉትን ጩኸት አስመልክቶ ይህን አስተያየት አቅርቤያለሁ። 

አቶ ዕቁባይ ሰመረ  ከአዲስ አበባ / ነጻ አስተያየት 

ጎበዝ ሻዕቢያ በትግራይ የጅምላ ጭፍጨፋ አላካሄደም? ሻዕቢያ በትግራይ እናቶች ጓዳ የተርከሰከሰው የሻዕቢያ ጭፍራ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ሊጥ፣ ዱቄት፣ ቡሃቃ፣ ድስት፣ ጭልፋ፣ ገረወይና አልዘረፈም? ሌማት ላይ ተጣብቆ ደረቅ እንጀራ ሳይቀር አላጋዘም? የቤት ጣራ፣ በርና ግድግዳ፣ መስኮት፣ ማገርና ካስማ አልነቀለም? ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ስልክ አልነጠቀም? ፋብሪካ ነቅሎ አላጋዘም? ማጋዝ ያልቻለውን በቦንብ አላወደመም፣ ሆን ብሎ የትግራያ ሴቶችን ዕድሜ ሳይመርጥ በኤች አይቪ ቫይረስ አልበከለም? አስገድዶ አልደፈረም? በእህቶቻችን ማህጸን ውስጥ ባዕድ ነገሮችን አልከተተም? ደብዳቤ በመጻፍ ማህጸን ውስጥ ዘር ማንዘራችሁን አጠፋለሁ የሚል ደብዳቤ አላስቀመጠም? ይህ የቅርብ ጊዜ የሻዕቢያ ወጉ አልነበረም።

ይህን ሁሉ የዘገቡትና በወቅቱ እንደ አምላክ ቃል ሲሰራጩ የነበሩት፣ ሲ.ኤን.ኤን፣ ቢቢሲ፣ ቪኦኤ፣ ሮይተርስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ወዘተ ሚዲያዎች ውሸታሞች ነበሩ? ድምጸ ወያኔ፣ የትግራይ ቲቪ፣ የትግራይ አክቲቪስቶች፣ በዓለም ዙሪያ ደረታቸውን እየደቁ ሲያለቅሱ የነበሩት የትግራይ ተወላጆች ሻዕቢያን ሲያወግዙ የነበረው በፈጠራ ክስ ነበር?

እስኪ ለትዝታ አባ ሰረቀ ብርሃን በወቅቱ ያሉትን ላስታውሳችሁ፤

አባ ሰረቀ ብርሃን የሚባሉት ቄስ በወቅቱ፣ በትኩሱ “የኤርትራ ወታደር ነው ትግራይን እያጠፋ ያለው ፣ በመረጃ በማስረጃ የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡  አብያተ ክርስትያናትን እያጠፋ ያለ የኤርትራ ወታደር ነው፡፡ ህዝባችንን እየገደለ ያለ የኤርትራ ወታደር ነው፡፡እህቶቻችንን አህዛብ በማያደርጉት ደረጃ እያራከሰ ያለው አብዛኛው የኤርትራ ወታደር ነው፡፡ የትግራይን ንብረት በሙሉ ያወደመ የኤርትራ ወታደር ነው፡፡የትግራይን ሀብት በሙሉ ጭኖ የወሰደ የኤርትራ ወታደር ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ንብረት ያለው ያለው ኤርትራ ነው፣ አብዛኛው ንብረቶች የተጫኑት ወደ ኤርትራ ነው፡፡” ብለዋል።

እሳቸው ያሉትንና በወቅቱ የሰጡትን ምስክርነት መካድ ይቻላል? የትግራይ አክቲቪስቶች፣ የውጭ አገር ሚዲያዎችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች፣ ሰለባዎችና የሰላባ ቤተሰቦች በገሃድ ወጥተው ሲናገሩ የነበሩት የሻዕቢያ ግፍ ሃሰት ነበር? የትግራይ ሕዝብ ውሸታም ነው ማለት ነው? የትግራይ እናቶችና እህቶች፣ በትግራይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ውሸታሞች ናቸው። ሻዕቢያ ጻድቅ ነው እያላችሁ ነው? ወይስ የሻዕቢያ የግፍ ክምር በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አንደበት ለዚያውም ምስክር ተጠቅሶ ሲገለጽ ወደ ጽድቅ ይቆጠራል እያላችሁ ነው? ለዚህ ነው ባርነትና ባንድነት እርቃናቸውን ታዩ ለማለት የወደድኩት።

እናንተ ሻዕቢያ አውሬ ነው ስትሉ የከረማችሁ፤ እናንተ ሻዕቢያን ከሰይጣን ጋር በማመሳሰል ስትረግሙ የነበራችሁ፣ዛሬ ሻዕቢያ ለትግራም ለኢትዮጵያም ሕዝብ ክንፍ ያለው መልዐክ ነው እያላችሁን ነው? ሻዕቢያ እጁ ላይ ደም የለም፤ በምግባሩም ሌብነት አያውቀውም፣ ህይወቱ ሁሉ የጽድቅ ነው? እያላችሁ ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ለሚያነሱ ምን ምላሽ አላችሁ? ባንዳነቱና ባርነቱ ህሊናችሁን ቢደፍነውም ማለቴ ነው።

እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ስለ ሻዕቢያ አውሬነት ሲነገር፣ ከተፈጠረ ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚያተራምስ ሽፍታ ስለመሆኑ ዝርዝር መረጃና ማስረጃ ሲቀርብ በዚህ ደረጃ ያልተቃወማችሁ ዛሬ በምን ሂሳብ “ኢሳያስና ጀሌዎቹ አይነኩ” አላችሁ? በዚህ ደረጃ ተከስክሶ ለኢትዮጵያ መከራዋ ለሆነ፣ እራፊያም ደሃ ሰገዳችሁ?

በቅርቡ አቶ ጌታቸው ረዳ ጦርነቱ ከተጀመረ ሻዕቢያ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ትግራይን ስለሚያጠቃ፣ ልዩነታችን አቻችለን አብረን እንሁን ማለታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው መክረውን ነበር ብለው ሲመሰክሩ አልሰማችሁም?

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በፓርላማ የሻዕቢያን ክፉ ተግባር በደፈናው አንስተው፣ በትግራይ የሚፈጽመውን ክፉ ተግባሩን  እንዲያቆም አቶ ገዱ አንዳርጋቸውንና ፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ እንዲሁም ሌሎች ሶስት ባለስልጣናትን አስመራ “የትግራይን ህዝብ አትንካ” በማለት መላካቸውን ይፋ ማድረቸው ያንጫጫችሁ ሳይመሽ የትግራይንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቁ። ባንዳነትና ባርነት አይጠቅምምና  ለልጆቻችሁ ክፉ ታሪክ አታኑሩ።

አብይ አህመድ ለፓርላማ ሲናገሩ ሻዕቢያን በወቅቱ በኃይል ማስቆም አይቻልም ነበር ብለዋል። ምክንያቱም እድሜ ለትህነግ አቅም የለም ነበር። ሁለት አስርት ዓመታት ራሱን ምሽግ ውስጥ ቀብሮ ሻዕቢያን ሲከላከል የኖረ የአገር መከላከያ በክህደት ታርዶ ነበር። ወቅቱ ሌላ ጠላት የሚጨመርበት አልነበረም። ከዚህ አንጻር መንግስት ሻዕቢያን ለምን አልወጋህም ተብሎ ሊከሰስ የሚችልበት አመክንዮም የለም።

በመሆኑም ጊዜው ሲደርስ ምስክር በመጥራት ሻዕቢያ የፈጸመውን በጅምላ ይፋ ሲደረግ እንደ ዜጋ ከመወጋገዝ ይልቅ፣ በቁጭት ደረታችንን በደቃን ነበር፡፡ መመኪያችን በክህደት ታርዶ የባንዳና የጠላቶቻችን ተላላኪዎች እንዲጨፍሩብን በር መክፈታችን ባስለቀሰን ነበር። የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው።

ከዚህ አውሬ ድርጅት ጋር፣ ከዚህ ኢትዮጵያን ለማጥፋትና ለማተራመስ ቅጥረኛ ሲፈለፍል፣ በመሃል አገር ወኪሎቹን አሰማርቶ በሚሰርቀው ሃብት ከሚተዳደር ማፍያና አሸባሪ፣ እንዲሁም በወንጀልና በደም ከተጨማለቀ ቡድን ጋር ህብረት ተደርጎ “እንዴት ቀላቢያችን ተነካ” ብሎ ማበድ ከቀላቢያቸው በላይ ወንጀለኛ የሚያሰኝ ነው።

እርቅና ሰላም ይሻላል ተብሎ እንጂ ሻዕቢያና ደቀመዝሙሮቹ አዲስ አበባ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ የሳይበር ዘመቻ የሚከፍቱ፣ በሌብነት የተሰማሩ፣ ከዜጎች ጉሮሮ የሚነጥቁ፣ ማጅራት የሚመቱ፣ ቀደም ሲል ከእርሻ ምርት ጀምሮ የቁም ከብት እየነዱ ሲያልቡን የኖሩ፣ ሰላም ብሎ መሳሪያ ያወረደውን ወታደር ጥርስ አውልቀው ያባረሩ አረመኔዎች ናቸው። በምንም መለኪያ ሊታመኑ የማይችሉ እባቦች ናቸው። የትግራይን ሕዝብ “ልቡ የማይታወቅ” እያሉ በቦታ ስያሜ ይፈርጃሉ እንጂ እንደ ሻዕቢያና ደቀመዝሙሮቹ ያለ ሸለመጥማጥ የለም። ይህን በዘመናችን ያየነው ሃቅ ነው።

ሻዕቢያና ደቀመዝሙሮቹ ያበላች፣ ያሳደገች፣ ያጠጣች አገርን “በባርነት የያዘች” በማለት ወንጅለው ከተለዩዋት በሁዋላ ዛሬም ድረስ እንደ መዥገር ተጣብቀውባት የሚጠቧት የበሉበት ወጪት ሰባሪዎች ናቸው፤ የከዷት አገር ውስጥ በቀበሌ ቤትና በኪራይ ቤቶች አስተዳደር መኖሪያ ይዘው፣ በመንግስት ተቋማት ተቀጥረው፣ ተሽከርካሪ ገዝተው እየነገዱና የውጭ ምንዛሬ እያጠቡ የሚፈነጩ ልበ ጥቁሮች ናቸው።

ይህ የሻዕቢያ ኮልኮሌና መሪ ለምን ተነካ በሚል መጮኽ ከላይ በተዘረዘሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁስል ላይ አሲድ መርጨት፣  ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር አግልሎ እያንዳንዱን ዜጋ ገባሪ ላደረገው ከሃጂ “አበጀህ” ብሎ የማፈንደድ ያህል ነው። ታሪክ ፍርድ ይስጥ። ለማንኛውም በፓርላማ የተነሳው ጉዳይ ትንሿ ናጥ ገና ብዙ ጉድ አለ። በአጠቃላይ ማንም ይናገረው ማንም የሻዕቢያና ጭፍሮቹ ወንጀል በኢትዮጵያዊያን ዘነድ ታትሞ የሚኖር ነው። በሌላ ጽሁፍ እመመለሳለሁ። ለማንኛውም ጠቅላይ ሚ ኒስትሩ የተናገሩትን እንደወረደ እነሆ። 

“ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ነገር ነበር፤ ታውቃላችሁ። እኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልግም፣ ይቅርብን ብለን ሞክረናል። አምስት አመት ለምነናል።

ጸቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባህር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም። በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ውጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ ኋላ ተከትሎ ሽሬ ገብቶ የአንዳንድ ግለሰቦች ቤት ማፍረስ፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ጸብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም እንጂ።

አክሱምን ይዘን ስናልፍ አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል። ዓድዋን ይዘን ስናልፍ ዓድዋ ሄዶ ፋብሪካዎች ሲፈታ፣ ሲሰርቅ ጸብ ተጋግሏል። ዓዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅለው የማይነቀለውን ሲያፈራሱ ጸቡ ጫፍ ደርሷል።

ግን የኢትዮጵያ መንግስት ያኔ በዚህም፣ በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም። ውስን ኃይል ነበረን፤ ሽሬን ከያዝን በኋላ ያጠቃውን ጠላት እንከተል ነበር እንጅ የያዝነውን ቦታ እያጸናን አንሄድም ነበር።

ይሄ ጉዳይ ለዛሬ ዋጋ የለውም። ለታሪክ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ ግን አክሱም ወጣቶች ሲገደሉ፣ ዓድዋ ሲዘረፍ፣ አዲግራት ሲዘረፍ በርካታ ሰዎች ወደ ኤርትራ ልኬያለሁ።

የላኳቸው ሰዎች ገሚሱ አሁን ከኛ ጋር የሉም። ለምሳሌ ክቡር አቶ ገዱ ያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ከአንዴም ሁለቴ ኤርትራ ልኬያቸዋለሁ። የላኳቸው የትግራይ ህዝቤን አታጎሳቁሉ፣ ሀብቱን አትዝረፉ፣ ጸቡ ከትህነግ እንጅ ከትግራይ ህዝብ አይደለም በሚል ነው።

አቶ ገዱ አሁን እኛ ጋ የሉም። ግን ክር / ማተብ አላቸው፤ ህሊና አላቸው። ዛሬ ቢደብቁ በታሪክ ውስጥ ይወጣል። ስለምን ጉዳይ እንደተነጋገሩ እሳቸውም ያውቃሉ፤ ሻዕቢያም ያውቃል፤ እኛም እናውቃለን። አሉ አልሞቱም። እሳቸው (ገዱ) Access ይደረጋሉ ሊናገሩ ይችላሉ።

ጉዳዩ በእሳቸው መፈታት ሲያቅተው አቶ ደመቀን ልኬያለሁ። አቶ ደመቀ አሁንም እኛ ጋር የሉም፤ በህይወት ስላሉ ለእምነታቸው ለህሊናቸው ሊጠየቁ ይችላሉ። ለምን ጉዳይ እንደሄዱ ያውቃሉ።

ታስታውሱ ከሆነ መቐለ ልንገባ ትንሽ ሲቀረን የሦስት ቀን ‘አልቲማተም’ ብለን አውጀን ነበር። ብዙው ምስጢሩ አልገባውም።

የቸገረን እኛ ሽሬን ስንለቅ ከኋላ ይገባሉ። አክሱም ስንለቅ ከኋላ ይገባሉ። መቐሌ ስንገባ ደግሞ ገብተው ትልቁን ከተማ Damage ያደርጋሉ ብለን፥ ካሁን በኋላ ከውቅሮ እናልፋለን ብትሉ ወያኔን ትተን ወደ እናንተ ነው የምንዞረው በውጊያው ብለን ውቅሮ ላይ የሚጠብቅ ኃይል አስቀምጠን ነው መቐሌ የገባነው።

ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም ‘ እንዴት ትህነግ ሳይጠፋ፣ ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል ? ‘ በሚል ነው የመጨረሻ ጫፍ የደረሰው ጸቡ። ከዚህ ኃይል ጋር ነው እንግዲህ ያኔ የTPLF ሰዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንስራ ያሉት።

የትግራይ ህዝብን የሚጎዳ እና የሚጠቅም ነገር ይሄ መንግስት ነው የሰራው ወይስ TPLF? (ሁሉም TPLF ላይሆን ይችላል፤ አክራሪ TPLF በሚል ይውሰድ) ማነው? የሚለው ዛሬ ብዙ Emotion፣ ብዙ ፕሮፓጋንዳ፣ ብዙ ውሸት ስላለ ነው፤ ነገ ግን ታሪክ ያወጣዋል።

ማንም ሰው እውነትን ለጊዜው መሸፈን እንጅ ከነአካቴው ማጥፋት አይችልም። እኛ መጨረሻ ፕሪቶሪያ ስንፈራረም መቐለ ለመግባት አንድ ቀን ነበር የቀረን፤ አሸንፈናል ጦርነቱን።

ግን መቐለ መግባት ድል አይደለም። ህዝባችንን የማንጠብቅ ከሆነ ተመልሶ ይዘረፋል፣ ይገደላል። ያ ከሚሆን ሰላም ይሻላል። የኛው ህዝብ ነው ከሚጎዳብን ይቅርብን ብለን ነው የወሰነው።

ዛሬ የTPLF አንዳንድ ሰዎች ያላቸውን አቋም ሳይ ምን ያክል ህዝባቸውን እንደሚጠሉ፣ ምን ያክል የህዝባቸውን በደል እንዳሚያምኑ ነው የሚገባኝ።

እውነተኛው ፈራጅ ስለሚያይ ማንም አያሸንፈንም። TPLF በኤርትራ ወታደር ዘረፋ እንዳይካሄድበት ስንጠብቀው ኖረን አማራ ክልል ሲገባ ያደረገው ነገር ያሳፍራል። ፋብሪካዎች አፍርሷል። ት/ቤት አቃጥሏል። ባንክ ዘርፏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መቐለ ነበረ በብቸኝነት፤ TPLFን አባሮ ሻዕቢያን ሳያስገባ። መቐለ አንድ ቤት የፈረሰ አታገኙም።

TPLFስ ቢሆን አማራ ክልል መጥቶ እንደዚያ አይነት ነገር ማድረግ ነገ ለሚቀየር ታሪክ አስፈላጊ ነበር? እንደዚህ ያለው ኢትዮጵያን ያላስቀደመ ለጊዜው ለሚዲያ ጫወታ የሚደረግ የፓለቲካ ስብዕና በዘላቂነት በራሳችን ህዝብ ላይ ጉዳት የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን በታሪክ መነጽር ሊጋባው በየነን ዛሬ ታሪክ እንዳነሳቸው በታሪክ ውስጥ ይነሳል ” ብለዋል። እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ይህን በመናገራቸው ነው “ለምን ሻኧቢያ ተነካ” በሚል ተቃውሞ የተነሳው። የቀደሙ ንግግሮች አውዳቸውን እንዲስቱ ተደርጎ እየትቀረበ ያለው። ሻዕቢያን የሚያስወድድ መንፈስ ባርነትና ባንዳነት!!

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች እንዴት ተቋረጡ? እንዴትስ እንዲጀምሩ ተወሰነ?

አዲስ ሪፖርተር - ላለፉት አምስት ቀናት የተቋረጠው የአየር ትራንስፖርት...

የክምችት ብር መጠን 4 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ደረሰ፤ የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር ላይ የተደረገው ጭማሪ ጥያቄ አስነሳ

አዲስ ሪፖርተር - ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ቴሌብርና ሌሎች...