አዲስ ሪፓርተር – የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና በቅርቡ በሶማሊላንድ በተካሄደው ምርጫ አሸናፊ የሆኑት ፕሬዝዳንት አብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ)፣ ሶማሊላንድን እንደ ሉዓላዊት ሀገር የሚቀበል ይፋዊ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ይህ ታሪካዊ ክስተት ባለፉት 30 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ፍለጋ ስትኳትን ለነበረችው ሶማሊላንድ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ ለአፍሪካ ቀንድ ደግሞ አዲስ የጂኦፖለቲካዊ ምዕራፍ ከፋች ነው።
ይህ እውቅና የተሰጠው “በአብርሃም ስምምነት” (Abraham Accords) መንፈስ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት የወጣ መግለጫ ያመለክታል ። ሁለቱ ሃገራት በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በጸጥታ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ሰፊ ትብብር ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ሳር ሁለቱም ሀገራት አምባሳደሮችን ለመሾም እና ኤምባሲዎችን ለመክፈት ዝግጅት እንዲጀምሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ ውሳኔ እስራኤልን ለሶማሊላንድ እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ የተባበሩት መንግስታት (UN) አባል ሀገር አድርጓታል።

በቀንዱ ላይ የሚፈጥረው ጂኦፓለቲካዊ አንድመታ
ይህ የእስራኤል ውሳኔ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የነበረውን የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር “ጨዋታ ቀያሪ” (Game Changer) ክስተት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እስራኤል በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ ያላትን ስልታዊ ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድገዋል። ሶማሊላንድ በቀይ ባሕር የባቢል አል-መንደብ ወሽመጥ አቅራቢያ የምትገኝ በመሆኗ፣ እስራኤል በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የኢራን ደጋፊ የሆኑ እንደ ሁቲ ያሉ ኃይሎችን ለመቆጣጠር እና የባህር ላይ ደህንነቷን ለማስጠበቅ የሚያስችል ወታደራዊና የደህንነት ትብብር ለመመስረት እድል ይሰጣታል። ይህ ደግሞ ቀይ ባህርን የአረብ ሃገራት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ቀጠናዊ ኃይሎችም የፉክክር መድረክ እንዲሆን ያደርገዋል።
ከኢትዮጵያ አንጻር ሲታይ፣ እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷ በጥር 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን የመግባቢያ ሰነድ (MoU) የሚያጠናክር እና ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ የሚሰጥ ይሆናል። ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እስራኤል በይፋ መደገፏ፣ ሌሎች የምዕራባውያን ሃገራት በተለይ አሜሪካ እስራኤልን ተከትለው ተመሳሳይ የእውቅና እርምጃ እንዲወስዱ መንገድ ይከፍታል። ይህ ሁኔታ ሶማሊላንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የሉዓላዊነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ትልቅ ግፊት ይፈጥራል።
የግብፅ፣ ቱርክና ሶማሌ ይፋዊ ተቃውሞ

በሌላ በኩል፣ ይህ ውሳኔ በቀጠናው አዲስ የዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ቀስቅሷል። ሶማሊያ፣ ግብፅ፣ ቱርክ እና ጅቡቲ የእስራኤልን እርምጃ ማውገዛቸውን እሩሳሌም ፓስት ዘግቧል። በተለይም የሞቃዲሾ መንግስት ይህንን እርምጃ “እንደ ሉዓላዊነት መደፈር” እና “የሶማሊያን የግዛት አንድነት መጣስ” አድርጎ ስለሚቆጥረው፣ ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ከረረ ጠብ ሊያመራው ይችላል። በተጨማሪም እንደ ግብፅ ያሉ ሀገራት እስራኤል በአፍሪካ ቀንድና በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ያላትን ተጽዕኖ ማሳደግ እንደ ስጋት ስለሚመለከቱት፣ የቀጠናው ፖለቲካ በሁለት ጎራ በኢትዮጵያ-እስራኤል-ሶማሊላንድ በአንድ በኩል እና ሶማሊያ-ግብፅ-ቱርክ በሌላ በኩል) እንዲከፈል ሊያደርግ ይችላል።
በመጨረሻም ይህ ስምምነት ከሰብአዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ አንድምታም አለው። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ሶማሊላንድ በጋዛ ለተፈናቀሉ ስደተኞች መጠለያ ለመስጠት ፍቃደኛ መሆኗ ለዚህ እውቅና መፋጠን አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ በሙስሊሙ ዓለም እና በአፍሪካ ህብረት ዘንድ አወዛጋቢ ሊሆን ቢችልም፣ ሶማሊላንድ ግን የራሷን የሀገርነት ጥያቄ ለመመለስ ማንኛውንም አይነት የዲፕሎማሲ ካርድ ለመጠቀም መወሰኗን ያሳያል።
በአጠቃላይ የእስራኤል እውቅና መስጠት የአፍሪካ ቀንድን የጸጥታ መዋቅር የሚቀይር እና ለበርካታ ዓመታት የቆየውን የቀጠናውን ፖለቲካዊ ካርታ አዲስ መልክ የሚሰጥ ነው።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






