ለገዳይና ሟች እኩል ሃውልት የሚተክለው አማራ ክልል – በመላኩ አለበል  አንደበት፤ ደመቀ መኮንን ለምን ዝም ይላሉ?

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ አቶ ምግባሩና አቶ ቢኒያም አንዱዓለም በባህር ዳር በግፍ ከተገደሉ በኋላ የአሁኑ የአፋብን የጦር አዛዥ ብረጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በግልጽ ቋንቋ የጥቃቱ አስተባባሪ ብሪጋድየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ መሆናቸውን መስክረው ነበር። የመሰከሩትም ለበቃሉ ነው ይህንን ሊንክ ያድምጡ። https://www.youtube.com/watch?v=JqciCsIyqyc

ከግድያው በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርት በፌደራል መንግስት አቃቤ ህግ አማካይነት ከቀረበ በኋላ ምርመራው ወደ አማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ተመራ። አማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊው አቶ ምግባሩ በመገደላቸው ምክትላቸው ስራቸውን በብቃት እያከናወኑ ምርመራው ወደ ዋናዎቹ የወቅቱ አመራሮች ሄደ። በድንገት ምርመራው እንዲቆም አቶ ደመቀ አስወሰኑ። ለምን? እንዴት? ከዛስ? አማራ ክልል የሚናጥበት ቁልፍ ከዚህ ጉዳይ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ብዙ ተብሏል። 

አቶ መላኩ አለበል ይህንን ባያነሱም የአማራ ክልል አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰበት መነሻ በዚያች ክፉ ቀን ሰኔ 15 የተፈጸመው ግድያ እንደሆነ አመላክተዋል።

ተርመጥምጦ የቀረው የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ግድያ “አማራ ክልል ሟችና ገዳይን እኩል አጀገኖ ይፎክራል” ከሚለው ወደፊት የሚጣራ ስላቅ ውጪ የሚጨበጥ መረጃ በቅርብ ካሉት አካላት አልተሰማም። ወይም ደፍሮ የሚያፈርጥ ይፈትህ ወዳድ ጀግና አልተገኘም። በሰፈርና በአካባቢ የሚያስቡ የተሰገሰጉበት አማራ ክልል ይህን ግፍ የሚያፈርጥ ጀግና ይፈልጋል። የሟቾቹ ደም ይጮሃል። የወቅቱ አመራሮች አዲስ አበባን ጨምሮ “በሸነና” ይላሉ። አገሪቱ በጥቅሉ፣ አማራ ክልል በተለየ እንዲታወክ ሌት ተቀን የሚሰራውም ፍርድና ፍትህን ፍርሃቻ ስለመሆኑ ይህ ምስክር ነው። 

በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከተፈጸመው አስከፊ የግድያ ጥቃት የተረፉት የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ አለበል ቀኑን አስመልክተው “ከዋዜማው እስከ ተቋማዊ ስብራት” ያስዳሰሰ አጭር ጽሁፍ በማህበራዊ ገጻቸው አሰራጭተዋል። 

Yibeltal Atnafu የተባሉ አስተያየት ሰጪ፣ “ሰኔ 15 እንዲሁ በአንድ ጀንበር የተከሰተ ክስተት አይደለም ይልቁንም የቅድመ አደጋ ምልክቶች በግላጭ እየታዩ እነሱን ሊያርም የሚችል ስትራቴጂካዊ አመራር በመጥፋቱ የተከሰተ አሳዛኝ ክስተት እንጅ ” በማለት በአቶ መላኩ አለበል ጽሁፍ ስር አስተየት ሰጥተዋል። 

“መቼና የት የሚለው ካልሆነ በስተቀር ያልተገባ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ችግር ሊከሰት እንደሚችል ብዙዎቻችን ከሰኔ 15 በፊት በነበሩ መድረኮች ታዝበን ነበር። በተለያዩ የአማራ ክልል የአስተዳደር እርከኖች የነበርን አመራሮች ክልሉን አንድ የሚያደርጉ የአስተሳሰብ ግንባታዎችን ልንጨብጥና የጋራ ተልዕኮዎችን ልንቀበል በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠን ባህርዳር ከገባን በሗላ በመድረኩ የምንታዘበው ውረድ እንውረድ አይነት ፉክክር ነበር ማለት ይቻላል” ሲሉ አደጋው የሚጠበቅ እንደሆነ ይበልጣል አጥናፉ ጠቁመዋል።  

“ይህ ለአማራ ክልል ቀርቶ በቀበሌ ደረጃ ለሚካሄድ መድረክ የማይመጥን የስድብና ነቆራ ንትርክ መጨረሻው በምን ሊቋጭ እንደሚችል ለመገመት የፖለቲካ ሀሁ… ብቻ ማወቅ በቂ ነበር ። በየትኛውም መድረክ የሚነሳ የሃሳብ ፍጭት ተፈጥሯዊ ነው ፤ ለተሻለ ድምዳሜም ያደርሳል ። ነገር ግን በመናናቅ የታጀበ ሂስ አይሉት ግለ ሂስ አይነት የቃላት ጦርነት ከግለሰቦች መስዋዕትነት ባለፈ በክልላችን ሰማይ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ እንዳልፈ በቁጭት ያነሱት አስተያየት ሰጪው፣ ” የችግሩን መነሻም ሆነ የተጠያቂነት አድማሱን ልናጠበውም ሆነ ልናሰፋው እንችል ይሆናል ዋናው ምክንያትም ሆነ ተጠያቂ ግን በወቅቱ የነበረው የአመራር ስብስብና የችግሩን ቅድመ ማስጠንቀቂያ pro active ሆኖ መቀልበስ ያልቻለው አካል ነው ። አሁንም ቢሆን ከሰኔ 15 ትምህርት መውሰድ እንጅ ዓመት እየጠበቅን መብሰልሰል ፋይዳ ስለሌለው እያንዳንዳችን ከአውራጃዊ አስተሳሰብ ከፍ ባለ መልኩ ትልቁ የወል ትርክት ላይ ማተኮር ይኖርብናል” ሲሉ የወቅቱ አመራር ላይ አተኩረዋል። 

የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ በነጥብ ዘርዝረው ለትምህርት እንዲሆን ባቀረቡት ጽሁፍ ውስጥ የሚሰማ ስሜት ስለመኖሩ ግን ጥርጥር የለም። በየትኛውም ስሌት ገዳይ ሌተናል ጄኔራል አሳምነውና ዶክተር አንባቸውን ጨምሮ አብረዋቸው የተገደሉት እነ ምግባሩ እኩል ጀግና ሊባሉ አይችሉም። 

የግድያውን ወንጀል ለማጣራት ኃላፊነት ከፌደራል መንግስት ወስዶ የነበረው የክልሉ ፍትህ ቢሮ ጥልቅ ምርመራ እያደረገ ጫፍ ሲደርስ አቶ ደመቀ መኮንን በክልሉ የፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ምርመራው እንዲቆም ማስወሰናቸውን አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች። ሙሉ ሪፖርቱን ለማቅረብ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ምላሽ ለማካተት ሲባል፣ እንደ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣን ምላሻቸውን ማካተት አግባብ በመሆኑ በሚቀጥለው ሳምንት እሳቸውን አካተን እናትመዋለን። አቶ መላኩ አለበል በሰጡት ጥልቅ ምክንያታዊነት ያለው ትነተና ይህን የሚድበሰበስ ጉዳይ ስለምን አያፈነዱትም የሚል ጥያቄም አዲስ ሪፖርተር አላት። 

የሰኔ 15 ዋዜማ እና ተቋማዊ ስብራት፡ ከውጤትና ምክንያት አዙሪት መውጫ መንገድ | በመላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር 

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ፣ የክልሉን ሕዝብ ወደማያባራ የግጭት አዙሪት ያስገባና በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ አስከፊ ክስተት ነው።

ይህ ድርጊት የክልሉን የፖለቲካ ሥልጣን ያዘበራረቀ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ በክልሉና በሀገሪቱ ለሚታዩት ዘርፈ-ብዙ ቀውሶች ከፍተኛ ድርሻ ያለው፣ የውጤትና የምክንያትን ባሕርይ አጣምሮ የያዘ የጋራ አንድነታችን ላይ የተጠመደ ስልታዊ ሽብልቅ ነው። 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ታሪካዊ ጣት-መጠቆሚያ ለመሆን ወይም ግለሰቦችን ለመውቀስ ወይም ለመክሰስ ሳይሆን፣ ከሂደቱ ልንወስደው የሚገባንን መዋቅራዊ ትምህርት መመርመርና ዘላቂ መውጫ መንገዱን ለማመላከት ብቻ ነው። 

“የሰኔ 15 ዋዜማ” የሚለውን ርእስ የመረጥኩበትም ምክንያት፣ ዕለታዊውን የወንጀል ድርጊት ብቻ ለይቶ ከመመልከት ይልቅ፣ ከ2010 ዓ.ም የለውጥ መነሻ ጀምሮ የነበረውን ስልታዊና ፖለቲካዊ ምኅዳር በጥልቀት መገምገም ተገቢ ነው ብዬ በማመኔ ነው።

ሰኔ 15 በአንድ በኩል ከዕለቱ በፊት ለነበሩት መዋቅራዊ ውጣ ውረዶች “ውጤት” ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ በክልሉ ለቀጠሉት መናጋቶች ትልቅ “ምክንያት” ሆኖ የሚጠቀስ የታሪክ መገናኛ ነጥብ ነው። ለወደፊት ስንቃችን ይሆን ዘንድ በዋዜማው የነበሩትን መዋቅራዊ ምክንያቶች በሚከተሉት አምስት ዋና ዋና ምሶሶዎች መክፈል እንችላለን፦

1. የሽግግር ወቅት የፖለቲካ ክፍተት (Transition and Security Vacuum)

በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ከአንድ የተማከለ የተጠናከረና ጨቋኝ የቁጥጥር ሥርዓት ወደ አዲስ ምኅዳር እየተሸጋገረች ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ የቀድሞው የፀጥታና የቁጥጥር መዋቅር ሲላላ፣ አዲሱ ሥርዓት ግን ራሱን በተቋም ደረጃ አላደራጀም ነበር። ይህ የተፈጠረው የፀጥታና የሥልጣን ክፍተት (Security Vacuum)፣ ሕጋዊ ተቋማትን አዳክሞ መደበኛ ያልሆኑ ኃይሎችና የታጠቁ ቡድኖች የክልሉን መንግሥት ሕጋዊ ሞኖፖሊ (Monopoly of Violence) እንዲገዳደሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

2.  የአክራሪ ብሔርተኝነት መነሳትና “እኛ እና እነሱ” ትርክት

ሽግግሩን ተከትሎ የመጣው ነፃነት ኃላፊነት ባለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገራቱ ፣ አክራሪና የፓለቲካ ነጋዴ ብሔርተኝነት እንዲገንን አድርጓል። የታሪክ ትርክቶች ሚዛናቸውን ስተው “እኛ እና እነሱ” ወደሚል የፖለቲካ መገፋፋት ተቀየሩ። ይህ ጽንፈኝነት የኢትዮጵያዊነትንና የጋራ አብሮነትን ድምፆች ያዳከመ ሲሆን፣ ችግሩ በአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ መልክ የተስተዋለ መዋቅራዊ ተግዳሮት ነበር።

3. ተቋማትን የበላ “ሕዝበኝነት” (Populism)

ፖለቲካው ከሕጋዊና ተቋማዊ አሠራር ይልቅ በስሜትና በፈጣን የሕዝብ ድጋፍ ማግኛ ስልቶች (Populism) ሲመራ፣ ተቋማዊ አሠራሮች እንደ ማነቆ መታየት ጀመሩ። ሕዝበኝነት ሲበረታ ግለሰቦች ከተቋማት በላይ ይገዝፋሉ፤ ሥርዓትም በሕግ ሳይሆን በቡድን ስሜት ይነዳል። በክልሉ ተፈጥሮ ለነበረው መዋቅራዊ መናጋት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ይኸው ስሜት-መር ፖለቲካ ነው።

4.  የፀጥታ ተቋማት ስብራትና የዕዝ ሰንሰለት መላላት

በወቅቱ የነበረው የፀጥታ መዋቅር የዕዝ ሰንሰለት (Chain of Command) የተዳከመና ውስጣዊ የታማኝነት ጥያቄዎች የተደቀኑበት ነበር። ከሁሉም በላይ፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ የስትራቴጂክ ትንተና እና ቅድመ-መከላከል (Proactive Intelligence) አቅም እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ አልፎ ተርፎም ውሳኔ ሰጪው አካል ጋር በወቅቱ የሚደርስ ባለመሆኑ ለጥፋቱ በር ከፋች ሆኗል።

5.  መደበኛ ያልሆነ ፖለቲካ እና የአመራር ቁመና (Shadow Politics)

የሰኔ 15 ክስተት የመንግሥትና የድርጅት መደበኛ አሠራር ከአዳራሽ በስተጀርባ (Behind the Scenes) ባሉ፣ ተጠያቂነትና ውክልና በሌላቸው አካላት የሚዘወርበት ምኅዳር የፈጠረው ውጤት ነው። ይህንን መደበኛ ያልሆነ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአመራሩ ቁመና በጽናት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ በበርካሽ ሕዝበኝነት (Populism) የተደፈቀ በመሆኑ የፖለቲካውን መሪነት ወደ ማጣት አድርሶናል።

ማጠቃለያ እና የመውጫ መንገድ

ስለዚህ፣ የሰኔ 15ትን አሳዛኝ ግድያ እንደ አንድ “የብቸኛ ወንጀል ድርጊት” (Isolated Criminal Act) ብቻ መመልከት ስህተት ነው። ክስተቱ የተዳከሙ ተቋማት፣ የፖለቲካ ሽግግር መናጋት፣ የሕዝበኝነት መስፋፋት እና የፀጥታ ክፍተቶች በአንድነት ተደራርበው የፈጠሩት መዋቅራዊ ችግር ነው።

በሰኔ 15 እና እሱን ተከትሎ በተፈጠሩ ግጭቶች ሁሉ የተሰውትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ነፋሳቸውን ይማር!

ዝግጅት ክፍሉ በዚህ ዘገባ ዙሪያ መረጃ ለሚያደርሱን ወረታ እንከፍላለን። ለፍትህ ዋጋ የምትሰጡ፣ በግፍ ወላጆቻቸውን ላጡ ድምጽ መሆን የምትወዱ የምታውቁትን መስክሩ፤

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related