አዲስ ሪፖርተር (ዋሽንግቶን) — “ኢትዮጵያ ወደብ ልትወስድባችሁ ነው። ድሬደዋና የሶማሌ ክልል ወደ ኦሮሚያ ሊካተቱ ነው፤ ሶማሊላንድንም ልታስገነጥል ነው” ወዘተ በማለት ንግግር ያደረጉት በትውልደ ኦሮሞነታቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሳ ናቸው። ፕሮፌሰሩ ይህንን ሲሉ ከጎናቸው ያስቀመጧቸው ፕሮፌሰር መሐመድ ሃሰንን እና አብዲራህማን ማሃዲ (ማዴይ) የሚባሉትን የሞቃዲሾ ተወላጅ ነበር።
እ.ኤ.አ እስከ መጋቢት 2025 ዓ.ም ድረስ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩት አብዲራህማን ማሃዲ (ማዴይ)፥ ኦጋዴንን ለመገንጠል ከተመሰረተው ኦብነግ (ONLF) ከተባረሩ በኋላ ወደ ኤርትራ የተመለሱ እና በአሁኑ ወቅት ምንም ተዋጊ ኃይል የሌላቸው መሆኑን በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክሩባቸዋል። ማዴይ በቅርቡ በሱዳን በተካሄደው የ“ጽምዶ” ስብሰባ ላይ ከአስመራ በቪዲዮ ኮንፈረንስ (Zoom) ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል ፕሮፌሰር መሀመድ ሃሰን ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በቀጠናው ተቀባይነት እንዲኖራቸው የፖለቲካ ሽፋን የሚሰጡ፣ መጽሐፋቸውን በማረም እንዲሁም መግቢያና መዝጊያውን በማዘጋጀት ቁልፍ ሥራ የሠሩ ናቸው። በዚህም ተግባራቸው በአስመራ በተደረገ ሕዝባዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአደባባይ የተመሰገኑ ሲሆን፥ ሥራና ሙያቸውን መነሻ በማድረግ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስን “ነብይ” የማድረግ ሥራ ላይ በታማኝነት እንደሚንቀሳቀሱ በርካታ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ባለፈው ሰኔ 19 ቀን 2026 ዓ.ም (June 19, 2026) በሎንዶን በዝግ የተካሄደውና “በምስራቅ ኢትዮጵያ የትጥቅ ትግልን ማቀጣጠል” በሚል መሪ ቃል የተመራውን ስብሰባ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል፣ ከላይ የተጠቀሱትን ግለሰቦች እና አንዳርጋቸው ጽጌን በመያዝ ማካሄዳቸውን የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል “ከምርጫው በፊት ትርምስ ማስነሳት ቀዳሚ አጀንዳዬ ነው” በሚል መርህ ለተቋቋመው ግብረ-ኃይል በቦርድ ሊቀመንበርነት እንዲመሩ ከተመረጡ በኋላ፥ “አልፈልግም፣ ሌሎች ኃላፊነቶች አሉብኝ፤ የቦርድ ሰብሳቢው የአደባባይ ሰው መሆን የለበትም” በማለት ያቀረቡትን ማመልከቻ አዲስ ሪፖርተር ቀደም ሲል ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ፕሮፌሰሩ “እንዴት ምስጢሩ ወጣ?” በሚል ለባልደረቦቻቸው ከፍተኛ ወቀሳ የሰነዘሩ ቢሆንም፥ መድረኩ ግን ለውይይት ዕድል ለመስጠት ጥረት አድርጎ ነበር።
የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ በዚሁ መነሻነት ለፕሮፌሰሩ በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው በመደወል፦ “እንዴት ከሶማሊያ ተወላጆች ጋር ተቀምጠው ኢትዮጵያ ላይ ያሴራሉ? የኦሮሚያ ክልል ድሬደዋንና የሶማሌ ክልልን ለመጠቅለል ስለማሰቡ ምን መረጃ አለዎት? እውን እያራመዱ ያሉት የራስዎን ሐሳብ ነው? ከግብፅ እና ከትህነግ ጋር በቀጥታ አብረው እንደሚሠሩና በተደጋጋሚ በሞቃዲሾ፣ ቱርክና ኬንያ ታጣቂዎችን ለማደራጀት እንደሚመላለሱ የሚነገረውን እንዴት ያብራሩታል?” የሚሉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ሞክሯል።
ይሁን እንጂ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል “የሚከፈሉ ሚዲያዎች ሕዝባዊ ትግሉን ለማኮላሸት እየሠሩ ነው። አዲስ ሪፖርተር አንዱ ነው” በማለት በተለያዩ ወቅቶች የተዘገቡ ዜናዎችን ሊንክ በማድረግ ቅሬታ ከመሰንዘር ባለፈ፥ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከሃያ ጊዜ በላይ በስልክ ቢሞከርና የጽሑፍ መልዕክት ቢላክላቸውም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
በዚሁ ሳቢያ ዘገባውን አቆይቶ ለመልቀቅ የተገደደው ተባባሪያችን እንደገለጸው፥ የሶማሌ ክልል ተወላጅ እንደሆኑ በማስመሰል በሎንዶኑ የዝግ ስብሰባ ላይ እንዲመክሩ ከፕሮፌሰሩ ጋር አብረው የተጓዙት አካላት ከስብሰባው በኋላ የሁለት ቀናት ወርክሾፕ (የሥልጠና መድረክ) አዘጋጅተዋል።
ከሶማሊላንድ፣ ከጅግጅጋ እና ከናይሮቢ በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑበት የዩቲዩብ መድረክ ላይ በዚሁ ወርክሾፕ የተካሄደውን ሥልጠናና አጀንዳ በማንሳት አጋልጠዋል። በተለይም ተቀማጭነታቸው በሎንዶንና በአሜሪካ የሆኑ የሶማሊላንድና የኢትዮጵያ ተወላጆች በሰጡት መረጃ መሠረት፥ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል “ባላችሁ የግንኙነት አግባብ ሁሉ አሰራጩ” በማለት ያስተላለፉት መመሪያ ከፍተኛ ቅሬታን ቀስቅሷል።
በግልጽ በተካሄደው ወርክሾፕ ላይ ቅሬታቸውን የገለጹ ተሳታፊዎች በሶማሌ ክልል የሚካሄዱትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመጥቀስ፥ “መንግሥት ይህንን ያህል ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በከፈተበት ሁኔታ፥ የእነሱ ሐሳብ ከልማቱ ጋር ይጋጫል” በማለት ጥያቄ አንስተዋል። የፕሮጀክቶቹን ስም ዝርዝርና የተመደበውን በጀት በመጥቀስ፣ የተሠሩ ከፍተኛ የልማት አውታሮችና መሠረተ-ልማቶችን በመዘርዘር “ይህንን ክልል አተርምሰን ምን ልናገኝ ነው?” በሚል በቁጣ የጠየቁ ተሳታፊዎች መኖራቸውን ምንጮች አመልክተዋል።
የወርክሾፑ ተሳታፊዎች እንዳሉት ከሞቃዲሾ ተወላጆች መካከል የድጋፍ አስተያየት የሰጡ ቢኖሩም፥ የኦብነግ መሪ ተብለው ለቀረቡት ግለሰብ ግን ከጅግጅጋ ወደ ሎንዶን ያመሩ የሶማሌ ክልል ተወላጅ “የተወለድከው ሞቃዲሾ ነው። አንተ የሞቃዲሾ ሰው ነህ” በማለት ክፉኛ ወቀሳ ሰንዝረውባቸዋል።
በዝግ በተካሄደው ስብሰባ ላይ “ከኦላ (OLA)፣ ፋኖ፣ ቤኒሻንጉል፣ ትህነግ፣ ጋምቤላ እና በሱዳን ካሉ ኃይሎች ጋር የተፈጠረው ጥምረት የሶማሌ ክልልና የአፋር ክልል ነፃ አውጪ ታጣቂዎችን አካቶ ወደ ኦፕሬሽን ለመግባት ከጫፍ መድረሱ” ተመልክቷል።
ይህንን ሥራ በበላይነት የሚመሩት ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል፥ “በሰላማዊ ተቃውሞ እናደራጃለን” ከሚለው የአብሮነትና የአቶ ነዓምን ዘለቀ የጋራ መድረክ ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ እንደሆኑ ይታወቃል። የዚህ ስብስብ አመራሮች በተደጋጋሚ “ኢትዮጵያን እናድን” የሚል መግለጫ የሚሰጡ ቢሆንም፥ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ማንነታቸው በውል ከማይታወቁ አካላት ጋር በስተጀርባ የሚሠሩት ሥራ በባልደረቦቻቸው ዘንድም ጥያቄ እያስነሳባቸው ይገኛል።
ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል “ኦሮሞ ድሬደዋን እና የሶማሌ ክልልን ሊጠቀልል ነው። ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን ልታስገነጥል ነው፤ የባሕር በራችሁን ልትወስድ ነው” በሚል የሞቃዲሾ ተወላጆችን ለማነሳሳት የተጠቀሙበት አግባብ በሌሎች ወገኖች፥ በተለይም በሶማሊላንድና በሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲሁም ዜናውን በሰሙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ሐዘንን ፈጥሯል።
የሻዕቢያን አጀንዳ ተሸክመው ከመጡ ኃይሎች ጋር በመሆን በምስራቅ አቅጣጫ ተዋጊ ኃይል ለማደራጀት ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ከወራት በፊት መዘገባችን አይዘነጋም።
ይህንን አካሄድ የሚቃወሙ ወገኖችን አነጋግረን ያዘጋጀነውን ዝርዝር ዘገባ በቀጣይ የምናቀርብ ይሆናል። ይህ እንቅስቃሴ በአሜሪካ ያሉ ሦስት ወገኖች የየራሳቸውን ጥምረት (ጽምዶ) ለመመሥረት እያደረጉት ያለው እሽቅድምድም አካል ስለመሆኑ ለአሁኑ አዲስ ሪፖርተር ማረጋገጥ አልቻለችም።
ይሁን እንጂ በአሜሪካ ለክልል ነፃ አውጪዎች ወኪል በመሰየም የተለያዩ አካላትን ለማግባባት እነ ሻለቃ ዳዊት፣ እነ ፕሮፌሰር ባደግ እንዲሁም በትህነግ በኩል ያለው ሩጫ መጧጧፉን ጠቅሰን፥ ለሁለት የክልል ነፃ አውጪ ወኪል ነን ባዮች ለእያንዳንዳቸው አሥር ሺህ ዶላር መሰጠቱን የዋሽንግቶን ተባባሪያችን መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






