አዲስ ሪፖርተር – የደህንነት ሚኒስትሩ ተስፋዬ የዶርዜ ተወላጅ ሲሆን የመጀመሪያ ስሙ ጩባ ጦሌ እንደነበርና አዲስ አባባ መጥቶ ክርስትና ከተነሳ በኋላ የአሁኑ ስም እንደተሰጠው አገር ቤት የቤተሰቦቹ ጎረቤት የነበረ እስረኛ አጫውቶኛል። ተስፋዬ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት በተስፈኝነት እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ በሕዳር 1949 ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የዕጩ መኮንኖች ኮርስ ተሳታፊ ሆኖ በዚያው ዓመት በሰኔ ወር ከአስር ወራት በኋላ በምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ ተመረቀ።
በመጀመሪያ ጎንደር ጎርጎራ ቀጥሎም ኤርትራ አገልግሏል። በእሥራኤሎች ይሰጥ የነበረውን የአራት ወራት የውጊያ መረጃ ኮርስ በሀገር ውስጥ ቀጥሎም ተመሳሳይ ትምህርት ለአራት ወራት በአሜሪካን ሀገር ወስዷል።ከዚያም በኋላ ሆለታ በነበረው የአዛዥነትና መምሪያ መኮንንነት ኮርስ የውጊያ መረጃ አስተማሪ ሆኖ አገልግሏል።
በሰኔ 1966 ደርግ እንደተቋቋመ በኮሎኔል መንግሥቱና በጄነራል ተስፋዬ ጠቋሚነት በእነኮሎኔል ተካ ቱሉ ይመራ በነበረው የደርግ የደህንነት ኮሚቴ ተጠሪ በመሆን በአገር አስተዳደር ስር የመረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ ኃላፊ ሆኖ ሐምሌ 19፣ 1966 ተመደበ። ኮሚቴው በስሩ የፀጥታ፣ የልዩ ካቢኔን፣ የልዩ ፖሊስ ምርመራን፣ ኢሚግሬሽንን የያዘ አካል ነበር።

በ1971 መዋቅሩ በምሥራቅ ጀርመን ባለሙያዎች የአገርና የሕዝብ ደህንነት ሚኒስቴር ተብሎ እንዲጠራና በስሩም የውጭ አገሮች ጥናትና ምርምር፣ የአገር ውስጥ ደህንነት፣ የይለፍና ቪዛ፣ የማዕከላዊ ምርመራ፣ የኢኮኖሚ መምሪያ፣ የባለሥልጣኖች ጥበቃ መምሪያን ያቀፈ እንዲሆን ጥናቱ ለመንግሥት ቀርቦ ተቀባይነት አገኘ። መዋቅሩ ከጸደቀ በኋላ በደርግ ረዳት ፀሐፊነቴና በአስተዳደርና ሕግ ኮሚቴ ኃላፊነቴ በሚኒስትርነት የሚመደበውን ግለሰብ ማቅረብ የኔ የሥራ ድርሻ ነበር።ለዚህ ቦታ ተወዳዳሪ የነበሩት የደህንነት ኮሚቴ ኃላፊዎች ኮሎኔል ተካ ቱሉና ኮሎኔል ካሣሁን ታፈሰ ነበሩ። በኔ በኩል ግን ከ1966 እስከ 1971 ድረስ ባከናወነው ሥራ ከሁለቱ የደርግ አባላት ሚዛን ደፍቶ ያገኘሁት ተስፋዬ ወልደሥላሴ ስለነበር ሁለቱ የደርግ አባላት አባል በሆኑበት ለደርግ ቋሚ ኮሚቴ በዕጩነት አቀረብኩት። ሁለቱም የደርግ አባላት እራሳቸውን ለቦታው አጭተው ስለነበር ከፊት ለፊቴ ተቀምጠው ፊታቸው ሲለዋወጥ አየሁ። ስለዕጩነቱ ሊቀመንበሩ አስተያየት ሲጠይቁ ግን አንድም ተቃዋሚ
አልነበረም። ዕጩነቱ ጸድቆ በማግስቱ ሊቀመንበሩ ዘንድ ቀርቦ “ነብስ ኢትአምር ቀታሊሃ”(ነብስ ገዳይዋን አታውቅም) እንደሚባለው በሚኒስትርነት እንዲሾም አደረግኩ።
ከጊዜ በኋላ እንደተረዳሁት ግን ተስፋዬ እንደሚነገርለት የጠለቀ የኢንተሊጀንስ ባለሙያ፣ ተመራማሪና ፖሊሲ ቀያሽ ሳይሆን ጥሩ የመረጃ ወኪልና ወሬ አቀባይ ነው።ሊቀመንበር መንግሥቱን ሲፈራ የጉድ ነው። ሊቀመንበሩ ትዕዛዝ ሳይሰጡ የፊታቸውን መለዋወጥ እያየ ወይም ከባድ ትችት በሰው ላይ ሲሰነዝሩ ከሰማ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ በርካታ ስህተቶችን ፈጽሟል። ወዳጅና ዘመድ የሚባል ነገር አያውቅም። ማታ የሚገድለውን ሰው ስቆና አጫውቶ ይሸኛል። መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ በጀት የተመደበለት ከመከላከያ ቀጥሎ ወሳኝ የመንግሥት መዋቅር ነበር።
ተስፋዬ እንደተሾመ ግን ከጥቂቶቹ በስተቀር በሙያው ከፍተኛ ችሎታና ልምድ የነበራቸውን አንድም በጡረታ አሊያም በሹመት አራቁቶ ሥልጣኑን ሊቀናቀኑት በማይችሉ፣ ሙያና ስነ ምግባር በጎደላቸው አድር ባዮች ሞላው።መረጃ መለዋወጥ በሚል ሰበብ በንጉሡ ጊዜ ጀምሮት የነበረውን የሞሳድና የሲ.አይ.ኤ የወኪልነት ሥራውንም ቀጠለበት። በዓለም አቀፍ ወዛደራዊነት መሠረት በሱማሌ ጦርነት ወቅት ከጎናችን ተሰልፈው ውድ ሕይወታቸውን የሰዉ የኩባ ወታደሮች አስከሬን ወደ ሀገራቸው ለመውሰድ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በደህንነቱ ክፍል ሳጥኖቹ በመፈተሻቸው በሁለቱ አገራት መካከል ከፍተኛ መቃቃርን ፈጠረ። የኢሕአዴግ መንግሥት ኩባዊያን በሶማሊያ ጦርነት ጊዜ ለከፈሉት መስዋዕትነት ትግላችን አጠገብ ያሰራላቸውን የመታሰቢያ ሃውልት ምረቃ ላይ ተገኝተው የነበሩ የኩባው ምክትል ፕሬዝዳንት “እኛ የመጣነው መስዋዕት ለመክፈል እንጅ ወርቅ ለመውሰድ አልነበረም” ሲሉ ያን ጊዜ ቅሬታቸውን በምሬት ገልጸዋል።
በዚያ ክስተትም በወቅቱ የተደሰቱት ምዕራባዊያን ሀገራት መሆናቸው ግልጽ ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ በአንድ የምዕራብ
ጀርመን ቄስ አስተባባሪነት ይሰበሰቡ የነበሩ የኦነግ አባላትን ለመግደል የደህንነት ሚኒስትሩ ሁለት የፈንጂ ባለሞያዎችን ወደ ምዕራብ በርሊን ልኮ ነበር። ፈንጂው ሲጠመድ በድንገት ፈንድቶ አንድ እጅና እግሩ ተቆርጦ በጀርመን ፖሊሶች ተያዘ።ሆስፒታል ከገባ በኋላ ሁለት ዓይኑን አጥፍተው በራሳቸው አውሮፕላን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አምጥተው ጣሉት። በመጀመሪያ ደረጃ ግዳጁ ቢሳካም ኖሮ የደርግን መንግሥት በአሸባሪነት ከማስፈረጅ በዘለለ የኦነግን ዓላማ የሚያሰናክል አልነበረም። በዋናነት ግን የምዕራብ ጀርመን መንግሥት በደርግ ላይ ከፍተኛ ቂምና ጥላቻ እንዲቋጥር ያደረገ
ድርጊት ነበር። ኢትዮጵያውያን ወደ ምዕራብ ጀርመን ያለ ቪዛ የመግባት የነበራቸዉ ዕድልም ተዘጋ።
ተስፋዬ ወልደሥላሴ እስከ 1976 ድረስ እጅግ ታማኝ የነበረ ሲሆን ከዚህ በኋላ በሥራው ሲደላደል ልቡ እየሸፈተ ወደ ክህደት እያመራ መጣ። በእንደነዚህ ዓይነት አሰራር ከወዳጆቻችን ጋር ሲያቃቅረን፣ በሌላ በኩል የሐሰት መረጃ በማቅረብ መንግሥትን ሲያሳስት፣ ግለሰቦችን እንደፈለገ በማሰር ዘግናኝና ጨካኝ ምርመራ እንዲካሄድባቸው በማድረግ ሕዝብና መንግሥትን ሲያራርቅ ቆይቷል። በንጉሡ ጊዜ ሴራና አድማ እየጠነሰሱ ነው ተብለው ክትትል ተደርጎባቸው መረጃው ከተጠናቀረ በኋላ ሴራቸው እንደተደረሰበትና የጀመሩትን አድማ እንዲያቋርጡ መክረውና ዘክረው ከችግር የሚያድኑ እንደ ኮሎኔል ወርቅነህ አይነት የፀጥታ ሹም የነበራት ሀገር ጨካኝ ገራፊዎችንና እበላ ባይ የሕግ ምሁራን ተብየዎችን አሰባስቦ የሐሰት ወንጀል በመፍጠር ሰውን ለማጥፋት በሚጥር የደህንነት ሹም መተካቱ የሚያሳዝን ነው።
የእኔና የተስፋዬ መቃቃር የጀመረው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ፓርቲው የመከላከያና አስተዳደር መምሪያ (ደህንነትንም ያጠቃልላል) ከተዛወርኩ በኋላ ነበር። ከደህንነት መሥሪያ ቤቱ በየሳምንቱ ለፕሬዝዳንቱ የሚቀርበው መረጃ በቢቢሲና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተዘገቡ ዜናዎችን፣ ከግልጽ ምንጭ የተላለፉ ወሬዎችን፣ ወቅት ያለፈባቸውን አንዳንዴም ከእውነት የራቁና ግምታዊ አስተያየቶችን የያዙ ነበሩ። እነዚህን የመረጃ አቀራረቦች በመተቸት ለፕሬዝዳንቱ አንድ የጥናት ጽሑፍ አቀረብኩላቸው።እሳቸውም ጽሑፉን ተመልክተው ለተስፋዬ ከሰጡት በኋላ ነበር የሁለታችን ቅራኔ የተጀመረው።
በትግራይ ተወላጆች ላይ ሲያካሂድ የነበረው ዘመቻ ግን ጠለቅ ያለ ግብና ዓላማ ቢኖረውም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በዚህ አጋጣሚ እኔንም ለማስመታት አጋጣሚ ሆነለት። ቁጭ ብየ የሰቀልኩትን ቁሜ ማውረድ አቃተኝ።
አብዮቱናትዝታዬ፤ ፍስኃደስታ፤418-21
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






