እነ ጀዋር መሃመድ እና መሰሎቹ የድንቁርና ጌቶች መሃመድ ዳጋሎ (ሃሚቲ) የሚመራው ጃንጃዊድ ሚንሻ በዳርፉር ለተፈፀመው የዘር ማጥፋር ወንጀል እንድ ብቸኛ ተጠያቂ አድርገው በማቅረብ የወንጀሉ ዋነኛ መሪ የነበረውን ጀነራል አልቡርሃንን ከደሙ ንፁህ አድርገው ያቀርቡታል። ይህ ግን ፍፁም ስሁት ትርክት ነው።
አለባቸው ጉብሳ – ነፃ አስተያየት
ጀዋር መሃመድና ሌሎች ኢትዮጵያዊን ሊሕቃን በተለይም በውጭ ሃገር የሚኖሩ ዲያስፓራዎች በሱዳን ጦርነት ዙሪያ ያላቸው ስሁት የጂኦፓለቲካ ግንዛቤ የሃገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለታሪካዊ ጥላቶቻችን አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ይህ ስሁት ግንዛቤ የሚመነጨው በዋናነት ከሃገራቸው ብሄራዊ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን በማስቀደም ከባንዳነትና ከትላላኪነት የሚመነጭ ሲሆን በሌላ በኩል በሱዳን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፉ ባላንጣዎችን የሕዝብ ድጋፍና ቅቡልነት፣ ከሌሎች ሃገራት ያላቸውን የጥቅም ትስስር እና የጦርነቱን ዳራ በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ጀዋር መሃመድ ከልጅትነት እስከ እውቀት የዘለቀው የባንድነት የፓለቲካ የትግል የተደገፈው በግብፅ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄርና ሌሎች ግጭቶችን በመቆስቆና በማቀጣጣል ህዝብ ለህዝብ፣ ህዝብ ከመንግስት ጋር እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር በማድረግ እና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት እምነት እንዳይጣልባቸው አድርጎ ሃገራዊ አንድነትን በመሸርሸር የግብፅን ብሄራዊ ጥቅም እያስከበረ ይገኛል። ከዚህ አንፃር አዲስ ሪፓርተር በተከታታይ በሰፊው የዘገበችውን የጀዋር መሃመድን የተላላኪነትና የባንድነት ግብር አንባቢ ይህን ሊንክ ተጭኖ እንዲያነብ እጠቁማለሁ።
በዚህ ፅሁፍ እነዚህ ኢትዮጵያውን ሊሕቃን ሳያውቁ በስህተት እያወቁ በባንዳነት ድፍረት አይናቸውን በጨው አጥበው በሱዳን ጦርነት ዙሪያ የሃገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት የሚያነሷቸውን ስሁት ትርክቶች ለማጥራት እንሞክራለን።
የጀንጃዊድ ሚንሻ የዳርፉር ዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ
እነ ጀዋር መሃመድ እና መሰሎቹ የድንቁርና ጌቶች መሃመድ ዳጋሎ (ሃሚቲ) የሚመራው ጃንጃዊድ ሚንሻ በዳርፉር ለተፈፀመው የዘር ማጥፋር ወንጀል እንድ ብቸኛ ተጠያቂ አድርገው በማቅረብ የወንጀሉ ዋነኛ መሪ የነበረውን ጀነራል አልቡርሃንን ከደሙ ንፁህ አድርገው ያቀርቡታል። ይህ ግን ፍፁም ስሁት ትርክት ነው።
በዳርፉር የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂነትን ወደ አንድ ግለሰብ (ሄሜቲ) ብቻ ማጥበብ የታሪክን እውነት ከማዛባቱም በላይ በወቅቱ የነበረውን ስርአታዊ የወንጀል መዋቅር ይሸፍናል። ሄሜቲ እና የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች በመሬት ላይ የነበሩ ቀጥተኛ ወንጀል ፈጻሚዎች ቢሆኑም፣ ድርጊቱ የተቀነባበረውና በከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ የታጀበው ግን በወቅቱ በነበረው የዑመር አል-በሽር መንግስት እና በከፍተኛ የጦር መኮንኖች አማካኝነት ነበር።
ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን በወቅቱ በዳርፉር ግጭት ውስጥ የነበራቸው የወታደራዊ መረጃ እና የኦፕሬሽን አመራር ሚና፣ የጦር ሰራዊቱ ለሚሊሻዎቹ የሰጠውን ስልታዊ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ያረጋግጣል። ይህንን ሃሳብ ሳሙኤል ቶተን (Samuel Toten) “The Darfur Genocide: The Role of the Janjaweed and the Sudanese State” በሚለው ጥናታዊ ጽሁፍ ውስጥ በዝርዝር እንዳሰፈረው ወንጀሉ የግለሰቦች ሳይሆን የመንግስት ተቋማትና የጦር አመራሮች የጋራ ውጤት ነበር።
የሄሜቲ ታዋቂነት እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል (RSF) ግዙፍነት ትኩረትን ቢስብም፣ የቀድሞው የሱዳን መደበኛ ጦር (SAF) አመራሮች ከዚህ ተጠያቂነት ሊነጠሉ አይችሉም። ሄሜቲ በወቅቱ የአል-በሽር እና የከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች “መሣሪያ” ሆኖ ያገለገለ እንጂ ራሱን ችሎ ጦርነት የሚከፍት ሉዓላዊ ኃይል አልነበረም። በዳርፉር የተካሄደው የፀረ-አማጽያን ዘመቻ ከመደበኛው ጦር ጋር በቅርብ የተቀናጀና በጄነራሎች ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚመራ ነበር። በመሆኑም አንዱን የጦር መሪ የጥፋት ሁሉ ምንጭ አድርጎ በመሳል ሌላኛውን እንደ ንጹህ ታዛቢ ማቅረብ በሱዳን ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ግፍና ስር የሰደደውን የፍትህ ጥያቄ ማጣጣል ይሆናል።
የጋራ ተጠያቂነት (Collective Responsibility) መርህ በዳርፉር ጉዳይ ላይ ወሳኝ የሚሆነው ወንጀሉ የታቀደውና የተፈጸመው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ስለነበረ ነው። የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) በአል-በሽር ላይ የክስ ማዘዣ ሲያወጣ፣ ትኩረቱ የግለሰቦችን ትዕዛዝ ሰጪነትና የመንግስትን ስልታዊ የጥፋት እርምጃ ማሳየት ላይ ነበር። ጁሊ ፈሊንትና አሌክስ ዴ ዋል በጋራ በፃፉት “Darfur: A Short History of a Long War” የተሰኘው የምርምር ስራ እንደሚያስረዳው፣ የሚሊሻዎችና የመደበኛ ጦር አዛዦች ትስስር እጅግ የተቆላለፈ በመሆኑ፣ ሄሜቲን ብቻ ለይቶ መወንጀል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት እንጂ የፍትህ ፍለጋ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። አል-ቡርሃን እና መሰል ከፍተኛ መኮንኖች በወቅቱ በነበረው ወታደራዊ የዕዝ ሰንሰለት ውስጥ የነበራቸው ሚና የወንጀሉ “ጠንሳሽና አስፈፃሚ” ተካፍይነት ደረጃ ላይ የሚፈረጁ ናቸው።
በአጠቃላይ በዳርፉር ለጠፋው የሰው ህይወትና ለደረሰው ውድመት ሄሜቲን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የወቅቱን ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራር በጋራ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ጀዋር መሃመድ እና ሌሎች ሊሕቃን የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚያናፍሱት የሃሰት ትርክ በስሜታዊነት አንዱን ወገን ነጻ የሚያደርግ ትንታኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን እንዳይረዳ የሚያደርግ የባንዳነት ተግባር ነው።
የሱዳን ግጭት ተዋናዮች ቅቡልነት እውነታ
ሌላኛው እነ ተጋዳላይ ጀዋር መሃመድ በሱዳን ግጭት ውስጥ የሚነዙት የሃሰት ትርክት በጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሰራዊት (SAF) ሕጋዊና ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው በሌላ በኩል በተቃራኒው በጄነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) ደግሞ ሕገ-ወጥ አንጃ ታጣቂ አድርጎ ማቅረብ ነው። በመሰረቱ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ያለው ጦርነት ላዩን ሲታይ በሕጋዊ ተቋም እና በታጣቂ ቡድን መካከል ያለ ግጭት ቢመስልም፣ ውስጣዊው እውነታ ግን እጅግ የተወሳሰበ ነው። በዚህ ወር Foreign Affairs መጽሔት ለንባብ ባበቃው How the War in Sudan Could End በተሰኘው ጥልቅ ትንታኔ የአል-ቡርሃን አስተዳደር የሱዳንን ሕዝብ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ይወክላል የሚለው መከራከሪያ መሠረተ ቢስ እየሆነ እንደመጣ ይገልጻል። ይህ የሆነበት ምክንያት የቀድሞው የዑመር አል-በሽር አምባገነን ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይና ተጠቃሚ የነበሩ የፓለቲካ ሊሕቃን እና የፖለቲካ እስልምና አቀንቃኞች (Muslim brotherhood) በከፍተኛ ሁኔታ ተመልሰው በአልቡርሃን ወታደራዊ ሰአስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው እያገለገሉ መሆናቸው ነው። ይህ ሁኔታ ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚታገሉ የሱዳን ወጣቶችን እና የሲቪል ማህበረሰቡን ተስፋ ያስቆረጠ ከመሆኑም በላይ፣ የአል-ቡርሃንን ቡድን ሕዝባዊ ቅቡልነት በክፉኛ የጎዳው ሐቅ ነው።
በሌላ በኩል፣ ሄሜቲ እና የፈጥኖ ደራሹ ሃይል (RSF) ምንም እንኳ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በጭካኔያቸው ቢታወቁም፣ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ሕዝባዊ ተቀባይነት ችላ ማለት አይገባም። ከላይ የተጠቀሰው የፎርየን አፌር ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ሄሜቲ በተለይ በዳርፉር እና ከሱዳን ማዕከላዊ የፖለቲካ ሥልጣን ተገልለው በቆዩ “ዳር” አካባቢዎች (peripheries) ዘንድ የራሱ የሆነ ማህበራዊ መሠረት አለው። ሄሜቲ ራሱን “የጭቁኖች ጠበቃ” አድርጎ በመሳል፣ በማዕከላዊ የካርቱም ልሂቃን ላይ ቅሬታ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማሰባሰብ ችሏል። ይህ ማለት በሱዳን ውስጥ ያለው ፉክክር በአንድ “ቅዱስ” እና በአንድ “ወንበዴ” መካከል ሳይሆን፣ የተለያየ ፍላጎትና የኅብረተሰብ ክፍልን በሚወክሉ ሁለት ወታደራዊ ኃይሎች መካከል መሆኑን ያሳያል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ጀዋርና ሌሎች ባንዳ ሊሕቃን ፈጥኖ ደራሹን እንደ ሰላም ፀር አድርገው ከሚያቀርቡት በተቃራኑ በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር (SAF) ራሱ በአሁኑ ወቅት የሱዳን የለውጥ ኃይሎችን (Forces for Freedom and Change) እና የሲቪል አስተዳደሩን ወደ ጎን በመግፋት ግጭቱን በድርድርና በእርቅ ከመፍታት ይልቅ ስልጣን በወታደራዊ ኃይል ብቻ እንዲቀጥል እየሰራ ይገኛል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ሌሎች የዲሞክራሲ አቀንቃኞች እንደሚገልጹት፣ የአል-ቡርሃን አስተዳደር ለብሔራዊ ዕርቅ ዝግጁ አለመሆኑ ለሱዳን መፈራረስ ትልቅ ስጋት ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ሄሜቲን ጨምሮ በግጭቱ ውስጥ ድርሻ ያላቸውን ሁሉንም አካላት በማነጋገር ወደ ድርድር እንዲመጡ መወትወቷ፣ የሱዳንን ሉዓላዊነት ከማክበርና ከማስጠበቅ የሚመነጭ እንጂ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ከመስጠት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ፖለቲካን እንደ ሞራል ዳኝነት ሳይሆን እንደ እውነታዊ የኃይል ትንተና (Realpolitik) ለሚመለከት አካል፣ የኢትዮጵያ አቋም የሚደገፍ ስልታዊ እርምጃ ነው።
ግብፅና ቱርክ ከሱደን ሕዝብ ደህንነትና ሰላም ይልቅ ብሄራዊ ጥቅማቸውን ስለማስቀደማቸው
ጀዋር መሃመድ እና ሌሎች ሊሕቃን በተዳጋጋሚ ከሚያቀርቧቸው ስሁት ትርክቶች መካከል የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በጀነራል መሃመድ ዳጋሎ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል በመደገፍ ሱዳን ውስጥ በውክልና ጦርነት እየተሳተፈች ብሄራዊ ጥቀሟን አደጋ ላይ ጥላለች የሚል ነው። ይህ ለዚህ መከራከሪያ ሃሳብ የሚያቀርቡት ማስረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሆን ተብሎ ተቀነባብሮ በተለያዩ አለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደ ሮይተርስ፣ አልጀዚራ አረብያ እና ሌሎች ብዙሃን መገናኛዎች የሚቀርቡ ክሶችን ነው። አዲስ ሪፓርተር በነዚህ ሚድያዎች የቀረቡ ዘገባዎች ሆን ተብሎው የተፈበረኩ የውሸት ትርክቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ ስላጋለጠች፣ አንባቢ ይህንኑ እንዲያነብ እንጋብዛለን። ሌላው ይህ የጀዋር መሃመድ የሃሰት ትርክት በሱዳን ጦርነት ውስጥ ቱርክና ግብፅ በጀነራል አልቡርሃን ለሚመራው የሱዳን ጦር የሚሰጡትን ቀጥተኛ ወታደራዊና የዲፕሎማሲ ድጋፍ የሚመነጨው ለሱዳን ሕዝብ ደህንነትና ለኡላዊነት በመነጨ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። ይህ ፍፁም የተሳሳተ አቀራረብ ነው።
ግብፅ እና ቱርክ በሱዳን ጦርነት የሚሳተፉት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርጉት የጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ነው። ግብፅ ለጄነራል አል-ቡርሃን የምታሳየው ወገንተኝነት እና ቱርክ ለወታደራዊው ምክር ቤት የምትሰጠው ድጋፍ ከጀርባው የቆዩ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ርዕዮተ-ዓለማዊ ምክንያቶች አሉት። The Washington Institute for Near East Policy የተሰኘው ተቋም ባወጣው “Sudan’s Crisis: The View from Cairo” የተሰኘ የጥናት ጽሁፍ እንደሚያብራራው፣ የግብፅ እና የሱዳን ጦር ሰራዊት (SAF) ያላቸው ግንኙነት ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የጠነከረና ተመጋጋቢ የሆነ “ወታደራዊ ወንድማማችነት” ላይ የተመሰረተ ነው። ካይሮ የሱዳን ጦር ሰራዊትን እንደ ብቸኛ ህጋዊ ተቋም መመልከቷ፣ በቀጠናው ያላትን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የምትከተለው ስትራቴጂ ነው።
ሌላኛው የግብፅ ዋነኛ ስጋት እና የድጋፏ መሰረት ከታላቁ የህዳሴ ግድብ እና ከዓባይ ውሃ ፍሰት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የጥቁር ዓባይ ዋነኛው መተላለፊያ እና ስትራቴጂካዊ ቦታዎች በአሁኑ ወቅት በአል-ቡርሃን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው፣ ካይሮ ይህንን ወታደራዊ ኃይል መደገፍ ለውሃ ደህንነቷ ወሳኝ እንደሆነ ታምናለች።
ከኢኮኖሚ አንጻር ሲታይም ግብፅ ከአል-ቡርሃን አስተዳደር ጋር ያላት ግንኙነት ለህልውናዋ አስፈላጊ ነው። ግብፅ በአሁኑ ወቅት ያለባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከሱዳን ጋር በምታደርገው የወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት ግብይት ላይ እንድትደገፍ አድርጓታል። የሱዳን ጦር ሰራዊት ቁጥጥር ስር ያሉ የወርቅ ማዕድናት እና የንግድ መስመሮች ለካይሮ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። Middle East Eye ባወጣው “The Battle for Gold: Egypt’s Economic Interests in Sudan” የተሰኘ ዘገባ እንደሚጠቁመው፣ ይህ የጥቅም ትስስር ግብፅ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ላይ ከአል-ቡርሃን ጎን እንድትቆም የሚያደርጋት ሌላኛው የ”Realpolitik” ማሳያ ነው።
የቱርክን ተሳትፎ ስንመለከት ደግሞ ጉዳዩ ወደ ርዕዮተ-ዓለማዊ ፍላጎት ያዘነብላል። ቱርክ በፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን መሪነት የቀድሞውን የኦቶማን ተፅዕኖ በአፍሪካ ቀንድ ለመመለስ የምታደርገው ጥረት፣ ከአል-ቡርሃን አስተዳደር ጋር እንድትቀራረብ አድርጓታል። በአል-ቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ ምክር ቤት ውስጥ የቀድሞው የአል-በሽር አጋር የነበሩ የፖለቲካ እስልምና አቀንቃኞች (Muslim Brotherhood) በአስተዳደሩ ውስጥ ከፍተኛ የሹመት ቦታ ማግኘታቸው ለቱርክ ትልቅ እድል ፈጥሯል። ቱርክ እነዚህን ኃይሎች በመደገፍ በሱዳን እና በቀይ ባሕር አካባቢ ያላትን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተጽዕኖ ለማስፋት ትጠቀማለች።
ቱርክ ለሱዳን ጦር የምትሰጠው ድሮኖች እና የጦር መሣሪያዎች ድጋፍ፣ በአካባቢው ካላት ስትራቴጂካዊ ፍላጎት የሚመነጭ ነው። በተለይም የሱዋኪን ደሴት (Suakin Island) ላይ ያላት የልማት እና የወታደራዊ መሠረት የመመሥረት ሕልም ከአል-ቡርሃን መንግስት ጋር በሚኖር መልካም ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው።ቱርክ በሱዳን በኩል የአረብ አገራትን ተጽዕኖ ለመገዳደር እና የራሷን የኢኮኖሚ መስመር ለመዘርጋት የአል-ቡርሃንን አስተዳደር እንደ አስተማማኝ አጋር ትመለከታለች።
ግብፅና ቱርክ በሱዳን ጦርነት የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ጉዳይ ላይ የምትከተለውን ሚዛናዊ ዲፕሎማሲ የበለጠ አስፈላጊ ያደርገዋል። ግብፅ እና ቱርክ የራሳቸውን ርዕዮተ-ዓለማዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ መወገናቸው፣ ግጭቱ እንዲራዘም እና የሱዳን ሕዝብ መከራ እንዲባባስ እያደረገ ነው። ኢትዮጵያ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ያላትን ግንኙነት በመጠቀም የቀጠናዊ ሰላምን ለማምጣት የምታደርገው ጥረት፣ ከነዚህ ሀገራት ጠባብ ፍላጎት በተቃራኒ የቆመ ሰፋ ያለ የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ ነው።
እንግዲህ የጀዋር መሐመድ እና ሌሎች ቅጥረኛ ተላላኪ ሊሕቃን ትችት የሃገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡት ይህንን ውስብስብ የጂኦፖለቲካ እውነታ ችላ በማለት ነው። ብሔራዊ ጥቅም ማለት በቀጠናው ፍላጎት ካላቸው ሃያላንና መካከለኛ ሃገራት ጋር በብልሃት በመደራደር የሀገርን ህልውና ማስቀጠል እንጂ በሞራል ጥያቄዎች ብቻ ተወስኖ ዲፕሎማሲያዊ ክፍተት መፍጠር አይደለም።
ከዚህም ባለፈ፣ ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በአሁኑ ወቅት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ የሚታዩ የውስጥ ግጭቶችን በመጠቀም ብሄራዊ ጥቅማቸው ለማስጠበቅ በስልጠና፣ በትጥቅ፣ በፕሮፓጋንዳ እና በወታደራዊ መረጃ እየደገፏቸው እንደሆነ የቀጠናው ጂኦፓለቲካ ተንታኞች የሚስማሙበት እውነታ ነው። የውክልና ጦርነት ዋነኛ ግቡ ተቃራኒ ሀገርን በውስጥ ችግሮቿ ተጠምዳ እንድትዝል እና እንድትዳከም ነው። ኢትዮጵያ በሱዳን ጉዳይ ላይ የምታሳየው ተሳትፎ ይህንን ስጋት ለመቀነስ እና በድንበሮቿ አካባቢ ወታደራዊና ፖለቲካዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ስልታዊ እርምጃ ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ጉዳይ ላይ የሚከተለው መንገድ ከስሜታዊነት የጸዳ እና በታሪካዊ እውነታዎች ላይ የተመሰረተ ነው። ጆርጅ ፍሪድማን እንደሚያስተምረን፣ የሀገር መሪዎች ቀዳሚ ግዴታ ለሀገር ህልውና አስገዳጅ የሆኑ ውሳኔዎችን መወሰን ነው። ግብፅ እና ሱዳን ላለፉት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የውክልና ጦርነት ለመመከት፣ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው እና በሌሎች አማራጭ የውጭ ጉዳይ ግብ ማስከበሪያ መሳሪያዎች የምትወስዳቸው እርምጃዎች የብሔራዊ ጥቅሟ ለማስከበር ነው። ይህ አካሄድ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ፣ ጠላቶቿ በውክልና ጦርነት ሊያደርሱባት የሚችሉትን አደጋ ቀድሞ ለማክሸፍ የሚያስችል ብቸኛ አማራጭ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






