አዲስ ሪፖርተር ዜና – ለሶስት አስርት ዓመታት በማዕቀብ ተቆልፎባት የኖረችው ኤርትራ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ሰንሰለቱ ተበጥሶላት ነበር። ጦርነትም፣ ሰላምም ባልነበረበት ሁኔታ ተዘግቶባት የነበረችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም አውርደው ብዙም ሳይቆዩ አሁን ወዳሉበት ደረጃ ደረሱ።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምንት መፈረሙን ተከትሎ ያኮረፉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ሰሞኑን አሜሪካ መልሳ ልትዋዳጃቸው ማቀዷ ተሰምቷል። ዜናው መልካም ቢሆንም ኢሳያስ ግን አይቀበሉትም የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው። በሌላም በኩል ኢትዮጵያና ኤርትራን በማስገደድ የማስማማት አካሄድም ሊኖር እንደሚችል እየተጠቀሰ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ቲቦር ናጊ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወቅት የአሜሪካን የአፍሪካ ፖሊሲ በበላይነት መርተዋል። በወቅት በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ለውጦች ላይ ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ዲፕሎማት በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል በተካሄደው የድንበር ጦርነት አሜሪካን በመወከል ጦርነቱን ለማስቆም በተደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና ነበራቸው።
“ግሎባል ፓወር ሺፍት” በሚል ርዕስ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዎል ስትሪት ጆርናል The Wall Street Journal አሜሪካ ኤርትራ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማላላት ዕቅድ እንዳላት መግለጹን ተከትሎ ነው። ዎላ ስትሪት ጆርናል አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ እየቀነሰ የመጣውን ተፅዕኖዋን ለማስመለስ እንዲሁም የሩሲያንና የቻይናን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ መስፋፋት ለመግታት ስትል፣ ከኤርትራ ጋር የነበራትን የቆየ ፍጥጫ ወደ ጎን በመተው አዲስ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመርና የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ለማስከበር ፍላጎት እንዳላት መስማቱን አስታውቆ ነበር።
ናጊ እንደሚሉት አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ከመልፋት ይልቅ፣ እንደ ሶማሊላንድ ካሉ አማራጮች ጋር ብትሠራ የተሻለ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ምክንያቱም የኤርትራ መንግሥት ለለውጥ ዝግጁ አይድለም። አይታመንም። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም፣ የኤርትራ መንግሥት ግንኙነቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ “ብቃትም ሆነ ፍላጎት የለውም” ብለዋል።
ኤርትራን “ግዙፍ የእስር ቤት ካምፕ” ሲሉ የገለጹት እሳቸው፣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ግንኙነቱ ቢስተካከልና አገሪቱ ብትከፈት የሥልጣን መንበራቸው ሊናወጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል። “በኤርትራ ውስጥ ሕገ-መንግሥት የለም፣ ምርጫ የለም፣ ብሔራዊ አገልግሎትም እስከ ዕድሜ ልክ ነው” ሲሉ የአገሪቱን ሁኔታ አስረድተዋል።
ዲፕሎማቱ እሳቸው ኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት አሥመራ ድረስ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ተደጋጋሚ ንግግር ማድረጋቸውን አመልክተው፣ በወቅቱ ለአሜሪካ ሴኔት በሰጡት ምስክርነት “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዓይነት አዎንታዊ ግንኙነት ከኤርትራ ጋርም እንዲኖራት ትፈልጋለች” ብለው እንደ ነበርም ይገልጻሉ። ነገር ግን የኤርትራ ባለሥልጣናት ለአዎንታዊ ግንኙነት ምላሽ የመስጠት ብቃትም ሆነ ፍላጎት እንዳልነበራቸው፣ብዙ ጊዜ በንግግር ከተስማሙ በኋላ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ወደ ኋላ እንደሚሉ አስረድተዋል።
ይህንኑ አባባላቸውን ሲያጠናክሩ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ በአንድ ወቅት ደርግን ለመጣል አብረው የታገሉ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግን መስማማት ባለመቻላቸው ወደ ጦርነት ማምራታቸውን የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ አውስተው። መለስ ዜናዊ ስለ ኢሳይያስ ሲናገሩ “በየቀኑ አዲስ ሰው ሆኖ ነው የሚነሳው፣ ምን እንደሚያደርግ አታውቅም” በማለት እንደነገሯቸው ያስታውሳሉ።
አቶ መለስ በተደጋጋሚ የኤርትራ አመራር፣ በተለይም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “የቀጣናውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታ ያላገናዘበ፣ በስሜትና በወታደራዊ ጡንቻ ላይ ብቻ የተመሰረተ ግትር አቋም የሚከተሉ ይሏቸው ነበር” በ“ዜሮ ድምር ፖለቲካ” መስለው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባህሪ “እኔ ካላሸነፍኩ ሁሉም ይጥፋ” የሚል አይነት እንደሆነና ይህም ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንቅፋት እንደነበር፣ ከዚያም በላይ አቶ መለስ በአንድ ወቅት የኤርትራን አመራር “ባህሪው የማይገመት” (Unpredictable) እና የነገሮችን አካሄድ በምክንያታዊነት (Rationality) የማይመረምር እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
በአጠቃላይ አቶ መለስ የፕሬዝዳንት ኢሳያስን ግትርነት እንደ ግል ባህሪ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው አለመረጋጋትና ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መበላሸት እንደ ዋና ምክንያት አድርገው ያቀርቡት ነበር። በተለይ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኤርትራ አመራር ችግር የድንበር ሳይሆን የባህሪና የአስተሳሰብ ችግር መሆኑን ሲገልጹ “አጉራ ዘለል” በማለት ነበር።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አቶ መለስም ሆን ህወሃትን ከቶውንም ሊታመኑ የማይችሉ፣”የመንደር ፖለቲካ የሚያራምዱ” (Parochial) በዘር ላይ ያተኮረ ከፋፋይ ሥርዓት የዘረጉ በማለት ይተቹ ነበር። ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክቶ “ቅጥረኞች” (Agitators/Mercenaries) ይላኡቸው ነበር። ህወሃት የውጭ ኃይሎችን በተለይም የአሜሪካን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚላላክ እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ወይም ለቀጣናው ሰላም የማይሰራ ድርጅት እንደሆነ አድርገው ይገልጹት ነበር።
በዚሁ መካረር ኢሳያስ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ሆነ። በዚህም ኤርትራ ከዓለምና ከአህጉሩ ተገለለች። ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ኤርትራ ታፍና ወየበች። በዚህ መካከል ለውጥ መጣ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2018 ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው፣ ለዓመታት በኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀብ እንዲነሳ ቀጥተኛና ወሳኝ ሚና መጫወቱን ፖለቲከኞች ዝርዝር መረጃ በማቅረብ ይመሰክራሉ።
አብይ አሕመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ጸብ ማብቃት አለበት” በሚል የወሰዱት እርምጃ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኤርትራ የነበረውን አመለካከት እንዲቀይርና የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሣሪያ ሽያጭና የጉዞ እገዳ በሙሉ ድምፅ እንዲያነሳ መንገድ ከፈተ። ይህ የዲፕሎማሲ ስኬት ኤርትራ ለዓመታት ከነበረችበት የገለልተኝነት አጥር እንድትወጣና ወደ ቀጠናዊ ፖለቲካው እንድትመለስ ትልቅ በር የከፈተ የፖለቲካ ውለታ ተደርጎ ተወሰደ። ይህ ውለታ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ተቀየረ። ግንኙነቱ ሞተ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከተበላሸ በኋላ ከአሜሪካ የወጣው ዜና መነጋገሪያ ሆኗል። አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ የፈለገችበት ዋናው ምክንያት፤ ኤርትራ በቀይ ባሕር ስትራቴጂካዊ የባሕር መስመር ላይ ያላትን ወሳኝ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በመጠቀም፣ በአካባቢው እየታየ የመጣውን የሩሲያ እና የቻይናን ተፅዕኖ ለመመከት እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን ለማስጠበቅ ካላት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል፣ በተለይም አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከስቶ በሆርሙን ሰርጥ የገጠመውን ችግር አስመልክቶ ሙሉ ቀይ ባህርን እስከ ባብ ኤልማንደብ ለመቆጣጠር እንደሆነ ይገመታል።
እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ፣ አሜሪካ ግንኙነቱን ለማደስ ብትፈልግም የኤርትራ መንግሥት ለራሱ ህልውና ሲል ግንኙነቱ እንዲሻሻል አይፈቅድም።
ዲፕሎማቱ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ማስተካከል የማይፈልጉበትን ተግባራዊ ምክንያት እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ። ግንኙነቱ መደበኛ ከሆነ አገሪቱ መከፈት ይኖርባታል። ይህም “ግዙፍ የእስር ቤት ካምፕ” ያሏትን ኤርትራ ግድግዳዎች እንዲናዱ ያደርጋል።
ግንኙነቱ ከታደሰ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ፣ ሕገ መንግሥት እና ምርጫ እንዲኖር ዓለም አቀፍ ጫና ይበረታል። ይህ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ አገሪቱን አሁን በሚቆጣጠሩበት የቁጥጥር ሥርዓት ለመምራት ስለሚያዳግታቸው ግንኙነቱ እንዲስተካከል አይፈልጉም ባይ ናቸው።
ከኤርትራ ጋር ለማደስ የታሰበው ግንኙነት፣ ኤርትራ ከቻይና፣ ሩሲያና ኢራን ጋር ካላት ግንኙነት ጋር ተያይዞ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ ቢቸገሩም፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ አሁን ባሉበት ሁኔታ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ የሁለቱን አገራት ችግር እንዲፈታ አስገዳጅ ጉዳዮችን ልታስቀምጥ እንደምትችል እየተሰማ ነው።
የቀጠናው የፖለቲካ ተንታኝ ኖርዌጂያኑ ፕሮፌሰር ኬቲል ትሮንቮል “የአሜሪካና የኤርትራ መቀራረብ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የኃይል ሚዛን ሊቀይረውና ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ አማራጮቿን እንድትመረምር ሊያስገድዳት ይችላል” በሚል አስተያየታቸውን ለሰጡት አስተያየት አቶ ጌታቸው ረዳ በአሜሪካ እና በኤርትራ መካከል ይፈጠራል የተባለው አዲስ መቀራረብ እንደሚባለው ቀላል ሳይሆን እጅግ ውስብስብ መሆኑን መሆኑን አመልክተዋል።
የዶናልድ ትራምፕ አማችና የአረብ እና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ፋረስ ቡሎስ ወደ አስመራ ያደረጉት ጉዞ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማለስለስ እና አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ለመጀመር የምታደርገው ጥረት አካል ተደርጎ መወሰዱን አስመልክቶ ናጊ በተናገሩት ላይ አስተያየታቸውን ያከሉት አቶ ጌታቸው፣ “ጉዳዩ ከሚታየው በላይ ጥልቅ ነው” በማለት ገልጸውታል።
ምንም እንኳን የኤርትራና የአሜሪካ መቀራረብ ለቀጠናው መልካም ቢመስልም በአሁኑ ወቅት ግን ይህ የመሳካት ዕድሉ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም የአሜሪካ እና ኤርትራ መቀራረብ እውን የሚሆን ከሆነ ግን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “በጣም አስፈላጊ እና ወሳኝ ከሆነችው ጎረቤታቸው ኢትዮጵያና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እርቅ እንዲያወርዱ ወይም እንዲቀራረቡ” አቅጣጫ የሚሰጣቸው መሆኑን የግድ ይጨምራል ብለዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






