አዲስ ሪፖርተር – የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በገበያ ላይ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርገዋል የተባሉ 13 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ። የክስ መዝገቡ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው የቀረበው።
በተጠቀሰው ወንጀል አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው 1ኛ አቶ ዲባራ ፉፋ (የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ 2ኛ አቶ ሹምአለም ብርሃኔ (የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ 3ኛ አቶ እስጢፋኖስ ጌትነት (የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ክትትል ባለሙያ)፣ 4ኛ አቶ ይላቅ አወቀ፣ 5ኛ አቶ አበላ ግዛው፣ 6ኛ አቶ ጌታቸው አሞኘ፣ 7ኛ ወ/ሮ በረከት ወርቁ፣ 8ኛ አቡሽ አያለ ገነት፣ 9ኛ አቶ ይልቃል የኔሰው 10ኛ የኛ ፔትሮሊዮም ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ 11ኛ አቶ እስማለም ምህረቱ፣ 12ኛ አቶ አባይነህ አወል እና 13ኛ አቶ ብስራት አበባው መሆናቸው ተመልክቷል።
በአንደኛ ክስ፣ 1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ከመመሪያ ውጭ ለተቋማት የነዳጅ ግዥ ፈቃድ በመስጠት እና ከ7ኛ ተከሳሽ (በረከት ወርቁ) ጋር በመመሳጠር ተከሳሿ 466,058 ሊትር ነጭ ናፍጣ በኮንትሮባንድ ለወርቅ አምራቾች እንድትሸጥ አድርገዋል። በዚህም በመንግሥት ላይ ከ8.4 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ፤ በገበያ ላይ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርገዋል። ግለሰቦቹ ስልጣንን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል እንደፈጸሙ ተገልጿል።
1ኛ፣ 6ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር 8ኛ ተከሳሽ በድምሩ ከ1 ሚሊየን 284 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ያለአግባብ እንዲያገኝ በማድረግ በመንግሥት ላይ ከ22.59 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስና የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ማድረጋቸው በክስ ሁለት ላይ የሰፈረው ምግለጫ ያስረዳል።
1ኛና 6ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን ያለአግባብ በመገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በሌላ ክስ 9ኛ ተከሳሽ (የኛ ፔትሮሊዮም ኃ/የተ/የግ/ማህበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ) ከህግ አግባብ ውጪ የነዳጅ አከፋፋይነት ፍቃድ እንዲያገኝ በማድረግ በመንግሥት ላይ ከ21. 3 ሚሊየን ብር በላይ ላይ ጉዳት ደርሷል።
1ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት እንዲሁም 9ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በአራተኛው ክስ 11ኛ፣ 12ኛ እንዲሁም 13ኛ ተከሳሾች የነዳጅ ጭነትና ግዥ ሀገር አቀፍ የነዳጅ ሰንሰለት ስርዓትን በመጣስ በአጠቃላይ 1.9 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መንግሥት እንዳይቆጣጠረው አድርገዋል ተብሏል።
መንግሥት ድጎማ ያደረገበትን ነዳጅ ከጅቡቲ በመጫን 17.8 ሚሊዮን ብር በላይና በገንዘብ የማይገመት ጉዳት በማድረስ በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግሥትን ሥራ በማይመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል። ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለግንቦት 10 ቀጠሮ መያዙ መያዙን የፋና ዘገባ ያስረዳል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






