የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለመጠናቀቅ ሁለት ወራት ብቻ በቀሩት የዘንድሮው የፈረንጆቹ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7.2 በመቶ ያድጋል ሲል ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔ ትንበያውን ይፏ አድርጓል። መንግስት ቀደም ሲል የአዲስ ዓመት የኢኮኖሚ እቅዱን ሲያስታውቅ ከስማንት በመቶ በላይ እደገት እንደሚመዘገብ ማስታወቁ አይዘነጋም።
የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዓመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች የሚገኙ 45 ሀገራትን ያካተተ የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚዳሰስ ሰነድ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተጓዘበትን ሁኔታ መልካም ከሚባሉት አገራት ምድብ ተርታ አስቀምጦታል።
የድርጅቱ ሪፖርት እንዳመለከተው ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት በውጫዊ የገበያ ሁኔታ በእጅጉን ሲፈተኑ መቆየታቸውን የገለፀ ሲኾን፣ እንደ የሸቀጦች ዋጋ ንረት፣ የዓለምአቀፍ የንግድ ሁኔታ ማሽቆልቆል እንዲኹም ከፍተኛ የሆነ የብድር ጫና መደራረብ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ መኾኑን ጠቅሶ ሆኖም የመቋቋም አቅም ያሳየ ኢኮኖሚ እንደነበር በሪፖርቱ አመላክቷል።
ለዚህም በበጎ ሁኔታ ያስቀመጠው እንደ ኢትዮጵያና ናይጀሪያ ባሉ አገራት የተተገበረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን በሪፖርቱ የቀረበ ሲኾን ምንም እንዃን የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪዎች ቢያጋጥማቸውም ኢኮኖሚያቸውን የዋጋ ንረቱን መቋቋም የሚችል አቅም ያለው ነው ሲል የገንዘብ ተቋሙ መስክሯል።
የተፈጠረው የመቋቋም አቅም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በተፈጥሮ ሐብት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላደረጉ አገራት እጅግ ጠቃሚ ሆኖ መገኘቱን የገለፀው ይኸው የገንዘብ ተቋሙ ሪፖርት አጠቃላይ የተመዘገበው የዋጋ ግሸበት በኩል ግን ከፍተኛ እንደነበር አትቷል። አገራቱ በተለኩበት የኢኮኖሚ መመዘኛ መሰረት በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ባለ ሁለት አሐዝ መኾኑን በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያን አስመልክቶ በሰጠው ሌላኛው ትንበያው በመጪው የፈረንጆች ዓመት አገሪቱ የሚኖራት የኢኮኖሚ እድገት 7.1 በመቶ እንደሚሆንም የአገራት ኢኮኖሚ በሚለካበት አመታዊ ሪፖርቱ ላይ ገልጿል። ድርጅቱ ይህን ይበል እንጂ፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የቀረበው ትንበያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት 9 በመቶ በላይ ለማስመዝገብ ውጥን መያዙን ፕሬዝዳንት ታዮ አፅቀ ስላሴ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት መክፈቻ ባደረጉት ንግግር መግለፃቸውን የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በበኩላቸው የ2017 በጀት አመት የመንግስት የስራ አፈፃፀም አስመልክተው ለምክርቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለቀው በጀት አመት 8.8 በመቶ እድገት የተመዘገበበት እንደነበር ሲናገሩ ተደምጠዋል ነበር።
በገንዘብ ድርጅቱ እና በመንግስት በኩል በቀረቡት አሃዞች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያስመዘግበዋል ተብሎ በቀረበው የትንበያ መካከል 1.8 በመቶ የሚሻገር ልዮነት ይታያል። ሆኖም የገንዘብ ተቋሙ በተለያዮ መለክያዎች ባስቀመጠው መስፈርት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበጎ ሁኔታ የተመለከቱበት መኾኑን በሰነዱ ላይ ተገልጿል።
የገንዘብ ተቋሙ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ ከሳህራ በታች ባሉ አገራት ጠንካራው ኢኮኖሚ ከመኾኑ በተጨማሪ ደጋግሞ በበጎ ጎን ከጠቀሳቸው አገራት መካከል የሚመደብ ነው። በተለይም የኢኮኖሚ ክለሳዎችንና ማሻሻያዎችን ከተደረጉ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የዋጋ ንረትን የመቋቋም አቅም በፍጥነት ከፈጠሩ አገራት ምድብ ተርታ ማስቀመጡ የሪፖርቱ ትንበያ ያስረዳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ እንደ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ቤኒን እና ኮትዲቯር ያሉ አገራት በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት መለክያ ፈጣን እድገት የተመዘገበባቸው አገራት መኾናቸውን የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አመታዊ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል ።
በመጨረሻም ፣ በዚሁ ቀጠና ያለው የኢኮኖሚ እድገት በተረጋጋ ሁኔታ እንደሚቀጥል በትንበያው የተገለፀ ሲኾን በአንዳንድ አገራት በሚጠበቀው በላይ የማደግ አዝማምያ ሊኖር እንደሚችል ሪፖርቱ ቢናገርም አንዳንድ ብሎ የጠቀሳቸው አገራት ግን በስም አልገለፀም።




