አዲስ ሪፖርተር ዜና – “አራት ልጆች አሉኝ። ቤቱን ከተከራየሁ ሁለት ዓመቴ ነው። አሁን ጊዜው ስላበቃ ኪራይ እንድጨምር ወይም እንድለቅ ተነግሮኛል። ጭማሪ መክፈልም ሆነ ሌላ ቦታ ለመከራየት አልችልም። የልጆች ትምህርት ቤትን ጨምሮ አቅሜ አይፈቅድም። ምን ላድርግ? ግራ ገብቶኛል” ይላል ለአዲስ ሪፖርተር በስልክ ጭንቀቱን ያስረዳ የአዲስ አበባ ነዋሪ።
በአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ዋጋ የሚተመነው “ኮሚሽናቸውን በሚያሰሉ ቀማኛ ደላሎች ነው” የሚሉ በርካታ ቅሬታ አቅራቢዎች፣ መንግስት አከራዮችን ብቻ ሳይሆን ደላሎችን መላ ሊላቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።
ከተለያዩ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ የሚጎርፈው ብቻ ሳይሆን፣ ከኤርትራና ከሌሎች አጎራባች አገራት ያለፈቃድ አዲስ አበባን ያፍናት የህዝብ ብዛት ለደላላና አከራዮች ዘረፋ ዋና ምክኛት እንደሆነ የሚናገሩ ዜጎች መንግስትም በዚህ መልኩ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
የመንግስት ሰራተኞች ከውጭ ሳንቲም ከሚላክላቸው ህገወጥ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ስለማይመጣጠን የቤት ኪራይ ገበያው እየጎዳቸው እንደሆነ የሚናገሩ፣ ህገወጦች የሰፈሩበትን፣ የተከራዩበትን፣ እያንዳንዷን ቤት የቀበሌ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ቢያውቁም ምንም እንደማይተነፍሱ አመልክተዋል። በጎን የሚወሸቅላቸው ገንዘብ ከወንጀለኞች ጋር ተባባሪ እንዳደረጋቸውም አመልክተዋል።
የሶስት ወይም የአራት ወር ቅድሚ እንዲከፈል የሚወስኑት ደላሎች መሆናቸው ሌላው መከራ እንደሆነ የሚናገሩ፣ እነሱ ከሚያገኙት ኮሚሽን ሲሉ የተከራዩን አቅም የሚፈትን ተግባር እንደሚፈጽሙ አመልክተዋል። በዚህ መሰሉ የደላሎች ተግባር የተማረሩ በተለይም የመንግስት ሰራተኞች “መንግስት አዲስ መመሪያ የሚያወጣ ከሆነ እንዲህ ያለውንም አሰራር ይፈትሽ” ሲሉ አስተያተ ሰጥተዋል።
ከዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመት የተሰራ ደሳሳ ቤት የሚጥየቅበት ኪራይ ቤቱን ለመስራት ከወጣበት ሳንቲም በላይ እንደሆነ ያመልከቱ፣ አስተያየት ሰጪዎች “በቤት ኪራይ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ አግባቦች የሚታዩ የዋጋ ጭማሪዎች ፈር የለቀቁ፣ የዋጋ ስያሜ አመክንዮን የዘነጉ፣ ተቆጣጣሪና ሃይ የሚል አካል የሌለበ፣ ዝም ብሎ በዘፈቀደ ዋጋ መቆለል መብት የሆነበት አደገኛ ሁኔታ ሰፍኗል። ይህ አደገኛ ነው። ወደፊትም ለመቆጣጠር ያስቸግራል። በጥናት አንድ ሊባል ይገባዋል” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 30 የሚያበቃውን የቤት ክራይ ውል ተንተርሶ አከራዮች ተከራዮችን እያስጨነቁና መከራ እያሳዩ እንደሆነ በስፋት ቅሬታ እያሰሙ ያሉ ነዋሪዎችን አዲስ ሪፖርተር አነጋግራለች። አከራዮች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ለተከራዮች ከማሳወቃቸው በዘለለ “ልቀቁ” በሚል እያስፈራሩ ነው።
አንዳንዶቹ አከራዮሽ ” ቤቱን እፈልገዋለሁ ውጡ ፣ ቤቱ ተሽጧል ” በማለት ተከራዮች ላይ ጫና እየፈጠሩባቸው ነው። እነዚህ ተከራዮች ከላይ በተዘርዘሩት ችግሮች ሳቢያ “ወዴት ይሂዱ?” የሚለው ጥያቄ አስቸኳይ ልጓም ካልተበጀ የሚፈጠረው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አይሆንም።
ከቤት ኪራይ ጭማሪ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ መቅደስ ወ/ጊዮርጊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ” ተከራዮች በህግ የተሰጣቸው መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። አከራዮችም መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተድምጠዋል።
ኃላፊዋ “በከተማችን ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ የኪራይ ቤቶችን መዝግበናል ወደ ሲስተም አስገብተን ቋት ውስጥ ነው ያለው” ካሉ በኋላ ቤቶቹ የት ክ/ከተማ ፣ የት ወረዳ ፣ የትኛው የቤት ቁጥር ፣ ባለስንት መኝታ ቤት በስንት ብር ተከራየ ፣ ማነውስ የተከራየው የሚለው ዳታ አብሮ መሰባሰቡን አስታውቀዋል። አንድ አከራይ ግዴታ ያለበት ቤቱን ለሁለት ዓመት እንዲያከራይ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊዋ፣ ግዴታው ሁለት ዓመት ቢሆንም ማራዘም እንደሚቻል አመልክተዋል።
“በዚህ እሳቤ አከራዩ ዋጋ ጨምሩ ማለት አይችልም። ዋጋ መጨመር የሚችለው መንግሥት ነው። በዓመት አንድ ጊዜ ሰኔ 30 ላይ በወጣው የዋጋ ጥናት መሰረት ዋጋ መጨመር የሚችለው መንግሥት ነው” ሲሉ ተከራዮች የዋጋ ጭማሪን እንዳይቀበሉ አስታውቀዋል።
ምሳሌ ጠቅሰው ሲያስረዱ፣ አንድ ቤት አንድ ሺህ ብር ተከራይቶ ቢሆን መቶ ብር መጨመር የሚችለው መንግስት እንደሆነ አመልክተዋል። የገበያ ጥናት ሰርቶ በምን ያህል መጠን ዋጋ ከፍ እንዳለ አስልቶ የሚጨምረውን የመቶኛ ስሌት ይፋ የሚያደርገው መንግሥት እንደሆነም አመልክተዋል።
“2017-2018 በጀት ዓመት የተጨመረ ዋጋ ስላልነበረ በነበረው ነው የሚቀጥለው ብለን አሳውቀን በነበረው ነው የቀጠለው። ዘንድሮም ዋጋ እያጠናን ነው። ስለዚህ የዋጋ ጥናቱ በሚመልሰው መልስ መሰረት ወይ በነበረት ይቀጥላል። የጨመረ ዋጋ ካለ በይፋ መንግሥት ያሳውቃል። እስከዛ ድረስ አከራዮች ዋጋ ጨምሩ የማለት መብት የላቸውም ፤ አሰራሩም አይፈቅድላቸውም” ሲሉ ኃላፊዋ ተከራዮች መብታቸውን አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
ተከራዮችም መብታቸውን መጠቀም አለባቸው። አከራይ ዋጋ ጨምር ስላለው ብቻ ዋጋ መጨመር አይገባም። ውላቸው እኛ ጋር አለ። ውላቸው የሚያበቃው ከሰኔ 30 በኋላ ነው። ውላቸው ውስጥ ሆነው ዋጋ መጨመር ስለማይጠበቅባቸው እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም በቅርባቸው ወረዳ አለ ስራ አስፈጻሚ የሚመራው ፣ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አለ ፣ ክፍለ ከተማም አለ ወረዳው ካልፈታ ክፍለ ከተማ ይፈታል፣ ቢሮ እኛም ጋር አለ” በማለት ኃላፊዋ ተከራዮች በተዋረድ የተጠቀሱት አካላት ዘንድ ቀርቦ ማሳወቅ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ኃላፊዋ ይህንን ቢሉም አይን ያወጣው የየመዋቅሩ ሌብነት ተከራዮች መብታቸውን ለማስከበር ለሚያቀርቡት ጥያቄ እንቅፋት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይሰማል። በኃላፊነት መቀመጫ ላይ ተቀምጠው “አምጣ” የሚሉ ማየት የተለመደ በመሆኑ መንግስት ሊያስብበት እንደሚገባ በተለያዩ አግብቦች ቅሬታ የሚያሰሙ እየገለጹ ነው።
“አከራይ ዋጋ ጨምር ስላለው ብቻ የሚጨምር ተከራይ ካለ መብቱን እየተጠቀመበት አይደለም። መንግሥት በተከራይ እና አከራይ መካከል ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ጥረት አድርጓል እያደረገም ነው፤ አሰራርም የተበጀተው ተከራዮች ቢያንስ 2 ዓመት የሆነ ቦታ ተረጋግተው እንዲቀመጡ ነው” ሲሉ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያስታወቁት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ መቅደስ ወ/ጊዮርጊስ “አከራዮችም በተከራዮች በኩል የሚደርስባቸውን ያልተገቡ ነገሮች (ቤቱን ላልተገባ ነገር መጠቀም) መከላከል የመንግስት ድርሻ ነው” ብለዋል። “አከራዮች ተከራዮችን ውጡልኝ፣ ዋጋ ጨምሬ ነው የማከራየው ማለት ስለማይችሉ፣ ይሄ በጥቆማ ቢደረስበት ከክልከላዎቹ ውስጥ አንዱ ስለሆነ በሕግ ያስጠይቃቸዋል ” ሲሉ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ በአንድ ግድግዳ የተያያዘ የጭቃ ቤታቸው የተወረሰባቸው ዜጎች ለግማሽ ምዕተ ዓመት ከሚያገኟት ቅንጣቢ አበል ውጪ ሳንቲም ተጨምሮላቸው አያውቅም። ኢትዮጵያ እነዚህን ዜጎች እንዴት እንደምታያቸው እንደማይገባቸው የሚናገሩ፣ ከእነዚህ ምስኪኖች ላይ በአስርና ሃያ ብር ወይም ከዚያ በታች ተከራይተው፣ በሺህ ብሮች እያከራርዩ የሚኖሩ ምንም ባላወጡበት ቤት “ኪራይ እንጨምራለን” በሚል ተከራይን ሲያሰቃዩ የበታች አመራሩ ዝምታን መመረጡ በርካቶችን ያሳዘነ የአዲስ አበባ ውጓ ነው። የአገሪቱ የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ኃላፊነት ያላቸው በሙሉ “ደርግ ቤት ሲቀማ ሁለት ብር፣ አስር ብር፣ ሃምሳ በር፣ መቶ ብር … አበል እንዲከፈላቸው የተደረጉ ዜጎች፣ በአገሪቱ ታላላቅ ህንጻ የሚሰሩ ባለሃብቶች እና እነዚህ ዜጎች የሚተዳደሩበት የተዥጎረጎረ ህግ ሊስማማ የሚችልበት አሰራር ሊበጅ ይገባልና። እነዚህን በ2 ብር አበል ግማሽ ምዕተ ዓመት የዘለቁ ዜጎችን ልታሰቡ የግባችኋል” የሚል ለህሊና የሚሆን ጥያቄ አቅርበዋል።
አዲስ ሪፖርተር በዚህ አግባብ ያሰባሰበችውን መረጃ በቀታይ ታትማለች።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






