አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ጃል መሮ ሰሞኑን አንድ ሰዓት ከአስራ ሰባት ደቂቃ በፈጀው ቃለ ምልልሱ “ነጻ፣ ሉዓላዊ ድንበር ያላት፣ የኦሮሚያ ሪፖብሊክ ለመመስረት አብረውን ከሚሰሩት ጋር ተስማምተናል” ባሉ ማግስት ቀደም ሲል “ጽምዶ” በሚል መጠሪያ ተቋቁሙ ተቃውሞ የበዛበት ጥምረት ስሙን ቀይሮ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና” በሚል መተካቱ ይፋ ሆነ። “ለህልውና የሚለው ቅጥያ የገበያው የዳቦ ስም ነው፤ ለውጥ የለውም” የሚል አስተያየት ተሰጥቷል።
“የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና” የሚለው ትብብር ይፋ የተደረገው ትግራይ ውስጥ ሲሆን፣ ይፋ ያደረገው በአቋም የተከፋፈለው የአፋብን ሊቀመንበር ዘመነ ካሴ አማካይነት ነው። ዘመነ ካሴ መቀለ ሆኖ በትግራይ የተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ ያድርገው የስም ለውጥ “እናቸንፋለንና እናሸንፋለን” በሚል የዘዬ ልዩነትን ርዕዮተ ዓለም አድርገው የተጋደሉትን እንዳስታወሳቸው ለአዲስ ሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የኦሮሞ አንጋፋ ፖለቲከኛ አመልክተዋል።
የአብን ስራ አስፈጻሚ “አማራን በማይረሳ ደረጃ የችግር አረንቋ ውስጥ በከተተ፣ ባጠፋ፣ በገደለ፣ ኢትዮጵያን ሆን ብሎ እንድትበተን ህገመንግስት አርቅቆና ለዚሁ ዓላማው ነዳጅ እንዲሆነው ልዩነትን ሲሰብክና ህዝብን ሲያባላ በነበረ ድርጅት ሚዲያና ቢሮ ውስጥ በመቀመጥ ‘ህወሃት ስለ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ጨነቀው’ የሚል መግለጫ በአንድ አማራ ነኝ ባይ አንደበት መስማት ያማል” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
ሰባት ራሳቸውን ነጻ አውጪ፣ ግንባር እና ንቅናቄ በማለት በመቀለ ስምምነት ፈጥረው “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና” በሚል መጠሪያ ለመጠራት ተስማምተዋል የተባሉት፣ አፋብን፣ ትህነግ ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ፣ የጉሙዝ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የኦጋዴን ህዝብ ነፃነት ግንባርና የአፋር ብሄራዊ አንድነት ግንባር እንደሆኑ የትብብሩ ሰብሳቢ እንደሆኑ የተነገረለት ዘመነ ካሴ ነው። ዘመነ በአፋብን ስም ይህን ጥምረት መሪ ሆኖ ከመቀለ በህወሃት ሚዲያዎች ይፋ መናገሩን ተከትሎ ሌሎች የአፋብን አደረጃጀቶች የተቃውሞ መግለጫ እንደሚያወጡ እየተሰማ ነው። የዘመነ የትብብሩ መሪነት ቀደም ሲል በታወቅ ማግስት እስክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ የፋኖ አመራሮችና አባላት ተቃውሞ ማሰማታቸው አይዘነጋም።
በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት አስወግደው የሽግግር መንግስት ለመመስረት ያስችለናል ያለው ይህ አዲሱ “ጽምዶ” በይፋ ስሙን እንደሚቀይር የጋራ መደረኩ አባላትን ጠቀሰን መዘገባችን አይዘነጋም። ዘመን ካሴ በይፋ ያልዘረዘራቸውና በደፈናው ሌሎች ከተባሉት መካከል ሱዳን፣ ኤርትራ በስም ተጠቅሰው የተካተቱ ሲሆን ሌሎች አገራት እንዳሉበት ለዚህ ስራ የተከፈተው ድረ ገጽ በይፋ በፊት ለፊት ገጹ አስፍሯል። ድረ ገጹን እንዲያስተዳድሩና በዚሁ ጥምረት ዙሪያ የሚሰራጨውን ፕሮፓጋንዳ እንዲመሩ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኩል የተሾሙትን ኃላፊ “ኢሳያስ የሃያ ሁለት ዓመታት ተቃዋሚያቸውን “እየፈረሰ ነው” ለተባለው “ጽምዶ” የቅስቀሳ አስተባባሪ አድርገው ሾሙ” በሚል ርዕስ ይፋ ማድረጋችን ይታወሳል።

በሚታወቁ የመንግስት ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመውና ዋና የ”ጽምዶ” ተዋንያኖች “የመጣመድ ባህሪ የላቸውም። አዲስ አበባ ሲደርሱ ኢትዮጵያን ያፈርሷታል” በሚል በህዝብ ዘንድ አመኔታ የተነፈገው ይህ ህብረት፣ ስሙን ቀይሮ መምጣቱ የዚሁ የተቃውሞው ውጤት እንደሆነ ተመልክቷል። “ህልውና” የሚል ሃረግ የተጨመረው “ለምን ከጣላቶቻቹህ ጋር ተስማማቹኽ” የሚለውን ክስና ውግዘት ለመቋቋም እና “መንግስት ያሳደረብንን የህልውና ስጋት ለመቋቋም ተጣመርን” የሚል መልስ ለመስጠት እንደሆነ ከላይ ህየጠቀስናቸው አንጋፋ የኦሮሞ ፖለቲከኛ ተናግረዋል።
“ስያሜው ለገበያ ነው” ያሉት እኚሁ ፖለቲከኛ፣ ሻዕቢያና ወያኔ አዲስ አበባንና አስመራን ለመካፈል የጋራ ጥቅም እንዳስማማቸው አስታውሰዋል። ጥቅማቸውን ካገኙ በኋላ ግን መሰረታዊ ፋላጎታቸው ለተደጋጋሚ ጦርነት እንደዳረጋቸው አመልክተዋል።
የሱዳንን መንግስት ተባብረው የጣሉ፣ የሶማሊያውን ዜያድባሬ ህብረት ፈጥረው የአስወገዱ፣ ደቡብ ሱዳን አብረው ነጻ ያወጡ ሁሉም ከድል በኋላ አገራቸውን እንዳፈራረሱ ያመለከቱት የሶማሌ ክልል ፖለቲከኛ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ተሰባስበናል የሚሉትም ከዚህ የተለየ እድል እንደሌላቸው አመልክተዋል። የተለያዩ እጆችም ስላሉበት ጉዳዩን መንግስት ክፍትፍት አድርጎ ለህዝብ ቢያሳውቅ ጥሩ እንደሆነ መክረዋል። የሰላማዊ ውይይት ጉዳይ ትኩረት እንደሚሻውም አሳስበዋል።

“እናቸንፋለን የጎንደር ዘዬ ነው። እናሸንፋለን የሸዋ ዘዬ ነው። ሁለቱም ትርጉማቸው አንድ ሆኖ ሳለ በ’ቸ’ እና ‘ሸ’ ልዩነት ሳቢያ ደም መፋሰሱን ያስታወሱት አንጋፋው ፖለቲከኛ፣ “ጽምዶና አሁን ተፈጠረው የተባለው ህብረት እንደ እናቸንፋለንና እናሸንፋለን የዘዬ ልዩነት ካልሆነ በቀር ያው በዓላማ፣ በርዕዮተ ዓለም፣በመርህና በተፈጥሯቸው የማይመሳሰሉ በመሆናቸው ስም ቢቀያይሩ ለውጥ የለውም” ብለዋል። የ“ሸ” እና የ“ቸ” ልዩነት ከተጫረሱ በኋላ እንደገባቸው የቀድሞ “ታጋዮች” ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ዜጋ አለ ብለው እንደማያስቡ አመልክተዋል። አክለውም “ምነው የሶማሌና የደቡብ ክልል ግንባርና ንቅናቄ አላከተቱም” በማለት የምጸት ጥያቄ አንስተዋል።
“ትብብሩ” በስልጣን ላይ ያለውን የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት በመጣል “ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት” ለማቋቋም ትልም እንዳለውም ዘመነ ካሴ በመግለጫው ይፋ አድርጓል። ዘመነም ሆነ መግለጫ ተብሎ በሃወሃት ሚዲያዎች የተሰራጨው ጽሁፍ መንግስትን ክፉኛ ከመተቸታቸው በዘለለ፣ ስለ መሰረታዊ ልዩነታቸው ያነሱት ነገር የለም።
“መንግስት እንጥላለን” በማለት በአማራ ክልል በኩል ፋኖን አደራጅተው ያሰማሩት ኃይሎች ገና ከጅምሩ “የጋላን መንግስት እናስወግድ” የሚል መፈክር በአደባባይ ለጥፈው እርዳታ ሲያሰባስቡ እንደነበር የሚጠቅሱ፣ አሁን ይህን ህዝብ የህልውና አደጋ እንደሆነ አድርገው ለህብረታቸው መጠሪያ ማድረጋቸው አያስገርማቸውም። እንዲያውም የኦሮሞን ህዝቡና ተቃዋሚ ድርጅቶችን አንድ ያደርጓቸዋል ባይ ናቸው።
በአሜሪካ አቶ ነዓምንና አቶ ልደቱ አጣምረው በመሰረቱት ትርምስ አመቻች ግብረኃይል ውስጥ ህወሃትን ከሚወክሉት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አባይ ግደይ፣ “… ኢትዮጵያ ሶስት አገር ትሆናልች” በማለት ከድል በኋላ የተያዘውን አማራጭ ይፋ ማድረጋቸውን በማንሳት ህበረቱ “ኮስሞቲክ እየተቀባባ ኢትዮጵያን ለማዳን ቢናገረም እውነቱ ጃል መሮና አቶ አባይ፣ እንዲሁም በህይወት እያለን ኢትዮጵያ ስትፈራርስ ማየት ነው ምኞታችን የሚሉት የህወሃት ግብ ተሸካሚዎች ምስክርነት ነው” በማለት ህዝብ በግልጽ ይህን አውቆ ምርጫውን እንዲያስተካክል መንግስት ያለ አንዳች መሸፋፈን የአካሄዱን አደገኛነት ማስታወቅ እንዳለበት አመልክተዋል።

የኦጋዴን ነጻ አውጪ ቡድን በገሃድና ማንም ሊክደው በማይችለው መልኩ ኦጋዴንን እንደሚገነጥል የድሮው ቢቀር በቅርቡ ሎንደን ላይ እነ አቶ አንዳርጋቸው፣ ፕሮፌሰር መሃመድ፣ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ባዘጋጁት የጽምዶ ስብሰባ ላይ “ከታላቋ ሶማሊያ” አቀንቃኞች ጋር አንድ ላይ ሆነው ኦጋዴንን እንደሚያስገነጥሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ራሱን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በማለት የሚጠራው ቡድን 27 ዓመታት አገር እየመራ በተገንጣይ ስም የቆየው አመቻችቶ ለመገንጠል እንደሆነ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ኃላፊዎቹ መስክረዋል። ለውጡን ተከትሎ ወደ መቀለ በመሸሽ “የፌደራል ኃይሎች” ብሎ ሌላ መንግስት ለማቋቋም እና የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሰነድ አዘጋጅቶ የነበረው ህወሃት ዛሬም ድረስ አጀንዳው መገንጠል ነው። አሰብን የሰጠውም “ስንፈልግ ከኢትዮጵያ ከመውሰድ ይልቅ ከኤርትራ መውሰድ ይቀላል” በማለት በመሪው አማካይነት ለአባላቱ በድፍረት የተናገረ ድርጅት ነው።
ለዚህ ውሳኔውና ዓላማው ስኬት እንቅፋት እንዳይሆንበት አማራውን በማኒፌስቶ ሳይቀር ጠላት አድርጎ በመፈረጅ፣ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለሰላሳ ዓመታት ከልማትና ዕድገት ለይቶ፣ ሴቶችን አምክኖ ሲመራ፣ በቅርቡ ጦርነት ክልሉን በማውደም፣ በመዝረፍ፣ በጅምላ በመግደል፣ በአስማራ ህዝብ ላይ የማይረሳ ግፍ በፈጸመው የህወሃት ሚዲያ “ስለ አማራ ህልውና አደጋ ማውራት የኦሮሞ ህዝብን የህልውና አደጋ አድርጎ መውሰድ ነው” በማለት በይፋ ቅሬታ የተሰማቸው ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።
ጃዋር መሐመድ “ራሳችሁን ግልጽ አድርጉ” በማለት ያቀረበው ጥያቄ የመላው ኦሮሞ ጥያቄ መሆኑን የጠቆሙ፣ አማራ ክልልም ህወሃት የፈጸመባቸውን በማይረሱ “ፍም እጅ ያላቸው” ይህንን ትብብር ሊቀበሉ እንደማይችሉ ከወዲሁ ያስታወቁ አሉ። እነዚህ ወገኖች ውሎ አድሮ መግለጫ እንደሚያወጡና አቋማቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ለትብብሩ ቅርብ የሆኑ ዘመነ ካሴና ሌሎች በተለያዩ የአማራ ተቆርቋሪ እንደሆኑ በሚነገርላቸው የድረገጽ ሚዲያዎች በመቅርብ ማብራሪያ እንዲሰጡ እቅድ መያዙም ታውቋል።
“ኦሮማይ መጽሃፍ በድጋሚ ለዚህ ትውልድ ሌተርክለት ይገባል” የሚሉ “የአንድ ሰው የግል ንብረት ከሆነችው ኤርትራ የሚጠነሰስ ኢትዮጵያን የመበጣጠስ አጀንዳ በኢትዮጵያዊያን ህብረት እንዲመከት መንግስት ከሚታየው በላይ ግልጽ እንዲሆን ማሳሰቢያ ቀርቧል።
የተፈጠረበትን ስራውን የማይሰራው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትም ሪባን መቁረጥና በዓላት እየጠበቀ መግለጫ ከማውጣት ይልቅ ህዝብ እውነቱን እንዲያውቅ የዕለት ተዕለት ስራውን እንዲሰራ፣ መንግስትም ከአዲስ መንግስት ምስረታው ጎነ ለጎን ተቋሙን እንዲያየው አሳስበዋል።
“ዘመነ ካሴ የሚመራው ይህ ስብስብ ህወሃትን አሁን ካለው መንግስት በላይ ኢትዮጵያን የሚወድ፣ ለኢትዮጵያ ችግር የሚጨንቀው፣ ለኢትዮጵያ ችግር እንቅልፍ ያጣ አድርጎ ያስቀምጣል። አሰብን የሸጠውን ህወሃት ኢትዮጵያን ይርወደብ ባለቤት ለማድረግ በይፋ እየጠየቀ ያለውን፣ ከታላላቅ የዓለም አገሮች ጋር ስምምነት አድሮ ይህን ህልሙን ለማሳካትና የኢትዮጵያዊያንን ቁጭት ለማደስ የሚሰራ መንግስት ይከሳል” ያሉ፣ ለመሆኑ እነ ዘመን በቀይ ባህር ላይ ያላቸው ግልጽ አቋም ምንድን ነው? በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ።
“የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ዓይነትም አሁን የናያቸው ዓይነቶችም በአማራ ስም ተፈጥረዋል” ያሉ ይህን ጉዳ ሳያዩ ያለፉ እድለኞች መሆናቸውን በስፋት ማነጻጸሪያ በማቅርብ አስረድተዋል። “አይረሴው አስራት አፈር ይቅለልዎ” በማለት ሃዘናቸውን በቁጭት ገልጸዋል። መተባበርን እንደማያወግዙ አመልክተው፣ አገር ከሸጠና ካሻሻጠ ጋር የሚደረግ ስምምነትን ነገ የሚፈርስ ቢሆንም፣ በህዝብ ስም መነገዱ አሳዛኝ እንደሆነ አመልክተዋል።
አዲስ ሪፖርተር ያነጋገረቻቸውን የተለያዩ አካላትና ድርጅቶች ሙሉ ሪፖርት በነገው ዕለት ታትማለች። በዚህ ዜና ውስጥ የተካተተው ከዚሁ ጥቅል ሪፖርት ላይ የተቀነጫጨቡና ከዚህ ቀደም ከተዘገቡት ዘገባዎች የተወሰዱ ናቸው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






