የስብሰባ መረጃ በማያያዝ ብሔራዊ አገራዊ የምክክር ሂደቱ እንዳይሳካ ዘመቻ እንዲከፈት ከስምምነት መደረሱን አስቀድመን ሪፖርት አድርገን ነበር። ራሳቸውን “የሰላማዊ ትግል አባት” አድርገው የሚያቀርቡ ቀበኞች፣ የምክክር ሂደቱን ለማጨናገፍ በሻዕቢያ በኩል በጀት መመደቡን እነዚሁ አካላት ሲናገሩ እና በጀት ሲመድቡ የሚያስረዳ መረጃም ይዘን ነበር። ምክክሩን የማጨናገፉ መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በውይይት ከፈቱ እና አንድ ከሆኑ ጥቅማቸው የሚነካባቸው አገራትና ቡድኖች “አድርጉ” ያሉትን በፕሮፓጋንዳና በጠብመንጃ በማከናወን ኢትዮጵያን የጦርነት ቀጠናና የጎበዝ አለቃ መፈንጫ ማድረግ ነው። ተወደደም ተጠላም የከሸፉት ኦፕሬሽኖች በሙሉ የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነበሩ። የፕሮፓጋንዳው ክንፍ ፈርሶ ወደ ግልጽ ቅጥፈት ሲሸጋገር፣ ባለጠብመንጆቹ የጠየቁትን ጠይቀዋል ወደፊት ይፋ የርሚሆን ይሆናል።
አዲስ ሪፖርተር፣ አዲስ አበባ — በተለያዩ አገራት የሽግግርና የብሔራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ የክልላዊ ወይም የጂኦፖለቲካ ተፎካካሪ አገሮችና ቡድኖች የራሳቸውን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ በጎረቤት አገር የሚካሄድ አገራዊ የመግባባት ሂደት እንዲከሽፍ ወይም በጥርጣሬ እንዲሞላ የተለያዩ የስነ-ልቦና እና የመረጃ ጦርነቶችን (Disinformation Campaigns) ማካሄዳቸው በጂኦፖለቲካ ታሪክና አሰራር ውስጥ የሚጠበቅና የተለመደ ክስተት ነው። ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ከዛው አገር ውስጥ በሚቀጥሯቸው ተላላኪዎች አማካይነት ነው።
የተለያዩ የጂኦፖለቲካ ተንታኞችና የደህንነት ባለሙያዎች እንደሚያመላክቱት፣ የውጭ ኃይሎች በሌላ አገር በሚካሄድ አገራዊ ምክክር ላይ ጣልቃ የሚገቡበትና የመረጃ ጦርነት የሚያካሂዱት በተለያዩ ስልቶች ነው።
ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ብሔራዊ መግባባትን የምትፈጥረው አገር፣ ወደ አንድነት፣ አገራዊ ጥንካሬና መረጋጋት ካመራች፣ በክልላዊና ዓለም አቀፍ ድርድር ላይ ያላት አቅም ይጨምራል። ይህ ደግሞ በውሃ፣ በድንበር ወይም በጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ከሚፎካከሩት አገራት ወይም ቡድኖች ጥቅም ጋር ስለሚጋጭ፣ አገሪቱ በውስጥ ውዝግብና ጦርነት እንድትጠመድ፣ እንዲሁም ሰላሟ እንዲናጋ አጥብቀው ይሰራሉ።
ለዚህም ውጥናቸው በሕዝብና በኮሚሽኑ መካከል የነበረውን እምነት መሸርሸር ቀዳሚ አጀንዳቸው ነው። ምክክሩ “የአንድ ወገን ነው፣ ውጤት የለውም ወይም የይስሙላ ነው” የሚሉ ትረካዎችን (Narratives) በማህበራዊ ሚዲያ እና በገንዘብ በሚደገፉ የመገናኛ ብዙኃን በማሰራጨት የሕዝቡን ተሳትፎና እምነት ለመሸርሸር ሌት ተቀን ይተጋሉ።

“በሀገራዊ ምክክር የቀረቡ ሐሳቦች ለፖለቲካ ልምምዳችንና ለሀገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ ትልቅ ነው። የሀገራዊ ምክክር ውጥን እና ዓላማ ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ፣ ዘመንን ሊያሻግሩና ሀገርን ሊያጸኑ በሚችሉ የሐሳብ አውዶች ዙሪያ ለመወያየት እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ያየነውም ይሄንኑ ነው።” ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
የተቃዋሚና የብሔር ኃይሎችን አቋም ማክረር ሌላው ስልታቸው ሲሆን፣ በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ወይም ለመሳተፍ የሚነሳሱ ወገኖችን “የመንግሥት አሻንጉሊት ሆናችሁ” በሚል ፍረጃ የሐሰት መረጃ በመንዛት ሂደቱን ጥለው እንዲወጡ ግፊት ያሳድራሉ። እነሱ የተሻሉና አገር ወዳድ መስለው ለብሔራዊ ሰላም የሚረባረቡትን ወገኖች “ባንዳ፣ የታሪክ ተወቃሽ” እያሉ ያሸማቅቋቸዋል።
ከዚሁ ሁሉ ሩጫቸው በተጨማሪ የደህንነት ስጋት እንዲሰፋ በድንበር አካባቢዎችና በግጭት ቀጠናዎች ግጭቶች እንዲስፋፉ በማድረግ የምክክሩ የሕዝብ ተወካዮች ከሁሉም አካባቢ ተወክለው ውይይት እንዳይካሄድ ያስተጓጉላሉ። ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ በዚህ መሰሉ ሴራ በብሔራዊ ምክክር፣ እርቅና ሰላም ለማካሄድ የሞከሩ አገራት በውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ በሆኑ ወይም የራሳቸውን ጥቅም ባስቀደሙ ባንዳዎች አማካይነት ብዙ ዋጋ እንደከፈሉ ዓለም ምስክር ናት። ኢራቅ፣ የመን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሊቢያ ወዘተ ይጠቀሳሉ። የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “ኢትዮጵያውያን እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው ያለፉ ጠንካራና ጽኑ ሕዝቦች ናቸው” እንዳሉት አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከስምምነት ደርሶ ለአሁኑ የበቃው ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ አልፎ ነው።
ከላይ ከተገለጹት ውስጥ በኢትዮጵያ ያልሆነው ምንድን ነው?
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ፣ በፓርላማ የዜና አውድ ይፋ በተደረገበት ቀን “እንደሚፈርስ አስጠነቀቀ” ከሚለው ታሪካዊ የክህደት ዜና ጀምሮ፣ ከላይ በተገለጸው አግባብ ዘመቻ እንደተጀመረበት የሚታወስ ነው። እንደተቋቋመ፣ ዜጎች ገና ሳይሰሙ የማፍረስ ዘመቻ የተከፈተበትና ላለፉት አራት ዓመታት ከላይ በተዘረዘሩት መነሻዎች አጀንዳና ስልት እየተቀያየረ ሲቀጠቀጥ ነበር።
“ምክክሩ፤ ከተመካከርን፣ ከተነጋገርንና ከተደማመጥን ውጤት ላይ እንደምንደርስ ያየንበት ነው” የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
ምክክሩ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያን እንደ አገር ስጋት ላይ እንዲወድቁ ያደረጓቸውን “በሕግና ሕገ-መንግሥት” የታሰሩ ጉዳዮችን ያለማቅማማት እንዲከስሙ የሚያደርግ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በፈጠራ ትርክትና ከረዥም ዓመት በፊት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጸሙ ግድፈቶችን በመቆስቆስ ሕዝብን ከሕዝብ ለማፋጀት ዘወትር ለሚተጉ በሩን የሚዘጋ ውሳኔ ስለሚያጸድቅ ዘመቻው በረበብ እንዲከፈትበት ሆኗል።
ያቆዩትን ብንተዋቸው እንኳ ምክክሩ ሊጀመር ሳምንታት ሲቀሩ “ብልጽግና አጀንዳዎቻችንን ሊነጥቀን ነው” በማለት በሻዕቢያ በሚመራውና በሚደገፈው “ሕዝባዊ አመጽ አደራጅ የጋራ መድረክ” ላይ በጀት ተመድቦ ዘመቻ እንዲከፈት አቋም ተይዞ ነበር። በተመረጡ ሻዕቢያ ክፍያ በሚያከናውንላቸው ሚዲያዎችና፣ በተቃዋሚ ጎራ ባሉ ድርጅቶችና አገር ቤት ባሉ ፓርቲዎች አማካይነት በመናበብ ኮሚሽኑ እና አመራሮቹ ላይ በፈጠራ ዘመቻ እንዲከፈት በተወሰነው መሠረት ተፈጸመ።
በገፊና ጎታች ስልት አንዱ ሌላውን እየተቀበለ የምርጫ ኮሚሽኑና አባላቱ ይወቀጡ ጀመር። አመራሮቹ “ሌቦች፣ ባንዳዎች፣ የኦህዴድ አገልጋዮች፣ ከሐዲዎች…” ወዘተ እየተባሉ ስም ወጣላቸው። ስማቸው እስከ አያትና ቅድመ አያት እየተቆጠረ በብሔር ተፈረጁ። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ “ተሰብሳቢዎች በደህንነት ሰዎች ታሰሩ፣ ታፈኑ፣ ወዳልታወቀ ቦታ ተወሰዱ፣ ተደበደቡ…” ወዘተ እየተባለ ሰበር ዜና ይሰራ ጀመር።
“ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ የተካሄደው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ታሪካዊ እና ለአፍሪካ አህጉር አርአያ የሚሆን የሰላም ሂደት ነው” የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ
እያንዳንዱን ቀን ከምክክር አዳራሹ የሚወጡ መልካም ዜናዎች በበለጠ የፈጠራ ዜና እየተመረቱ ሕዝብ እምነቱ እንዲሸርሸር የተከፈላቸው ሁሉ በበሉት መጠን የሐሰትና የፈጠራ ዘመቻቸውን አጧጧፉ። ከዚሁ ጎን ለጎን ከየአካባቢው ተወክለው የመጡ የምክክሩ አባላት ላይ ማስፈራሪያ ሳይቀር ተበተነ። የኢትዮጵያን መከራ ለመቅረፍ የታተሩ “ፀረ-ኢትዮጵያ” ተብለው ሲወገዙ ከረሙ።
ከዚሁ ጎን ለጎን አገሪቱን በተለያዩ አቅጣጫዎች በጦርነት ለመጥበስ ከግብፅ፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራ ጋር ያበሩ የአገር ውስጥ ታጣቂዎች “ጽምዶ” የሚባል ሕብረት ፈጥረው ምክክሩን ለመቅደም ተራወጡ። ረጋ ብለው ለሚያስቡ ከምርጫው ጀምሮ በሰላማዊ ትግልና በጠብመንጃ ተደግፎ ያልተሞከረ የትርምስ አጀንዳ አልነበረም። በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ሰላም ነስቶ፣ አተራምሶና የጦርነት አውድማ አድርጎ ለማሽመድመድ ያልተሞከረ ሙከራ የለም። የዚህ ሁሉ ሴራ አከፋፋዮች በይፋ መፍረሳቸውን ያስታወቁ እንዳሉት በብሄር እሳቤና በብስጭት ሳቢያ ተስፋ ቆርጠው ለጊዜው መሰብሰብ እንኳን አልቻሉም።
በሕጉ መሠረት የኮሚሽኑ ሕጋዊ ሥልጣን ገደብ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑ፤

የኮሚሽኑ ዋነኛ ሚና የሕዝብን አጀንዳዎች ሰብስቦ የመፍትሔ ምክረ-ሐሳብ ማዘጋጀትና ማቅረብ እንጂ፣ የትኛውንም የፖለቲካ ወይም የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ውሳኔዎች የመወሰንና የመተግበር ሕጋዊ ሥልጣን የለውም። ሊኖረውም አይችልም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ኮሚሽኑን አራጊ፣ ፈጣሪ፣ ሕገ-መንግሥት ቀዳጅና የፖለቲካ ውሳኔ የሚወስን አካል በማድረግ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ውሳኔዎች እንደተወሰኑ በማስመሰል ያልተቆፈረ የጥፋት ጉድጓድ አልነበረም። ይህ ሁሉ ሲሆን የነበረው በክፍያና ለጠላት ኃይሎች በተገዙ የኢትዮጵያ “እንግዴ ልጆች” መሆኑ ሐዘኑን ቢያበረታውም፣ ባንዳነት ጌጣቸው የሆኑ እነዚህ ሴረኞች ሕዝብ በሂደት አንጥሮ ስለለያቸው ልክ እንደ ምርጫው ይህም ከስሟል። አልተሳካም።
476 ምክረ-ሐሳቦችን ተቀብሎ፣ መርምሮ፣ ወደ ሕግ ቀይሮ እና በበጀት ደግፎ የመተግበር ፍጹም ሥልጣንና ኃላፊነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) እና የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ቀጣይ ሥራ መንግሥት ምክረ-ሐሳቦቹን በተግባር እያዋላቸው መሆኑን የመከታተልና የመገምገም፣ የማሳሰብ፣ እና መልካም ዜጎች ለአገራቸው የሚያደርጉትን ማድረግ ነው። ከዚህ የዘለለ ነገር የላቸውም።
“እኔ ከሀገሬ አልኮበለልኩም ፣አልሸሸሁም ፣ በቀረችኝ አጭር እድሜየም ሀገሬን ነው ማገልገል የምፈልገው “ፕሮፌሰር መሰፍን አርዓያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያደረጉትን ንግግርና ያስተላለፏቸውን ዋና ዋና መልእክቶች መሠረት በማድረግ የተቀናጀ የዜና ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ዕለቱ የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት የሚጸናበት፣ የጋራ መሻትና ተስፋ የተገለጠበት ልዩ ቀን መሆኑን ያስገነዘቡት በዚሁ መመዘኛ ነው።
ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ጊዜያዊ የፖለቲካ መድህን ለመፈለግ ሳይሆን ለአገር ዕድገትና ዘላቂ ፍኖት ለመተለም የተካሄደ ነው። በውይይቱ ወቅት የተቃረኑ እይታዎች ለጋራ ጥቅም የሚውሉበትና አዳዲስ ሀሳቦች የሚወለዱበት አዲስ አገራዊ መድረክ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ምንም የሚያለያይ ጉዳይ እንደሌለ በማስመሰል፣ ተሰብሳቢዎች እንዳልተስማሙ፣ በበርካታ ጉዳዮች መለያየታቸው በስፋት ሲዘገብ ቢከርምም የተስማሙባቸውን ጉዳዮች በስምምነት፣ ልዩነት ያሰነሱትን የአዲስ አበባ ጉዳይ በልዩነት ይዘው አጠናቀዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓውድ ከተቃርኖና ከኃይለ-ቃል በጸዳ መልኩ፣ በይቅርታ፣ በመከባበርና በመደማመጥ ላይ የተመሠረተ አዲስ መንገድ መጀመሩን ኮሚሽኑ አሳይቷል።
ፕሬዚዳንቱ ሀገር የሚገነባው በፖለቲካ ውል ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ግንኙነት፣ በመተጋገዝ፣ በመተሳሰብና በእውነት ትስስር እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም ምክክር በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ባህል ውስጥ የቆየ ሀብት ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የዘመናዊ አገር ግንባታ ካስማ እንዲሆን መልክና ቅርፅ ተበጅቶለት እንዲተገበር ተደርጓል። ተመካካሪዎች ያቀረቧቸው ምክረ-ሐሳቦች ለፖለቲካ ልምምድና ለአገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ አሻራ አኑረዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አክለውም የቀረቡትን ምክረ-ሐሳቦች ወደ ተግባር ለመቀየር እውነትን ፊት ለፊት የማየት ድፍረትና ተግባራዊ ስብዕና እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ጉዞ መስቀለኛ ሳይሆን ቀጥ ያለ የልማትና የኅብረት መንገድ እንደሚሆን በመግለጽ፣ በሂደቱ ለተሳተፉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምክክሩ በቀረቡት አገባቦች ፍርድ ቤቶች፣ የምርጫ ቦርድ እና የመከላከያ ሠራዊት ከአንድ ፓርቲ ተጽዕኖ ነፃ ሆነው ሕዝብን ብቻ እንዲያገለግሉ ያደርጋል፤ ለጦርነት የሚባክነው በጀት ወደ ልማት እንዲዞር በማድረግ የውጭ ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን ይስባል፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአህጉሪቱ ላይ ያላትን ታሪካዊ ተሰሚነትና ዲፕሎማሲያዊ መሪነት መልሳ እንድታገኝ ያደርጋታል።
ይህ እንዳይሆን የሚሹ “ኮሚሽነሩ አገር ጥለው ኮበለሉ” በማለት በብስጭትና በክስረት ስሜት በሞት ሲዛበቱ ተደምጧል። እህታቸው አርፋ ለቀብር አሜሪካ ሄደው በማግስቱ የተመለሱትን ቆፍጣና ኢትዮጵያዊ ከማድነቅና የትውልድ አርአያ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ፣ በሐዘናቸው ውስጥ የፖለቲካ ቁማር ለማጫወት የደፈሩ “ሆዳም ባንዳዎችን” አይተናል።
ፕሮፌሰር መስፍን “አገሬን ጥዬ ወዴትም አልሄድም” ሲሉ በምክክር ጉባኤተኞች ፊት ሲናገሩ በስፍራው የነበረው የአድናቆት ሞገስ፣ የተሰጣቸው ክብርና እሳቸውም የሰጡት ምላሽ ለመጪው ትውልድ አርአያ እንዲሆኑ “ብሔራዊ ጀግና” ስለመባላቸው አመላካች ነው።
በሌሎች ተመሳሳይ ብሔራዊ ምክክርና እርቅ ባደረጉ አገራት በሕዝቦች መካከል ሃይማኖታዊና ብሔር ተኮር ግጭት እንዲቀሰቀስ እና እሳት እንዲነሳ፣ አገራዊ መግባባት እንዳይደረስ የውጭ ጠላቶች እጃቸውን በማስገባት ምክክሩ የአገሪቱን ችግር ከመፍታት ይልቅ አገሪቱን ወደ ረጅም የእርስ በእርስ ጦርነትና ውድመት እንዲያመራ እንደተደረገው ሁሉ፣ የኢትዮጵያን ምክክር ቀድመው የተደራጁት አልሆነላቸውም እንጂ ድንበር ጥሰው ገብተው ጦርነት ለማቀጣጠል የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።
ሁሉም ሳይሳካ ኢትዮጵያ አሸንፋለች። በባንዳነት የሚቀደዱ ሚዲያዎች ያለ አንዳች ሐፍረት በእህታቸው ሞት ምክንያት አሜሪካ የሄዱትን ፕሮፌሰር መስፍንን “ከጂ” ብለው አገራቸውን ጥለው እንደኮበለሉ፣ የኦሮሞ ወኪሎች አላሰራ እንዳሏቸው ተጠቅሶ ከላይ በተገለጸው አግባብ በሕዝብ መካከል ልዩነት ለመዝራት የሰሩት እሬት እሬት እያላቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። መርዛቸውን መልሰው ልሰዋል። “እኔ ከሀገሬ አልኮበለልኩም፣ አልሸሸሁም፣ በቀረችኝ አጭር ዕድሜዬም ሀገሬን ነው ማገልገል የምፈልገው” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያነት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሚና በድል ዘግተዋል።
መጀመሪያ ወደ ምክክሩ “አንገባም” ብለው የነበሩ፣ ለምነው ምክክሩን እንዲቀላቀሉ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት ተካተው በየቀኑ ለሐሰት ፕሮፓጋንዳ ማገዶ እያቀበሉ ቢዘልቁም አልተሳካላቸውም። እነሱ የሐሰት ማገዶ ያቀበሏቸው ሚዲያዎችም ልክ “ፕሮፌሰሩ ኮበለሉ” ካሉ በኋላ የተፉትን መርዝ መልሰው እንደላሱት፣ “የደህንነት አባላት ሠላሳ የሚሆኑ የምክክር ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን አሰረው ወዳልታወቀ ቦታ ወሰዷቸው” በማለት ዜና ከረጩ በኋላ መልሰው “ውሸታችንን ነው” ብለዋል።
ከፍተኛ በጀት የፈሰሰበት የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ አስተባባሪዎች “ምርጫውን ማክሸፍ ሳንችል ቀረን፣ ይህን ምክክር ካላከሸፍን አጀንዳ እናጣለን” በማለት በስፋት ተንቀሳቅሰው፣ በመጨረሻ ተበትነዋል። ምክክሩ እየተጠናቀቀ ሲሄድ ባልታወቀ ምክንያት መሰብሰባቸውን አቁመዋል። ምርጫም፣ ምክክርም አልቋል። ቀጣዩ እርምጃቸው ምን ይሆን? አለቆቻቸውና ቀላቢዎቻቸው የሚሰፍሩላቸውን አጀንዳ ሲተነፍሱ ተቀብለን እናቀርባለን።
በምክክሩ ወቅት ስምምነት ያልተደርርሰባቸው ጉዳዮችም ሆኑ በምክር መልኩ በስምምነት ለመንግስት የቀረቡት ጉዳዮች በስረኞች ምህረትና በፖለቲካ መቻቻል በመጪው አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ በርካቶች ይጠብቃሉ። ሰባት ቀን ሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ የጸለዩ፣ በየቤታቸው ያነቡ፣ ሁከትና ረብሻ “በቃን” ብለው በየእምነታቸው የተጉ “ኢትዮጵያ አሸነፈች” ብለዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






