በትብብሩ ውስጥ የሚሰማው “ውዥንብር” በአጭሩ “እሰሩንና አጀግኑን” ነው “እስር ሲያምራችሁ ይቅር”

Date:

“ልብ ላላችሁ እውነቱ ይህ ነው። ብዙ ዝርዝርም አለ። “መጀመሪያ ዕውቅና ባልሰጡት ምርጫ ላይ ‘ግቡ አትግቡ’ የሚል አተካራ ውስጥ መግባት አያስፈልግም… በትብብሩ ምክር ቤት የተወሰነ ምንም ዓይነት ውሳኔ የለም” — አቶ አብርሃም ጌጡ (የመኢአድ እና የትብብሩ ፕሬዝዳንት)

አዲስ ሪፖርተር ዜና | ነጻ አስተያየት

በቅርቡ በተጠናቀቀው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘው ጥምረትና አባላቱ እያሳዩት ያለው አቋም፣ ስብስቡ ግልጽ መመሪያና የጋራ የፖለቲካ መርህ የሌለው፣ እንዲሁም በሕግና መዋቅር ያልተደገፈ የዘፈቀደ አሠራር የሚከተል መሆኑን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል። አባላቱም በተለያየ ደረጃ የሚያንጸባርቁት ሐሳብ ይህንኑ እውነታ ያረጋግጣል። ቅዠቱም ሩጫውም “እሰሩኝና ልጀኝ፣ እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” ጨዋታ ነው።

የፓርቲው አመራሮችና በምርጫ አሸናፊ የሆኑት አባላት በሕዝብ ድምጽና በምክር ቤት መግባት ዙሪያ የሚሰጧቸው እርስ በርሱ የሚጋጩ መግለጫዎች፣ የጥምረቱን ስትራቴጂያዊም ሆነ ፖለቲካዊ መዋቅር መበላሸት በግልጽ የሚያጋልጥ ሆኖ ተገኝቷል።

የመረጣቸውን ሕዝብ ገፍትቶ በፓርላማ “ግቡ/አትግቡ” መመሰቃቀል

ትብብሩ “ምርጫው መመዘኛ አያሟላም፣ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል” በማለት ሂደቱን ሙሉ በሙሉ እንደማያውቀውና አሸናፊዎቹም ወደ ምክር ቤት እንዳይገቡ ቀደም ሲል መወሰኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጌትነት ወርቁ ቢገልጹም፣ የትብብሩ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ ግን ይህንን ውሳኔ ውድቅ አድርገውታል። ይህ ሁኔታ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ አቶ ጌትነት በጓሮ ሌሎች የማያውቁትን ተልእኮ ከውጭ አካላት ተቀብለዋል የሚለውን አሉባልታ ያጎላዋል።

“መጀመሪያ ዕውቅና ባልሰጡት ምርጫ ላይ ‘ግቡ አትግቡ’ የሚል አተካራ ውስጥ መግባት አያስፈልግም… በትብብሩ ምክር ቤት የተወሰነ ምንም ዓይነት ውሳኔ የለም” — አቶ አብርሃም ጌጡ (የመኢአድ እና የትብብሩ ፕሬዝዳንት)

እንግዲህ ፕሬዝዳንቱ የማያውቁት፣ ለአቶ ጌትነት ብቻ የሚታያቸው ሕጋዊ አግባብ ምን ይሆን? ከላይ እንደተጠቀሰው በጓሮ የዶለቱት አጀንዳ ከሌላቸው በቀር።

የትብብሩ ሰብሳቢ ከሰጡት ማረጋገጫ አንጻር እነ አቶ ጌትነትና “ውርጋጥ” የተባለችው ሚስጥረ ያዘጋጁት መግለጫ፣ ትብብሩ በይፋዊ መዋቅሩ ተወያይቶ የወሰነው ወጥ አቋም እንደሌለው የሚያሳይ ነው። ይህም ይፋዊ መግለጫዎቹ ተቋማዊ ውሳኔን ሳይሆን የግለሰቦችን ስሜት ተከትለው የሚወጡ መርህ አልባ መሆናቸውን ከማረጋገጥ ውጪ ሌላ ምንም የሚነግረን ነገር የለም።

በሕግና በመዋቅር ያልተደገፈ አደረጃጀት

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ወይም ጥምረት ሲመሰረት አባላቱን የሚገዛበት፣ ዲሲፕሊን የሚያስከብርበትና የጋራ ውሳኔ የሚያሳልፍበት ሕጋዊ ማዕቀፍ ሊኖረው ይገባል። ሆኖም የትብብሩ ፕሬዝዳንት በራሳቸው አንደበት እንደተናገሩት፦ “ትብብሩ የተመሰረተው ለጊዜያዊ ጉዳይ ብቻ ነው። ከላይ እስከ ታች የተዘረጋ የራሱ መዋቅር የለውም። በአባላቱና በዕጩዎቹ ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ የመውሰድ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሥልጣን የለውም” አቶ ምርጫው ብናሸንፍም አገር መምራት አንችልም ብለው አስቀድመው የተናገሩት ገና ድሮ የገባቸው ገብቷቸው ነበርና አመስኛቸዋለሁ።

ፕሬዝዳንቱ እውነታውን በዚህ መልኩ ካስረዱ፣ ታዲያ አቶ ጌትነት “የመረጣቸውን ሕዝብ ድምጽ አክብረው የሚቀበሉትን በዲሲፒሊን እንቀጣለን፣ እናባርራለን” እያሉ ከመሰሎቻቸው ጋር የሚደሰኩሩት ማንን ለማስደሰትና የትኛውን ሒሳብ ለማወራረድ አስበው እንደሆነ የሚመለከተው አካል ሊያጠናው ይገባል።

ጥምረቱ በሕግ ያልተደገፈ፣ ጥንካሬ የሌለውና እንዲሁ በይስሙላ የተፈጠረ ስብስብ ሆኖ ሳለ፣ ደንብ የሚተላለፉትን የሚያርቅበትና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መዋቅር ሳይኖረው “እርምጃ ይወሰዳል” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ሲናፈስ የነበረው ወሬ የዚሁ መርህ አልባ አሠራር ማሳያ ነው። ይህ ሁኔታ ከአቶ ጌትነት ልዩ አጀንዳ የሚቀዳ ስውር ግን ግልጽ ሴራ መኖሩን አመላካች ነው። አቶ ጌትነትና የኢህአፓን ያደፈ ካባ የደረበችው ባልደረባቸው፣ በባልደረቦቻቸው ሊጠኑና ሊመረመሩ እንደሚገባ የሚጠይቁ ሰዎች እያደር እየበዙ የሄዱትም በዚሁ መነሻ ነው።

“ያረጀና ያፈጀ አካሄድ”፦ ውል የተገባበት የአመጽ ሕልም

በትብብሩ ስም ተወዳድረው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ወንበር ያሸነፉት አቶ ሙሉጌታ አበበ፣ የትብብሩን “ምክር ቤት አንገባም” የሚል የቀድሞ አቋም እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚንጸባረቁትን ሐሳቦች “ከ20 ዓመታት በፊት የነበረ ያረጀ ያፈጀና የማያወጣ አካሄድ” በማለት አጣጥለውታል። ማጣጣልም ሳይሆን ለማሰብ እንኳ የማይመች ምናምንቴ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

እነ አቶ ጌትነት ግን በጓሮ ተደራድረው ሊያስነሱት ያሰቡት ትርምስ ሕልም ሆኖ በመቅረቱ መርህ፣ ሕግና ዘመኑን የዋጀ እሳቤ ምናቸውም አይደለም። ደም በፈሰሰበት ሁሉ ተንደርድረው በመግባት የአዞ እንባ ሲያፈሱ የሚታዩት፣ ሕልም የሆነውን ትርምስ ለመቀስቀስ ካላቸውና ከተሸጡበት ውል መነሻነት በመሆኑ፣ በአካባቢያቸው ያሉ አካላት ራሳቸውን ከዚህ ነውር ሊያርቁ ይገባል።

አሸናፊዎቹ ዕጩዎች የፓርቲውን/የትብብሩን የፖለቲካ ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ወደ ምክር ቤት እንደሚገቡ በተዘዋዋሪ የገለጹበት ሁኔታ፣ በትብብሩ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ልዩነትና መርህ አልባ ሩጫ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም አሸናፊዎቹ በሙሉ የመኢአድ አባላት መሆናቸውን ይፋ ማድረጋቸው፣ በትብብሩ ሥር ያሉ ፓርቲዎች በጋራ ዓላማ ሳይሆን በየግል ጥቅማቸው ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸውን ያሳብቃል። በመሆኑም እነ አቶ ጌትነት “ሲቀዘቅዝ በእጄ” የሚለውን የብልጣብልጥ ፖለቲካ ለመጫወት እንኳ አያበቃቸውም።

የዚሁ ቡድንና የውጭው ሰንሰለት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሁም ሴራ መመርመር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከባሕር ማዶ ሆነው ሲነዷቸው የነበሩትን ባንዳዎች ገድል አሰባስቤ እመለሳለሁ። ከዚያም በገሃድ ከጠቀስኳቸው አካላት ጋር ፊት ለፊት እንገጥማለን።

በአጠቃላይ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ያሳየው እርስ በርስ የሚጋጭ የፖለቲካ ትርክት፣ ስብስቡ አገራዊ ኃላፊነትን ለመሸከም የሚያስችል ሕጋዊ መዋቅር፣ ግልጽ መመሪያና ወጥ የሆነ የፓርቲ ዲስፕሊን የሌለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። የፓርቲ አመራሮች አንዱ የወሰነውን ሌላው የሚያፈርስበት፣ ዕጩዎች ደግሞ የፓርቲውን መመሪያ “ያረጀና ያፈጀ” በማለት የሚያጣጥሉበት አሠራር ትብብሩ መርሃ አልባ በሆነ መንገድ እየተመራ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ለዛሬው ይኸው ነው። “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል ብዬ ስስናበት ” በማለት መዓዛ መሃመድ የምትባለው ባልደረባችሁ ” ይህ መንግስት አላስር አለኝ። መታሰር እፈልግ ነበር” ስትል ለእነ እንትና የተናገረችውን በማስታወሰ ነው። እናም እስር ሲያምራቹህ ይቅር!!

ይህ ነጻ አስተያየት ስማቸውን ለጊዜው ያልገለጹ የአመራሮቹ የቀርብ ሰው ነው። ምላሽ ወይም ማስተባበያ ካለ እናትማለን።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related