አዲስ ሪፓርተር — የቻይና እና የፓኪስታን መንግስታት በገልፍ ባህረ ሰላጤው እና በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ለማርገብና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ባለ አምስት ነጥብ የጋራ የሰላም ሃስብ ዛሬ በቤጂንግ ይፋ አድርገዋል።
ይህ ስምምነት ይፋ የሆነው የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የፓኪስታኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ኢሳቅ ዳር በቤጂንግ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነው። ሁለቱ ሀገራት የቀጠናው ሰላም መደፍረስ ለአለም አቀፍ ደህንነት ስጋት መሆኑን በመጥቀስ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አቅርበዋል፦
- አስቸኳይ የተኩስ አቁም
በጦርነት ውስጥ ያሉ ወገኖች በአፋጣኝ ግጭት እንዲያቆሙ እና ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ጥሪ ቀርቧል። በተጨማሪም ለተጎጂዎች ሰብአዊ እርዳታ ያለ ምንም እንቅፋት እንዲደርስ አሳስበዋል። - የሰላም ንግግር እና ሉዓላዊነት
ውይይት እና ዲፕሎማሲ ብቸኛው መፍትሄ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የሰላም ንግግሮች በአፋጣኝ እንዲጀመሩ ጠይቀዋል። በዚህ ሂደትም የኢራን እና የባህረ ሰላጤው ሀገራት ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ነፃነት መከበር እንዳለበት አጽንኦት ተሰጥቶታል። - ሲቪል ተቋማትን ከጥቃት መከላከል
በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ መሰረት በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ተጠይቋል። በተለይም የኃይል ማመንጫዎች፣ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች እና የሰላማዊ ኑክሌር መሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት እንዲቆም ጥሪ ተላልፏል። - የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ደህንነት
የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ለአለም አቀፍ ንግድ እና ኢነርጂ ዝውውር ያለውን ወሳኝ ሚና በመጥቀስ፣ በመንገዱ ላይ የታገቱ መርከቦችና ሰራተኞች እንዲለቀቁ እንዲሁም የንግድ መርከቦች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል። - የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሚና
ማንኛውም የሰላም ማዕቀፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር እና በአለም አቀፍ ህግጋት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበትና የድርጅቱ የበላይነት ሊከበር እንደሚገባ ሁለቱ ሀገራት ገልጸዋል።
ይህ የቤጂንግ መግለጫ አሜሪካን፣ እስራኤልንና ኢራንን በስም ሳይገልፅ መውጣቱ ያልተለመደ እንደሆነ ዲፕሎማቶች እየገለፁ ይገኛል። መካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት መውጣቱ፣ ቻይና እና ፓኪስታን በቀጠናው ዲፕሎማሲ ላይ ያላቸውን ተሰሚነት ለማሳደግ እንደሚፈልጉ የሚያሳይ መሆኑ ተነግሯል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






