አዲስ ሪፖርተር ዜና — የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሰከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ የሾማቸው ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የቀድሞው ስራ አስፈጻሚ ዶ.ር ረሻድ ከማል ይፋ አድርገውት የተጀመረውን የ”ዜሮ ፋይናን” ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተለያዩ አሰራሮች ላይ የዕግድ ደብዳቤ አወጡ። እግድ ቢታዘዝም የመርካቶ የዜሮ ፕሮጀክት ግንባታዎች እንደቀጠሉ ናቸው።
ፕሮጀክቶችን እየተዘዋወሩ በመጎብኘት ላይ የሚገኙት አዲሷ ተሿሚ እግዱን ያሳለፉት ከፕሮጀክቱ ጀርባ በከፍተኛ ደረጃ መመርመር ያለባቸው ጥቆማዎች በመቅረባቸው መሆኑን አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች። በተለይም ዜሮ ፕሮጀክት ላይ የህግ፣ የአሰራር፣ የውል አፈጻጸም እና የፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ ቀደም ሲል በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳይ መረጃ ለአዲስ ሪፖርተር ደርሶ ነበር። በመካከሉ ኃላፊዎች መቀያየራቸውን ተከትሎ ሪፖርቱን ከማተም የዘገየን ቢሆንም አዲሷ ኃላፊ እግዱን ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ዝርዝር ሪፖርቶች የምናዘጋጅ መሆኑን ከወዲሁ እናስታውቃለን።
ስራ አስፈጻሚዋ የዜሮ ፋይናንስ ፕሮጀክቶች፣ የቤት ኪራይ ውል፣ የመሬት ጥያቂዎች፣ ማንኛውም የንብረት ግዢና ክፍያዎች፣ እና ተመሳሳይ ጉዳዮች እንዲታገዱ ያዘዙት በትናንትናው እለት ማለትም ሹመቱን በተቀበሉ በሁለተኛው ቀን ነው።
ለዓመታት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወይዘሮ ጫልቱ በትናንትናው እለት ይፋ ባደረጉት ደብዳቤ እግዱን ማስተላለፋቸውን ተከትሎ የአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢዎች መርካቶ ተዘዋውረው እንዳዩት ከሆነ እንዲታገዱ የተባሉት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደቀጠለ ነው።
ተቋሙን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለስምንት ዓመታት ሲመሩ የቆዩትን ዶክተር ረሻድ ከማል በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ ወደ ኦሮሚያ ዞን መዛወራቸውን ተከትሎ ሚዲያዎች በስፋት ሲዘገቡት የነበረው የዜሮ ፋይናንስ ፕሮጀክት መታገዱ መነጋገሪያ ሆኗል።
የተቋሙን የህዝብ ግንኙነት በማነጋገር አስተያየታቸውን ለማከል በተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም ሊሳካ አልተሳካም። ሲገኙ አሳባቸውን እናካትታለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






