በዓለማችን የሙስና መመዘኛ መሠረት በጣም ዝቅተኛ ሙስና ይካሄድባቸዋል ተብለው የሚጠቀሱት አገራት በየዓመቱ የሚታወቁ ናቸው። ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ስዊትዘርላንድ፣ ኒው ዚላንድ፣ ስዊድን፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ኖርዌይ፣ ወዘተ በተደጋጋሚ እስከ 10 ባለው ቁጥር ውስጥ የሚገቡ አገራት ናቸው።
“ድመቷ ጥቁር ትሁን ወይም ነጭ ጉዳያችን ሊሆን አይገባም፤ አይጥ መያዝ እስከቻለች ድረስ ጥሩ ድመት ነች… አንድ አገር ለተጋፈጠችው ችግር መፍትሔ እስካመጣ ድረስ የምዕራብ ይሁን የምስራቅ፤ የካፒታሊት ይሁን የሶሻሊስት፤ የወግ አጥባቂ ይሁን የለዘብተኛ፤ ርዕዮተ ዓለሙ ሊያሳስበን አይገባም”
እነዚህ ሀገራት ሙስናን መቆጣጠር የቻሉት የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማቋቋም አይደለም (ሙስናን የሚዋጋ ተቋም የላቸውም ማለት አይደለም)። ለስኬታቸው ግን በዋነኝነት የሚጠቀሱት እሴቶች፤ ግልጽና መልካም አስተዳደር፣ ነጻና ገለልተኛ የፍትሕ አካላት፣ ጠንካራ የኦዲት ሥርዓት፣ ሕዝብ በተቋማት ላይ ያለው አመኔታ፣ እና የፀረ ሙስና ሕግጋትን በቆራጥነት መተግበር ናቸው።
ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች ጋር ለስኬታቸው በተጓዳኝ የሚነሱት ጠንካራና በሙያ የተካነ ሞጋች ሚዲያ፣ የመንግሥትን ነውር በድፍረት የሚያጋልጡ የሲቪክ ማኅበራት፣ ለማኅበረሰብ ንቃት የሚተጉ የሥነ ምግባር ተቋማት (ቤተ እምነቶች)፣ ወዘተ ናቸው።
የሙስና ቁጥጥርን በተመለከተ ወደ ሲንጋፖር ስንመጣ መልኩ ቀየር ይላል፤ ሀገሪቱ የሙስና ልምምዶችን መርማሪ ቢሮ ወይም (Corrupt Practices Investigation Bureau (CPIB)) ተብሎ የሚጠራ መሥሪያ ቤት አላት። “ፈጣን እና አስተማማኝ፣ ጽኑ ግን ርቱዕ” በሚለው መፈክር የሚመራው መሥሪያ ቤት አገሪቱን ከአውሮጳ ኃያላን እኩል በጣም ጥቂት ሙስና ከሚካሄድባቸው ሀገራት ተርታ አሰልፏታል።
ወደ ሀገራችን ስንመጣ፤ ኢትዮጵያ “የፌዴራል የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን” የሚባል መሥሪያ ቤት አላት። የኮሚሽኑ መፈክር ደግሞ “ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያ” ይላል። በፌዴራል መንግሥት ሥር ያለ፤ በጀት ከፌዴራል መንግሥቱ የሚበጀትለት፤ ኃላፊ በፌዴራል መንግሥቱ የሚሾምለት ተቋም እንዴት አድርጎ ነው በነጻነት ሙስናን የሚዋጋው? በሙስና የዝቅተኛው ደረጃ ላይ የሚገኙት አገራት እንኳ ያልደፈሩትን “ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያ” ብሎ እንዴት ለመፈከር በቃ? ሌላው ቢቀር ይህንን መፈክር በተግባር በዚህች ምድር ላይ መተግበር ይቻላል?

ኪሾር ማህቡባኒ የታወቁ ሲንጋፖራዊ ዲፕሎማት ናቸው፤ በተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር የነበሩ ሲሆን የጸጥታው ምክርቤትን ለሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩ፤ ዓለምአቀፋዊውን ጂኦፖለቲካ በጥልቀት የሚተነትኑ ምሑርና የዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በታተመውና The Asian 21st Century በሚለው መጽሐፋቸው ዓለምአቀፉን ሥርዓት በመዘወር እሲያ ማዕከላዊ ቦታ እንዳላት ይሞግታሉ።
ማህቡባኒ ሲያስረዱም፤ 21ኛው ክፍለዘመን የእስያ ብቻ ሳይሆን ከእስያ አገራትና ማኅበረሰቦች የሚገኘው ተሞክሮ ዓለምአቀፉን ተግዳሮቶች ለመቋቋም ትምህርት የሚገኝበትም ጭምር ነው ብለዋል። በመጽሐፋቸውም ያስረዱት ይኽንኑ ነው፤ “ገቢር ነበብነት (ፕራግማቲዝም) መለያው የሆነውና እና ለታሪክ ውስብስብነት ጥልቅ አክብሮት የሚሰጠው እሲያዊ እሳቤ ሰብዓዊ ዘር ለገጠመው ዘርፈብዙ ችግሮች መፍትሔ ማቅረብ የሚችል ነው” ይላሉ። ከእነዚህ ችግሮች አንዱ ሙስና ነው።
የሲንጋፖርን ልምምድና ስኬት የ“MPH formula” በማለት የሚገልጹት ማህቡባኒ፤ ሀገራቸው እኤአ በ1965ዓም ነጻ ስትሆን ሥፍር ቁጥር የሌለው ችግርና ተግዳሮቶች አፍጥጠውባት እንደነበር ያወሳሉ። የሲንጋፖር መሥራች አባቶች፤ ሊ ኩዋን ዬው እና ጊህ ኬንግ ስዊ በፊታቸው ከተደቀነው ችግር አኳያ ቢሳካ እንደ ስሪላንካ ለመሆን ነበር ለሀገራቸው ያለሙት፤ ሰላማዊና የበለጸች ሀገር ናት ብለው ቀንተውባት ነበር። አሁን ላይ ግን ሲንጋፖር ዓለምአቀፋዊ ኃይል ስትሆን ስሪላንካ ደግሞ በበርካታ ችግሮች የተተበተበች ሀገር ሆናለች።
ኢትዮጵያ ከሦስቱ መሥፈርቶች ሁለቱን ለመተግበር እየጣረች ነው ቢባልም ሦስተኛው ግን የተነካ አይመስልም። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተደጋጋሚ መዋቅራዊ ወይም ተቋማዊ ሙስና የለም ሲሉ ተደምጠዋል። አገር እየገዘገዘና ሕዝብን እያስከፋ ያለውን ደግሞ ጥቃቅን (ፔቲ) ሙስና በማለት ሲጠሩት ነው የሚሰማው። ለዚህም ይመስላል እስካሁን ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ እንጂ በሙስና ተይዞ የታሰረ ወይም ለፍርድ የቀረበ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ያልኖረው።
ማህቡባኒ ሲንጋፖርን ከስሪላንካ ጋር በማነጻጸር ሲናገሩ፤ “ስሪላንካ ሲንጋፖር የተከተለችውን ተመሳሳይ ምሥጢራዊ ቀመር (“MPH formula”) ብትከተል ኖሮ እንደ ሲንጋፖር፤ እንዲያውም በበለጠ ሁኔታ የተሳካላት ትሆን ነበር” ይላሉ። ይህም ቀመር ሦስት እሴቶችን ያካተተ ወሳኝ የስኬት ቀመር ነው። እነዚህም፤ ችሎታ መር (ምደባ በችሎታ)፤ ገቢር ነበብነት (ፕራግማቲዝም) እና ሐቀኝነት ናቸው። በማህቡባኒ አገላለጽ፤ meritocracy, pragmatism, and honesty ናቸው።
ችሎታ መር (ምደባ በችሎታ ወይም meritocracy) ማለት በሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሰዎች መመደብ የሚገባቸው በዕውቀታቸው፤ በብቃታቸው፤ በዓቅማቸው፤ በልምዳቸው መሆን ይገባዋል። እንጂ ለፓርቲ ባላቸው ታማኝነትና ውግንና፣ ለአስፈጻሚው አካል ባላቸው ታማኝነት (ካድሬአዊ ምድባ)፤ የብሔር ብሔረሰብ ተዋጽዖ ወይም ኮታ ለማሟላት ወይም ስብጥር እንዲኖር ለማድረግ፤ በግል የጥቅም ትሥሥር፤ በወገንተኝነት (በሰፈርተኝነት)፤ ወዘተ መሆን የለበትም።
ከዚህ እሴት አኳያ ስለ ሲንጋፖር ልምምድ ማህቡባኒ ሲናገሩ፤ “የምንመድበው ከሁሉ የላቀውን እጩ ነው፤ ሌላ ምንም መሥፈርት አልነበረንም፤ የሲንጋፖር ሕዝብ አብዛኛው ቻይናዊ ቢሆንም ለሥራው የሚመጥን ብቁ ሰው ስናገኝ ቻይናዊ ባይሆንም እናሠራዋለን፤ የሲንጋፖር ስኬት የመጀመሪያው ተጠቃሽ ነጥብ በችሎታ መመደብ የሚለው ነው” ይላሉ።
ሁለተኛው ገቢር ነበብነት ወይም ተግባራዊነት ወይም ፕራግማቲዝም ነው። ከሲንጋፖር መሥራች አባቶች አንዱ የሆኑትን የዶ/ር ጎህ ኬንግ ስዌ “ሲንጋፖር የምትጋፈጠው ማንኛውም ችግር ከዚህ በፊት የሆነ አካል በሆነ ሁኔታ የገጠመው ነው” ይሉ እንደነበር ማህቡባኒ ይጠቅሳሉ። ስለዚህ ለሲንጋፖር ከጃፓን ስኬት ትምህርት መውሰድ ቀላሉ ነገር ነበር። “እንደ ስሪላንካ ያሉ ሀገራት ግን ከሲንጋፖር እንኳ መቅዳት አልቻሉም” በማለት ከሌሎች የስኬት ሞዴል መማር ሲንጋፖርን እዚህ እንዳደረሳት ይናገራሉ።
ገቢር ነበብነት ማለት የቀድሞው የቻይና ፕሬዚዳንት እንዳሉት ነው በማለት ማህቡባኒ ያስረዳሉ፤ “ድመቷ ጥቁር ትሁን ወይም ነጭ ጉዳያችን ሊሆን አይገባም፤ አይጥ መያዝ እስከቻለች ድረስ ጥሩ ድመት ነች”። አንድ አገር ለተጋፈጠችው ችግር መፍትሔ እስካመጣ ድረስ የምዕራብ ይሁን የምስራቅ፤ የካፒታሊት ይሁን የሶሻሊስት፤ የወግ አጥባቂ ይሁን የለዘብተኛ፤ ርዕዮተ ዓለሙ ሊያሳስበን አይገባም።

ሦስተኛውና ለመተግበር በጣም ከባዱ ሐቀኝነት ነው። ለብዙ ሀገራት በሙስና መዘፈቅና መክሰር ዋናው ምክንያት ይህንን ለመተግበር ባለመቻላቸው ነው ይላሉ ማህቡባኒ። በተግባራዊ ምሳሌ ሲያስረዱም እንዲህ ይላሉ፤
“ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ክዋን በቀዳሚነት መመሪያ ያደረጉት የበታች ባለሥልጣናት ሌቦችን መቅጣት ሳይሆን በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉትን ነበር። አንዴ አንድ ሚኒስትር ደኤታ ከነጋዴ ጓደኛው ጋር ለዕረፍት ወጥቶ ሲመለስ ኤርፖርት ላይ ተይዞ ታሰረ፤ ለምን እንደታሰረ ሲጠይቅም፤ ‘ከነጋዴ ጓደኛህ ጋር ለዕረፍት ስትሄድህ እሱ ያንተን ወጪ በሙሉ መክፈሉ ሙስና ስለሆነ ነው’ አሉት፤ በሚኒስትር ደኤታ ደረጃ ለዚህች ጉዳይ ተብሎ መታሰሩ በሌሎች ላይ “ነግ በኔ” አስከተለ፤ ሲንጋፖር ሙሉ በሙሉ ከሙስና ባትጸዳም ያስተላለፈው መልዕክት ግን ቀላል አይደለም”።
ሲንጋፖር በዕድገትም ሆነ ሙስናን በመዋጋት ጥሩ ትምህርት የምትሰጥ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ከሦስቱ መሥፈርቶች ሁለቱን ለመተግበር እየጣረች ነው ቢባልም ሦስተኛው ግን የተነካ አይመስልም። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተደጋጋሚ መዋቅራዊ ወይም ተቋማዊ ሙስና የለም ሲሉ ተደምጠዋል። አገር እየገዘገዘና ሕዝብን እያስከፋ ያለውን ደግሞ ጥቃቅን (ፔቲ) ሙስና በማለት ሲጠሩት ነው የሚሰማው። ለዚህም ይመስላል እስካሁን ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ እንጂ በሙስና ተይዞ የታሰረ ወይም ለፍርድ የቀረበ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ያልኖረው።
አንድ በቅርቡ የተከሰተ ምሳሌ ላቅርብ፤ በጣም ሀገሯን የምትወድና ለማገልገል ቁርጠኛ የሆነች ወጣት የውጪ ትምህርት ዕድል አግኝታ ካገር ከመውጣቷ በፊት መንጃ ፈቃዷን ለማሳደስ ወደሚመለከተው ስትሄድ ወይ ወረፋ መጠበቅ እንዳለባት አለበለዚያ ጉቦ መስጠት እንዳለባት በግልጽ ተነገራት። ጊዜ ስላልነበራት ሁለተኛውን አማራጭ መከተል ግድ ሆነባት፤ ለማሳደስና ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ እጅ መንሻውን ገቢ የምታደርግበት አካውንት ቁጥር ተሰጣት፤ ሁሉንም ፈጽማ ወጣች።
መንጃ ፈቃዷን በውጭ ጉዳይ ሰነድ ማረጋገጫ ማሳየት ስለነበረባት እዚያ ስትሄድ ከበር ላይ ነው የፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ የሆነው ሌላ የባንክ አካውንት ቁጥር የሰጣት። ከዚያ ፖሊሱ ባመቻቸላት መሠረት ጉዳይዋን በፍጥነት ለመፈጸም ቻለች። ነገርግን አንድ ትልቅ ጥያቄ በአእምሯ ውስጥ ተጫረ፤ “ተምሬ ስመለስ እንዴት ነው እዚህች ሀገር ላይ የምኖረው፤ መረን የለቀቀው ጥቃቅን ሙስና አካል ሠርቶ፤ ልብስ ለብሶ፤ በየቢሮው እየተጎማለለ ነው” ብላ በታላቅ ተስፋ መቁረጥ ጉዳይዋን አጫወተችኝ።
ይህ አንድና ተራ የሚባል ክስተት ነው፤ ግን ሕዝቡ የሚያውቀውና በየዕለቱ የሚኖረው ሕይወት ነው፤ ለምን ችላ ተባለ? ጥቃቅኑ ሙስና አይደል ትላልቆቹ ሻርኮችን የሚመግበው? ይህንን የምለው ሲስተምን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሠራ ያለውን ሳልዘነጋ፤ የመሶብን ትልቅ ፋይዳ ሳልረሳ ነው። ጥያቄው ትልልቆቹ ሻርኮች ለምን ዝም ተባሉ ነው።
ወደ ማጠቃለያ ስመጣ፤ ሀገራችን የሲንጋፖርን ፈለግ ብትከተል የሚጠቅማት ይመስለኛል። የሙስናውን ጉዳይ ለዲጂታይዜሽን ብቻ መተው የለበትም። አስደንጋጭ ትምህርት ሰጪ እርምጃ መወሰድ አለበት። ጥቃቅኑን ሙስና የሚያኮሰምን፣ የሚያደርቅ ተግባራዊ ውሳኔ ይወሰድ።
ከሚጻፈው፣ ከሚወራው በላይ መንግሥት ሌቦቹን ያውቃቸዋል፤ መረጃው አለው፤ ማስረጃ አለው፤ ወደ ተግባር ይቀይረው። በአመራር ላይ ያሉትን ካለፈው ሥርዓት ልማድ ያልተላቀቁትን ሙሰኞች ለፍርድ ያቅርባቸው፤ የአስፈጻሚው ሰይፍ በሙሰኞች ላይ ያለ ምሕረት ይመዘዝ። ሕዝብም በመንግሥትና ተቋማቱ ላይ እምነት ይኑረው።

ሙስናን ለመዋጋት የወጡ ሕጎች በተግባር ይዋሉ፤ አፈጻጸማቸው ክትትል ይደረግበት፤ በተለይ ዋናው ኦዲተር የሚያወጣቸው የምርመራ ሥራዎች ተግባራዊ ይሁኑ፤ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰነዳቸውንም በራቸውን ለሚዲያ ክፍት ያድርጉ።
ሌላው የፓርቲና የመንግሥት ሥራ መለያየት አለባቸው፤ ለፓርቲ ሥራ የመንግሥት/የሕዝብን ሃብት መጠቀም መቆም አለበት፤ ወይም ፓርቲው ሲጠቀም መክፈል አለበት፤ ካድሬን ባለመብት ማድረግ መቆም አለበት።
የፌዴራልና ፀረ ሙስና የሚባለው መ/ቤት ከስሙና መፈክሩ ጀምሮ እንደገና ይፈተሽ። ለበሽታ፣ ፀረ በሽታ ሳይሆን የጤና ሚኒስቴር፤ ለመሃይምነት፣ ፀረ መሃይምነት ሳይሆን የትምህርት ሚኒስቴር፤ ለግጭት፣ ፀረ ግጭት ሳይሆን የሰላም ሚኒስቴር፤ ኖሮን ለሙስና እንዴት “ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያ” እያለ የሚፈክር የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኖረን? እንዴትስ እስካሁን ይህንን አካሄድ ለመቀየር አልታሰበበትም?
ስለዚህ አዲስ የመጠሪያ ስም ጀባ ልበል፤ “የፌዴራል ሥነምግባርና ተጠያቂነት ኮሚሽን” Federal Ethics and Accountability Commission በሚለው ይቀየር፤ ወይም የተሻለ ስም ካለ ይሰጠው፤ ብቻ “ፀረ ሙስና” የሚለው መጠሪያ ይወገድ፤ ለትርጉምም ለትምርትም የተሻለ ነው።
በጥቅስ ላብቃ፤ ጋዜጠኛው ካርል ክራውስ እንዳለው፤ “ሙስና ከሴተኛ አዳሪነት የከፋ ነው፤ ይኸኛው የግለሰብን ሞራል የሚጎዳ ሲሆን ሙስና ግን የአንድን ሀገር ሞራል አደጋ ላይ የሚጥል ነው”። እንዴት እና ለምን ብለን ከጠየቅን ፖፕ ፍራንሲስ እንዳሉት ድሃው ሕዝብ ነው የሙስና ከፋይ። መታወቅ ያለበት ግን ሁልጊዜ ሲከፍል እንደማይኖር ነው።
መክብብ ማሞ – ነጻ አስተያየት
ዝግጅት ክፍሉ / ይህ ጽሁፍ የጸሃፊውን አቋም ብቻ የሚያንጸባርቅ፣ የጸሃፊው አሳብና እምነት ብቻ ነው። በመቃወምም ሆነ በድጋፍ ምላሽ መስጠት ለሚሹ ሁሉ መድረኩ ክፍት ነው።