በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ብሔራዊ ምክር ቤት ስም በአቶ ዳውድ ኢብሣ የሚመራው የኦነግ ክንፍ ከሰኔ 30 እሰከ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ያካሄደውን ስብሰባና ያስተላለፋቸዉን ዉሳኔዎች የህግ መሰረት የላቸዉም በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ በሙሉ ዉድቅ አደረገ፡፡
ይህ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሣኔ በ 9 ገጾች የተጻፈ ሲሆን ለሁለቱም የኦነግ መሪዎች ማለትም ለአቶ ዳውድ ኢብሣ እና ለአቶ አራርሶ ቢቅላ እንዲደርሣቸው ተደርጔል።
በዚሁ መሠረት በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ እንደተመለከተዉ በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራዉ ቡድን ከዛሬ 6 ዓመት በፊት በአዋጅ ቁ 573/2000 በቦርዱ ከተመዘገቡት 48 የድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከግማሽ በታች የሚሆኑት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ብሔራዊ ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ በሚል ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓም ስብሰባ በመቀመጥ በአቶ አራርሶ ቢቅላ የሚመራውን እና አብዛኛው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን የያዘ እንዲሁም የድርጅቱን የበላይ አመራሮችና የምክር ቤቱ አባላትን ከፓርቲዉ ማባረሩንና ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ በምትካቸዉ ሌሎች ሰዎች እንደሚተካ መግለጫ ማዉጣቱና ለቦርዱም ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
የእነ አቶ ዳውድ ኢብሣ ቡድን ለመጥራት የወሰነዉን ጠቅላላ ጉባዔ የሚያዘጋጅ የራሱ አዘጋጅ ኮሚቴ መሰየሙንም ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቡድኑ አካሄድኩ ያለዉን የምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባዔ እና ጉበዔዉን የጠራዉ አካል ያደረገዉ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ እንዲያቀርብ በማዘዝ የተባለዉን የቡድኑን ቃለ ጉባዔ ዉሳኔዎች ላይ መልስ እንዲሰጡበት በአቶ አራርሶ ቢቅላ ለሚመራው ኦነግ ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ቦርዱ በላከላቸዉ መሰረት አመራሮቹም ምላሽ እንዲሰጡ ተደርጔል፡፡
የምርጫ ቦርዱ የስራ አመራር ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓም ባደረገዉ ስብሰባ በእነ አቶ ዳዉድ ኢብሳ ቡድን የቀረበለትን ቃለ ጉበዔ እና በቃለ ጉበዔዉ ላይ በአቶ አራርሶ ቢቅላ የሚመራው የኦነግ ክንፍ የሰጡትን መልስ መርምሮ ዉሳኔ በመስጠት ጥቅምት 26 ቀን 2018 በጻፈው ደብዳቤ ለሚመለከታቸዉ ለሁለቱም አካላት ዉሳኔዉን አሳዉቋል፡፡
የስራ አመራር ቦርዱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የአቶ ዳዉድ ኢብሣ የሚመራው የኦነግ ክንፍ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችን በመወንጀል ሙሉ በሙሉ ከስልጣናቸዉ አግደናል በማለት ያሣለፈዉን ዉሳኔ ህጋዊ ተቀባይነት የለዉም ብሏል፡፡ አመራሮቹ ከፓርቲዉ ስለመልቀቃቸዉ ያቀረቡት የጽሑፍ ማመልከቻ የለም፣ ወይም ከፓርቲዉ የሚያሰርዛቸዉ አንዳችም ምክንያት የለም ብሏል ቦርዱ፡፡ እነዚህ አመራሮች በፊትም አሁንም የኦነግ አባላትና አመራሮች መሆናቸዉ አየታወቀና እነርሱም ራሳቸዉ አሁንም የድርጅቱ አባላት ማሆናቸዉን እየገለጹ ባለበት ሁኔታ፡ አመራሮቹን ራሳቸዉ በራሳቸዉ ከድርጅቱ ያወጡ በማለት የሰጠዉ ዉሳኔ የህግ መሰረት የሌለዉ ከመሆኑም በላይ የአባላትን መብት የሚጋፋ በመሆኑ ቦርዱ ዉሳኔዉን ዉድቅ አድርጎታል ሲል ወስኗል፡፡ በተጨማሪም የእነ ዳውድ ኢብሣ ቡድን አግደናል ያላቸዉ የኦነግ አመራሮች በቀጣይም የአባልነት መብታቸዉ ተጠብቆ የአመራር ሃላፍነታቸዉን እንደሚቀጥሉ ቦርዱ በደብዳቤው አጽንኦት ሰጥቶ አረጋግጧል ።
የምርጫ ቦርዱ በመቀጠል በብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ ተመረጠ የተባለዉ የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴም ሆነ በምክር ቤቱ ጸደቀ የተባለዉ የአደራጅ ኮሚቴ ማቋቋሚያ መመሪያ እና በአጠቃላይ በም/ቤቱ ተወሰኑ የተባሉ ዉሳኔዎች በስብሰባዉ መገኘት የነበረባቸዉ አብዛኛዉ አመራር አባላት ባልተገኙበት የተወሰኑ መሆናቸዉን በመዘርዘር ምልዓተ ጉባዔው ባልተሟላበት የተደረገ ስብሰባ እንደመሆኑ ዉሳኔዎቹን ቦርዱ ዉድቅ አድርጓል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የምክር ቤቱ ስብሰባ በራሱ አካሄድና አፈጻጸም ዉድቅ መደረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን የም/ቤቱን ስብሰባ እንዲካሄድ ለመወሰን በመተዳደሪያ ደንቡ በተቀመጠዉ መሰረት ከ8 የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ቢያንስ 2/3ኛ ወይም 6 ሰዎች መገኘት ሲገባቸዉ 4ቱ(አራቱ) ብቻ ተገኝተዋል ያለዉ ቦርዱ የም/ቤቱን ስብሰባ ለመጥራት የተደረገዉ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዉ ስብሰባ ራሱ ምልዓተ ጉባዔ ባልተሟላበት የተካሄደ ስለሆነ በህጉና በመተዳደሪያ ደንቡ ተቀባይነት የለዉም በማለት 4ቱ የስራ አስፈጻሚ አባላት ያደረጉትን ስብሰባ እና ያስተላለፉትን ዉሳኔ ዉድቅ ማድረጉንም ቦርዱ በይፋ አሳውቌል፡፡
ቦርዱ በመቀጠል በምርጫ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 መሰረት በቦርዱ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢያንሰ በየሶስት(3) ዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ እንዳለባቸዉ አስገዳጅ ድንጋጌ ቢኖርም የአቶ ዳዉድ ኢብሳ ቡድን ላለፉት ስድስት(6) ዓመታት ጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ መቆየቱን ቦርዱ በዉሳኔ መግለጫው አረጋግጧል፡፡
ቡድኑ አሁን ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ የሚያደረገዉ እንቅስቃሴ አፈጻጸሙ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁ. 1162/2011 እና የፓርቲዉ አመራሮችና አባላት መብት ባከበረ እና በጠበቀ መሆን ይገባል ሲልም ኣሳስቧል፡፡
ቦርዱ በፓርቲዉ አመራር መካከል የተፈጠረዉን አለመግባባት ለመፍታት ረጅም ርቀት የሄደ መሆኑን ጠቅሶ ቢሆንም እስካሁን መፍትሔ ባለመገኘቱ የፓርቲዉን ህልዉና የሚፈታተን አደጋ አሁንም ከፊቱ ተደቅኖ እንዳለ በማሳሰብ በመጨረሻ ይሆናል ያለዉን የራሱን የመፍትሔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም በአቶ አራርሶ ቢቅላ የሚመራው የኦነግ ክንፍ በምክትል ሊቀመንበሩ በአቶ ቀጄላ መርዳሣ በኩል የቦርዱን ውሣኔ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላለፉት 5 ዓመታት ቀደም ሲል በነበሩ አንዳንድ የቦርዱ አባላት ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ምክንያት ይህንን የተዛባዉን ጉዳይ ለማቃናት አዲሱ የቦርዱ ስራ አመራሮች በዚህ ልክ መርምሮ ፍትሃዊ ዉሳኔ ለመስጠት ያደረውን ጥረት አመስግነዋል።ፍትህ ተነፍገዉ እና ተገፍተዉ ለቆዩ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች፣ እንደዚሁም ለድርጅቱ መልሶ መንሰራራት ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራሩን በድጋም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
አክለውም ቦርዱ በቦርዱ መቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 እና በአዋጅ 1162/2011 በተሰጡት ስልጣንና ተግባር መሰረት የድርጅቱን ችግር በህጉ መሰረት ለመፍታት የሚያደርገዉን ጥረት ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል።
ማሣሰቢያ :-ይህ የምርጫ ቦርድ ውሣኔ በ9 ገጾች የቀረቡና በጣም በርካታ ዘርዘር ያሉ ሀተታዎች ያሉት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
National Election Board of Ethiopia NEBE የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ





