ከኤርዶጋን ጉብኝት ማግስት የእስራኤል ፕሬዝድንት ወደ አዲስ አባባ እንዳሚመጡ ተሰማ፣ አንድምታው ምን ይሆን?
አዲስ ሪፓርተር አዲስ አበባ — የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን እና የሳዑዲ አረቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከፍተኛ ልዑካናቸው ይዘው አዲስ አበባን በተከታታይ ጎብኝተው በሄዱ ማግስት፣ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ይስሐቅ ሄርዞግ በቀጣይ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል። ይህ ጉብኝት በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ቀጠና እየተካሄደ ያለው የጂኦፖለቲካ ሽኩቻ አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አመላካች እንደሚሆን ተመልክቷል።
ይህ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ጉብኝት ተራ ዲፕሎማሲያዊ ኩነት ሳይሆን፣ የኃያላን አገራትን ፍላጎትና የቀጠናውን የኃይል ሚዛን የሚቀይር ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑን የቀጠናው የጂኦፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ።
የእስራኤል ፕሬዝዳንት ጉብኝት ዋና ማጠንጠኛው ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር ለማግኘት ስለምታደርገው ጥረት እና እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን እውቅና አስመልክቶ ዙሪያ ለመምከር እንደሆነ ይታመናል። እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷ በቀጠናው ያሉትን እንደ ግብፅ፣ ቱርክ እና ሳዑዲ አረቢያ ያሉ አገራትን ክፉኛ አስቆጥቷል። አዲስ ሪፓርተር በወቅታዊ ጂኦፓለቲካ ትንታኔዋ እንደዘገበችው ከዚህ በፊት በጥላትነት ተፈራርጀው የነበሩት ቱርክና ግብፅ የጋራ ጥላታቸውን እስራኤልን ለመመከት አዲስ ስትራቴጅካዊ አጋርነት መስርተዋል።
እስራኤል ለሱማሊላንድ ከሰጠችው እውቅና ጀርባ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እጅ እንዳለበት የሚነገር ሲሆን፣ ይህም እስራኤል በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ያላትን የደህንነት ተፅዕኖ ለማስፋትና የኢትዮጵያን የባህር በር ህልም በመደገፍ ታሪካዊ ወዳጅነቷን ለማጽናት የወሰደችው እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።
በተቃራኒው፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን እና የሳዑዲ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ተከታታይ ጉብኝት፣ ይህንን የእስራኤልንና የኤምሬቶችን በቀጠናው እየፈጠሩት ያለውን ይዞታ ለመግታት የታለመ የዲፕሎማሲያዊ ግፊት አካል ስለመሆኑ ጉብኝቱን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቱርክና ሳዑዲ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው እውቅና ተቀባይነት እንዳያገኝ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር እንድትገታ ለማሳመን እየሞከሩ እንደሆነ ለአራት ኪሎ ቅርብ የሆኑ የዲፕሎማሲ ምንጮች ይገልፃሉ። ይህ ደግሞ አዲስ አበባን የሁለት ተቃራኒ ጎራዎች የፍላጎት ማዕከል አድርጓታል።
ይህ የቀጠናው ፍጥጫ እስከ ዋሽንግተን የዘለቀ የፖለቲካ ትኩሳት መፍጠሩም ተስተውሏል። ለፕሬዝዳንት ትራምፕ እጅግ ቅርብ የሆኑት ሴናተር ሊንዚ ግርሃም በአቡዳቢ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሳዑዲ አረቢያ በአብርሃም ስምምነት አባል በሆነችው አረብ ኤምሬትስ ላይ የምታሳየው ተቃውሞ “ስህተት” መሆኑንና የአሜሪካ-ሳዑዲ ግንኙነትን እንደሚጎዳ መናገራቸው፣ የምዕራባውያን ፍላጎት ከእስራኤልና ከኤምሬቶች ጎራ ጋር መሆኑን ፍንጭ ሰጥቷል። ይህም ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር የምታደርገው ስምምነት ጠንካራ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ከለላ ሊኖረው እንደሚችል ያሳያል። ይህንን አካሄድ የሚከታተሉ ቀደም ሲል ጀምሮ ኢትዮጵያ የተካተተችበት አዲሱ አሰላለፍ ጎልቶ የወጣና አሸናፊ እንደሚሆን አስቀድመው መናገራቸው ይታወሳል።
ከእስራኤል በኩል የሚመጣው ድጋፍ ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስንቅ ነው። እስራኤል ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር እንድታገኝ የምታደርገው ድጋፍ፣ በቀይ ባህር ላይ ያላትን ብቸኝነት ለመቀነስና የንግድ መስመሯን ከጠላቶቿ ስጋት ለመታደግ ካላት ስትራቴጂካዊ ፍላጎት የሚመነጭ ነው። ፕሬዝዳንት ሄርዞግ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ፣ ይህንን የባህር በር ጉዳይና የቀጠናዊ ደህንነት ትብብርን በሚመለከት ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ አሁን ላይ “የዜሮ ድምር ፖለቲካ” (Zero-sum game) እየሆነ መጥቷል። አንዱ ወገን የሚያገኘው ስኬት ለሌላኛው ወገን እንደ ስጋት የሚታይበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ትኩሳቱን በጨመረ ቀጠና ውስጥ የፕሬዝዳንት ሄርዞግ ጉብኝት፣ እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ሚና ይፋዊ የማድረግና የኢትዮጵያን የባህር በር ህልም ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረግ ትልቅ እርምጃ ነው።
ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ በዚህ የኃያላን አገራት ሽኩቻ መካከል የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚጠብቃት የሚመክሩ አሉ። በአንድ በኩል ከእስራኤልና ከኤምሬቶች የሚገኘው የቴክኖሎጂና የደህንነት ድጋፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከቱርክና ከሳዑዲ ጋር ሊፈጠር የሚችል የዲፕሎማሲ መሻከር ሚዛኑን ጠብቆ መጓዝን ይጠይቃል። የሄርዞግ ጉብኝት ኢትዮጵያ የትኛውን ጎራ እንደምትመርጥ ወይም እንዴት ሚዛኑን እንደምትጠብቅ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግልጽ መልዕክት የሚሰጥ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የዚህ ጨዋታ ማዕከል ሲሆን፣ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ጉብኝት ደግሞ በጨዋታው ላይ አዲስና ወሳኝ እርምጃ ነው። ይህ ጉብኝት በቀጠናው ያለውን የኃይል አሰላለፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና የኢትዮጵያን የወደፊት የባህር በር እጣ ፈንታ የሚወስን ትልቅ ክስተት ሆኖ ይመዘገባል።
አዲስ አበባ ትኩረት ያደረገው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ውጤት፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ወይስ ወደ አዲስ ቀጠናዊ ውጥረት የሚከት ይሆናል? የሚለው ጥያቄ የብዙ ተንታኞች ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል።
የቱርክ ፕሬዚዳንት፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሚሶም አዛዥ፣የእንግሊዝ የውጭ ስከሬታሪ፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር፣ የዩናይትድ ስቴጽ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የሚጠቀሱት ናቸው።
በዲፕሎማሲ “ኩስመና” የሚታማው የኢትዮጵያ መንግስት በሚከተለው የዝምታ ፖሊሲ መነሻ ብዙ ነገሮችን አደባባይ ባያወታም መሬት ላይ የሚታዩት እውነታዎች የመንግስትን ስኬታማ የዲፕሎማሲ አካሄድ የሚያስዩ እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማኘት አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ እንደምትከፍል መንግስት በተደጋጋሚ ማስታወቁ የሚታወስ ነው። በኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች ዘንድ ደግሞ ይህ የመንግስት አቋም ትክክል ተደርጎ አይወሰድም። ይልቁኑም ለሌሎች አገሮች ፍላጎት የማዘንበልና የመከራከር አዝማሚያ ያሳያሉ። በዚህም ሳቢያ ብሄራዊ ጥቅምና የፓርቲ ጥላቻ ተለያይተው ሊታዩ እንደሚገባ ከየአቅጣቻው እየተጠቆመ ነው።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






