አዲስ ሪፖርተር ዜና – ምርጫ መካሄድ እንደሌለበት በተቀመጠው አግባብ መሰረት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖች ውጤታማ ባለመሆናቸው አዲስ የድህረ ምርጫ የአመጽ ዕቅድ በአሜሪካ ኤርትራ ኤምባሲ ውስጥ መቀረቡ ታወቀ። ዕቅዱ የቀረበው ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ በተጓዙ ሰዎች ሲሆን፣ የዕቅዱ ዒላማም የሸዋ ኦሮሞ ኦሮቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች መሆናቸው ተሰምቷል።
የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ እንዳለው የተጠቀሰውን ዕቅድ ያቅረቡት ክፍሎች ኤርትራ ኤምባሲ የተወሰዱት በአቶ ነዓምን አማካይነት ነው። አቶ ነዓምን የአቶ ልደቱን አብሮነትን ጨምሮ በአንድ ላይ ጠቅ;ልለው “ምርጫውን ማሰናከል” የሚለውን ዕቅድ ለመተገበር የሚንቀሳቀሰውን ግብረኃይል የሚመሩን የሻዕቢያ ወኪል እንደሆኑ አብረዋቸው የሚሰሩትን በመጥቀስ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
የሻዕቢያን ዕቅድ በማስፈጸም የሚታወቁት አቶ ነዓምን ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ ያቀኑ ምልምሎቻቸውን ይዘው በአሜሪካ ኤርትራ ኤምባሲ የተገኙትም በዚሁ አግባብ ነው። የዜናው ሰዎች እንዳሉት እንግዶቹ ባቀረቡት ዕቅድ የኤምባሲው ኃላፊዎች ተደስተዋል።
ተባባሪያችን እንዳለው አዲስ አበባ ተቀምጠው ጥናቱን እንደሰሩት የተናገሩት እንግዶቹ፣ የሞዐ ተዋህዶ ክንፎች ናቸው። “ጥናት” ያሉትን ዕቅድ ያቀረቡት እነዚሁ የሞዐ ተዋህዶ ክንፍ አባላት ሸዋን የመረጡበትን ምክንያት “የአገዛዙ ዋና የድጋፍ ማዕከል ነው” በሚል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዋና የድጋፋቸው መሰረት የሸዋ ኦሮሞና ጅማ መሆኑን ያመለክቱት እነዚሁ ክፍሎች፣ ሌላው የኦሮሚያ ክፍል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሙስሊም በመሆኑ ለያዙት ዕቅድ ተመራጭ እንዳልሆኑ አመልክተዋል።
በሸዋ ኦሮሞ ላይ እንደሚሰራ የተመለከተው ዕቅድ የሚተገበረው ከምርጫው በኋላ ሲሆን፣ የአምጽ ዕቅዱን በአሜሪካ ኤርትራ ኤምባሲ ያቀረቡት ሰዎች፣ “አለን” ባሉት መረጃ ብልጽግናን ወክለው የሚመረጡት አብዛኛዎቹ የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ተከታዮች በመሆናቸው የሸዋን ኦሮሞ ለማነሳሳትና አመጽ ለማቀጣጠል አመቺ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዕቅዱ ሲቀርብ የነበሩ ምስክሮችን ዋቢ ያደረገው ተባባሪያችን እንዳለው፣ ጃዋር አምቦ ባዶ እግሩን የገባው፣ ሰላሌ ቄሲስ በላይን ይዞ ያመራው የሸዋ ኦሮሞዎችን ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሆነ አስታውሰዋል። ቄሲስ በላይ በማጭበርበር ወንጀል ተፈርዶባቸው እስር ላይ እንደሚገኙ ይታውሳል። ምንም እንኳን በአካሄድ ችግር ባይሳካለትም፣ የሸዋ ኦሮሞን እጁ ለማስገባት የሄደበት ርቀት የሸዋን ተጽዕኖ ስለተረዳና ያለፉትን ተሞክሮዎች ስላጤናቸው እንደሆነ የአመጽ ሰነዱን ያቀረቡት እንደ ማስረጃ ተጠቅመው አመልክተዋል።
“ሞዐ ተዋህዶ” የሚባለው የኃይማኖት ክንፍ በህቡዕ ፋኖን ሲያደራጅ እንደነበር፣ አሁንም ከንቅናቄው ጀርባ እንዳለ በይፋ መገለጹ የሚታወስ ነው። የሞዐ ተዋህዶ መሪ መሆናቸውን የሚናገሩትን መምህር ፋንታኹን ዋቄ የአንደኛው ፋኖ የሚዲያ ክንፍ ከሆነችው መዐዛ መሐመድ “በቃ አሁን ከፋኖ ለምን እጃችሁን አታነሱም” በሚል ላቀረበችላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ነበር ይህን ማረጋገጫ የሰጡት።
የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ በቀነኒሳ ሆቴል ከተካሄደው የሞዐ ተዋሕዶ ስብሰባ በኋላ የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ ከሶስት የሞዐ ተዋሕዶ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ የተገኙት መምህር ገብረመድኅን እንየው፣ መምህር ያረጋል አበጋዝና መምህር ፋንታኹን ዋቄ ሲሆኑ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የውክልና ጉዳይ ነበር።
“እናንተን ማን ወክሏችሁ ነው ይህንን ጉዳይ በኦርቶዶክስ ምዕመናን እና በቤተ ክርስቲያኗ ስም የምታራምዱት” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በዋነኛነት ያስረዱት ጉዳቱና ችግሩ የሚታይና ማስረጃም ሆነ ውክልና የሚያስፈልገው እንዳልሆነ ጠቅሰው የውክልና ጥያቄ ሤራዊና በውስጡ ትክክለኛ እሳቤ የሌለው የተንኮልና ውዳቂ ሃሳብ እንደሆነ በእንደምታ አስረድተው ነበር።
በኤርትራ ኤምባሲ የተገኙት የዚህ እሳቤ አራማጆች፣ በአቶ ነዓምን አማካይነት በጀትና ያስፈልጋል ያሉት እንዲሟላ አቅርበዋል። አቶ ነዓምን ይህ ሲያደርጉ በአመጽ አደራጅ ግብርኃይል ውስጥ ላሉት አመራሮች አለማሳወቃቸው ቅሬታ እንዳያስነሳ “ይህ የኃይማኖት ክንፍን ተጠቅሞ የሚሰራ ስራ በመሆኑ ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋር ሳይነካካ ቢሚስጢር ይከናውናል” የሚል መመሪያ እንዲሰጥ ተደርጓል። የህወሃት ክንፍ ሆነው የአምጽ አደራጅ ግብረኃይሉን የሚመሩት አቶ ልደቱን ጨምሮ ይህን እንቅስቃሴ እንዳያውቁ መደረጉ ግን ውሎ አድሮ መከፋፍል ሊያስነሳ እንደሚችል ጉዳዩን የሚከታተሉ ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም “እኛ ከግብጽና ከኤርትራ የሚከፈለን ገንዘብ የለም። አጉል መጠቀሚያ አታድርጉን” በማለት በግብረኃይሉ ስብሰባ ላይ የተናገሩ መኖራቸው ይታወሳል። ይህንኑ የቅሬታ ዘገባ ስናቀርብ አቶ ጂረኛና የኢትዮጵያን አድን ወኪል ዶከተር ሚካኤል “ይህ ግልጽነት የጎደለው አደረጃጀት ነው። በዚህ መልኩ መቀጠል አይቻልም” ብለው ፊት ለፊት አቶ ነዓምንን ተቃውመው ነበር።
“ሞዐውያን” በየሚዲያው በቀነኒሳ ሆቴል ስብሰባቸውም ሆነ በተለያዩ አውዶች ተካሂደው ይፋ በሆኑ ቪዲዮውች አማካይነት እንደተሰማው፣ የልዕለ እሴት ባለቤት ናቸው። ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለምዕመኗ ነው የቆምነው እንደሆኑ ይናገራሉ። ዳግም ወደ ቤተመንግስት መግባት በይፋ የቆሙለት ዓላማ ነው።
በአቶ ነዓምን አቅራቢነት አሜሪካ ኤርትራ ኤምባሲ ውስጥ ዕቅዳቸውን ያቀረቡት ክፍሎች ይህንኑ የሞዐ ተዋህዶ መዋቅር እንደሚጠቀሙና በይፋ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የጸጥታና የድህንነት ሁኔታን የሚከታተለው ጥምር ኃይል በመሳሪያ የተሞከሩ ሙከራዎች በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ስለማያመጡ የኃይማኖት ልዩነት ለማስነሳት ሙከራ እንደሚደረግ አስቀድሞ ማስታወቁ አይዘነጋም።
መምህር ፋንታኹን ዋቄም ሆኑ ሌሎች የሞዐ ተዋህዶ አመራር እንደሆኑ የሚናገሩ ስለዚህ ዕቅድ በይፋ ያሉት ነገር የለም። በአሜሪካ ኤርትራ ኤምባሲ የቀረበው ይህ አዲሱ የድህረ ምርጫ ዕቅድ በእና መምህር ፋንታኹን ዋቄ ዕውቂያ ስለመካሄዱ እዛቸውን በስልክ ለማግኘት ቢሞከርም አልተቻለም። ዝግጅት ክፍሉ በማናቸውም ጊዜ ፈቃዳቸው ከሆነ አስተያየታቸውን ለማከል ይወዳል። የኤርትራ ኤምባሲ ኝ በተደጋጋሚ ጥያቄው ቢቀርብለትም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






