ወንጀሉ በኢትዮጵያ ወነጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት እስር ያስቀጣል
አጀንዳ ለመሆን በሚልና ገቢ ለማግኘት ሲባል ከኢትዮጵያዊያን ባህልና የኃይማኖት እሲቶች ባፈነገጠ መልኩ አጊጠው አደባባይ ላይ በወጡ “የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነን ባዮች” መታሰራቸው ተገለጸ። ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። ወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን እስከ አንድ ዓመት ሊያሳስር እንደሚችል አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አስታውቀዋል። እንዲህ መስለ ባህል አጨናጋፊ ጉዳዮች ላይ መንግስት ይበልጥ ቁጥጥርና ህግ ማስከበር ላይ ተመሳሳይ መድረክ ከሚያዘጋጁት ዋና ተዋኛኖች ጭምር አስተማሪ ቅጣት እንዲወስድ ዜጎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ህሳድር 30 ቀን 2018 ዓ.ም በራሱ ገጽ ይፋ እንዳደረገው በ3ኛው የ”G-Power TikTok Creative Award” ላይ በአደባባይ እና በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ላይ በታዩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አመልክቷል። ፖሊስ እንዳስታወቀው ተጠርጣሪዎቹ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህልና ሥነ-ምግባር ባፈነገጠ አኳኋን እርቃን የሚያሳይ አለባበስ ለብሰው በሕዝብ ፊት በመታየታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። ተውኛኖቹ ብቻ ሳይሆኑ የሽልማት ተብዬው አዘጋጆች ጭምር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
ፖሊስ ይፋ እንዳደረገው፣ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ወንጌላዊት ገብረ እንድርያስ በርሄ (ኤቫን)፣ በረከት ፀጋዬ ጅፋር፣ መቅድም ደረጄ መንግስቱ፣ ግሩም ገዛሀኝ ቀጭኔ እና ዮሃንስ መኮንን ሀ/ማርየም (ጃኒ) ይገኙበታል። ምርመራው የተጀመረው በዝግጅቱ ላይ በቀጥታ የተሳተፉትን፣ ዝግጅቱን በስፖንሰርነት የደገፉትን እንዲሁም ፕሮግራሙን ያቀነባበሩትን ግለሰቦች የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ነው።

የፌደራል ፖሊስ እንደገለጸው፣ ይህ ምርመራ ከሕብረተሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጡ አለባበሶችና መጤ ባህሎች ተስፋፍተው በትውልዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያስከትሉ ለመከላከል ያለመ ሲሆን፣ ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል።
አዲስ ሪፖርተር የሕግ ባለሙያ የሆኑትን ሮቤል በዳዳን ስለ ቅጣቱ እና የሕግ ማሻሻያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል። በዚሁ መሰረት የሕግ ገጽታ በተመለከተ የሕግ ባለሙያው “ተጠርጣሪዎቹ በሕጉ መሰረት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሊጣልባቸው የሚችለው ቅጣት ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራት ሊሆን ይችላል” ሲሉ ህግ አጣቅሰው ተናግረዋል።
የሕግ ባለሙያው በ1996 የወጣውን የወንጀለኛ ህግ ጠቅሰው እንዳሉት ከሆነ ህጉ መሻሻል አለበት። ቅጣቱ ከዛሬ 22 ዓመት በፊት በገንዘብ ከሆነ እስከ 1000 ብር እንደሆነ ያስታወሱት ባለሙያው፣ ቅጣቱ አሁን ላይ አስተማሪ እንደማይሆንና ወነጀሉን የሚያበረታታ እንደሆነ አመልክተዋል።
ሌላ የህግ ባለሙያ “አንድ ሺህ ብር ከፍዬ እወጣለሁ የሚሉ አፈንጋጮችን ያራባል” ሲሉ ህጉ መሻሻል እንዳለበት አመልክተዋል። ባለሙያው የቅጣቱ ዓላማ አስተማሪነትና አስደንጋጭነት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ ሕጉ የኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ግምት ውስጥ በማስገባት መሻሻል እና የቅጣቱ መጠን መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሕግ ባለሙያው ሮቤል በዳዳ የገለጹት የቅጣት መጠን (ከ3 ወር እስከ 1 ዓመት እስራት ወይም 1000 ብር የገንዘብ ቅጣት) እና የሕጉ ዘመን (1996 ዓ.ም.) የሚመለከተው የኢትዮጵያ ወንጀለኛ ሕግ (Criminal Code) አንቀጽ 641ን ነው ተብሎ ይታመናል።
አንቀጽ 641 (በሥራ ላይ ከነበረው የ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ የተወሰደ) የሚያወሳው ስለ ሕዝብ ሥነ ምግባርን የሚጻረር ወይም አስጸያፊ ድርጊት ሲሆን፣ ድርጊቱ ሥነ ምግባር የጎደለው፣ የሕዝብን ሰላም የሚረብሽ ወይም ኃፍረትን የሚያስከትል ከሆነ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ዋናው ድንጋጌ አንቀጹ ድርጊቱን በሕዝብ ፊት ለፈጸሙ ወይም እንዲፈጸም ላደረጉ ግለሰቦች ቅጣት ያስቀምጣል። ድንጋጌው በሕግ ባለሙያው እንደተጠቀሰው ለፍርድ የሚቀርብ ግለሰብ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ይደነግጋል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






