አዲስ ሪፖርተር – ዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ሰሞኑን ባወጣው አዲስ ሪፓርት መሰረት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በፕሪቶሪያው ስምምነት የቆመው ደም አፋሳሽ ጦርነት በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፣ በትግራይ ኃይሎች እና በኤርትራ መካከል በሚታይ አዲስና ውስብስብ ውጥረት ሊያገረሽ አፋፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ቀደም ሲል በትግራይ ኃይሎች ላይ ተባብረው የዘመቱት አዲስ አበባ እና አስመራ፣ ዛሬ ባልተጠበቀ ሁኔታ የከረረ ጠላትነት ውስጥ በመግባታቸው ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ስጋት ደቅነዋል። ይህ መሻከር ደግሞ በትግራይ ውስጥ ካለው የፖለቲካ መከፋፈል እና በጎረቤት ሱዳን ከሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ጋር ተዳምሮ፣ መላውን የአፍሪካ ቀንድ ወደ ማይታወቅ ቀውስ ሊከት እንደሚችል ተገምቷል።
የወደብ ጥያቄ እና የአዲስ አበባ – አስመራ ግንኙነት መላላት
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሻከር የጀመረው የፕሪቶሪያው ስምምነት የኤርትራን ፍላጎት ሳያካትት መፈረሙን ተከትሎ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የባሕር በር” ጥያቄን ዳግም ማንሳታቸው ግንኙነቱን ወደ ለየለት ጠላትነት ቀይሮታል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እንደምትጠቀም መግለጿ፣ በአስመራ በኩል እንደ ሉዓላዊነት መደፈር እና እንደ ወረራ ማስጠንቀቂያ ተቆጥሯል። በዚህም ምክንያት የኤርትራ መሪ ኢሳይያስ አፈወርቂ ከቀድሞ ጠላታቸው ከሕወሃት “አሮጌው ጠባቂ” (Old Guard) ቡድን ጋር ስልታዊ መቀራረብ መጀመራቸው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ እንደ ጀርባ መውጋት ተቆጥሮ የሁለቱን አገራት ወታደራዊ ዝግጅት ወደ ከፍተኛ ደረጃ አድርሶታል።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ከአስመራ ጋር ያላት ግንኙነት ሲሻክር፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ቡድኖችን እና የአፋር ብሔርተኞችን መደገፍ መጀመሯ ለአካባቢው ሰላም ተጨማሪ ስጋት ሆኗል። አዲስ አበባ የአሰብ ወደብን በኃይል ልትይዝ ትችላለች የሚለው ግምት፣ ኤርትራ ከግብፅ እና ከሱዳን ጦር ጋር አዲስ ግንባር እንድትፈጥር አድርጓታል። ይህ የቀጣናው ኃይሎች አሰላለፍ ለውጥ፣ የቀድሞውን የሰላም ተስፋ አጨልሞ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉትን ቅራኔዎች በሙሉ በአንድ ትልቅ ግጭት ውስጥ እንዲሰባሰቡ እያደረገ ይገኛል።
የትግራይ ውስጣዊ ሽኩቻ እና የአስተዳደራዊ ለውጡ አንድምታ
በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተው የፖለቲካ መከፋፈል ለፌዴራል መንግሥቱ ሌላው የራስ ምታት ሆኗል። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የጌታቸው ረዳ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው የሕወሃት ክንፍ መፈንቅለ መንግሥት መሰል ግፊት መወገዱ የክልሉን ፖለቲካ አወሳስቦታል። አዲሱ የትግራይ አመራር ከኤርትራ ጋር የሚያሳየው “የዝምታ ስምምነት” አዲስ አበባን በእጅጉ አስቆጥቷል። የፌዴራል መንግሥቱ ይህንን መቀራረብ ለመመከት የክልሉን በጀት በማገድ እና በትግራይ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የታጠቁ ኃይሎችን (ለምሳሌ የትግራይ ሰላም ኃይሎች) በመደገፍ የክልሉን ኃይል ለመከፋፈል እየሞከረ ነው።
ይህ ውስጣዊ ሽኩቻ ወደ ታች ወርዶ በደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች ወደ ግጭት ማምራቱ ክልሉ ገና ከጦርነት አላገገመም የሚለውን እውነታ ያመላክታል። በትግራይ ሰራዊት (TDF) ውስጥ ያለው የመከፋፈል ስሜት እና በጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራው አዲሱ አስተዳደር በሁለቱ ጽንፎች መካከል ያለው አቋም፣ የክልሉን የወደፊት እጣ ፈንታ ግልጽ እንዳይሆን አድርጎታል። ትግራይ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ጫና እና በአስመራ ስልታዊ መጠቀሚያነት መካከለኛ ሆና ቀርታለች።
የሱዳን ጦርነት ተጽዕኖ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች
በጎረቤት ሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በኢትዮጵያና ኤርትራ ውጥረት ላይ “ነዳጅ የማርከፍከፍ” ያህል ሆኗል። ኢትዮጵያ ከኤምሬትስ ጋር በመሆን የፈጣን ድጋፍ ኃይልን (RSF) ትደግፋለች ተብሎ መጠርጠሯ፣ የሱዳን ጦርን ከምትደግፈው ኤርትራ ጋር የሚያጋጭ ሌላ ግንባር ከፍቷል። ይህ ደግሞ በሱዳን ድንበር በኩል የሚደረገውን የወታደራዊ መሣሪያ ዝውውር እና የተኪ ኃይሎች እንቅስቃሴን አባብሶታል። ግጭቱ ከቀጠናዊ አልፎ የአረብ አገራትን ፍላጎት ጭምር እያሳተፈ በመሆኑ፣ መፍትሔው ከወትሮው በተለየ መልኩ ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚጠይቅ ሆኗል።
ሪፖርቱ እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጠው፣ እንደ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ አገራት በአዲስ አበባ እና በአስመራ መካከል ድብቅ የዲፕሎማሲ መስመር እንዲከፍቱ ነው። በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ ያላትን የባሕር በር ፍላጎት በሰላማዊ መንገድና በንግግር ለመፍታት እንደምትፈልግ በጀመረችው አግባብ ልትቀጥልበት እንደሚገባና ሪፖርቱ አበራታቷል። ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ የሚያስከትለው ሰብዓዊ ቀውስ ከቀደመው እጅግ የከፋ እንደሚሆን በማሳሰብ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት የበኩላቸውን እንዲረባረቡ መክሯል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






