አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — ኤፍሬም ማዴቦ “ሀገሬ እንደ ሶማሊያ እንድትሆን አልፈልግም፤ መንግሥት አልባ ከመሆን በሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢቀጥሉ እመርጣለሁ” የተናገሩበትን ምክንያት አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች። “የትግራይን ሕዝብ ነፃ አወጣለሁ” የሚለው ህወሃት እና በእሱ ሥር ያሉ የተበታተኑና ኃይል የሌላቸውን ቡድኖች በመያዝ እንደ ቀድሞ ዘመን የሽምቅ ውጊያ ወይም የሽብር ተግባሩ እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጦለታል። የሻዕቢያ ወዳጅ የሚባሉት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ “ጽምዶ” ኢትዮጵያን መንግሥት አልባ የሚያደርጋት ጥምረት መሆኑን በድፍረት በሻዕቢያ ሚዲያ ላይ ወጥተው የተናገሩትም በዚሁ መነሻ እንደሆነ ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ማዕከል ያደረገ መሳይ ጥያቄ ያቀርባል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይሻል ነገር እንደሌለ መሳይ እየደጋገመ ያነሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ነጥሎ ማቆሸሽ፣ እሳቸውን ከሕዝብ መለየትና ማቃቃር ላይ የተመሠረተውን የሻዕቢያና የህወሃት ፕሮፓጋንዳ ከሚያራምዱት ሚዲያዎች አንዱ የሆነው አንከር ሚዲያ ላይ የቀረቡት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ “ይህንን የምናገረው ከልቤ ነው፤ ከመንግሥት አልባነት ዐቢይ ይሻላል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በኢትዮጵያ ትርምስ ማስነሳትን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው የጋራ መድረክ ላይ በገሃድ የሻዕቢያ ወኪል ከሆኑት ከአቶ ነዓምን ዘለቀ ጋር ጥብቅ ወዳጅነትና የሥራ ግንኙነት ያላቸው አቶ ኤፍሬም፣ በአስመራ ህወሃት፣ ፋኖ እና ሻዕቢያ የደረሱበትን ስምምነት አውቀዋል።
ህወሃት ወደ ሽምቅ ውጊያና መሠረታዊ የልማት አውታሮችን ወደ ማውደም፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ ወደሚገድብ የሽብር እንቅስቃሴ እንዲዛወር አቅጣጫ እንደተቀመጠለት የሰሙት ኤፍሬም ማዴቦ፤ ወዳጃቸው ይህን እንዳጫወታቸው በግል የፌስቡክ ገጻቸው “መንግሥት አልባ ከመሆን አብይ ይሻላል” በማለት “ጽምዶ” የፈጠሩት ቡድኖች ሊስማሙ እንደማይችሉ ገልጸው ለጠፉ።
የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ዲሲ ተባባሪ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ወገኖች ጠቅሶ እንዳለው፣ ህወሃት ወደ ሽብር ተግባር እንዲመለስ አቅጣጫ የተቀመጠለት በሻዕቢያ በኩል ቢሆንም እሱም ተስማምቷል። መረጃውን የሰጡ ወገኖች እንዳስረዱት ከዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ምክንያት በጦርነት የታሰበውን ግብ ማሳካት እንደማይቻል በመታመኑና ኢትዮጵያን ወደ ረጅም ጊዜ ውጥንቅጥ የሚከተው ይህ ስልት ብቻ በመሆኑ ነው።
ከሁለት ወር በፊት “የድሮን ጥቃት ፍርሃቻ፤ መሣሪያና ሎጂስቲክስ በጋማ ከብት እያመላለስን ነው። ይህን ስናጠናቅቅ ያለምንም ጥርጥር ጦርነት እንጀምራለን፤ ድርድር ብሎ ነገር የለም” በማለት አቶ ልደቱና አቶ ነዓምን ተጣምረው በሚመሩት የትርምስ አመቻች ግብረኃይል ስብሰባ ላይ የህወሃት ወኪል አቶ አባይ ግደይ መናገራቸውን በመረጃ አስደግፈን ማመልከታችን ይታወሳል።
“ራሱን ተፅዕኖ ፈጣሪ አድርጎ በማየት ተሳስቷል” በሚል የሚገለጸው ልደቱ አያሌው፣ ጥምረቱን ለማዳን በአደባባይ “ጽምዶ የኢትዮጵያ መዳኛ ነው” በማለት ሰነድ አዘጋጅቶ ባሰራጨ ማግስት አቶ ኤፍሬም፣ እነ አቶ ልደቱ ሊሞሻሽሩት እየተጣደፉለት ያለውን ጽምዶ በቁጣ፣ በሻዕቢያ በሚደገፍ ሚዲያ ላይ ወጥተው ይፋ ተናገሩ።
መሳይ መኮንን “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ አነጣጥረህ ተኩስ” የሚለውን የሥራ መመሪያ ለአፍታም ባለመዘንጋት፣ አቶ ኤፍሬምን “ሳያጣሩ ለምን እዚህ ድምዳሜ ላይ ደረሱ?” በማለት ይጠይቃል። አቶ ኤፍሬምም “ምንድነው የማጣራው? እኔኮ ሀሳባቸውን ይንገሩን ነው ያልኩት፤ ምክንያቱም የርዕዮተ-ዓለም፣ የሀገራዊ አስተሳሰብ ልዩነት አላቸው፤ አንዳንዶቹም እርስ በእርስ ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ ናቸው” በማለት “ተጣመድን” ያሉት ድርጅቶች የመጣመድ ባህሪ እንደሌላቸው ያስረዳሉ። ምክንያቱ ባይታወቅም “መለስ” በማለት መሳይን በመጥራት፣ ተመልካች እንዳያሳስት በመማጸን እና በማሳሰብ ደግመው ደጋግመው የተጣመሩት እንኳን ሊስማሙ እርስ በእርስ ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ ኃይሎች መሆናቸውን ያመለክታሉ።
“የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት” በሚል በቅብብሎሽ ፕሮፓጋንዳ ይፋ የተደረገው ወታደራዊ ጥምረት ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲያሴሩ የነበሩ ሀገራትና ኃይሎች መሪነት የተቀነባበረ እንደሆነ ገና ከጅምሩ በአዲስ ሪፖርተር ሲዘገብ እንደነበር ይታወሳል።
የሻዕቢያ ወኪል እንደሆኑ የሚነገሩላቸው አካላት ሳይቀሩ ሻዕቢያ በሚከፍላቸው ሚዲያዎች አማካይነት የጥምረቱን ሴራ ማጋለጥ መጀመራቸውን ተከትሎ በገሃድ የታየውን መከፋፈል ለመጠገን አቶ አንዳርጋቸው “ህወሃት የወልቃይት ጉዳይን እንደማያነሳ በሻዕቢያ አደራዳሪነት ለፋኖ አረጋግጧል” በሚል የተሰጠው ጽምዶን የማዳን ማብራሪያ እስከ ተራ ስድድብ የደረሰ የሰሞኑ አጀንዳ እንደነበር አይዘነጋም። አቶ አንዳርጋቸውን “የበግ ለምድ ለባሽ” በማለት “ባንዳነት የማይሰለቸው” ሲል ህወሃት አቃሏቸዋል።
“ሌሎች አጋሮቻችን (የጽምዶ አካላት) ውጊያ ጀምረዋል፤ እኛም በቅርቡ እንቀላቀላለን” በማለት ውጊያው ከጫፍ መድረሱ በተነገረ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ህወሃት መሣሪያና ሎጂስቲክስ በጋማ ከብት ከቦታ ቦታ ማጋጋዝ መጀመሩ በተሰማበት ሳምንት፣ ህወሃት በሸረሪና ግንባር ከፍተኛ ኃይልና ከባድ መሣሪያ መከዘኑን የሚያውቁ የህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች “ሰበር ዜና አለን” በማለት ውጊያው በሁሉም አቅጣጫ ከመከፈቱ በፊት የድል ዜና ያሰሙ ነበር።
በሳምንት ጊዜ ውስጥ በሸረሪና ግንባር በሁለት ሰዓት ውጊያ፣ መረዋ የነበረ ኃይልና መሣሪያ በድንገት በድሮን ከተመታ እና የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የመሣሪያ ክምችቶች መውደማቸው ከተሰማ በኋላ ነው ህወሃት ያሰበውን ውጊያ ለመጀመር የተሳነው።
ይህንን ተከትሎ እነ ዘመነ ካሴን በመያዝ ወደ አስመራ የተጓዘው ህወሃት፣ በተባለው መሠረት ውጊያ ማድረግ እንደማይችል ገምግሟል። ሻዕቢያ በምንም ይሁን በምንም ውጊያ መጀመር እንዳለበት ቢያሳስብም፣ ህወሃት በድሮን የደረሰበትን ጉዳትና በሕዝብ ዘንድ የገጠመውን ተቃውሞ በመዘርዘር ያሉትን ውስን ታማኝ ኃይሎች በማሰማራት ወደ ሽብር ጥቃት እንዲዛወር ከስምምነት ላይ ተደርሷል። አቶ ኤፍሬምም ይህንን ውሳኔ ከወዳጃቸው ከአቶ ነዓምን ሰምተዋል።
ይህ መረጃ ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞ የሻዕቢያ ወዳጅ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ በአንከር ሚዲያ ላይ እየተቆጡ አስተያየት ለመስጠትና ከዚያ አስቀድመው በግል የፌስቡክ ገጻቸው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል እሳቤ የተሰባሰቡትን ቡድኖች ኮንነው “ሀገሬ መንግሥት አልባ እንድትሆን አልፈልግም” ለማለት የደፈሩት። ከሻዕቢያ የሚከፈለውን መሳይ በብስጭት እዚህ ድምዳሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ስብሰቡን ሊያደምጡ እንደሚገባ ሊሞግት ሲሞክር፣ “ዓላማቸውና እቅዳቸው የሚታወቀውን ምን ብለን እንሰማቸዋለን?” በማለት ቁጣ ቀላቅለው መልሰዋል። መሳይም እንዳይሳሳት መክረውታል።
የስምምነቱ መረጃ ካላቸውና ለጊዜው ስማቸውን ካልጠሯቸው ሁለት ሰዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ህወሃት ወደ ቀድሞ ሽምቅ ውጊያ ሲገባ በትልልቅ ቡድን ከመንቀሳቀስ በአነስተኛ አባላትና ሴሎች ተከፋፍሎ ድንገተኛ ጥቃት በማድረስ እና በፍጥነት በመሰወር ድሮ ያደርግ እንደነበረው ለማድረግ መወሰኑን አስታውቀዋል። ድልድይ፣ የባቡር መስመር፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመግታትና በመሳሰሉት የሽብር ተግባራት ላይ እንደሚሳተፍ አመልክተዋል።
ከፊት ለፊት ፍልሚያ ይልቅ በሕንፃዎች፣ መንገድ ዳር እና የመንገድ ዋሻዎች መግቢያ ላይ ፈንጂዎችን በማጥመድ የሀገር መከላከያን እንቅስቃሴ መግታት፣ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማወክ ላይ የተመሠረተው አዲስ የህወሃት የቤት ሥራ አቶ ኤፍሬምን እንዳስቆጣቸው ከቅርብ ወዳጆቻቸው ተናግረዋል። የዋሽንግቶን ተባባሪያችን እንዳለው አቶ ኤፍሬም ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በዚሁ ዙሪያ ያሉ አካላት በሰሙት መረጃ አዝነዋል።
“የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ እንጂ ሀገራችን እንድትበታተን አቅደን አናውቅም” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡንና በተከታታይ የተወጠነውን ሴራ ለማጋለጥ ቃል የገቡ የጋራ መድረኩ አባል፣ አቶ ኤፍሬም “ለምን አብይ ይቀጥል ይላሉ?” ለተባሉት “ንግግሬን አታጣም መሳይ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ እምነት አልባ ነው። ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ መተማመን የለበትም። ሦስት መንግሥት አይቻለሁ፤ በአንደኛው ትንሽ ልጅ ነበርኩ፣ ሁለቱን ግን በደንብ አውቃቸዋለሁ። እነዚህ በርዕዮተ-ዓለም ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ ናቸው” በማለት ጥምረቱ የትም የሚደርስ እንዳልሆነ አመላክተዋል።
“ወያኔ፣ ፋኖ እና ሸኔ ምንድነው የሚጋሩት? የት ጋር ነው የሚስማሙት?” ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ “መሳይ” እላለሁ ብለው “መለስ” ካሉ በኋላ፤ “የርዕዮተ-ዓለም አንድነት አላቸው? በብሔር ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያ ማንነት ላይ አንድ ናቸው?” በማለት ጥምረቱ ሀገር የሚበታትን መሆኑን አስታውቀዋል።
እናም “አቢይ ይቀጥል ነው ያሉት?” በማለት መሳይ ደግሞ ሲጠይቅ፣ አቶ ኤፍሬም “ተመልካች አታሳስት፤ የነሱ አካሄድ ቶቢያን ሀገር አልባ ከሚያደርጋት በፊት አቢይ ይቀጥል ነው ያልኩት” ብለዋል። መሳይ አስከትሎ “አቢይ ይቀጥል ማለት ዋጋ አያስከፍልም ወይ?” ላለው፣ አቶ ኤፍሬም “እከፍላለሁ” በማለት መልሰዋል።
መሳይ፣ አቶ ኤፍሬምን ለማሳጣት “እንደ ግለሰብ አይደለም፣ እንደ ማህበረሰብ ነው የምጠይቅዎት” ሲል፣ “እኔ እንደ ማህበረሰብ አልተናገርኩም፤ ማንንም አልወከልኩም፤ በግሌ ነው የተናገርኩት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
መሳይ፣ አቶ ኤፍሬም በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ይህን ሀሳብ እንዳነበበ ይገልጽና፣ “እስቲ ያልከውን ቃል በቃል ንገረኝ፤ ያልከውን እኔ አሳስቼ ሊሆን ይችላል” በማለት መሳይ አቶ ኤፍሬም “አብይ ይቀጥል” ማለታቸውን በሌላ አውድ ለማሳየት ሲፈልግ፣ “አቢይ ይቀጥል የሚለውን ቃል ብቻውን አታሰማ፤ እኔ እንደዚያ አላልኩም፤ ይህንን ቃል እንደገና እንዳትደግመው፤ ምክንያቱም ተመልካቹን ያሳስታል” በማለት በተደጋጋሚ እርማትና ማሳሰቢያ እየሰጡ አጠናቀዋል።
ኤፍሬም ማዴቦ መሳይን “አጥናው” በማለት እንዲያነብና እንዲመረምር በማሳሰብ ተግሣፅ የተሞላበት አስተያየት የሰጡት ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን በማወዳደር መሳይ ላቀረበው የስጋት ንፅፅር ነው። ከብርጭቆ የወጣ የውሃ ጠብታ፣ ኔፕልስን ካጠፋው የኤልኒኖ ማዕበል ጋር ማወዳደር እንደማይቻል በማመልከት ኢትዮጵያን የሚገጥማት አደጋ ውስብስብ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሶማሊያ አንድ እምነት፣ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚነገርባት ሀገር መሆኗን በማመልከት፣ በኢትዮጵያ ያሉትን የቋንቋ ብዛት፣ የብሔር እና የአመለካከት ብዛት በማንሳት አሁን የተጣመሩት አዲስ አበባ ቢገቡ እርስ በእርስ ሲታኮሱ ሀገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እንደምትገባ፣ መንግሥት አልባ እንደምትሆን አስታውቀዋል። የሶማሊያ ችግር አሁን ላይ ትንሽ ማገገም ቢያሳይም፣ ኢትዮጵያ አንዴ እዚህ ችግር ውስጥ ከገባች መውጫ እንደማይኖር አመልክተዋል። “ሀገሬ እንደ ሶማሊያ እንድትሆን አልፈልግም” ብለዋል።
ሀገርና መንግሥትን እንዳይቀላቅል “መርምር” በማለት ያስታወቁት ኤፍሬም ማዴቦ፣ መጀመሪያ መንግሥት አልባ መሆን እንደሚቀድም አስታውቀው፣ ሀገር አልባነት ከመንግሥት አልባነት በኋላ የሚመጣ ውድቀት መሆኑን ለመሳይ አስረድተውታል።
“ዋይት ሃውስ፣ ስቴት ዲፓርትመንት እና የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴርን መረጃ አሰባስቦ አትላንቲክ ካውንስል ‘ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ 85 በመቶ ትፈርሳለች’ የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ አስረድተው ነበር። ስለ መፍትሔውም በወቅቱ ተነጋግረው ነበር። ይህ የሆነው ለውጡ በደጃፍ ላይ በነበረበት ወቅት ነበር። አቶ ኦባንግ ምስክር ናቸው” በማለት አስተያየት የሰጡ የዋሽንግቶን ነዋሪ፤ ዛሬ ፔንታጎን እና ስቴት ዲፓርትመንት ገብተው ስለ ምስራቅ አፍሪካ፣ ስለ ቀይ ባህር ደህንነት ውል የሚፈጽም የሀገር መከላከያ ተገንብቶ በአደባባይ እየታየ “ኢትዮጵያ ልትፈራርስ ነው” በሚል የሻዕቢያን ቅዠት የሚቃዠው ‘አርበኛ’ መሳይ መኮንን ህወሃት እንደሚሻል አድርጎ ሲስል መስማት አሳፋሪ ነው። ኢትዮጵያ ለገባችበት ቀውስ ዋና ተጠያቂውና የሴራው ጠማቂ ህወሃት እንደነበር ሲለፍለፍ የነበረ ሰው ዛሬ ይህን ሲል መስማት “እንኳንም በአካል ያላወቅኩት፣ ያላነጋገርኩት” የሚያሰኝ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






