ትህነግ በድሮን ፍርሃቻ በጋማ ከብት ተደግፎ ውጊያ ለመጀመር ተዘጋጅቷል፤ “ይፎክራሉ እንጂ አይዋጉም” የሁለቱ የትህነግ ሰዎች ግጭት – የዝግ ስብሰባው የ”ቅምሻ”ሪፖርት

Date:

አዲስ ሪፖርተር – የስብሰባው ቅምሻ ከዋናው ስብሰባ በላይ ሚስጢርና የልብ መሻት በድንገት የተገለጡበት ነበር። የዚያኑ ያህል ከአንድ አሳብና ድርጅት የተቀዱ ከፍተኛ አመራሮች በመሰረታዊ ጉዳይ የተለያየ ቅምሻ ያዘጋጁበት ነበር። “ነገሩ አልቋል። የብልጽግና መቃብር እየታየኝ ነው” በሚል አንደኛው ሲናገሩ፣ “ቢፎክሩም ወደ ጦርነት አይገቡም። ያስማሙዋቸዋል” በማለት ተሰብሳቢዎቹን ግራ አጋብተዋል። ይህ የጦርነት ዝግጅትና የቅድመ ድል ዜና የሚነገረው “የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኛነት የጋራ የትግል መድረክ” ላይ ነው። 

“ጦርነት ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም፣ ተጠባባቂ ኃይል ያስፈልጋል። ይህ ተሰርቷል። የዓለም ሚዲያዎችና የእኛው ሰዎች ሳይቀር ከአዲስ አበባ ተንጫጭተዋል” በማለት ትህነግ ለጦርነት ዝግጅት አፈሳ የሚያካሂድበትን መነሻ አስረዱ። አከሉና የድሮን ጥቃት ስለሚፈራ በኮምቦይ መነቃነቅ ስለማይቻል፣ ሎጂስቲክ በአጋሰስና በሰው ኃይል እየተጓጓዘ ዘመቻው እየተካሄደ መሆኑን አመለከቱ። ባልደረባቸው “እኔ እንኳን ቢፎክሩም ወደ ጦርነት የሚገቡ አይመስለኝም” በማለት ተናገሩ።

“የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኛነት የጋራ የትግል መድረክ” በሚል ጥላ ስራ ምርጫ እንዳይካሄድ፣ ቅቡልነት እንዳይኖረው፣ አመጽ በማቀጣጠል የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሻዕቢያ ክንፍና የትህነግ ክንፍ የሆኑት አመራሮች እንዲጣመሩ ተደርጎ እንደነበር በተደጋጋሚ የስብሰባውን ተሳታፊዎች በመጥቀስ በተደጋጋሚ መዘገባችን አይዘነጋም። 

የጋራ መድረኩ ባሰብው ልክ የፈጸመው ተግባራዊ ጉዳይ ባለመኖሩ ራሱን ገምግሞ አዲስ የቀጣይ የትግል የትኩረት አቅጣጫዎችና መርሃግብሮች አዘጋጅቶ ነበር። “ውድቀት” የሚል ስም ሰጥቶ ስራውን የገመገመው ይህ ስብሰብ ያወጣው አዲስ ዕቅድ በፕሮፌሰር ሕዝቅዔል “አንዱ በሌላው ስራ ጣልቃ መግባት የለበትም” በሚል ተተችቶ፣ ሌሎች ደግሞ “የትጥቅ ትግልና ሰላማዊ አመጹ መነጣጠል  የለባቸውም” በማለት በቀረበው ዕቅድ ላይ ሃሳብ ከሰጡ በኋላ፣ የግምገማው ሰነድ ለሁሉም ተበትኖ እንዲመከርበት ቀጠሮ ተይዞ ነበር። 

በተደጋጋሚ ስብሰባ ተሳታፊዎች አቶ ልደቱና አቶ ነዓምን / የትህነግ እና የሻዕቢያ ክንፍ ጠርናፊዎች ናቸው/ ጨምሮ መገኘት ባለመቻላቸው ሲንከባለል ቆይቶ ረቡዕ ዕለት በዕቅዱ ለመወያየት ስብሰባ ተጠርቶ ነበር። ከሌላው ጊዜ በተለየ ስምንት የሚጠጉ አባላት በተገኙበት ስብሰባ ሌሎች እስኪገቡ “መረጃ እንለዋወጥ” ተብሎ በተከፈተው የቅምሻ መድረክ የትህነግ ወኪል የሆኑት አቶ አባይ ግደይ “ሳምንቱ ሕዝብ የማሳመን ስራዎች የተሰሩበት ነበር” በማለት ኢንጂነር ግደይ ከተናገሩ በኋላ ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል። 

“በፕሪቶሪያ ሰበብ እጅ እግራቸው ተይዞ ቆይቶ እንጂ በሰላማዊ ስምምነት የሚደረግ ነገር እንዳልነበር አስቀድሞ ታውቋል” በማለት ቀደም ሲል “የፕሪቶሪያው ስምምነት ለዝግጅት ነው” በሚል በትህነግ አማካይነት የተገለጸውን ደግመዋል። 

በተለያዩ ስብሰባዎች ሱዳን ወዳለው የትግራይ ኃይል በመሄዳቸው ስብሰባ መካፈል እንዳልቻሉ የሚገልጹት አቶ አባይ፣ የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋና ኦባሳንጆ ቢያስፈራሩም ተቀባይነት እንዳላገኙ ገልጸው እንዳስታወቁት መሬት ላይ እርምጃዎች ተጀምረዋል። ዋናው ኃይል [ትህነግ] በቀጥታ ጦርነት እንዳልገባበት አመልክተው ነገሩ የቀናት ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል። 

አውሮፓና አሜሪካኖች የተሳሳተ ሂሳብ ሰርተው እንደነበርና ከዚያው ስህተታቸው መውጣት እንዳቃታቸው ያስታወቁት አቶ አባይ፣ ትህነግም ሆነ ወታደሩ አለመፍረሱን አመልክተዋል። ይልቁንም ጽምዶ ተፈጥሮ እየጠነከረ መሆኑን ገልጸው በሱዳን ጦርነት አርሚ 70 እና ስሙን ሳይለዩ የትግራይ ኃይል የሚነቀሳቀስበት የኩምሩክ አቅጣጫን ድል እንደ ማሳያ አሳይተዋል። 

የሱዳን እና የኤርትራን ተሳትፎ፣ የፋኖና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጥምረት አወድሰው መንግስት መደናገጡን በማስታወቅ “ጉዳዩ ሁሉ በብልጽግና መቃብር ላይ ሆኗል። እናንተ ትግርኛ ስለማትሰሙ እንጂ ነገሩ ያበቃ ነው” በማለት በእምነት የተናገሩት አቶ አባይ፣ “ጻድቃን፣ ጌታቸው፣ አንዳንድ ጄኔራሎች፣ አፋር የሰፈረው የሰላም ኃይልን ይዘው የሚጨርሱት መስሏቸው ነበር አልሆነም” በማለት ድርጅታቸው ወደ አሸናፊነት እንደሚያመራ አመልካተዋል። አሁን ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ አሜሪካ መሆናቸውን አመልክተው የሚሆነውን እናያለን ብለዋል። 

አቶ አባይ ከአሁን በኋላ ስምምነት የሚባል ነገር እንደማይኖር አመልክተው፣ “ህገ መንግስቱ የሚፈቅደውን ሁሉ መሞከር አይቀርም” ሲሉ ከድል በኋላ ለመገንጠል ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል። በዚሁ ንግግራቸው መልሰው “ጉልበታቸውን ካሳዩ በኋላ ድርድር ሊኖር ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል። ድርድሩ ሁሉን እንዲያካትት ምኞት መኖሩን አስታውቀዋል። 

“አዲስ አበባ እስክንገባ ብቻችን እንሸከመዋለን ማለት አይደለም፥ ብዙ አጋሮች አሉን ።አዲስ አበባ በር ላይ ፋኖ አለ፣የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አለ ስለዚህ ብዙ ወዳጆች አሉን” በማለት ሞንጀሪኖ ሰሞኑን መናገራቸው አይዘነጋም። ዶክተር ደብረጽዮንም ካሁን በኋላ በሰላም የሚፈታ ጉዳይ እንደሌለና ብልጽግናን መቅበር ብቻ አማራጭ እንደሆነ ማናገራቸው አይዘነጋም።

የቀድሞ የትህነግ መስራችና የፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት፣ በትግሉ አመራር ቀዳሚ የሚባሉት ኢንጂነር ግደይ ዘርዓጽዮን በበኩላቸው “በትግራይና በፌደራል መንግስት መካከል ያለው ሁኔታ ተካሯል” ካሉ በኋላ “እኔ እንደሚመስለኝ ቢፎክሩም ወደ ጦርነት የሚገቡ አይመስለኝም” ብለዋል። 

ኢንጂነር ግደይ “ጽምዶ ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ስለሚያሰጋው ብዙ የሚሄድ አይመስለኝም” በማለት የሚያውቁትን ተናግረዋል። ይልቁኑም በሽምግልና የሚያልቅ ይመስለኛል። መካከላቸው ገብተው ያስታርቋቸዋል” ብለዋል። ቀደም ሲል በተደረገ ስብሰባ “የብልጽግናን መንግስት የተረዳነው አይመስለኝም። ከማን ጋር እየተዋጋን እንደሆነም አ፤ልገባንም። የደህንነት ባለስልጣኖቻቸው አሜሪካ ተገኝተው ከአሜሪካ የጸጥታ መዋቅርና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መክረዋል። ባለን መስመር እናጠናዋለን” በማለት ለዲፕሎማሲው አገባብ ቅርብ መሆናቸውን የተናገሩት ኢንጂነሩ “ሽምግልና አለ” በሚል የሚሰማውን ጭምጭምታ ይፋ ሲያደርጉ ከምንም ተነስተው እንዳልሆነ ከተሳታፊዎቹ መካከል መረጃ የሰጡን አመልክተዋል። 

አዲስ አበባ የሚገኙ የቀድሞ የሚታወቁ ጄኔራል “እመነኝ ትህነግ ጦርነት አይጀምርም። ኃይል አሰባስቦ ለመደራደር ነው አሳቡ” በማለት ከወራት በፊት ለአዲስ ሪፖርተር መናገራቸው አይዘነጋም። 

መረጃውን አሰባስቦ የላከው የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ እንዳለው፣ ስብሰባው ላይ ቀደም ሲል የሚታወቁት የአጋር ድርጅት ወኪል እንደሆኑ የሚናገሩት አልተገኙም። በስብሰባው ላይ ኢንጂነር ሙሉጌታ “ጉንጭ አልፋ” ሲሉ ዕቅዱን የነቀፉ ሲሆን አቶ ጂሬኛ ደግፈዋቸዋል። አቶ ልደቱ ለአባላቱ ወርክሾፕ እንደሚያስፈልግ በማንሳት የግንዛቤ ችግር እንዳለ አመልክተዋል። 

የሰላማዊ ትግል በሚል ስም መጠቀሙ ለውጪው ማህበረሰብ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ በዚሁ መቀጠል እንዳለበት የሰብአዊ መብት ተከራካሪ እንደሆኑ የሚናገሩት የስብሰባው ካቦ አቶ ያሬድ ተናግረዋል። ሰላማዊ ትግል የሚለው ስም በአገር ቤት ላሉ የህቡዕ ተባባሪዎች መደብቂያ እንደሚመች፣ መንግስት ሲነካቸው ለመጮህም እንደሚጠቅም፣ የውጭውን ማህበረሰብና ሰላማዊ ትግል ብቻ የሚሉ ወገኖችን ለማሰባሳብ ሲባል የመረጠ እንጂ በውስጠ ታዋቂ የሚሰራው የሚታወቅ እንደሆነ አመልክተዋል ይህን ባሉበት አንድበታቸው “እኔ መቼም የመብት ተከራካሪ በመሆኔ የትጥቅ ትግል በምንም ዓይነት መልኩ አልደግፍም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወኪል፣ የትህነግ ወኪል፣ የፋኖ፣ የሻዕቢያና ወዘተ ታጣቂ ኃይል ወኪሎችና ሌሎች ታጣቂዎችን በውክልና የሚያደራጁ በተካተቱበት የጋራ መድረክ ሰብሳቢ የሆኑ አቶ ያሬድ፣ አዲስ ሪፖርተር መረጃ እያወጣ ስለሚያስቸግር ለኤፍ ቢ አይ እንዲከሰስ የሚል ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም። አቶ ያሬድ በተሻለ ክፍያ አቶ ልደቱ ከሚመሩት የትህነግ ክንፍ ወደ አቶ ነዓምን የሻዕቢያ ክንፍ መዘዋወራቸውን አባላቱ መናገራቸው ይታወሳል። 

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related