የአሜሪካ የቪዛ ዕግድ “ከህወሓት አክራሪ ኃይሎች ጀርባ ሆነው ድጋፍ የሚሰጡ ኃይሎች” የተባሉትን አስደንግጧል፤ “ዕግዱ ወደ ከፍተኛ ማዕቀብና ፍረጃ የሚሰፋና የሚያድግ ነው”

Date:

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ|የአሜሪካ መንግስት የጣለው የቪዛ ዕገዳ የመጀመሪያ የሌሎች ማዕቀቦችና ፍረጃዎች መንደረደሪያ መሆኑ ተመለከተ፤ አሜሪካ የጣለችው የቪዛ ክልከላ ውሳኔ ዒላማ የሚያደርገው በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፉ፣ ተጠያቂ በሚሆኑ አካላትና ተባባሪዎቻቸው ላይ እንደሆነ መገለጹ የዚሁ ዕቅድ ማሳያ ነው ተብሏል።

መግለጫው «ኃላፊነት ባለባቸውና ተባባሪ በሆኑ ግለሰቦች» ላይ ያነጣጠረ ነው ማለቱ፣ ከህወሓት አክራሪ ኃይሎች ጀርባ ሆነው ድጋፍ የሚሰጡ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ ግለሰቦች ወይም አብረው የሚሰሩ ሌሎች ቀጠናዊ ኃይሎች (የኤርትራን መንግሥት ጨምሮ) ሊሆኑ እንደሚችሉ መግለጫውን የተመለከቱ ወገኖች እየገለጹ ነው።

የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግተን ተባባሪ ያናገራቸው የጋራ መድረክ አባል፦ “የህወሓት መስራች የነበሩት ኢንጂነር ግደይ፣ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት አብረው መክረዋል። የምንዋጋው ከማን ጋር እንደሆነ ያወቅን አይመስለኝም። ባለን ግንኙነት እስክናጣራው ድረስ ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው በማለት በአመጽ አደራጅ ግብረኃይል ስብሰባ ላይ ማሳሰቢያ ከሰጡ በኋላ ስጋት ነበር” በማለት ይጀምራሉ።

በግብረኃይሉ ውስጥ ምርጫውን ማጨናገፍ እንዳልተቻለ ከተታመነ በኋላ፣ ያለው አማራጭ የሃይማኖት ክንፉንና ታጣቂ ኃይሎችን አጣምሮ የሚንቀሳቀሰውን “ጽምዶ” መደገፍና አብሮ መስራት ብቸኛው አማራጭ ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑን አዲስ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት ዘግባ ነበር። የተለያዩ ታጣቂዎች ከህወሓት ጋር ሆነው በጋራ ጥቃት ለመጀመር በቋፍ ላይ እንደሆኑም ተመልክቶ ነበር። እያደራደሩና እያስማሙ የነበሩ አካላት በስብሰባው ላይ ሪፖርት ሲያቀርቡ የሚያስረዳ ኦዲዮም ለአዲስ ሪፖርተር ደርሶ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

“መንግሥት ከአሜሪካ ጋር እየመከረ ነው። ምን አልባትም ጉዳዩ ወደ ሽብርተኝነት ፍረጃ ሊያድግ ይችላል” በሚል በዚሁ መድረክ ላይ በስጋት መነሳቱን አስታውቀን ነበር። በሰላማዊ ትግል ስም ታጣቂ ኃይሎችና ወኪሎቻቸው የሚሳተፉበት ግብረኃይል ውስጥ ካሉት መካከል፤ አገራቸውን የሚወዱ ነገር ግን ዋናዎቹ የሚያውቁትን ምስጢር የማያውቁ አሉ። ሰሞኑን የግብረኃይሉ ሰብሳቢ የተደረጉት ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሳ “የቦርዱ መሪ የአደባባይ ሰው መሆን የለበትም” በማለት ምርጫውን አለመቀበላቸውን ባሳወቁበት ደብዳቤ “እኔ ከስራ አስፈጻሚው ከተለየሁ ቆይቻለሁ” ማለታቸውን መረጃ እንዳላቸው አመላካች አድርገው ወስደውታል።

“የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የቪዛ እገዳው በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ በሰላም ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ኃላፊነት ባለባቸውና ተባባሪ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው” ማለታቸው ስጋት የፈጠረው፤ ውሳኔው እየጠነከረ የሚሄድ፣ ተከታይ አሳሪ ጉዳዮች የሚኖሩትና እያደር ሊሰፋ የሚችል እንደሆነ ባለሙያዎች እየገለጹ በመሆኑ ነው።

የአሁኑን መግለጫ የፖለቲካ ተጠያቂነትን ወደ አንድ ወገን ማዞር (Targeted Blame) እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች፣ ዋሽንግተን ከዚህ ቀደም በነበሩት መግለጫዎቿ በተደጋጋሚ «ሁሉም ወገኖች» የሚል አጠቃላይ የአገላለጽ ዘይቤ ትጠቀም እንደ ነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን የቪዛ እገዳው «በህወሓት ጽንፈኞች (Hardliners)» ላይ ብቻ ማነጣጠሩ፣ አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ በድጋሚ እያገረሸ ላለው ውጥረትና ግጭት ተጠያቂው በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ ነው የሚል ግልጽ የፖለቲካ አቋም ለመያዟ ማረጋገጫ ነው።

መግለጫው ቀደም ሲል በትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) እና በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት (ENDF) መካከል የተከሰተውን ቀጥተኛ ግጭት በይፋ ጠቅሷል። ይህም አሜሪካ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ መውደቁን በጽኑ እንደሚያሳስባትና ስምምነቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ለማስገደድ የወሰደችው የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን ያሳያል። ይህ እርምጃ የመጀመሪያው ከሆነ “በቀጣይ ምን ሊከተል ይችላል?” የሚለው ነው አሁን ላይ ትኩረት የሳበው።

የእገዳው መመሪያ ግለሰቦቹና ተባባሪዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን በተለይ «የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸውን» ጭምር ማካተቱ ትልቅ ትርጉም አለው። ብዙዎቹ የፖለቲካ እና የጦር አመራሮች ልጆቻቸው ወይም የትዳር አጋሮቻቸው በአሜሪካ የሚኖሩ፣ የሚማሩ ወይም ለሕክምና የሚመላለሱ በመሆናቸው፣ ይህ ዓይነቱ ማዕቀብ በአመራሮቹ ላይ ቀጥተኛና ከባድ የስነ-ልቦና እንዲሁም የውስጥ ፖለቲካ ጫና የመፍጠር አቅም አለው።

የአሜሪካ መንግሥት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ‹‹ቪዛ ለማያስፈልጋቸውስ?›› የሚል ጥያቄ በመሰንዘር የማዕቀቡን ወቅታዊ ፋይዳ ለማጣጣል ሞክረዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ፦ “በአሁኑ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቪዛ የማይፈልጉ ተፈናቃይ ዜጎች አሁንም በረሃብና በበሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በመሆኑም ትኩረትን በጥቂት ግለሰቦች ላይ በተጣለ የቪዛ እገዳ ላይ ከማድረግ ይልቅ፣ መሠረታዊ ዕርዳታና ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ምስኪን ወገኖች ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል። አቶ አማኑኤል አክለውም ይህ የተጣለው የቪዛ ማዕቀብ አሁን ባለው ተጨባጭና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለእነሱ እንብዛም የሚያሳስብ ወይም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዜና አለመሆኑን በግልጽ አስታውቀዋል።

በአሜሪካ መንግሥት የወጣው ይህ የመጀመሪያ የተባለ እርምጃ፣ በአሜሪካ የሚኖሩ የህወሓት ሰዎችን ቤተሰቦች፣ ከፍተኛ አመራሮችንና በተለያዩ ደረጃዎች አብረዋቸው የሚሰሩትን ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ሚዲያዎች ሳይቀር እንዳስደነገጠ የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ ባሰባሰበው መረጃ አረጋግጧል።

መግለጫው «ኃላፊነት ባለባቸውና ተባባሪ በሆኑ ግለሰቦች» ላይ ያነጣጠረ ነው ማለቱ፣ ከህወሓት ጽንፈኞች ጀርባ ሆነው ድጋፍ ለሚሰጡ ወይም አብረው ለሚሰሩ ሌሎች ቀጠናዊ ኃይሎች ጭምር የተሰጠ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ተደርጎ እንደሚወሰድ የሚናገሩ ወገኖች፦ “የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት መቀሌ ተገኝተው ጦርነት መጀመር እንደማይቻል፣ ጦርነቱ በቀጣናው የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስተጓጉል ጠቅሰው ከሰጡት ማሳሰቢያ ጋር ይያያዛል። ወይም የአሁኑ ውሳኔ የዚያ ማስጠንቀቂያ ተከታይ ነው” የሚል አቋም አላቸው። አሜሪካ በተመሳሳይ ኤርትራንም ማስጠንቀቋንና የሱዳን መሪ ጄኔራል አልቡርሃንን በሽብር መፈረጇንም ከዚህ ውሳኔ ጋር ማያያዝ ጠቃሚ እንደሆነ ያነሳሉ።

ይህ የአሜሪካ መግለጫ በህወሓት የውስጥ ያለውን ክፍፍል እንደሚያጎላው የሚናገሩና ቅጣቱ ውስጥ ውስጡን እንደ ረመጥ ለቆየው ሌላ ዙር ክፍፍል ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን አዲስ አበባ ያሉ የቀድሞ የህወሓት መኮንኖች እየገለጹ ነው። አሜሪካ የደብረጽዮንን ቡድን «ጽንፈኛ» ብላ መፈረጃዋ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት መሬት ይፈጠፍጠዋል። በጽንፈኛነት የተፈረጀውን የፓርቲውን ክንፍ የውጭ አገር አመራሮችን ደግሞ ከዲፕሎማሲው መድረክ ይገፋቸዋል።

በዚህ ደረጃ የአሜሪካን የቪዛ ገደብ የሚመለከቱ ወገኖች፣ ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችልም ቅድመ እይታቸውን ያጋራሉ። የቪዛ እገዳውን የሚያጣጥሉና “እርባና የለሽ” ከሚሉት በተለየ፣ ስጋቱ ያለባቸው ክፍሎች፦ “እርምጃው ሊጠብቅ፣ ሊሰፋ እና ከዚያ በላይ ወደ ፅኑ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ሊሸጋገር ይችላል። ይህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወሰደው የቪዛ ገደብ ውሳኔ ከፍተኛ የፖለቲካ ትርጉም ያለው ሲሆን፥ ሂደቱ ካልተቀየረ እርምጃው ሊያድግ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው” ሲሉ ህወሓት አቋሙን እንደሚያስተካክል ይናገራሉ።

እነዚሁ ወገኖች አክለው፦ “እርምጃው አሁን ባለበት አይቆምም። በትግራይ ክልል ያለው ውጥረት ካልረገበ እና አመራሮቹ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በሰላማዊ መንገድ ካልተስማሙ አሜሪካ ‘ያሉኝን የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሣሪያዎች በሙሉ እጠቀማለሁ’ ስትል አስጠንቅቃለች” በማለት የህወሓት ብቸኛ አማራጭ ወደ ፕሪቶሪያው ስምምነት ማቅናት እንደሆነ ይገልጻሉ። መንግሥት ኦባሳንጆ ወደ ትግራይ ሲሄዱ “ድርድሩ ፕሪቶሪያ አልቋል፤ የቀረው ትግበራው ነው” ማለቱን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም። አሜሪካም ጥያቄዋ ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት ተመለሱ የሚል ነው።

“ማዕቀቡ የተነጣጠረው በግለሰቦቹ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ እነሱን ደግፎ በሚያቆመው የስልጣን፣ የገንዘብ እና የደጋፊዎች መረብ (Network) ላይ ጭምር በመሆኑ ተባባሪዎችን በሙሉ የመብላት ዕድሉ ከፍተኛ ነው” የሚሉት ወገኖች፣ በቅርቡ የህወሓት የገንዘብ ምንጮች፣ የንግድ ተቋማትና ከእነሱ ጋር የገንዘብ ግንኙነት ያላቸው ላይ የሚያነጣጥር ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ትናንትናው ዕለት አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ባለቻቸው አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን አስመልክቶ ከመንግሥት ወገን የተባለ ነገር የለም።

አሜሪካ በቅርቡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ዙሪያ አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስትራቴጂካዊ ስምምነት ማድረጋቸው አይዘነጋም። ስምምነቱ በውጭ አገር ያሉ የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶች አጋርና አመራሮችን ማስደንገጡም የሚታወስ ነው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

U.S. Imposes Visa Restrictions on Hardline TPLF Members and Families, Citing Threats to Peace

ADDIS REPORTER ADDIS ABABA — The United States government...

መመህር ፋንታሁን ዋቄና ተባባሪዎቻቸው ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ እንዲደረግ ክስ ቀረበባቸው

አዲስ ሪፓርተር ዜና ፡- በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፣"በሃይማኖት ሽፋን...