ሰርጉ በድንገት ወደ ለቅሶ ተቀየረ። ሰርግ የተጠሩ እናት ድንገት እንባቸው ወረደ። ራሳቸውን ሊቆጣጠሩ ቢሞክሩም አልቻሉም። እንባቸው እንደ ጅረት ውሃ መቆሚያ አጣ። ሲቃ እየያዛቸው “ልጄ ተርፎ ቢሆን እኔም እድረው ነበር” እያሉ አነቡ። ሰርጉ ላይ የነበሩት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ልጆቻቸውን ለህወሃት የገበሩ ነበርና ቁስላቸው አገረሸ። ሙሽራ የቆመበት የመቀለ ከተማ (ስምና ቦታ ልይቶ መጥቀስ አግባብ ባለመሆኑ ነው) ሰርግ ወደ ለቅሶ ተቀየረ። ሁሉም ታዳሚ ሆድ ሆዱን እየበላው አነባ። እርስ በርስ ተላቀሰ። ይህ አጋጣሚ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሆን ነው። ይህ የህወሃት ጦስ ውጤት ከሆኑት ማሳያዎች አንዱ ነው። ይህ የትግራይ መርገምት፣ የኢትዮጵያ መከራ የሆነ ድርጅት ምሱ ደም ነውና አሁን ደግሞ ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ይገኛል። እናም የትግራይ ኤሊቶችና ወጣቶች ቢሰሙ እንደዚህ ጮህኩ!!
መግቢያ
በመቆያ ምሕረተአብ (ነጻ አስተያየት)
አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — በኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም. የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ የሕወሓት አመራር የተከተለው የፖለቲካና የጦርነት መስመር ሀገሪቱን ለከፍተኛ የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ዳርጓል። ድርጅቱ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በኢሕአዴግ ውስጥ የተካሄደውን የአመራር ለውጥ ለማደናቀፍ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ለውጡ እውን ከሆነ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌ ባደረጉት ጉብኝት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ያገኙትን ሞቅ ያለ አቀባበል ተከትሎ በተፈጠረበት ድንጋጤና ቁጣ በመላ ሀገሪቱ ነውጥ ለማስነሳት ተረባርቧል። የቻለውን ሁሉ አድርጎ ሀገሪቱን አውኳል። የዘረፈውን ሀብትና ንብረት እየረጨ በመላው ሀገሪቱ የትርምስ ኃይል በማሰማራትና ስፖንሰር በማድረግ ሕዝብ እረፍት ነስቷል። ደም ፈሷል፤ የሰው ልጅ አልቋል፤ ምስኪኖች ተፈናቅለዋል፤ ንብረት ወድሟል፤ መሠረተ ልማት ፈርሷል፤ የተቀናጀ ዘረፋ ተካሂዷል። ዛሬም አልቆመም፤ እንዲያውም ተባብሶ ሀገሪቱን ለማፍረስ ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ሳይቀር በይፋ ጥምረት መስርቶ ለሌላ ዙር እልቂት “እፎይ” ሳይባል ድግስ እየደገሰ ይገኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን “የመንግሥት ትዕግሥት ሊያልቅ ቢችልስ?” ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው። መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ትዕግሥት ካለቀ ምን ሊከተል እንደሚችልም ማስላት ብልህነት ይሆናል።
ሕወሓት አብዝቶ የሚጠላውና የሚያስበርግገው ነገር ቢኖር ለውጥና አዲስ አስተሳሰብ ነው። ሥጋት፣ የስልጣን እና የጥቅም ይቀርብኛል ፍርሃት፣ ተጠያቂነትን የመሸሽ እንዲሁም ለግማሽ ምዕተ ዓመት የቆረበበት የማዕከላዊ ፖለቲካ ባህል የመከተል አባዜው በዘመኑ ሁሉ አንድ ቦታ «የተቸከለ» ድርጅት አድርጎታል። ለዚህም ነው በጫካ ሕይወቱ፣ መንግሥት ሆኖ በአራት ኪሎ፣ በመንግሥት ስም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ መማርና መዘመን አቅቶት ወደ ሽፍትነት ተመልሶ ዳግም የትግራይን ሕዝብና የኢትዮጵያን መከራ የሆነው።
በሕወሓት የሕይወት ታሪክ ውስጥ የውስጥ ሽኩቻ፣ የርስ በርስ ግድያ እና የስልጣን ሴራዎች ጎልተው የሚወጡ ወጉ የሆኑለት ናቸው። ይህ ክፉ ወጉ በበርካታ የቀድሞ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ታጋዮች በጽሑፍም ሆነ በቃለ መጠይቅ ምስክርነት የተሰጠበት፣ እሱም ሊክደው የማይችለው ገጽታው ነው።

ለሕወሓት እርም ከመሰከሩት መካከል ጎልቶ የሚጠቀሰው የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት እና የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት የአቶ ገብሩ አስራት ምስክርነት ነው። አቶ ገብሩ «ሉአላዊነት እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ» በተሰኘው መጽሐፋቸው እና በተለያዩ ቃለ መጠይቆቻቸው ላይ እንደገለጹት፤ ሕወሓት በትግሉ ወቅት የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ታጋዮች እና አመራሮች «ጸረ-ድርጅት» ወይም «ባንዳ» በሚል ስም ይፈርጃል። ሴራ ፈጥሮ ያፍናል፤ ይሰውራል፤ በግድያ ያስወግድ ነበር። ዛሬም ድረስ በዚሁ ተፈጥሮው ገፍቶበታል።
ለአስርተ ዓመታት በሀገሪቱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ የነበረውን ሙሉ የበላይነት ማስጠበቅን እንደ ብቸኛ የህልውና መንገድ አድርጎ የወሰደው ሕወሓት፣ ክፍት እና ዲሞክራሲያዊ አሠራርን ከመቀበል ይልቅ የቆየውን ግትር አሠራር ይዞ የዘለቀው ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው። ከዚህ ልክፍቱ ሊወጣ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ገብቷቸው አዲስ መንገድ ለመጓዝ የሚሞክሩትን እየበላ ትግራይን፣ የትግራይ ሕዝብን እንዲሁም መላው ኢትዮጵያን መከራ ውስጥ እየከተተ ነው።
ይህ ገሃድ የታየና የራሱ ልጆች የመሰከሩት ሀቅ እንደ መንደርደሪያ ለማሳየት ተጠቀምኩበት እንጂ፣ ዋናው ትኩረቴ ይህ ትግራይ ላይ እንደ አልቅት ተጣብቆ መርዙን እያመረተ ለጦርነት በመንደርደር ላይ ያለ እልቂት አምራች ድርጅት ጉዳይ ላይ የትግራይ ኤሊት ምን ማድረግ አለበት? የትግራይ ወጣቶችስ ምን ሊያደርጉ ይገባል? የሚለውን ጉዳይ ለመጠቆም ነው።
“የዕልቂት አንቴና” የሚባሉት በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ሕወሓት “የጠላቴ ጠላት” በሚል ካግበሰበሳቸው ታጣቂዎች፣ ሄዶ እግሩ ሥር ከወደቀለት የኤርትራ አምባገነን ጋር አብሮ፣ ከሱዳን እና ከግብፅ “ሀገሬን እናንተን ወክዬ ላተራምስ” በሚል መሐላ በሰበሰበው መሣሪያ፣ የትግራይ ወጣቶችና ታዳጊዎችን በጉልበት እያፈሰ በጦርነት ሊማግድ ከወዲያ ወዲህ እየተክለፈለፈ ነው።
አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የትግራይ ምስኪኖችን ሕይወት የበላና አካላቸውን አጉድሎ የወደፊት ተስፋቸውን ያጨናገፈው ሕወሓት፣ ከዚህ የከፋ ጉዳት የሚያስከትል የጦርነት እሳት እንዲለኩስ በታዘዘው መሠረት እዚያም እዚህም እንደ አበደ ውሻ ሲሯሯጥ ዝም ብሎ ማየት ለነገ የይቅርታ ዕድል አይሰጥምና የትግራይ ኤሊቶች ባስቸኳይ “እምቢ” ሊሉ ይገባል። ይህን ደም መጣጭ ድርጅት መላ ሊሉት ግድ ይላል። ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቅረፍ የሚተጉ፣ ዓለም የደረሰችበት እውነታና የኃይል አሰላለፍ የገባቸው የትግራይ ተወላጆች እያሉ በሕወሓት የጦርነት አንቴና እልቂት እየተጎተተ የትግራይ ልጆች ሕይወት የሚያልፍበት፣ የትግራይ እናት ባዶዋን የምትቀርበት ዘመን ያብቃ ሊባል ይገባል። ወቅቱ የአስራ አንደኛው ሰዓት ጥሪ ነውና ለንስሐ እንኳን የማያመች ጉዳት ከመድረሱ በፊት መረባረብ ይበጃል። “…. ኋላ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” እንዳለችው አንጎራጓሪ።
ከፖለቲካዊ መገለል እስከ ጦርነት ዝግጅት
ሕወሓት የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የትግራይ ተወላጆችን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከፌደራል አስፈጻሚ ተቋማት አስገድዶ በማስወጣት መቀሌ እንዲመሸጉ በማድረግ የትግራይን ሀገራዊ ውክልናና ተሳትፎ ሆን ብሎ አቋረጠ። ከዚሁ ጎን ለጎን ራሱን ለጦርነት በማዘጋጀት፣ ኮማንዶዎችን በማሰልጠንና የክልሉን ኃይል ከፌደራል መንግሥት በላይ በማስታጠቅ ኢትዮጵያን ይመራ በነበረበት ወቅት በጽኑ ይኮንነው የነበረውን ጥፋት ከአራት ኪሎ ዘወር ባለ ማግስት ያለ ይሉኝታ ገፋበት።
ዙፋን ላይ በነበረበት ወቅት ይዞት የነበረውን የመከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደኅንነትና ኢኮኖሚ በመጠቀም ሲቆጣጠረው ከነበረው በተጨማሪ ሰፊ ኃይል ገንብቶ ራሱን ለጦርነት አዘጋጀ። ያከማቸውን ሀብትና የገነባውን ኃይል ተማምኖ ታበየ። “ጦርነት ሠሪ ነን” በሚለው ያረጀ ትምክህትና ትረካ ሰክሮ ተከተዮቹንም አሰከረ።
የፌደራል መንግሥት የሰሜን ዕዝን ወደ ሌላ ግንባር ለማዛወር ሲሞክር ሕወሓት ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጋር የነበረውን ትስስርና ፍቅር እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ በቀጣይ ሠራዊቱን ለማጥቃትና ለመዝረፍ የነበረውን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት ሲል ሕዝቡን መንገድ አዘግቶ በመማጸን ሰሜን ዕዝ ከትግራይ እንዳይነሳ አደረገ። ሀገራዊ እርቅና ሰላም ለማውረድ የመጡ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ምልጃና ልመና በንቀት አራክሶ በመመለስ የጦርነት ዝግጅቱን በማጠናከር የይዋጣልን አታሞ መታ።
የክህደት ጥቃትና የጦርነቱ ማቀጣጠል
ሕወሓት አመች ነው ብሎ ያሰበውን ቀን ጠብቆ፣ የሰሜን ዕዝ አባላትን ደግሶና ጋብዞ አዘናግቶና አስተኝቶ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የክህደት ጥቃት ፈጸመ። (ይህ በሕይወት ከተረፉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የትግራይ ሀቀኛ ምስክሮች እና ቤተሰቦቻቸው በአደባባይ ምስክርነት የተሰጠበት የሕወሓት የማይረሳ ነውር ነው)። ይህንን ጥፋቱን ለመሸፈን ሲል ሕዝቡን «ተወረሃል» ብሎ በማሳመንና ሀገራዊ ክህደቱን ወደ «መኸተ» ትረካ በመቀየር ወጣቱን በሰው ማዕበል ውጊያ ማገደ። የራሱን ሠራዊት በማረድ የፈጸመው ክህደት ሳያንሰው፣ አስመራ ላይ ሚሳይል በማስወንጨፍ ኤርትራን ወደ ግጭቱ ጋበዘ፤ በዚህም በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥርስ ነክሶ የነበረውን የኤርትራ ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያና ወደ ጦርነቱ ቀጠና ተንደርድሮ እንዲገባ ምክንያት ሆነ።
ራሱ በለኮሰው እሳትና በተከተለው የውጊያ ስልት የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት «ጄኖሳይድ ተፈጸመብኝ» በሚል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ለመሸፈን ቢሞክርም አላዳነውም። በፕሮፓጋንዳ ብዛት ለደረሰው እልቂት ከደሙ ንጹሕ እንደሆነ ሊሰብክ ቢሞክርም አልሆነለትም። በመጀመሪያው ዙር ጥቃት በሺዎች የሚቆጠረውን ወጣት አስፈጅቶና ከፍተኛ ውድመት አድርሶ በሦስት ሳምንታት ውስጥ መቀሌን ለቆ ወደ ተምቤን በረሃ አፈገፈገ።
የፌደራል መንግሥት የሰላም አማራጮች እና የሕወሓት ተደጋጋሚ አሻጥር
የፌደራል መንግሥት ሕዝቡን ለማረጋጋት፣ ጊዜያዊ አስተዳደር መስርቶ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በመደብ የመልሶ ግንባታ ጥረት ቢያደርግም፣ በወቅቱ ከሕዝቡ በቂ ድጋፍ ባለመገኘቱና ግጭቱ መልኩን በመቀየሩ ሕዝቡ ፋታ ወስዶ እንዲያስብበት ሲል ከመቀሌ ለቆ ወጣ። ነገር ግን ከመከራ ያልተማረው የሕወሓት የበላይ አመራር ለውይይት ዕድል ከመስጠት ይልቅ በተፈቀደው በጀትና በተመደበው ከፍተኛ የመልሶ ማቋቋሚያ ሀብት ዳግም ኃይል አደራጅቶ ሁለተኛ ዙር ጥቃት በመክፈት በተተወለት ቀጭን መንገድ እንደ እባብ እየተሳበ ደብረ ብርሃን ድረስ መጣ። ደብረ ብርሃን ጫፍ እስኪደርስ ባለፈበትና ባገደመበት ዘራፊ ቡድን አቋቁሞ ዘረፈ፤ ከፍተኛ ውድመት አደረሰ። “በሬ ሆይ ሳሩን አየሁ ብለህ …” እንደተባለው ከደብረ ብርሃን ጫፍ ሲመለስ ወደፊት ታሪክ የሚገልጸውን ተጨማሪ ወጣቶችን አስጨረሰ፤ በሰው ማዕበል ያፈሰሰውን ኃይል አስበላ።
የሕወሓት ኃይል በብርቱ ብትር ተመቶ፣ የሞተው ሞቶ፣ የቆሰለው ቆስሎ፣ የተረፈው አምልጦ ወደ ትግራይ ከተመለሰ በኋላ፣ መንግሥት በተደጋጋሚ የተከዳና ቁጣ ውስጥ ያለ ሠራዊት ወደ ትግራይ ዘልቆ ጉዳት እንዳያደርስ በሚል ልጓም አደረገ። በትግራይ ውስጥ ሕወሓትን በማሳደድ ሂደት ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በማሰብ ለሰላም ዕድል ሰጥቶ ግጭቱን አቆመ። ሕወሓት ግን ለሰላም ዕድል ከመስጠት ይልቅ ቁስለኛ ሳይገግም በአዲስ ወጣት መመልመልና ማስጨረሱን ተያያዘው። በመጨረሻም በሲሼልስና በጅቡቲ በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ለውይይት ቢቀመጥም፣ «አዲስ አበባ ካልገባሁ» በሚል ሰበብ ግጭቱን ቀጠለ።
የፕሪቶሪያው ስምምነት እና የመንግሥት በጎ ፈቃድ
መንግሥት ገና ሰሜን ዕዝ ከመጠቃቱ በፊት የነበረውን የሰላም አቋም በመጠበቅ መቀሌ ለመግባት ቀናት በቀሩት ሰዓት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም አደረገ። ስምምነቱን ተከትሎም ትግራይን ለመገንባት ሙሉ ኃይሉን በማንቀሳቀስ ከመንግሥት፣ ከክልሎች፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ልማት አጋሮች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ ክልሉ አፈሰሰ። አገልግሎቶች ወዲያው እንዲጀምሩና የወደሙ መሠረተ ልማቶች በፍጥነት እንዲጠገኑ ተደረገ።
መንግሥት የሰላም ሂደቱን ለማጠናከር ከወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች መካከል፦
1. በስምምነቱ መሠረት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዋና ዋና ቦታዎችን መቆጣጠርና መቀሌ መግባት የነበረበት ቢሆንም፣ የሕወሓት ተደራዳሪዎች «የሥነ ልቦና ጫና ያመጣል» ብለው በመለመናቸው ሠራዊቱን ከማስፈር ተቆጠበ።
2. በስምምነቱ መሠረት መሣሪያ ለመፍታት የፈረመው ሕወሓት ሰባራ መሣሪያዎችን ብቻ በማስረከብ የተሻለውን መሣሪያ የመቅበር ድራማ ሲሠራ፣ መንግሥት «የተቀበረው በኢትዮጵያ ምድር ነው»
3. በሚል በትዕግሥት አልፎታል፤ ከልክ ያለፈ ትዕግሥት አሳይቷል።
4. ክልሉን ራሱ ሕወሓት እንዲያስተዳድር ሙሉ ድጋፍ ሰጠ። በስምምነቱ መሠረት መንግሥት ትግራይን የማስተዳደር ኃላፊነት እና በውል የተቀመጠ ድርሻ ቢኖረውም ለሰላም ሲል ተወላቸው።
በፓርላማ የተጣለውን የሽብርተኝነት ፍረጃ አነሳ።
5. ለሰላም ሲባል በከፍተኛ ወንጀልና ክህደት ጭምር የተሳተፉትን ሳይቀር የታሰሩትን ፈታ፤ እንዲታከሙና ወደ ውጭ ሀገር እንዲወጡ አመቻቸ።
6. ሕግ በማሻሻል የሕወሓትን ሕጋዊ ሰውነት (ሰርተፊኬት) መለሰ፤ ሌላም ሌላም ….
የሕወሓት የውስጥ ውድቀት፣ ዘረፋ እና አዲሱ አደገኛ ሕብረት
እነዚህ ሁሉ በጎ እርምጃዎች ቢወሰዱም፣ አክራሪው የሕወሓት ኃይል የፕሪቶሪያውን ስምምነትና ለትግራይ ሕዝብ ሲባል የሚደረጉትን ድጋፎች ለጊዜ መግዣ ተጠቅሞ የሚከተሉትን ጥሰቶች በአደባባይ ፈጸመ፦
1ኛ፣ ለሕዝብ የሚላክ የእርዳታ እህል መሰወር፣ በሰው መነገድ እና ኬላ አቁሞ ጉቦ መቀበል።
2ኛ፣ የወርቅ ዘረፋን አስፋፋ፤ ተቧድኖ የወርቅ ማውጫ በማቋቋም ሀብት ማጋበስ ተያያዘው።
3ኛ፣ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ የተደረገውን ስምምነት ማደናቀፍና፣ እነሱን አግቶ የፖለቲካ ድራማው መጫወቻ አደረጋቸው። ተፈናቃዮች እንዲመለሱ የሚጠይቁትን “ባንዳና ከሐዲ” እያለ በመግለጫ ማሸማቀቅን ዋና ሥራው አደረገ።
4ኛ፣ ለተፈናቃዮች እንኳን ሊያዝን ከሚያገኟት ውስን እርዳታ ግብር ጥሎ መዋጮ ይሰበስብ ጀመር።
5ኛ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጥናት መሠረት 76% የዘረፋና አስነዋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳደረሰ ጠቅሶ ከከሰሰው ሻዕቢያ ጋር ተወዳጀ፤ ከዝርፊያው፣ ከጅምላ ግድያው በላይ በትግራይ እናቶችና ታዳጊዎች ማሕፀን “አጠፋችኋለሁ፣ መካን ትሆናላችሁ” እያለ ደብዳቤ ከላከ፣ ባዕድ ነገሮችን በመጨመር ካሰቃያቸው ሻዕቢያ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ተመሳሳይ ወንጀሎችን በ18% ፈጽሟል በሚል ከሚከሰሰው የፋኖ ኃይል ጋር ተወዳጀ።
6ኛ፣ ትግራይን በጊዜያዊነት እንዲያስተዳድር የተሰየመውን አስተዳደር እግር ቆረጠ። አቶ ጌታቸውን ማባረር፣ በራሱ ውትወታ የተተኩትን ጄኔራል ታደሰንም ወዲያውኑ አባረረ።
7ኛ፣ የስልጣን ጥሙን ለመወጣትና የዘረፈውን ሀብት ለማስጠበቅ ሲል ስልጣኑን በግድ መቆጣጠር ስላለበት፣ በጉልበት ስልጣን ይዞ ትግራይን ዳግም የደም መሬት ለማድረግ ጦርነት እየደገሰና እየሞከረ ይገኛል።
8ኛ፣ የትግራይን ወጣት ለሱዳን መሸጥ፣ የግብፅ፣ የሻዕቢያ እና የአልቡርሃን ተላላኪ በመሆን ሀገር የማፍረስ ክህደቱን በማሳለጥ ኢትዮጵያን ሦስት ቦታ ለመክፈል ማቀዱን በአባላቱ አማካይነት መናገር ጀምሯል። ይህ ነውርና ክህደት ጌጡ የሆነ ድርጅት በአደባባይ ለኢትዮጵያውያን “ኢትዮጵያን የሚያፈራርስ ማኅበር ተመስርቷል” እያለ ነው።
የትግራይ ወጣትና ኤሊት ኃላፊነት
ከላይ በጨረፍታ የቀረቡት ማሳያዎች ሕወሓት ያለበትንና ያለፈበትን መንገድ ለማመላከት ያህል ጥቆማ የሚሰጡ ናቸው። ሕወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ራሱን ከላይ በተጠቀሰው አግባብ እያደራጀና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች አጀንዳ በማዘል የመጨረሻውን የጥፋት ደወል ለመደወል ከጫፍ ደርሷል። ለአራተኛ ዙር እልቂት ሕፃናትን ከእናት እቅፍ እየነጠቀ፣ የተሰናበቱትን እየመለሰና ከሻዕቢያ ጋር በመዶለት ለሌላ ጦርነት ድግሱን እያጧጧፈ ወደ ማገባደዱ ተቃርቧል። ይህ አስከፊ የዕልቂት ድግስ ለትግራይ ኤሊት የተሰወረ አይደለም። ይህን እልቂት ለማስቀረት ምን መደረግ እንዳለበት ከትግራይ ኤሊት የተሰወረም አይደለም። እናም ሳይመሽ የአስራ አንደኛው ሰዓት ጥሪ ይድረሳችሁ።
ለተበደለው የትግራይ ወጣትና ወላጅ የቀረበ የማስጠንቀቂያ ጥሪ፦
ይህ የሕወሓት የመጨረሻው የጥፋት ምዕራፍ ነው። ዓላማ የሌለው፣ ዕድሜውን የጨረሰ፣ እና የራሱን ልጆች በአውሮፓና በአሜሪካ ቪላ ገዝቶ የሚያኖር፣ በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምር ይህ ማሰብ የተሳነው ኃይል፣ የምስኪን የትግራይ ተወላጆችን ዕድሜና ጾታ ሳይለይ ለአራተኛ ዙር እልቂት ሊማግዳቸው ዝግጅቱን ጨርሷል።
የትግራይ ወጣት ሆይ! በቻልከው መንገድ ሁሉ ራስህን ለማዳን ፍጠን፤ ለነገ የተሻለ ሕይወትህ ስትል ዛሬን ከዚህ ጥፋት ራስህን አሽሽ። ባለፉት ጦርነቶች ይህ ክፉና አስተሳሰቡ ያረጀ ድርጅት ያደረሰውን ቁስል ወደ ጓደኞችህ ዘወር ብለህ ተመልከት። የሞቱትን፣ የቆሰሉትን እና አካለ ጎዶሎ የሆኑትን ቤተሰቦችህን ተመለከት። የወላድ መካን የሆኑትን እናቶች አስብ፤ ቤታቸው ጭር ያለባቸውን ቤተሰቦች ብዙም ሳትርቅ ከጎረቤቶችህ እይ። እናም እግርህ ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ወይም ወደ ማንኛውም ወገንህ በመሸሽ ሕይወትህን ታደግ!
- የዝግጅት ክፍሉ ማስታወሻ፦ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ናቸው። ጽሑፉ የእሳቸው አስተያየት እንጂ የዝግጅት ክፍሉን የሚወክል አይደለም። ተቃራኒ ወይም ደጋፊ ጽሑፍ ለመጻፍ ለሚፈልጉ ዝግጅት ክፍላችን ክፍት ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






